Sunday, 23 December 2018 00:00

ቃለ ምልልስ የጎንደር ከተማ ከንቲባ - ዕቅድ፣ ራዕይ፣ ተስፋና ስጋት

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

 · ግጭት፣ ህገ-ወጥ የመሣሪያ ዝውውር፣ የፀጥታ ስጋት፣ የመሠረተ ልማት ችግር--- ተጋርጠዋል
   · በተለየ ድምቀት ይከበራል በተባለው የጥምቀት በዓል፤ በርካታ ዳያስፖራዎች ይታደማሉ
   · ቻቺ ታደሰ የውጭና የአገር ውስጥ አርቲስቶች የሚሳተፉበት የሙዚቃ ኮንሰርት ታዘጋጃለች

   ባለፈው ነሐሴ 2010 ዓ.ም የጎንደር ከተማ አስተዳደርን እንዲመሩ ከንቲባ ሆነው ከመሾማቸው በፊት ላለፉት 15 ዓመታት ገደማ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ አገልግለዋል- ዶ/ር ሙሉቀን አዳነ፡፡ ከተማው በአገሪቱ ሁለተኛው ትልቅ ከተማ መሆኑን የሚገልጹት ከንቲባው፤ የዚያኑ ያህል ትልልቅ ችግሮች እንዳሉበትም ያስረዳሉ፡፡ ግጭትና ህገ ወጥ የመሳሪያ
ዝውውር ለከተማው የጸጥታና ደህንነት ስጋት ሆነው መቆየታቸውንም ይገልጻሉ። ከተማውን ሰላማዊና የጸጥታ ስጋት የሌለበት ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችንም ይጠቅሳሉ - ከንቲባው። በሚቀጥለው ወር በጎንደር ከተማ በልዩ ድምቀት በሚከበረው የጥምቀት በዓል ላይ በርካታ ዳያስፖራዎች ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከዚህ አንጻር ምን ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው በሚለውና በአጠቃላይ በከተማው ዙሪያ----ለሥራ ወደ ጎንደር የተጓዘችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ ከከንቲባ ዶ/ር ሙሉቀን አዳነ ጋር ተከታዩን ቃለ
ምልልስ አድርጋለች፡፡


    እርስዎ ከተማውን በከንቲባነት ለመምራት ከተረከቡ በኋላ የቅድምያ ትኩረትዎ አድርገው መሥራት የጀመሩት ምንድን ነው? ከተማውን በምን ሁኔታ ላይ ነው ያገኙት?
የጎንደር ከተማ አስተዳደር የተለያዩ ኃላፊዎች ይመሩት የነበረ ከተማ ነው፡፡ ሁሉም የቻሉትንና የአቅማቸውን ሰርተው አልፈዋል፡፡ እኔ ከመጣሁ በኋላ በርካታ ነገሮችን አይቻለሁ፡፡ እንደሚታወቀው ጎንደር ከተማ በአገሪቱ በስፋቱ ሁለተኛ የሚባል ከተማ ነው፡፡ ትልቅ መሆኑ ብዙ ትልልቅ ችግሮችም እንዲያጋጥሙት ሆኗል፡፡ ከተማውን ዞር ዞር ብለሽ አይተሽው ከሆነ መንገድና ሌሎች የአገልግሎት ተቋማትን መመልከትሽ አይቀርም፡፡ በማታ ወጣ ካልሽም አብዛኛው የከተማው ክፍል መብራት የሌለው በመሆኑ ጨለማ ነው። ገና ብዙ ነገር እንዲሟላለት የሚጠብቅ ከተማ ሆኖ ነው ወደ ኃላፊነት የመጣሁት፡፡ የተወሰኑ የተጀማመሩ ነገሮች አሉ፤ እነሱ ማለቅ አለባቸው፡፡ ነገር ግን የተጀመሩት ስራዎች ከተማው ከሚጠብቀው አንጻር በቂ ባለመሆናቸው ከዚያ በላይ ይጠብቃል። አገልግሎት አሰጣጡም ክፍተት ያለበት ነው፡፡ ለምሳሌ እኔን ለማነጋገር ሁለት ሶስት ጊዜ ወደ ቢሮዬ በመጣሽባቸው ጊዜያት፣ እኔን ለማነጋገር ቢሮዬ ጉዳይ ይዞ የሚመጣው ሰው፣ ገበያተኛ ነው የሚመስለው፡፡ ያ ሁሉ ሰው የሚያመላክተው በአገልግሎት አሰጣጡ ያልረካ መሆኑን ነው፤ ስለዚህም  ይህን ሁሉ ክፍተት የመሙላት ኃላፊነት ነው ያለብኝ፡፡
ባለጉዳዮች ከንቲባ ጽ/ቤት ከመምጣታቸው በፊት ችግሮቻቸውን የሚፈቱባቸው እንደ ክ/ከተማና ቀበሌ ያሉ የአስተዳደር ተዋረዶች የሉም?
እንዳልሽው ቢሮዎች አሉ፡፡ ነገር ግን ከስር ያሉት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ስራቸውን በአግባቡ እየሰሩ ባለመሆናቸውና ተገልጋዩም እርካታ በማጣቱ ነው፣ ቀጥታ ወደ ከንቲባ ፅ/ቤት የሚመጡት፡፡ ይሄ ሰፊ ክፍተት በአንድ ጽ/ቤት የሚቀረፍ ባለመሆኑ፣ በምን መልኩ ቢሰራ ነው ስር ነቀል ለውጥና የተገልጋይ እርካታ የሚመጣው የሚለውን፣ በኃላፊነት ወደ ከተማ አስተዳደሩ በመጣሁባቸው ሁለትና ሶስት ወራት  ውስጥ ለማጥናት ሞክሬያለሁ፡፡ በጥናቱ የተገኘው እንዳልኩሽ፤ በተዋረድ ያሉት ውሳኔ ሰጪዎች የፈጠሩት ክፍተት ነው ወደ ላይኛው ውሳኔ ሰጪ ሰውን የሚያመጣው፡፡ ይህን የአሰራር ስርዓት በመዘርጋትና ኃላፊነትን በተዋረድ በመስጠት፣ ህዝቡን በአግባቡ ለማገልገል፣ የአሰራር ሥርዓት ቅፅ አዘጋጅቼ ከታች ከቀበሌ ጀምሮ ለክፍለ ከተማዎችም ሆነ ለመምሪያዎችና ለሚመለከታቸው ሁሉ አሰራጭቻለሁ፡፡ አንዳንድ ቦታ ላይ በቅፁ መሰረት መስራት ጀምረው አበረታች ጅምር አለ፡፡ አንዳንድ ቦታ ደግሞ አሰራሩን ለመተግበር የማይፈልጉ አሉ፡፡ እነዚህንም መረዳት ያስፈልጋል፡፡ የእውቀት ችግር ነው ወይስ ቅንነት ማጣት? የሚሉትን ነገሮች የግድ መፈተሽ ስላለብኝ፣ እሱን ፈትቼ ነው መቀጠል ያለብኝ፡፡
ይህንን ለማድረግ በስድስቱም ክ/ከተሞች ላይ የዳሰሳ ጥናት ሰርቼ ጨርሻለሁ፡፡ በስራ ሰዓትም ቦታው ላይ እየተገኘሁ እነማን በስራ ገበታቸው ላይ ናቸው? የትኞቹ ላይ ሆን ተብሎ የማንጓተትና የማስተጓጐል ስራ እየተሰራ ነው? የሚለውን በዳሰሳ ጥናቱ ጨርሻለሁ። በዚህ መነሻነት ከክፍለከተሞች አመራሮች ጋር ተወያይተን ችግሮቹ በመኖራቸው ላይ ተስማምተን፣ በችግር አፈታቶቹ ላይ ስትራቴጂ ዲዛይን እየሰራሁ ነው፡፡ በሁሉም ቢሮ ስትሄጂ በአሁኑ ወቅት የሰዓት ፊርማ የለም፡፡ አንቺ ከፈለግሽ ትገቢያለሽ፣ ካልፈለግሽ ትቀሪያለሽ፡፡ አንድ ቦታ ሄደሽ “በዚህ ሰው ምክንያት ለምን የአገልግሎት አሰጣጡ ተስተጓጐለ?” ብለሽ ስትጠይቂ እንደዋዛ “አሁን እኮ እዚህ ነበር--ስላመመው (ስላመማት) አልመጣችም” ይሉሻል። እናም የቁጥጥር ሥርዓቱ በጣም የላላ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ ይሄን ነገር ለመቀየር እየሰራሁ ነው፡፡
እርስዎ ወደ ኃላፊነት የመጡበት ወቅት አስቸጋሪ ነው፤ በተለይ ከፀጥታ አንፃር፡፡ በሌላ በኩል ጐንደር የቱሪስት ከተማ ናት፤ መጪው ጊዜ ደግሞ ከመላው ዓለም ቱሪስቶች የሚታደሙበት የጥምቀት በዓል የሚከበርበትም ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ምን አይነት ዝግጅት እያደረጋችሁ ነው?
ጥሩ፡፡ የከተማውን ጉዳይ በተለይ የጥምቀትን በዓል በተመለከተ ብዙ ነገሮች አቅደን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ የመጀመሪያው ሥራ የፀጥታው ጉዳይ ነው፡፡ የፀጥታው ጉዳይ አስተማማኝ ካልሆነ እንኳን ቱሪስት ሊመጣ እዚህም ያለነው እንደ ልብ መንቀሳቀስ አንችልም፡፡ ስለዚህ ይሄ ቅድምያ የምንሰጠው ነው፡፡ እንደምታውቂው በቅርቡም በአካባቢያችን የተከሰተ ነገር አለ፡፡
የጭልጋው ጉዳይ ነው?
አዎ፡፡ በጭልጋና በመተማ በቅርቡ የተከሰተውን ሁሉም የሚያውቀው ነው፡፡ እነዚህ ግጭቶች ወደ ከተማው ዘልቀው ችግር እንዳይፈጥሩ፣ ከፀጥታ ሀይሉ ጋር ቀን ከሌት እየሰራን ነው፡፡ የፖሊስ ሃይል አለን፡፡ የአድማ ብተና ሃይልም እንደዚሁ አለን፡፡ ከመከላከያም የተመለሱ የሰራዊት ሃይልና በከተማ አገልግሎት ጽ/ቤት የሚመራ የደንብ ማስከበር ሃይልም አለን፡፡ ይህንን አቀናጅተን እየሰራን እንገኛለን፡፡ በተጨማሪም በአገሪቱ ህገ-ወጥ የመሳሪያ ዝውውር በስፋት ይታያል፡፡ ይህ ህገ-ወጥ የመሳሪያ ዝውውር ለአገሪቱ ተጨማሪ ስጋት ነው፡፡ ይህንን ስጋትም ለመቀነስ እየሰራን ነው፡፡
ህገ-ወጥ የመሳሪያ ዝውውርን ለመቆጣጠር ምዝገባ መጀመራችሁን ሰምቻለሁ፡፡ እስቲ የተጀመረውን ሥራ ያብራሩልኝ?
አዎ ምዝግባ ጀምረናል፡፡ ምን አይነት መሳሪያ፣ እነማን እጅ ላይ አለ፣ የሚለውን ለማወቅና መሳሪያ የያዘው ሁሉ ተጠያቂነት እንዲኖረው ለማድረግ ነው እየተሰራ ያለነው፡፡ ይሄ የቁጥጥር ሥራችን የበለጠ ጠንካራ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ አንድ መሳሪያ ተተኩሶ ሰው ላይ ጉዳት አድርሶ ቢገኝ፣ ያ መሳሪያ እማን እጅ ላይ እንደሚገኝ፣ ምን አይነት መሳሪያ ጉዳት እንዳደረሰ ስለሚታወቅ፣ በጉዳት አድራሹ ላይ እርምጃ ለመውሰድ ይረዳል ማለት ነው፡፡ ዛሬ ወደ አራተኛ ቀናችን ነው፡፡ (ቃለ ምልልሱ ባለፈው ሳምንት የተደረገ ነው) ለሚቀጥሉት 10 ቀናት ምዝገባው ይቀጥላል ማለት ነው፡፡
ሰው መሣሪያውን የማስመዝገብ ፍላጐቱ ምን ይመስላል?
የሰው ፍላጐት በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ከየክፍለከተማው ሰው ከምንገምተው በላይ እየጐረፈ ነው የሚያስመዘግበው፡፡ ዳታዎች አሉኝ፡፡ ሽጉጥ 358፣ አውቶማቲክ ክላሽ 243፣ እና በቃታ የሚሰራ 12-- በአንድ ቀን ብቻ ተመዝግቧል፡፡ በቀጣዮቹ አስር ቀናት ምን ያህል ሰው ሊመዘገብ እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ የፀጥታውን ሁኔታ አስተማማኝ ለማድረግ ይሄንን እየሰራን ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የከተማውን አጠቃላይ ንፅህና በተመለከተ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው፡፡ ከተማውን ተዘዋውረሽ ተመልክተሽ ከሆነ፣ በቋሚ የጽዳት ሠራተኞች እየተፀዳ ነው፡፡ ይሄንን በእርግጥ ለጥምቀት በዓል ብቻ ብለን የምንሰራው አይደለም፡፡ ከተማው የቱሪስት መዳረሻ እንደመሆኑ በማንኛውም ጊዜ ንፁህ ከተማ መሆን አለበት፡፡ ለቱሪስት ብቻ ሳይሆን የከተማው ህዝብም ለራሱ ንፁህ የሆነ ከተማ ውስጥ መኖር ይገባዋል። በመሆኑም የከተማውን ጽዳት ጉዳይ አጠንክረን ይዘናል፡፡
በቅርቡ በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ በተቀሰቀሰ ግጭት የአማራ ተማሪዎች መገደላቸውን ተከትሎ፣ አምስት ካምፓስና ከ47ሺ በላይ ተማሪዎችን በያዘው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ “የአማራ ተማሪዎች ማኅበር” በጠራው ሰላማዊ ሰልፍ፣ ግጭቶች ተነስተው ተማሪዎች መጎዳታቸው ይታወቃል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ ይህንን ችግር ለመፍታት ከዩኒቨርሲቲው ጋር በምን መልኩ ነበር ስትሰሩ የነበረው?
እኛ ጎንደር ዩኒቨርሲቲን እንደ አንዱ የከተማችን አካል ነው የምንቆጥረው፡፡ የተለየ ትኩረት የምናደርግበት ምክንያት አንደኛ እነዚህ ተማሪዎች አድገው ነገ አገር የሚረከቡ ዜጎች ናቸው፤ስለሆነም ደህንነታቸው ተጠብቆ ከስጋት ነፃ ሆነውና ትምህርታቸውን አጠናቅቀው፣ አላማቸውን እንዲያሳኩ እንፈልጋለን፡፡ በዚህ እምነቱ ከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ነው የሚሰራው፡፡ ወደተነሳሽበት ነጥብ ስመጣ፣ በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ በተነሳ ግጭት የተማሪዎችን ሞት ተከትሎ፣ “በየትኛውም ቦታ ለትምህርት የሄደ ተማሪ መገደል የለበትም” በሚል በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል፡፡ ሰልፉ በአብዛኛው የተካሄደው በአማራ ተማሪዎች ነው፡፡ የጠራውም ከላይ እንደጠቀስሽው የአማራ ተማሪዎች ማኅበር ነበር። ይህ ሲሆን ሌሎቹ ተማሪዎች ሥጋት ገባቸው፡፡
ለምን ሰጉ?
ያው ለምን ሁሉንም አልጠሩም በሚል በተለይ የኦሮሚያ ተማሪዎች ከፍተኛ ሥጋት ያዛቸው፡፡ እኔም መረጃው ስለነበረኝ የከተማውን የፀጥታ ኃይሎች አንቀሳቅሰን ጉዳዩን በቁጥጥር ስር አዋልነው፡፡ ችግር አልተፈጠረም፤ የተመታ ተማሪ አልነበረም፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ የወጡትም ልጆች ሰልፉን በሰላም አጠናቀቁ።  ይሄ ካለፈ በኋላ የኦሮሞ ተማሪዎች ከፍተኛ ስጋት አድሮብናል ብለው አመለከቱ፡፡ እነሱን ትሪት ወደ ማድረግ ስራ ገባን፡፡ በአጋጣሚ አዳራሽ ውስጥ የሰበሰብኳቸው እኔ ነበርኩኝ፡፡ ተነጋገርን፡፡ ተስማማን። ችግር እንደማይፈጠርና ኃላፊነቱን እኛ እንደምንወስድ አስረዳናቸው፡፡ የክልሉ ኃይል ሊገባብን አይገባም አሉ፡፡ “ያላችሁት አማራ ክልል ውስጥ ነው፤ እዚህ እስካላችሁ ድረስ የክልሉ ኃይል ሰላም የማስጠበቅ ግዴታ አለበት፡፡ ስለዚህ ጉዳዩን ሌላ ቅርፅ አታስይዙት፤ በቅንነት ተመልከቱት፤ የክልሉ ኃይል እዚህ የገባው እናንተን ለመታደግ እንጂ እናንተ ላይ ችግር ለመፍጠር አይደለም” ብለን ተወያየን፡፡ አብዛኛዎቹ ሀሳቡን ሲደግፉት፣ አንዳንዶቹ አልተቀበሉትም፡፡ “በክልሉ ኃይል ላይ እምነት የለንም፤ ፌደራል ፖሊስ ይግባልን” አሉ፡፡ እኛም “ጥሩ፤ ተቋሙም የፌደራል ነው፡፡ ፌደራል ፖሊስም ይህንን ተቋም የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ነገር ግን ነገሩን አጠንክራችሁ ይሄኛው ኃይል ይግባ፣ ያኛው ይውጣ ማለት ተገቢ አይደለም” አልናቸው። በአጋጣሚ ኦሮሚኛ ቋንቋ የሚችሉ አንድ የፌደራል ፖሊስ ኮማንደር ነበሩ፡፡ ከእሳቸው ጋር መድረኩን መርተን ተወያይተን፣ መግባባት ላይ ደርሰን ወጣን፡፡
ከዚያስ?
ቀጥሎ የሆነው ነገር ምን መሰለሽ? ሌሊቱን እነዚህ ልጆች ተሰባስበው አንድ ህንፃ ላይ አደሩ፡፡
የኦሮሚያ ተማሪዎች?
አዎ! አንድ ህንፃ ላይ ማደራቸው ከተማሪው ጋር ያላቸውን መስተጋብር ያበላሻል፤ አለመተማመንን ያጎለብታል፡፡ ሁለተኛ ችግር ቢከሰትም ተጋላጭ ያደርጋቸዋል፡፡ በዚያ ሌሊት ከመሃላቸው አንዱ ወጥቶ፣ ድንጋይ ወርውሮ መስኮት ሲሰብር ፌደራል ፖሊሶች ያዙት፡፡ በነጋታው በላያችን ላይ ድንጋይ ተወርውሮ፣ መስኮት ተሰብሮብናል ብለው ወጡ፡፡ ምንድን ነው የምትፈልጉት? አረጋግተናል ተወያይተን ተስማምተናል፡፡ የተደባደበ አለ? የለም፡፡ የደረሰባችሁ ሌላ ችግር አለ? የለም ግን ስጋት ላይ ነን አሉ፡፡ ሌሎችንም የኦሮሞ ልጆች ቀስቅሰው ወጡ፡፡ እንደገና ተወያየን፡፡ ተነጋገርን፤ ተግባብተን ስንጨርስ፣ በሌላ በኩል የአማራ ልጆች ግልብጥ ብለው ወጡ፡፡ ምክንያት ሲባል፤ “የኦሮሞ ልጆችን በተደጋጋሚና በትዕግስት እያወያዩ፣ እኛን ችላ ብለውናል” ብለው ነው የወጡት፡፡ አናግሩን የሚል መልዕክት ሲልኩ፣ እንደገና አማራዎቹን ሰበሰብኩ፡፡ የኦሮሞ ተማሪዎች ወደ ዶርም ሲሄዱ፣ ከአማራዎቹ ጋር እርስ በእርስ ስድድብ ጀመሩ፡፡ ስድድቡ ወደ ድንጋይ መወራወር አደገ፡፡ በሰውም በንብረትም ጉዳት ከመድረሱ በፊት የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር አዋሉት፡፡ ከዚያ በኋላ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህግ ት/ቤት ተማሪዎች “እስኪ መሃል ገብተን የማግባባት ሥራ እንስራና መፍትሄ እናምጣ” አሉ፡፡ የማግባባት ሥራው ላይ “ጉዳዩ ትክክል አይደለም፤ ሁለታችንን ሊከፋፍልና ሊያጋጭ የሚፈልግ አካል እንዳለ ተረድተናል፤ ስለዚህ መስማማት አለብን” ብለው ከተወያዩ በኋላ፣ በዚህ ሀሳብ ላይ እንደገና ሰልፍ አደረጉ፡፡
አማራና ኦሮሞዎች አንድ ላይ ሆነው ማለት ነው?
አዎ! “እኛ አንድ ነን ወንድማማች ነን፤ ልዩነት በመሃላችን መፈጠር የለበትም” በሚል ሰልፍ አደረጉ። ትምህርት በመጀመሩ ጉዳይ ላይ ግን “ተማሪ በየሄደበት ዩኒቨርሲቲ መገደል የለበትም” የሚል አቋም ያዙና፣ ይህንን ጉዳይ መንግስት ራሱ ሊፈታልን ይገባል በሚል አቋም ፀኑ፡፡ ከከፍተኛ የትምህርትና ሳይንስ ሚኒስቴር፣ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ወ/ማሪያም፣ ፕሮፌሰር አፈወርቅና ሌሎችም ከፍተኛ ባለስልጣናት መጡ። ውይይት ተደርጎ ችግሩ ተፈታ፡፡ አሁን የመማር ማስተማር ሂደቱ በጥሩ ሁኔታ ቀጥሏል፡፡ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ግን አሁንም የዩኒቨርሲቲውን ፀጥታ እንደ አንድ የከተማው ክፍል አድርጎ ትኩረት ሰጥቶ ነው የሚከታተለው የሚጠብቀው፡፡ የእኛ የፀጥታ ኃይሎች እስካሁንም በዩኒቨርሲቲው ውስጥ እየሰሩ ናቸው፡፡ እኛ ቀደም ሲል የሀይማኖት አባቶችን ይዘን፣ የዩኒቨርሲቲውን ምሁራንና ማህበረሰቡን ሰብስበን፣ ተማሪዎች ገና ሳይመጡ በፊት መማር ማስተማር ሰላማዊ በሆነ መንገድ የሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ መክረናል ተወያይተናል፤ አስቀድመንም ስራ ስንሰራ ነበር ማለቴ ነው፡፡ ለምሳሌ ምግብ፣ ውሃ፣ የዶርሚተሪ ጉዳዮች---የግጭት መንስኤ እንዳይሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አድርገን፣ ተግባብተን ነው ወደ ተማሪ ቅበላ የገባነው፡፡
ከአሜሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ በርካታ ዳያስፖራዎች ለጥምቀት እንደሚመጡ ተነግሯል፡፡ ከተለያዩ የዓለም አገራት በርካታ ቱሪስቶች ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ እንግዶቹን በጥሩ ሁኔታ ተቀብሎ ለማስተናገድ በቂ ሆቴልና ደረጃውን የጠበቀ መስተንግዶ ለማቅረብ ምን እየተሰራ ነው? ሆቴሎችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ፕሮፌሽናል የሆነ መስተንግዶ እንዲሰጡትስ ሙያዊ ድጋፍ ያገኛሉ?
የዘንድሮ የጥምቀት በዓል አከባበር ለየት ባለ መልኩ እንዲከበር እንፈልጋለን፡፡ ለየት ባለ መልኩ ስንል፣ አከባበሩ ይለያል ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን በበዓሉ ላይ የሚታደሙት በተለይ ከዚህ ከተማ ላለፉት በርካታ ዓመታት በስደት የቆዩ አሉ፡፡ በአሜሪካም በአውሮፓም፡፡ እነዚህ ሰዎች ለውጡም ያመጣው ምቹ ሁኔታ በመፈጠሩ በዚህ ዓመት የጥምቀት ታዳሚ ሆነው እንዲያሳልፉ ፍላጎት ነበረን። ስለዚህም ጋዜጠኛ አበበ በለው ከእነ አርቲስት አለምፀሐይ ወዳጆ ጋር ጎንደር በመጡ ጊዜ አሜሪካ ያሉ ዳያስፖራዎችን እንዲያስተባብሩልን፣ እኛም ማገዝ ያለብንን ልናግዝ ተግባብተን፣ አበበ ወደ አሜሪካ ከተመለሰ በኋላ የማስታወቂያ መልዕክቶችን ቀርፆ ወስዶ በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ሰራ፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ከአሜሪካ ወደ ጎንደር የሚመጡ 14 ያህል አውሮፕላኖች መኖራቸው ተረጋግጧል፡፡ 14 አውሮፕላን ሙሉ ሰው ለጥምቀት እንደሚታደም አበበ በለው መረጃ ሰጥቶኛል፡፡ ትኬት ሁሉ ገዝተዋል፡፡ እኛ ደግሞ እነሱን ለመቀበል እንደ ከተማ አስተዳደር በቂ ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡ ሆቴሎች ዝግጁ እንዲሆኑ፣ የቀድሞዎቹም አዲስ ወደ ስራ እየገቡ ያሉትም በጥሩ ሁኔታ አገልግሎት እንዲሰጡ አስፈላጊው ሁሉ  እየተደረገ ነው፡፡
ከተለያዩ አገራት የሚመጡት ዳያስፖራዎች ጥምቀትን አክብረው ከመመለስ ባለፈ ኢንቨስት ሊያደርጉ ቢፈልጉ ጎንደር ምን ያህል  አቅም አላት? ኢንቨስት እንዲያደርጉ የማግባባቱስ ጉዳይ ታስቦበታል?
ጥሩ! እንዳልሽው እኛም ጥምቀትን ታድመው እንዲመለሱ ብቻ አይደለም ፍላጎታችን፡፡ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ጎንደር ያላትን አቅም ለማሳየትና እነሱም ኢንቨስት እንዲያደርጉ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ መሬት ቢጠይቁ፣ በዚህ በዚህ ዘርፍ እንሰማራ ቢሉ፣ ምን መመቻቸት አለበት? ቶሎ ወደ ስራ እንዲገቡ መሟላት ያለበትስ ምንድን ነው? የሚለውን አጠቃላይ ሥራ የሚሰራ ኮሚቴ ተቋቁሞ፣ ስራውን በትጋት እየሰራ ይገኛል፡፡
ባልሳሳት በ2006 ዓ.ም እዚህ ከተማ ውስጥ ጥምቀትን ለማክበር የመጡ 2 ሺህ ያህል ዜጎች ስርቆት ተፈፅሞባቸዋል፡፡ የቻይናው አምባሳደር ስልክም ተሰርቆ ነበር፡፡ 27 ሌቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ፖሊስ አስታውቆ ነበር፡፡ አሁን እንግዶች ከሌቦች ሥጋት ነፃ እንዲሆኑ ምን ዓይነት ዝግጅት አድርጋችኋል? ከፀጥታ ሥጋት ባልተናነሰ ይሄም ስጋት ነው ብዬ ነው----
ይሄም ዋነኛው ትኩረታችን ነው፡፡ እርግጥ የስርቆትን ነገር ወደ ዜሮ ፐርሰንት ላናወርደው እንችል ይሆናል፡፡ ያን ያህል በጎላ ሁኔታ እንግዶች ለስርቆት እንዳይዳረጉ የፀጥታ ኃይሉ ነቅቶ እንዲሰራ ምክክሮችና ውይይቶች እየተደረጉ ነው፡፡ በተለይ ከዚህ ቀደም የፀጥታ መደፍረስ ስለነበረ፣ ያንን አጋጣሚ በመጠቀም ሌቦች ዘረፋ ያካሂዱ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ከተማ አስተዳደራችንን ጨምሮ የአራቱም ዞኖች የፀጥታ ኃይሎች ተሰማርተው እየሰሩ ስለሆነ፣ ስርቆቱንም ከዚሁ ጎን ለጎን በመከላከሉም ላይ ይሰራሉ ማለት ነው፡፡
የጥምቀትን በዓል ይበልጥ ለማድመቅ ምን የተለዩ ዝግጅቶች ይኖራሉ?
የጥምቀትን በዓል ከሃይማኖታዊ በዓልነቱ ባለፈ ወደ ፌስቲቫልነት ለማሳደግ የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ ለምሳሌ የሙዚቃ ኮንሰርቶች ይኖሩናል፡፡ አርቲስት ቻቺ ታደሰ ከውጭም ከአገር ውስጥም ታዋቂ ድምፃዊያን ይዛ ትመጣለች፡፡ የባህል ኤግዚቢሽን፣ የሰርከስ ትርኢት፣ የባህላዊ አልባሳት፣ የፋሽን ትርኢት፣ የቁንጅና ውድድርና መሰል በዓሉን የሚያደምቁ ዝግጅቶች ይካሄዳሉ። ለዚህም ከአርቲስት ቻቺ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመን፣ እንቅስቃሴ ላይ ትገኛለች፡፡ ከከተማችን ባህልና ቱሪዝም እንዲሁም ከወጣቶች መምሪያ ጋር በቅርበት እየሰራች መሆኑንም አውቃለሁ፡፡ ብዙ ዝግጅቶች አሉ። ቀደም ሲል የሆቴሎች እጥረት ነበር፡፡ አሁን አዳዲስ በኮከብ ደረጃ አቅም ያላቸው ሆቴሎች ተገንብተው እየተጠናቀቁ፣ ወደ ስራ እየገቡ ናቸው፡፡ ሙያተኛን በተመለከተ ከዚህ ቀደም ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሆቴልና በቱሪዝም ማኔጅመንት ተመርቀው የተሻለ ስራ ፍለጋ ወደተለያየ አካባቢ ይሄዱ ነበር፡፡ አሁን በከተማዋ ሆቴሎች ላይ የማይሰሩበት ምክንያት የለም፡፡ የሰለጠነ የባለሙያ እጥረትም ያጋጥማል ብዬ አላስብም፡፡ በተቻለ መጠን ሙሉ አገልግሎት ለመስጠት ያቅማችንን እያደረግን ነው፡፡ ፀጥታውን አስተማማኝ ለማድረግ ጥሩ ስራ ተሰርቷል፡፡ ከዚህ በፊት በፀጥታ መደፍረስ ክልላችን ሰለባ ነበር፤ አሁን ችግሩ ተፈትቷል፡፡ በተረጋጋ ስሜት ውስጥ ሆነን የምናከብረው በዓል በመሆኑ፣ ኑ አብረን እናክብር፣ ተደስታችሁ ጥሩ ቆይታ አድርጋችሁ ትመለሳላችሁ --- የሚል መልዕክት አለኝ። አመሰግናለሁ፡፡      

Read 817 times