Print this page
Sunday, 23 December 2018 00:00

ፈቃድ ጠባቂ ፓርቲዎች!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(5 votes)

      ለሁሉም ጊዜ አለው ይባላል፡፡ ይህን ጊዜ ለማምጣት እኛም፣ እኛን የሚቃወሙን ክፍሎችም ተረባርበንበት ይሆናል፡፡ ዛሬ “አማራ ነኝ” ማለት እና በአመራርነት መደራጀት፣ እንደ ትናንቱ “የወያኔን መንገድ ተከተላችሁ፣ አገር አፍራሾች” በሚል አያስወቅስም፡፡
የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአሕድ) እስከ 1995 ዓ.ም ይተዳደርበት በነበረው ደንቡ ውስጥ፤ “የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅትን ደንብ የተቀበለና ለድርጅቱ አላማዎች መሳካት የሚታገል ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የድርጅቱ አባል መሆን ይችላል” ይላል። በዚህ አንቀጽ መሠረት፤ አማራ ያልሆኑ ትግሬዎች ነን ወይም ኦሮሞዎች ነን ብለው አባል የነበሩ ሰዎች ስለመኖራቸው እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ አማርኛ አቀላጥፈው የሚናገሩ፣ አማራ ነን ያሉ ግን አማራ ያልነበሩ፣ ብዙዎች የድርጅቱ አባሎች ግን  አውቃለሁ። እንዲያውም አንዱ የአዲስ አበባ መኢአድ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልም ሆነው ነበር፡፡ ጥርጣሬ ሲበዛባቸው በራሳቸው ጊዜ ራሳቸውን አገለሉ፤ ማለትም ተልዕኮአቸውን ፈጽመው ወደላካቸው ድርጅት ተመለሱ፡፡
እንዲህ አይነቱን መብት በሕገ ደንቡ የያዘው መአሕድ፣ የሌሎች ብሔረሰቦች አባል የማድረግ ዝንባሌው የመነጨው ከሁሉም በላይ የኢትዮጵያ አንድነት ተጠብቆ፣ ሕዝቧ በሰላም እንዲኖሩ ካለው ከፍተኛ መሻት ነው፡፡ መዐሕድ ወደ አገር አቀፍ የፖለቲካ ድርጅት እንዲለወጥ ዋናው የገፋው ምክንያት ይኸው ነበር፡፡
መአሕድ ወደ መላው ኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት ድርጅት (መኢአድ 1995) እንዲለወጥ ጠቅላላ ጉባኤው በሙሉ ድምፅ ወሰነ፡፡ አዲሱን ፕሮግራም አፀደቀ፡፡ ከጠቅላላ ጉባኤ አባላት አንዱ እኔ ነበርኩና፣ የስምና የፕሮግራም ለውጡ እንዲፀድቅ አንድ ጥያቄ አነሳሁ፡፡ ጥያቄው “አሁን እንደ ከዚህ ቀደሙ ስለ አማራ ሕዝብ ብቻ የምናስብ ድርጅት አይደለንም፤ የመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ጉዳይ ጉዳያችን ሆኖአል። በየቦታው የሚደረጉ የብሔር እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡ ወያኔ አገር አፍራሽ ነው፤ የኢትዮጵያ አንድነት ለእርሱ ጉዳዩ አይደለም። ጠቅላላ ጉባኤው ለሥራ አስፈፃሚው ሥልጣን ሰጥቶት፣ መኢአድ ከኦነግ ጋር ድርድር እንዲጀምር ቢደረግ?” የሚል ነበር፡፡ ኢንጂነር ኃይሉ ሻውልና ሌሎች ሰዎች በጥያቄው በጣም ተደናገጡ። ሁሉም ሰው አፈጠጠብኝ፡፡ “እንኳን ከኦነግ ጋር ለመደራደር ሞክረን እንዲያውም ወያኔ አላሰራን ብሏል” በሚል መልስ ጥያቄው ተዘጋ፡፡ እኔም በዚህ ጥያቄ ሳቢያ በተፈጠሩ ውዝግቦች ለአንድ ወር ለሚጠጋ ጊዜ ወደ ድርጅቱ ቢሮ እንዳልገባ ተከለከልኩ፡፡
ይህ ጥያቄ ዛሬም ቢሆን ልክ ሆኖ የማይታያቸው ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ጥያቄውን ያስታወስኩት ግን ዛሬም ከመንግሥት ፈቃድ የሚጠብቁ ፓርቲዎች በዝተው ስለሚታዩ ነው፡፡ እኔ በ2012 የሚጠበቀው አገር አቀፍ ምርጫ መካሄድ የለበትም ብለው ከሚያምኑ አንዱ ነኝ፡፡ ይህ ምርጫ ዝም ብሎ ምርጫ እንዲሆን አልፈልግም፡፡ እኔም ሆንኩ ሌላው ሕዝብም አይፈልግም፡፡ ዝም ብሎ ምርጫ የማይሆነው ደግሞ አቅም ያላቸው ማለትም ስምና ፈቃድ የያዙ ሁሉ ሳይሆኑ፣ ሕዝብን ከጎናቸው ማሰለፍ የሚያስችል በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ መስኮች አገርን የሚለውጥ፣ የተጠናና የታሰበበት እቅድ ያላቸው ፓርቲዎች ወደ ውድድሩ ሲገቡ ነው፡፡ ፓርቲዎች አገሪቱ አሁን ከአለችበት ቦታ አንስተው ከአንድ ከፍታ ላይ ለማድረስ አልመው የተነሱ፣ ግባቸውን ከርቀት እያዩ የሚራመዱ ሆነው ሲገኙ ነው፡፡
እያንዳንዱ የፖለቲካ ድርጅት በአባላቱ ዙሪያ የሚያደርገውን መንደፋደፍ አቁሞ ወደ ሕዝብ በመግባት፣  አላማና ግቡን ማሳወቅም ይኖርበታል። የማሳወቁ ስራ በእሱና በደጋፊዎቹ ክልል ብቻ ሳይወሰን ወደ ተቀናቃኞችም ድረስ መዝለቅ ይገባዋል፡፡ የእርሱ ተቀናቃኝ የሆኑትም ስለ እርሱ እንዲያውቁ ማድረጉ፣ የተቀናቃኙን ግፊት እንዲለዝብ ከማድረግም በላይ እዚያ ቤትም ወዳጅ ለማፍራት ያስችለዋል ተብሎ ይታሰባል፡፡
እኛ የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል ስለሌለን እንጂ ኢሕአዴግ የመንግሥት ሥልጣ አስረከቦ መሰናበት የነበረበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ይህን መንግሥት መምራት አልቻልኩም ብለው እጅ በሰጡበት ጊዜ ነበር፡፡ ሰሞኑን እየሰማናቸው ያሉት በሕግ እሥረኞች ላይ የተፈፀሙት ወንጀሎች ደግሞ ድርጅቱ ሕዝብ ሳይጠይቀው ጓዙን ጠቅልሎ ከፖለቲካው አለም ጨርሶ መውጣት ነበረበት ያስብላል፡፡ ኢ-ሰብአዊ ወንጀል በመፈፀምም በሕግ መጠየቅ ያለበት መንግሥት መሆኑ በደንብ ሊሰመርበት ይገባል፡፡
ወደ ተቀናቃኝ ፖለቲካ ድርጅቶች እንመለስ። የምርጫው ጊዜ መራዘም አለበት የለበትም በሚል  የሚከራከሩ ፓርቲዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ የምርጫው ጊዜ ተራዘመም አልተራዘመም ፓርቲዎች ግን እራሳቸውን ማዘጋጀት አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ በጋራ ችግራቸው ላይ በጋራ መንቀሳቀስ ይገባቸዋል፡፡ የፓርቲዎች ምዝገባ፣ የምርጫ ሕጉና የፀረ ሽብር ሕጉ እንዲሻሻል መሟገት አለባቸው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ችግር አንዳቸውንም የሚያሳስባቸውና የሚያባትታቸው ሆኖ አይታይም፡፡
ፓርቲዎቹ አጀንዳ አድርገው ከመንግሥት ጋር ሊደራደሩበት የሚገባው ሌላው ጉዳይ ከምርጫ በኋላ ያለው አዲሱን መንግሥት የመመስረቻ ጊዜ ነው። ከግንቦት እስከ መስከረም የመንግሥት ሥልጣን በተሸናፊ ፓርቲ እጅ የሚቆየው ለምንድነው? ብለው መጠየቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህን ጥያቄ ለማንሳት ከመንግሥት ፈቃድ ማግኘትን እስካልጠበቁ ድረስ፡፡

Read 7054 times