Saturday, 22 December 2018 13:41

አዳም ረታ እና የኤግዚስቴንሻሊዝም ፍልስፍና

Written by  መኮንን ማንደፍሮ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(18 votes)


     ክፍል አንድ
በምዕራባዊያን የፍልስፍና ታሪክ ውስጥ እንደ ኤግዚስቴንሻሊዝም (existentialism) በኪነ-ጥበባዊ ሥራዎችና በግለሰባዊ የአኗኗር ባህል ላይ ታላቅ ተፅእኖን የፈጠረ ፍልስፍና የለም፡፡ የዚህ ፍልስፍና ዋና የጥናት ትኩረት የሰው ልጅ ነው፡፡ በመሠረታዊነትም ግለሰብን ማዕከል አድርጐ፣ በህልውና ውስጥ ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎችን ያጠናል፡፡
የኤግዚስቴንሻሊዝም ፍልስፍና የተነሳው በዋናነት የተፈጥሮአዊነትን (naturalism) እና የሐሳባዊነትን (idealism) ሜታፊዚካል መርህ በመቃወም ሲሆን ከፍሬዲሪክ ሺለር የሰብአዊነት ፍልስፍናዊ እሳቤ ጋር ተቀራራቢነት አለው፡፡
ኤግዚስቴንሻሊዝም የምዕራባውያን ፍልስፍና የቆመበትን የስፔኩሌቲቭ ፍልስፍና (speculative philosophy) የሚተች የፍልስፍና ፅንፍ ሲሆን የዚህ አይነቱ ፍልስፍና ዐቢይ ትኩረት፤ ከነባራዊ የሰው ልጅ ህላዌ መሠረታዊ ተግዳሮቶች እጅግ የራቀ እንደሆነ ይገልፃል፡፡ እንደ ኤግዚስቴንሻሊስቶች አመለካከት፤ የፍልስፍና መሠረታዊ አላማና ትኩረት የሰውን ልጅ ማዕከል ያደረገ መሆን ይገባዋል፡፡ ፍልስፍናው ከጥንታዊያኑ ታላላቅ የግሪክ ፈላሥፎች ጀምሮ እስከ መካከለኛው ዘመን ድረስ የዘለቀ ታሪካዊ መሠረት ያለው ሲሆን ይበልጥ ገናና የሆነው ግን በሃያኛው ክፍለ ዘመን ነው፡፡
ኤግዚስቴንሻሊዝም የጥናት ትኩረቱን በዋናነት ያደረገባቸው ብዙ ርእሰ ጉዳዮች ሲኖሩ ከእነዚህ መካከል ስለ ሰው ልጅ የነፃነት ወሰን፣ ግለሰባዊ ኃላፊነት፣ ቋሚና ተፈጥሮአዊ የሆነ ሰብአዊ ማንነት አለመኖር (the nonexistence of fixed human essence)፣ ሞት፣ እውነተኝነት፣ ብቸኝነት፣ እኩይ ሥነ-ልቦናዊ አመለካከት (bad faith)፣ ስለ ህልውና ትርጉም አልባነት (absurdity)፣ ከግለሰባዊ ማንነት በፊት ህልውና እንደሚቀድም (existence precedes essence)፣ ቀቢፀ-ተስፋ (despair)፣ ባይተዋርነት (strangeness)፣ ጭንቀት (anguish)፣ ከግለሰብ አቅምና ነፃ ፈቃድ ውጪ የሆነ ግለሰባዊ ማንነትንና ሁኔታን የመወሰን ሥልጣን ያለው አካል አለመኖር  (the nonexistence of determinism) እና ሌሎች ርእሰ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል፡፡
የዚህ ጽሑፍ ዋና አላማ በዘመናዊው የአማርኛ ቋንቋ ሥነ-ጽሑፍ ላይ ዐቢይ ተፅእኖውን ባሳደረው ታላቁ ደራሲ አዳም ረታ የፈጠራ የሥነ-ጽሑፍ ሥራዎች ውስጥ የሚገኙትን መሠረታዊ የኤግዚስቴንሻሊዝም ፍልስፍና ፅንሰ-ሐሳቦች መዳሰስ ነው፡፡
አዳም ረታ ዘመናዊውን የአማርኛ ቋንቋ ሥነ-ጽሑፍ ረጅም ርቀት ያሻገረ፣ ተለምዶአዊውን የልብወለድ ድርሰት አጻጻፍ አካዳሚያዊ ሕግ የሻረ፣ በምትኩም አዳዲስ የአጻጻፍ ዘይቤዎችን ያስተዋወቀ ታዋቂ ደራሲ ነው፡፡  የፈጠራ የሥነ-ጽሑፍ ሥራዎቹ ከብዙ አካዳሚያዊ የጥናት መስኮች (interdisciplinary) አቅጣጫ መተንተን የሚችሉ ናቸው፡፡ ሥራዎቹ ፍልስፍናዊ እሳቤዎችን፣ ሥነ-ማህበረሰባዊ ጉዳዮችን (sociological subjects)፣ ታሪክን፣ ሰብአዊ ሥነ-ልቦናዊ ጉዳዮችን፣ ኃይማኖትንና ፖለቲካን  በዋናነት አጠቃለው የያዙ ናቸው፡፡
የአዳም የፈጠራ ሥራዎች ኢትዮጵያዊነት የሚፈተሽባቸውን አጠቃላይ ህልውናዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ገፀ-ባሕርያቱን መሠረት አድርገው ከታሪክ፣ ከባህል፣ ከሥነ-ልቦናና ከፖለቲካ አንፃር ያስቃኙናል።  እነዚህን አጠቃላይ ህልውናዊ ነባራዊ ሁኔታዎች የሚፈተሽባቸውን መንገዶች ተከትለን ከምዕራባዊያን በተወረሰ ማንነት፣ የዕውቀትና የእምነት የአስተሳሰብ መሠረት (eurocentrism) እና የኢትዮጵያዊነት አሻራ የሚንፀባረቅበት አጠቃላይ የህላዌ ርዕዮተ-ዓለም (ethiocentrism) መካከል ያለውን ልዩነትና ግጭት እንረዳለን፡፡  የኢትዮጵያዊነት አሻራ የሚንፀባረቅበት የህላዌ ርዕዮተ-ዓለም (ethiocentric world view) በገፀ- ባሕርያቱ ግላዊ ሥነ- ልቦናዊ ሁኔታዎች፣ ሥነ-ማህበራዊ ትስስሮችና ኃይማኖታዊ እሳቤዎች አማካኝነት ተገልፀው ይገኛሉ፡፡
የፍልስፍናንና የሥነ-ጽሑፍን ጥብቅ ቁርኝት ተከትሎ ፈላስፋው በደራሲው ሥራ ላይ ወይም ደራሲው በፈላስፋው እሳቤ ላይ ተፅእኖን የማሳደሩ ሐቅ ተለምዶአዊ ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የተለያዩ የኤግዚስቴንሻሊዝም ፍልስፍና ፅንሰ- ሐሳቦችን በአዳም ረታ የፈጠራ ድርሰቶች  ውስጥ እናገኛለን፡፡
ኤግዚስቴንሻሊዝም የሰው ልጅ ህልውና ከማንነቱ መገለጫ ባሕሪው ይቀድማል (existence precedes essence)  የሚለውን ሜታፊዚካዊ መርህ አፅንኦት ሰጥቶ የሚሰብክ ፍልስፍና ሲሆን ቀደም ብሎ በብዙ ፈላስፎች ትምህርት ውስጥ ትልቅ ቦታ የነበረውን የሰው ልጅ ማንነት መገለጫ ባሕርይ ከህልውናው ይቀድማል (essence precedes existence) የሚለውን የኢሴንሻሊዝም (essentialism) ሜታፊዚካዊ አመለካከት ይቃረናል፡፡ ታዋቂዎቹ የግሪክ ፈላስፎች ኘሌቶና አሪስቶትል የዚህ ሜታፊዚካዊ አሳቤ ዋና አራማጆች ናቸው፡፡ ኘሌቶ በዚህ ዓለም ያለው ነገር ሁሉ ቋሚ (ዘላለማዊ) የሆነ መገለጫ ባሕርይ (eternal essence) አለው ብሎ ያምናል፡፡ ለኤግዚስቴንሻሊዝም ፍልስፍና አራማጆች፤ ይህ አይነቱ እሳቤ ፍፁም ስህተት ነው፡፡ እንደ ሳርተር አመለካከት፤ የሰው ልጅ እንደ ግኡዛን ቁሳዊ ነገሮች (nonconscious corporeal beings) ሊለወጥ የማይችል ቋሚ የሆነ ተፈጥሮአዊና ታሪካዊ ማንነት (መገለጫ ባሕርይ) የለውም፤  ነገር ግን ግለሰቡ በራሱ ምርጫና ኃላፊነት ማንነቱን ይፈጥራል። በዚህም አቅሙ ጠቅላላ ነባራዊ ሁኔታዉን ሳይገነዘብ በፊት ተቀብሎት ከነበረው (ማህበረሰቡ ከሰጠው) የማንነት መገለጫ ወጥቶ አዲስ ማንነትን መላበስ ይችላል፡፡ ይህን አመለካከት ማርቲን ሃይዲገርም ይደግፈዋል፡፡ እንደ ሃይዲገር እሳቤ፤ የጥንታዊው ፍልስፍና ዐቢይ ሜታፊዚካዊ ችግር፣ የሰው ልጅ ወደ ህልውና ከመምጣቱ በፊት በተፈጥሮ የተሰጠው ቋሚ የሆነ ማንነትና መገለጫ ባሕርይ እንዳለው አድርጐ ማቅረቡ ነው፡፡  በተቃራኒው የሰው ልጅ የማይለወጥ ተፈጥሮአዊ ማንነት (fixed human essence) የለውም፡፡  በተመሳሳይ መልኩ በአዳም የልብወለድ ሥራዎች ውስጥ የሚገኙት ገፀ-ባሕርያት፤ የቀደመ ታሪካዊና ሥነ-ልቦናዊ ማንነታቸውን (essence) ቀይረው አዲስ ሰብዕናን ሲላበሱና አዲስ ኑሮን ሲመሠርቱ እናገኛቸዋለን፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነን በደራሲው ተጠቃሽ መፅሐፍ “አለንጋና ምስር” የአጭር ልብወለድ ስብስብ ሥራ ውስጥ “ኦቾሎኒ” በተሰኘው ትረካ ውስጥ የሚገኘው ዋና ገፀ-ባሕርይ ስምኦን ነው። ስምኦን በእኩይ ሥነ-ልቦናዊ እምነት (bad faith) ውስጥ እያለ ማህበረሰቡ የሰጠውን መገለጫ (የመልኩን አስቀያሚነት) አምኖ ተቀብሎ በማንነቱ የሚሸማቀቅ፣ በራስ መተማመኑ የተሸረሸረ ግለሰብ ነበር፡፡
“…እድሜዬ አሥራ አራት እስኪደርስ በመልኬ እሰደብ ነበር (በኋላም ቀረልኝ ማለት ሳይሆን)፡፡ እኔም ተጨባጭ መረጃ ይዤ ከመከራከር ይልቅ የተባልኩትን በመስማት፣ ሰምቼም በማመን ዝቅተኛነት የወረረኝ፣ አስቀያሚ የተባለ ፊቴን ሰው ፊት በኩራትና በራስ መተማመን ማሳየት የሚከብደኝ ነበርኩ፡፡ የሥነ ልቦና በሽታ በሉት ብትፈልጉ… ‘አስቀያሚ’ ተብዬ መሰየሜ የፈጠረብኝን አጥንቴ ድረስ የተጠለለውን የውርደት ስሜት፡፡ ይኼን ኘሮፓጋንዳ የትኛው ጐረቤቴ ወይም የቤተሰብ አባል አውጥቶልኝ አምኜ ተከትዬው፣ እኔን የወጣትነት ጨለማ ውስጥ እንደከተተኝ አላውቅም።  የማውቀው ማፈሬን ነው…” (አዳም፣ 2ዐዐ4፡ 232-233)
“…በተለያየ ቴክኒክ፣ ባልገባኝ ብልጠትም የማላውቃቸውና የማያውቁኝ ሰዎች የሰሩኝ ቅኝ ግዛት ነበርኩ…”   (አዳም፣ 2ዐዐ4፡ 239)
እዚህ ታሪክ ውስጥ ስምኦን ግላዊ ሕይወቱን ለመቀየር ያለውን ነፃነትና ሚና በመረዳትና ኃላፊነቱን በመውሰድ ከእኩይ እሳቤ (bad faith) ወጥቶ ማንነቱን በመለወጥ ማድረግ ይፈልግ የነበረውን ነገሮች ሲያሳካ እናያለን፡፡ በ ታሪኩ ውስጥ የተገለፀችውን ሴት በፍቅር መማረኩና ከሌሎች ብዙ ሴቶች ጋር ፆታዊ ግንኝነትን መፍጠር መቻሉ የዚህ ጥረቱና ስኬቱ አንዱ ማሳያ ነው፡፡
“…የኔውኑ ከሲኒማ ቤት ወጥቼ የሆነ መአት ሕዝብ በሚመላለስበት ቡና ቤት፣ መአት ሕዝብ ባለበት… ሴትና ወንድ… ማንም ፊት ለፊት እንድታይ ሆኘ መቀመጥ ፈለግሁ፡፡ በአስጠላችኝ፣ በጠላችኝ የከተማዬ መንገዶች መጓዝ ፈለግኩ፡፡ እያፏጨው፣ እየዘፈንኩ…” (አዳም፣ 2ዐዐ4፡ 239)
“…በጐዳናዎች፣ በከተማው የሚታይ ሎጋ ሆኜ ወጣሁ፡፡ … እና እየቆየ በራስ መተማመኔ እያደገ ሌላ ሴት እንደሚፈልገኝ፣ አንደሚያየኝ ስረዳ ትሰለቸኝ ጀመር፡፡ … እኔ በተገኘው ክፍት ቦታ ሌሎች ሴቶችን ማማለል ወጣሁ፡፡ ብዙ ቀላቀልኩ፡፡ ቀድሞ ችላ የሚሉኝ የሚመስለኝን ደፈርኩ…” (አዳም፣ 2ዐዐ4፡ 241)
ግለሰባዊ ነፃነት (freedom of the subject) ሌላኛው ዐቢይ የኤግዚስቴንሻሊዝም ፍልስፍና መገለጫ ነው፡፡ እንደ ሳርተር እሳቤ፤ እያንዳንዱ ግለሰብ መሆን የሚመኘውን ለመሆን ፍፁም ነፃነት ያለው ሲሆን ይህ ነፃነቱም ሊሸሸው የማይችል ሐቅ ነው፡፡ እንደ እሱ እምነት፤ ሰው ነፃ አለመሆን አይችልም፤ ምክንያቱም ነፃ እንዲሆን ተፈርዶበታል፡፡ እያንዳንዱ ግለሰብ ለገዛ ህልውናው ኃላፊና ጌታ ነው፡፡ በሌላ አገላለፅ፤ ግለሰቡ የራሱ እግዜር ነው፡፡ በሕይወቱ አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታና ዕጣ ፈንታ ላይ እግዜር፣ ተፈጥሮና ማህበረሰብ አንዳችም ተፅእኖና ሚና የላቸውም፤ ግለሰቡ ይህን ግላዊ ሥልጣን በእኩይ እሳቤ (bad faith) ወድቆ ለእነዚህ አካላት አሳልፎ ካልሰጠ በቀር፡፡ ለግላዊ ኑሮ ነባራዊ ሁኔታ እነዚህን ውጫዊ አካላት ተጠያቂና ባለሙሉ ሥልጣን አድርጐ መቀበል፣ ራስን መዋሸት (self deception) እንደሆነ ሳርተር ይገልፃል፡፡
በኤግዚስቴንሻሊዝም ፍልስፍና አራማጅ ፈላስፎች፣ ግላዊ ሕይወትና በፈጠራ የሥነ-ጽሑፍ ሥራዎቻቸው ውስጥ በሚገኙት ዋና ገፀ-ባሕርያት ውስጥ ማህበራዊ ገዥ እሴቶችን (societal moral sanctions) የመቃወምና የመጣስ የሞራል አፈንጋጭነት (deviation) ተንፀባርቆ ይገኛል፡፡ የዚህ አመፅ ዋና ግብ፤ ግላዊ ነፃነትን መቀዳጀት ነው፡፡ ይህ አይነቱ ሁኔታ በአዳም የልብወለድ ሥራዎች ወስጥ በሚገኙት ገፀ-ባሕርያት ላይም በዋናነት የሚስተዋል ነው፡፡ የአዳም ገፀ-ባሕርያት ግላዊ ነፃነትን ፍለጋ ማህበረሰቡ የደነገገውን ጥብቅ ወግና ሥርአት ሲነቅሱ ይታያል፡፡ ይህ የገፀ-ባሕርያቱ እምቢተኝነት የሚስተዋለው ማህበረሰቡና ኃይማኖት ካበጀው ሕግ ባሻገር በራሳቸው እውነት፣ የሞራል እሴትና የህላዌ ትርጉም መኖርን የመምረጥ ዝንባሌ ውስጥ ነው፡፡ ለሳርተር ይህ አይነቱ ግላዊ የአኗኗር ሁኔታ ትክክለኛ (authentic existence) ነው፡፡ “ከሰማይ የወረደ ፍርፍር” በተሰኘው የአጭር ልብወለዶች ስብስብ ውስጥ “ሁለት ልጃገረዶች” በተሰኘው የደራሲው ታሪክ ውስጥ የተገለፀው ዋና ገፀ-ባሕርይ ከላይ የተገለፁት የኤግዚስቴንሻሊዝም ፍልስፍና መገለጫ የሆኑ የግለሰብ ግላዊ ባሕርያት ይንፀባረቁበታል፡፡
“…በሕይወቴ ወጥ ውስጥ ትንንሽ የእብደት ቅርንፉድ፣ የልክስክስነት ኮረሪማ፣ የባለጌነት ነጭ ሽንኩርት፣ የደደብነት ጥቁር አዝሙድ… የመሳሰለ ልጨምርበት እፈልጋለሁ፡፡ እነዚህ ቅመሞች ያሉበትን ሐጢያታዊ ማታና ምሽት ከሰዎች ጋር ልኖራት ግን አልፈልግም፡፡ ይህቺን አይነት እብደት ከሚያውቁት ሰው ጋር ሆነው ሲኖሯት ትቀጥናለች፡፡ ትዕዝብት፣ ትቺት፣ ‘ይቅርብህ’ ‘ጥሩ አይደለም‘ ‘ይደብራል’ የተሰኙ ቃላቶችና የሚከስቱዋቸው ስሜቶች ይወረወሩብኛል፡፡ በቂ ነፃነት የለውም፡፡ ያቺ የእብደት ቀኔ የእኔ ጦር ሜዳ ናት፡፡ ፊታውራሪ እኔ፣ ተራ ወታደር እኔ፡፡ አዛዥ እኔ ነኝ፣ ታዛዥ እኔ…” (አዳም፣ 2ዐዐ2፡97)
ዋና ገፀ-ባሕሪው በማህበራዊ የኑሮ ደረጃው ከከፍተኛው የህብረተሰብ መደብ (ከጨዋውና ከተከበረው) የወጣ ነው፡፡ በመሆኑም ካለው ማህበራዊ ደረጃ አንፃር ህብረተሰቡ ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸውን ማህበራዊ ወጐችና ኃይማኖታዊ እሴቶች በአኗኗሩ እንዲተገብር ይጠበቃል፡፡ በተቃራኒው የገፀ-ባሕሪው ድርጊቶች ግን የማህበረሰቡን እሴቶች የሚቀናቀኑ አፍራሽ ናቸው፡፡ ለአንድ የዚህ ህብረተሰብ አባል ዋና ገፀ-ባሕሪው ማህበረሰቡ ከፍተኛ  ቦታ ከሚሰጣቸው የመሳፍንት ወገን የወጣ መሆኑን ቢረዳ ድርጊቶቹ ፍፁም እንግዳ ይሆኑበታል፡፡ የገፀ-ባሕሪው ድርጊቶች በማህበረሰቡ የእሴት ሚዛን ቢዳኙ የግለሰቡን ማህበራዊ ክብርና ደረጃ (societal privileged status) ስለማያንፀባርቁ የሚወገዙ ናቸው፡፡ በታሪኩ ውስጥ ገፀ-ባሕሪው የማህበረሰቡ ጨቋኝ ወግና ሥርአት ሳይገድበው ውስጣዊ ፍላጐቱን ለማሳካት ትክክለኛ ናቸው ብሎ ያመነባቸውን ድርጊቶች ሲከውን  እናገኘዋለን፡፡  የዚህ አንዱ ማሳያ ኒኒ ከተባለች ሴተኛ አዳሪ ጋር የሚመሠርተው ግንኙነት ነው፡፡
“…ሃያ ብር አውጥቼ ሰጠኋትና የቀረውን እንድትይዘው ነገርኳት፡፡ ልብሷን አወለቀች፡፡ ጡቶቿ ድንኳን በሚያሳፍር መያዣዎች ተይዘዋል፡፡ ወገቧ ቢቀጥንም አጭር ነው … ወደ ፊኛዋ አካባቢ ቦርጭ ይሁን ምን ስሙን የማላውቀው ሥጋ አለ፡፡ እግሮቿ አጫጭሮች ናቸው፡፡ አልጋ ውስጥ ገባች፡፡ ኮቴንና ሱሪዬን አወለቅኩና ተከተልኳት…” (አዳም፣ 2ዐዐ5፡ 1ዐ2)
በገፀ-ባሕሪው ድርጊቶች ውስጥ የተገለፀው ግላዊ ባሕርይ፤ ነፃነትን ለማረጋገጥና ራስን በመሆን ሂደት ውስጥ የሚገኝን ደስታ ለማግኘት እያንዳንዱ ግለሰብ የሚወስደው ውሳኔ ማሳያ ነው፡፡ ስለሆነም ገፀ-ባሕሪው የማህበረሰቡን የሥነ-ምግባር እሴት ቸል በማለት ግላዊ ነፍሱን ለማስደሰት (engagment) በመጠጥ ሲሰክር ይታያል፡፡
“…በመጀመሪያ የማደርገው ነገር ያለገደብ መጠጣት ነው፡፡ ቢራ ሳይሆን ጂንና ብራንዲ…” (አዳም ፣ 2ዐዐ2፡ 99)

Read 2483 times