Saturday, 22 December 2018 13:38

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(5 votes)

 “--ማንነት ለሰው ልጅ ፅድቅና ኩነኔው ነው፡፡ ሰው ራሱን ሆኖ ሲገኝ፣ መልካምነት ዐመሉ ሲሆን ጽድቁን ይኖራል፡፡ ህሊናውን የሚፈታተን ዕኩይ ተግባር ሲያዘወትር ኩነኔውን ይኖራል፡፡ መልካምነት እውነት ነው፡፡ እውነት ደግሞ ጉልበት አለው፡፡ ነፍስን እያለመለመ ውስጥህን ደስ ያሰኛል፡፡--”
          
     “ነፍሱን አይማረው!” ይላል ያገራችን ሰው፤ ጨካኝ ሲያጋጥመው፡፡ … ወይ ደግሞ ሲሰማ፡፡ … በአሁኑ ወቅት የአገራችንን ክፉ ሰዎች እያየን ነው፡፡ (ለጊዜው ተጠርጣሪዎች እንበላቸው!) እናላችሁ ሰውዬ ክፉ ነው። የክፉዎች ክፉ!! ... ኢትዮጵያዊ አዶልፍ ሄክማን!! … ከቀድሞ ባለስልጣናት አንዱ ነው፡፡ “ፈስ ያለበት ዝላይ አይችልም” እንደሚሉት ሆነና ራሱን ሸሸገ። አጋጣሚ ሆኖ አማልክቶቹ ስለ ሰው ልጅ ጭካኔ ሲጨዋወቱ፤ ክፉኛ ስቅ ብሎተ ሞተ፡፡ መልዓከ ሞት ተንከባክቦ ሰማይ ቤት አደረሰው፡፡ ሃጢአቱ ተመዝኖ፣ ዘለዓለማዊ ፍርዱን ሊቀበል ከሌሎች ሙታን ጋር ተሰልፎ ተራውን ሲጠባበቅ፣ ሃይለኛ ነፋስ ነፈሰ፡፡ አማልክቶቹ ዓይናቸውን ጨፍነው ሲከፍቱ፣ የሰውየው ነፍስ ከነበረችበት ዕልም ብላለች፡፡ ገነትና ገሃነም ተበረበሩ፡፡ አልተገኘም፡፡ ህዋ ውስጥ ለሚገኙት ሌሎች ዓለማት መልዕክት ተላከ፡፡ እኛ ጋ አልመጣም አሉ። ነፋስ ተጠርቶ ተጠየቀ፡፡ … አላየሁም ብሎ ዋሸ። ወሬው እግዜር ጆሮ ደረሰ፡፡ … ዲያብሎስን ጥሩልኝ ብሎ አዘዘ።…
“አቤት ጌታ ሆይ! ፈለግኸኝ” አለ፣ እንደመጣ፡፡
“የት ነው የደበቅኸው?”
“ማንን?”
“ማንን?... የእንጀራ ልጅህን ነዋ!”
ዲያብሎስ እራሱን አከክ፣ አከክ እያደረገ… “ምን ያስደብቀኛል?.. የራሴ አይደለም እንዴ?” በማለት መለሰ፡፡
እግዜርም… “እሱ ያንተ አይደለም፣ አንተጋማ ይመቸዋል፣ ሌላ ገሃነም እሰራለታለሁ” አለ፡፡
 አጅሬ ዝም፡፡
“ከደበቅህበት አውጣው! አለዚያ በሱ ፋንታ ትገባለህ!” አለ እግዜር እየተቆጣ፡፡
ዲያብሎስም ደረቱን ለሁለት ከፍሎ፣ ጥቁር ልቡን እየጨመቀ … “እየው፤ እኔ ጋ የለም” አለ፡፡
“ታዲያ የት ነው?”
ዝም፡፡
እግዜር ተናደደ፡፡
ከዙፋኑ ብድግ ሲል፤… “ቆይ ተረጋጋ--” አለና ላቡን እየጠረገ፤
“ምናልባት ወላጅ አባቱ ጋ ይሆናል” ሲል ፍንጭ ሰጠ፡፡ ዲያብሎስ እየተንቀጠቀጠ፡፡
“አባቱ ማነው?”
እያቅማማ ነገረው፡፡ እማይጠረጠር ቦታ ነበር የደበቀው፡፡ ያውም ሃያ አራት ሰዓት ጥበቃ እየተደረገለት፡፡ … የት ይሆን?
***
 “ፅድቅና ኩነኔ … ቢኖርም፣ ባይኖርም …”
ወዳጄ፡- ሰው በሥራው፣ በባህሪው ከአንደበቱ በሚወጣው ቃላትና በገፅታው ብርሃን ማንነቱ ይንፀባረቃል፡፡ ማንነት ለሰው ልጅ ፅድቅና ኩነኔው ነው፡፡ ሰው ራሱን ሆኖ ሲገኝ፣ መልካምነት ዐመሉ ሲሆን ጽድቁን ይኖራል፡፡ ህሊናውን የሚፈታተን ዕኩይ ተግባር ሲያዘወትር ኩነኔውን ይኖራል፡፡ መልካምነት እውነት ነው፡፡ እውነት ደግሞ ጉልበት አለው፡፡ ነፍስን እያለመለመ ውስጥህን ደስ ያሰኛል፡፡ ክፋት፡- የፍርሃት፣ የተጠራጣሪነት፣ የተሸናፊነትና በራስ ያለመተማመን ስሜት ይፈጥራል፡፡ ክፋትን እያዘወተሩ “ልክ ነኝ” ማለት ህመም ነው፡፡
ብዙ ሊቃውንቶች “we are what we repeatedly do” በሚለው የፍሬዴሬክ ኒችና በመሰሎቹ አስተሳሰብ ይስማማሉ፡፡ “ሰው ለሚሰራው ስራ ኃላፊነት መውሰድ እንዳለበት፣በሰይጣንም ሆነ በእግዜር፣ በስርዓትም ሆነ በሌሎች ነገሮች ማሳበብ እንደማይችል አጥብቀው ያሳስባሉ፡፡ ኢን-ዲተርሚኒስት አቋም ያላቸው ሁሉ የዚህ አስተሳሰብ አቀንቃኞች ሲሆኑ ኤግዚስቴንሺያሊስቶቹ ግን በዋናነት የፍልስፍናቸው ምሰሶ አድርገውታል፡፡
ወዳጄ፡- እኔ እንደሚገባኝ፤ገነትና ገሃነም ወይም ፅድቅና ኩነኔ ከያንዳንዱ ግብርና ድርጊታችንን ተከትሎ፣ የሚሰማን ስሜት (State of Mind) እንጂ የቦታ ስሞች አይደሉም፡፡ ገነት መልካምነት፣ ክፋት ገሃነም ነው፡፡ ድርጊታችን እንደ ሪሞት ኮንትሮል እየመራ፣ ነፍሳችንን በሁለቱ የስሜት ጋሪዎች እየኮረኮረ፣ መንፈሳችንን እየናጠ፣ አንዴ አውሬ፣ አንዴ ሰው ያደርገናል፡፡ አውሬ ስንሆን ከጎናችን ሰው እንዳለ፣ ሰው ስንሆን ከጎናችን አውሬ እንዳለ እንረሳለን፡፡ ነገር ግን ሁለቱንም እያፈራረቅን ሆነን ከመገኘት አናመልጥም፡፡ … ያውም በየቀኑ፣ በየሰዓቱ … ምናልባትም በደቂቃዎች ልዩነት!!
ወዳጄ፡- አገርህ ላይ ክፉ መንግሥት፣ በራስህ ላይ ክፉ አለቃ፣ አጠገብህ ክፉ ጎረቤት፣ በትዳርህ ላይ ክፉ ባል ወይም ክፉ ሚስት ካጋጠመህ ገሃነብ ነው፡፡ አጋጣሚው ሲገለበጥ ደግሞ ገነት ይሆናል። … ለማንኛውም “ገነትህን ለማስከበር፣ ነፃነትህን ለማረጋገጥ፣ ራስህን ሆነህ ለመኖር የመንፈስ አጥር (aura) መገንባት ያስፈልግሃል” የሚሉ ብዙ ጠቢባን ያጋጥሙሃል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ሰብዕና፤ ሼክስፒር በሃምሌት፣ አርስቶትል በወርቃማው ህጎቹ፣ ኖቼ በዛራቱስትራ እንዲሁም ሌሎች በራሳቸው መንገድ ገልፀውታል፡፡ ጀምስ ኤ. ሚሽነር ደግሞ “በትክክል አስብ፤ የምትሰራው ጠቃሚ ከሆነ ስራ፤ በደንብ ስራ፣ ወደ ኋላ የማትልበትን፣ የማታቅማማበትና የማትደራደርበትን ጉዳይ ለይተህ ዕወቅ፤ ለራስህ ታማኝ ሁን፣ የሃሳብህን ጉልበት፣ ለጥበብ ያለህን ፍቅር፣ የተስፋህን ርቀት መዝነው፡፡ ለምትወዳት ሴት እንኳ ምን ያህል ራስህን መስጠት እንዳለብህ ድንበር አበጅለት፤ ያንተ ገነት እሱ ነው፡፡” በማለት ይመክረናል። የመጨረሻዋን ዓረፍተ ነገር የጨመረልን የዡሊየት ፍቅርና የዴዚዲሞና ንፅህና ዓይነቶች እንዳሉ ሆነው፣ ውበታቸውን ለስለላ የተጠቀሙበት፣ የሳምሶኗ ደሊላና የምስሯ ክሌዎፓትራ ዓይነት ሴቶች መኖራቸውን ለማስገንዘብ ይመስለኛል፡፡ በኛም ሃገር በ‹አገር ደህንነት› ስም ዜጎችን ሲያሸብር የነበረው ተቋም፤ እየከፈለ የሚጠቀምባቸው አደገኛ ሴቶች እንደነበሩ ሰምተናል፡፡ (Call girls እንዳሉ ሆነው!)
***
ወደ ጨዋታችን እንመለስ፡፡ እግዜር ዲያብሎስን በማፋጠጥ የወንጀለኛው ነፍስ የት እንደተደበቀች እንዲነግረው ማስገደዱን፣ አለበለዚያ በሱ ቦታ፣ራሱ እንደሚገባ እንዳስጠነቀቀው፣ ዲያብሎስም “ስራው ያውጣው” በማለት መንፈሱ የተደበቀበትን ቦታ እንደጠቆመ ተጨዋውተናል፡፡ ሰይጣን እንኳ በራሱ ሲመጡበት፣ ወንጀለኛ ወዳጆቹን አሳልፎ ከመስጠት ወደ ኋላ አይልም፡፡ ዲያብሎስ ከነፋስ ጋር ተመሳጥሮ፣ የወንጀለኛውን ነፍስ በማይጠረጠር ቦታ ነበር የደበቃት፡፡ ለሃገር አንድነትና ነፃነት በተዋደቁ ታላላቅ ኢትዮጵያውያን፣ ታላላቅ የጥበብ፣ የፖለቲካና የአስተዳደር ሊቃውንቶች መሃል፡፡ በታላቁ ካቴድራል ቅጥር ግቢ በሚገኝ መካነ መቃብር ውስጥ!!
ወዳጄ፡- “ወንጀለኛ ካልተቀጣ ያጠፋ አይመስለውም” ይባላል፡፡ ህግን መሰረት ያደረገ ቅጣት እንደ ክፉ ነገር መቆጠር የለበትም፡፡ ባለቅኔው እንዳለው፤ በፊደል ‹ሀ› ብሎ ያልተማረ፣ “ዋ” ብሎ በአሰር ይማራል፡፡ … “የእንቁላሉ ጊዜ በቀጣሽኝ--” ዓይነት!!
በነገራችን ላይ ታላቁ ቶማስ ጄፈርሰን … “That gov’t is best which governs least” ብሎ ነበር፤ የዜጎችን ነፃነት ክብር በገለፀበት ወቅት፡፡ “እንደ ሾህ ከሚዋጉ የሰላይ ዓይኖች ልደት ይሻለኛል” ያለውንስ ታውቀዋለህ? ደራሲ ሚካኤል ሌርሞንቶቭ ነው፡፡ ራሴ ጠይቄ፣ ራሴ ብመልስ ምን ይለኛል!!
ሠላም!!!

Read 1188 times