Saturday, 22 December 2018 13:37

ያሬዳዊው ሥልጣኔ

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(5 votes)

 ክፍል - ፫ ‹‹አዲሱ ሰው!!››
          
    ‹‹ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን ‹‹አዲሱን ሰው›› ልበሱ›› ኤፌ 4፡24፡፡
በየዘመናቱ የሰውን ልጅ ቀድሞ ከነበረበት የፖለቲካል ኢኮኖሚ፣ የሞራልና የመንፈስ ሁኔታ ወደ አዲስ ዓይነት ከፍታ ለማሸጋገር የተቀመሩ እሳቤዎችና የተደረጉ ሙከራዎች አሉ፡፡ እነዚህ እሳቤዎችና ሙከራዎች በአብዛኛው ሲቀመሩና ሲተገበሩ የነበረው ደግሞ በፈላስፎችና በሃይማኖት ሰዎች ነው፡፡
በእሳቤዎቻቸው ‹‹የአዲሱን ሰው›› እና ‹‹ማህበረሰብ›› ምፅአት ሲቀምሩ ከነበሩ ፈላስፎች ውስጥ ፕሌቶ፣ ኒቸ፣ ካርል ማርክስ እና ኦሾ የሚጠቀሱ ሲሆን፤ ከሃይማኖት ሰዎች ውስጥ ደግሞ ቡድሐ፣ እየሱስና መሐመድ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ይሄንንም ‹‹አዲሱ ሰው›› ፕሌቶ ‹‹በጎውና አዋቂው ሰው (Virtuous Person)›› ሲለው፤ ኒቸ፣ ካርል ማርክስ እና ኦሾ ደግሞ እንደ ቅደም ተከተላቸው ‹‹ልዕለ ሰብዕ (Super Man)››፣ ህብረተሰባዊ ሰው (Socialist Person)›› እና ‹‹የአዲሱ ሚሊኒየም አዲሱ ሰው›› ይሉታል፡፡
በዚህ ርዕስ ሥር በክርስትናና በፕሌቶ ፍልስፍና ውስጥ ‹‹አዲሱን ሰው›› ለመፍጠር የተቀመሩ እሳቤዎችንና የተደረጉ ጥረቶችን እንመለከታለን፡፡ እግረ መንገዳችንንም ‹‹የአዲሱ ሰው›› ፕሮጀክት የኢትዮጵያን ማህበረሰብ ከጥንታዊው የአክሱም ሥልጣኔ ወደ ያሬዳዊው ሥልጣኔ እንዳሸጋገረው እንቃኛለን፡፡
በፕሌቶ የሜታፊዚክስ፣ የሥነ ዕውቀት፣ የሥነ ምግባር፣ የሥነ ውበትና የፖለቲካ ፍልስፍና ውስጥ ዋነኛው ርዕሰ ጉዳይ ‹‹አዲሱን ሰው›› መፍጠር ነው፤ ይሄም አዲሱ ሰው የዕውቀትና የሞራል ልዕልናን የተጎናፀፈ ነው፡፡ ፕሌቶ ለዚህ የዕውቀትና የሞራል ልዕልና እንቅፋት ሆኖ ያገኘው ደግሞ የሰውን ልጅ ስሜትና ደመነፍሳዊ ባህሪ ነው፡፡ በመሆኑም፣ ፕሌቶ በፍልስፍናው ውስጥ አምርሮ ሲዋጋውና ሲጠየፈው የኖረው ነገር ቢኖር፣ የሰውን ልጅ ስሜትና ደመነፍሳዊ ባህሪ ነው፡፡ ለመሆኑ ፕሌቶ እንዴት ‹‹ስሜትና ደመነፍሳዊ ባህሪ የሰው ልጅ የሞራል ልዕልና እንቅፋቶች ናቸው›› የሚል ድምዳሜ ላይ ሊደርስ ቻለ?
ፕሌቶን ለዚህ ድምዳሜ ያበቃው በ399 ዓ.ዓ  እጅግ በሚወደው መምህሩ ሶቅራጠስ ላይ አቴናውያን የፈፀሙት ግፍ ነው፡፡ ሶቅራጠስ በወቅቱ ‹‹ወጣቶችን ለአመፅ ያነሳሳል፤ ወደ ከተማችንም አዳዲስ አማልክት ይዞ መጥቷል›› የሚል ክስ ከባለ ሥልጣናቱ ቀርቦበት ነበር፡፡ በወቅቱ ደግሞ የአቴንስ ዲሞክራሲ፣ የአቴናን የፍትህ ሥርዓት 500 አባላት ባሉት ሸንጎ የሚወሰን አድርጎት ነበር፡፡ እናም ከዕውቀት ይልቅ በስሜት የተነዱት የሸንጎ አባላት የሆኑት አቴናውያን፣ ሶቅራጠስን በቀረበበት ክስ ጥፋተኛ አድርገው በመርዝ እንዲገደል 279 በ221 በሆነ የአብላጫ ድምፅ ወሰኑበት።
ይሄ የአቴናውያን ውሳኔ ለፕሌቶ መቼም ቢሆን ይቅር የማይለው ብቻ ሳይሆን፣ አጠቃላይ የግሪክን ፍልስፍና ‹‹ስሜትና ዲሞክራሲ ጠል›› እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ከዚህም ባሻገር ውሳኔው ለፕሌቶ ‹‹የአቴናዊው ሰው›› እና ‹‹ማህበረሰብ›› ያጋጠማቸውን የሞራል መላሸቅ የሚያመላክት ነገር ነበረው፡፡ በመሆኑም፣ አቴናንና አቴናውያንን ከዚህ የሞራል ዝቅጠት ማላቀቅ፣ የፕሌቶ የህይወት ዘመን ፕሮጀክቱ ነበር፡፡ በዚህ ፕሮጀክቱ ውስጥ ‹‹ስሜት›› የሚባለውን ነገር እንዴት አድርጎ ከሰው ልጅ ህይወት ውስጥ ጠራርጎ እንደሚያስወጣው ሲያብሰለስል አንድ ድምዳሜ ላይ ደረሰ - ‹‹ብህትውና››ን መጠቀም!! ጀርመናዊው ፈላስፋ ኒቸ፣ ፕሌቶን ሲከሰው ‹‹በፕሌቶ ፍልስፍና ውስጥ ብህትውና የሌለበት ክፍል የለም፤ አጠቃላይ ፍልስፍናው ስሜትን፣ አካልንና ዓለምን የሚያወግዝ ነው›› ይለዋል፡፡
ብህትውና ለፕሌቶ የሰውን ልጅ ከእንስሳዊ (ደመነፍሳዊ) ዓለም ወደ የዕውቀትና የሞራል ልዕልና ማሸጋገሪያ መሳሪያ ነው፤ የ‹‹አዲሱ ሰው›› መፍጠሪያ መዶሻ ነው!! ‹‹አዲሱ ሰው›› (virtuous person) ለፕሌቶ ራሱን መግዛት የሚችል (moderate)፣ መንፈሰ ብርቱ (courageous) እና ምክንያታዊ (prudent) ነው፡፡ እነዚህ የ‹‹አዲሱ ሰው›› ባህሪዎች የሚገኙት ደግሞ ስሜትንና ደመነፍሳዊ ባህሪን በመጨቆን ወይም ደግሞ ብህትውናን በመጠቀም ነው፡፡
‹‹ስሜትና ደመነፍሳዊ ባህሪ የሰው ልጅ የሞራል ልዕልና እንቅፋቶች ናቸው›› የሚለውን ፕሌቶናዊ አመለካከት ክርስትናም ይጋራዋል፡፡ ስሜትንና ደመነፍሳዊ ባህሪ ለሞራል ልዕልና እንቅፋት ከሆኑ ደግሞ፣ ለመንፈሳዊ ህይወትም እንቅፋት መሆናቸው አይቀርም፤ ምክንያቱም፣ በክርስትና ውስጥ ‹‹አዲሱን ሰው›› በመፍጠር ሂደት ውስጥ ‹‹መንፈሳዊው ሰው›› የሚመጣው ‹‹የሞራል ሰው›› ከመጣ በኋላ ነው፡፡
ልክ እንደ ፕሌቶ ሁሉ ክርስትናም ‹‹ስሜትንና ደመነፍሳዊ ባህሪ ለሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ህይወት  እንቅፋቶች ናቸው›› ብሎ መነሳቱ እሱም ‹‹አዲሱን ሰው›› ለማምጣት በሚያደርገው ጥረት ውስጥ ብህትውናን እንደ መሳሪያ እንዲጠቀም አድርጎታል፡፡
ሆኖም ግን፣ የፕሌቶና የክርስትና ‹‹አዲሱ ሰው›› የተወሰነ ልዩነት አላቸው፡፡ የፕሌቶ ‹‹አዲሱ ሰው›› መዳረሻው ዕውቀትንና በጎነትን (knowledge and moral virtue) ያጣመረ ሰው ማስገኘት ሲሆን፣ ክርስትና የሚያልመው ‹‹አዲሱ ሰው›› ሰው ግን ከበጎነት ባሻገር ያለውን ‹‹መንፈሳዊ ሰው›› ነው፡፡ መንፈሳዊው ሰው ከበጎው ሰው በኋላ የሚገኝ ነው፡፡ በመሆኑም፣ ፕሌቶናዊው ብህትውና በጎው ሰው እስኪገኝ ድረስ የሚቀጥል ሲሆን፣ ክርስትያናዊው ብህትውና ግን ከበጎው ሰው በኋላም መንፈሳዊው ሰው እስኪመጣ ድረስ ይቀጥላል፡፡ በመሆኑም፣ በክርስትና ውስጥ ያለው ብህትውና በፕሌቶ ውስጥ ካለው ብህትውና ጠንከር የሚለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡
የልዩነቱ መነሻ ፕሌቶናዊው ፍልስፍናና ክርስትና ለሰው ልጅ ‹‹አካል›› ያላቸው አመለካከት የተወሰነ ልዩነት ስላለው ነው፡፡ ፕሌቶ ‹‹አካል ያልተገሩ ስሜቶች ማጠራቀሚያ ነው›› ሲል፤ ክርስትና በበኩሉ ‹‹አካል ያልተገሩ ስሜቶች ማጠራቀሚያ ብቻ ሳይሆን፣ የእርኩስ መናፍስትም መናኸሪያ ስፍራ ነው›› ብሎ ያስባል፡፡ በመሆኑም፣ ክርስትና የሚያልመው ‹‹አዲሱ ሰው›› ከአካሉ አውሬያዊ ስሜቶቹን የገራ ብቻ ሳይሆን ከውስጡ እርኩስ መናፍስትንም ያባረረ ጭምር ነው፡፡
በፕሌቶናዊው ፍልስፍና ‹‹አዲሱን ሰው›› ለማምጣት ‹‹ራስን መግዛት›› ወይም ‹‹ስሜትን መቆጣጠር›› (moderation) በቂ ነው፤ ይሄ ተግባር የሚመራው ደግሞ በአመክንዮ ነው፡፡ ክርስትና የሚያልመው ‹‹አዲሱ ሰው›› ግን ‹‹ራስን በመግዛት›› ብቻ አይመጣም፤ ‹‹ራስን ከመግዛት›› በተጨማሪ ነፍሱም መንፃት አለበት፤ ሂደቱ የሚመራው ደግሞ በአመክንዮ ሳይሆን በእምነት ነው፡፡
ይህ ‹‹አዲሱን ሰው›› የመፈለግ ሃይማኖታዊና ፍልስፍናዊ ፕሮጀክት እንዲሁ ተራ ቅዠት እንዳይመስላችሁ፤ ፕሮጀክቱ በውስጡ የሜታፊዚክስ፣ የሥነ ዕውቀት፣ የሥነ ምግባርና የሥነ ውበት አስተሳሰቦችን አሟልቶ የያዘ ስለሆነ፣ ከግለሰብ አልፎ ማህበረሰቦችን እንደ አዲስ የመፍጠርና የማነፅ ኃይል አለው፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ‹‹የአዲሱ ሰው›› ፕሮጀክት በግለሰብ ደረጃ አዲስ ማንነትንና አስተሳሰብን በመፍጠር ብቻ የሚወሰን ሳይሆን፣ ‹‹አዲስ ማህበረሰብን›› እና ‹‹አዲስ የሀገር ግንባታ›› ፕሮጀክትንም የሚያልም ሐሳብ ነው፡፡ በጥንታዊ ግሪክ ሥልጣኔና በክርስትና መካከል የነበረው ፉክክርም የዚሁ ‹‹የአዲሱ ሰው›› ፕሮጀክት ውድድር ነው፡፡
ክርስትና ይዞት የመጣው ‹‹የአዲሱ ሰው›› ፕሮጀክት አነሳሱ፣ የግሪኩን ‹‹የአዲሱ ሰው›› ፕሮጀክት የሚገዳደር ነበር፡፡ በስተመጨረሻም፣ ክርስትና ይዞት የመጣው ፕሮጀክት ብዙ ተከታዮችን ማፍራት ስለቻለ፣ የግሪኩ ‹‹አዲሱ ሰው›› ፕሮጀክት በተሸናፊነት ተጠናቀቀ፡፡ ክርስትና ይዞት የመጣው ‹‹የአዲሱ ሰው›› ፕሮጀክትም ለ1000 ዓመታት በአውሮፓ ብቸኛው ገዥ ሐሳብ ሆነ። የኒቸ ‹‹የልዕለ ሰብዕ›› ሐሳብ አነሳስም የክርስትናን ‹‹አዲሱ ሰው›› ፕሮጀክት ለመተካት ታልሞ የመጣ ሐሳብ ነው፡፡
እናም፣ ይሄ ‹‹የአዲሱ ሰው›› ፕሮጀክት ተፅዕኖው ነባር ሥልጣኔዎችን አንኮታኩቶ፣ በአዳዲስ ሥልጣኔዎች እስከ መተካት የሚደርስ ኃይል እንዳለው አሳይቷል፡፡ ይሄም ነገር በግልፅ የታየው ደግሞ በአውሮፓ ብቻ ሳይሆን፣ በኢትዮጵያም ውስጥ ነው፡፡
ክርስትና (በተለይም የብህትውና ክርስትና) ወደ እኛ ሀገር ሲገባ፣ በዋነኛነት ይዞት የመጣው ነገር ነባሩን የአክሱም ሥልጣኔ የሚገዳደር ‹‹የአዲሱ ሰው›› ፕሮጀክት ነው፡፡ ይሄም ፕሮጀክት በሂደት ብዙ ተከታዮችን ማግኘት በመቻሉ ጥንታዊውን የአክሱም ሥልጣኔ ሙሉ በሙሉ በመተካት፣ በኢትዮጵያ ብቸኛና ገዥ ፕሮጀክት ለመሆን ቻለ፡፡ ዶ/ር እጓለ ገብረ ዮሐንስም፤ ‹‹ያሬዳዊው ሥልጣኔ›› የሚሉት ይሄንኑ ከ6ኛው ክ/ዘ ጀምሮ ገዥ በመሆን የወጣውን ‹‹የአዲሱ ሰው›› ፕሮጀክት ነው፡፡ እናም በዚህ ‹‹በአዲሱ ሰው›› ፕሮጀክት የተወለደው ያሬዳዊው ሥልጣኔ፤ ‹‹ያሬዳዊውን ሰውና ማህበረሰብ›› ፈጥሯል - እስከ አሁን ዘመን ድረስ የዘለቀውን የኢትዮጵያ ማህበረሰብ!!!
ከአዘጋጁ፡- ብሩህ ዓለምነህ፤ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር ሲሆን “የኢትዮጵያ ፍልስፍና”  መጽሐፍ ደራሲ ነው፡፡ ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1520 times