Saturday, 22 December 2018 13:42

የሁለት ጉዞዎች ማስታወሻ!

Written by  አብይ ተስፋዬ አሳልፍ /አተአ/
Rate this item
(5 votes)

 ክፍል - 1
መነሻ - አዲስ አበባ
የምድር ጉዞ፡- አለም ገና - ሰበታ - ተፍኪ - ቱሉ ቦሎ - (ጉራጌ ዞን፣ ወለኔ ወረዳ፣  ደሳ ቀበሌ … ) … አቧራውን እንደ በረሃ አውሎ ንፋስ ወደ ሰማይ እያነሳን፣ እንደ ንፋሱ በደመ ነፍስ እየከነፍን፡፡
የሰማይ ጉዞ፡- ጆሃንስበርግ ፣ ፕሪቶሪያ፡፡ (በኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ዛምቢያና ዚምባቡዬ ሰማይ ላይ … (በእግዚአብሔር ሰማይ!) እንደ አሞራ በደመናዎች መሃል፡፡
***
ወደ ጉራጌ ዞን!
የጉዞዬ ዕለት ማለዳ ልነሳ መሆኑን ገና ሳስበው በመንፈስ ተጉላላሁ፡፡ ማታ እንቅልፍ እምቢ አለኝ፡፡ በቅርብ ጊዜያት እንዲያ ባለ ማለዳ ተነስቼ አላውቅም ነበር፡፡ እስከ እኩለ ሌሊት ፊልም እያየሁ አመሸሁና ስድስት ሰዓት አካባቢ ተኛሁ፤ ቅዠትና አደጋ የሞላበት ህልም፣  ምቾት የሌለው ሌሊት፤ ስባንን ሰዓቴ 9፡30። መልሼ ለመተኛት ብሞክርም እንቅልፍ እምቢ አለኝ። ወይ ፈጣሪ … እስከ 10፡30 አካባቢ ቁልጭ ብዬ ሳበቃ፣ መልሶ አሸለበኝና ድብን ያለ እንቅልፍ ወሰደኝ፡፡  በሰመመን እያለሁ የስልኬ እሪታ ሲያባንነኝ ተስፈንጥሬ ተነሳሁ፡፡
‹‹ሀሎ…››
‹‹…ኸረ ባክህ ውጣ፣  ሞተሃል እንዴ የማታነሳው! … አስረኛ ጊዜ’ኮ ነው ስደውል፡፡››
‹‹…ኦህ… ይቅርታ፡፡ አምስት ደቂቃ…›› እየተጨናበስኩ ተነሳሁና ኮተቴን ሰብስቤ …በጥድፊያ በረርኩ፡፡
ልክ ስወጣ የመስሪያ ቤታችን የመስክ መኪና አደባባዩ አጠገብ፣ ነጭ ጋቢ የደረበ አባወራ መስሎ ተገትሯል፡፡ ማለዳ ነው፣ መኪናው አዲስና ነጭ ስለሆነ እጅጉን ያምራል፡፡ አስራ አንድ ሰዓት የተቀጣጠርን ቢሆንም አሁን አስራ ሁለት ሊሞላ ነው፡፡ ሁለቱ ተሳፋሪዎችና ሾፌሩ ተናደውብኛል፡፡ እኔ ደግሞ ሃይለኛ ራስ ምታት እየፈለጠኝ ልቤን ያጥወለውለኛል፡፡ የራሳቸው ጉዳይ! ጥረትና ፍላጎትን የማይረዳ፣ ውጤትን ብቻ የሚመለከት ህዝብ፡፡
በመንገዶቹ ላይ መኪኖች ውር ውር ይላሉ እንጂ ገና ጭር እንዳለ ነው፡፡ ጥቂት ሰዎች ቱታቸውን ለብሰው ዱብ ዱብ እያሉ ያልፋሉ፡፡ ቀና ብዬ ሰማዩን በዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አስተዋልኩት፡፡ በሚያምር ቀለማት ተውቧል፣ ደስ አለኝ፡፡ ገባሁና ይቅርታ ጠይቄ በሩን ጥርቅም አደረኩ፡፡ የደህንነት ቀበቶውን እንዳሰርኩ መኪናው ወደፊት ተስፈነጠረ፡፡
የአየር ጤናን አስጨናቂ መስመር በማለዳው እንዳለፍን፣ ቁርስ ለመብላት ብዙ ቤቶችን ብንዳስስም በጠዋት ቁርስ የሚያዘጋጅ አንድም ቤት አላገኘንም። ስለዚህ … እናቸንፋለን! እያልን ጉዞውን እያዛጋን ተያያዝነው፡፡ ብልጭልጭ፣ መላጣና ፈርጣማ ሰውነት ያለው ሾፌራችን በጣም ተጫዋች ነው፡፡ በጉዟችን ላይ ምቾት ይሰማን ዘንድና ዘና እንድንል ይጠነቀቃል፡፡ ተሳስቶ መኪናችን በተቆፈረው አንድ የመንገዱ አካል ውስጥ ገብቶ ግራና ቀኝ ከናጠን፣ ፈገግ ብሎ ያየንና ይቅርታ ይጠይቀናል፡፡ ወዲያው ደግሞ ከማያልቀው የህይወት ልምዱ ያካፍለናል፡፡
***
ወደ ጆሃንስበርግ!
እሁድ ነበር፡፡ ወደ ጆሃንስበርግ የማደርገው በረራ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ነው፡፡ ሆዴን ባር ባር የሚል ስሜት ተሰምቶኝ ስለነበር፣ ምሳዬን መብላት አልቻልኩም፤ ቁርሴንም በቅጡ አላደረግሁም፡፡ በሰዓቱ ቦሌ ደርሼ ፍተሻዎቹን ለማለፍ ጫማና ቀበቶዬን መፍታት ስጀምር ረሃብ ጀመረኝ፡፡ እሱን አልፌ ሳበቃ የያዝኩትን ዶላር መጠን ወደሚያረጋግጠው ወጣት ተጠግቼ ፓስፖርቴንና ደረሰኜን ሰጠሁት፡፡
‹‹…ደረሰኙ የባንኩ ማህተም የለበትም…›› አለኝ በፈገግታ፡፡ አላየሁትም ነበር፡፡ እሁድ ነውና ምንም ላደርገው አልችልም፡፡ ካልተደረገበትም የእኔ ስህተት አልነበረም፡፡ እና … በሚል አስተያየት ስመለከተው፣ መልካም ምኞት ተመኝቶልኝ አሰናበተኝ፡፡ ደስ አለኝ። በጣም የገረመኝ ነገር ከደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ ጀምሮ ወደዛች ሃገር ቪዛ ለመስጠት የሚታየው ችግር ነበር። ቪቫ ላለመስጠት እጅጉን ይታገላሉ፡፡ ከቶ ይህቺ የማንዴላ አገር ምን ቢኖርባት ነው ብዬ አሰላሰልኩ፡፡
ቀጥሎ የሻንጣዬን ኪሎ ካስመዘንኩና ካስረከብኩ በኋላ ወደሚቀጥሉት የጉምሩክ ባለሙያ መስኮቶች ተሰለፍኩ፡፡ የውጪ በረራ አድርጌ ስለማላውቅ ምን እየተደረገ እንደሆነ ራሱ አልገባኝም፡፡ ወጣቱ የጉምሩክ ባለሙያ ወደ መስኮቱ ጠርቶ ፓስፖርቴን ካስተዋለ በኋላ ይጠይቀኝ ያዘ …
 ‹‹ደቡብ አፍሪካ ለምንድነው የምትሔደው?››
‹‹መስሪያ ቤቴ ለስልጣና ልኮኝ… ›› መልስ ሰጠሁ፡፡
‹‹ስንት ቀን ትቆያለህ?…››
‹‹አስር ቀን… ››
‹‹የመስሪያ ቤት መታወቂያህን ስጠኝ ‘ስኪ›› … እኔ ደግሞ ውጪ አገር እየሄድኩ ምን ይሰራልኛል ብዬ አንድም መታወቂያ አልያዝኩም፡፡ ፓስፖርቴን እንደ መታወቂያዬ በመቁጠሬ ነበር፡፡ ደነገጥኩ፡፡ እንዳልያዝኩ ነገርኩት፡፡ በቫይበር ወይም በሌላ መንገድ ፎቶ አስነስቼ እንዳስልክ ጠየቀኝ፡፡ የምኖረው ብቻዬን ስለሆነ ቤቴን ቆልፌ ነበር የወጣሁት፡፡ እንዳልመለስ የበረራ ሰዓቱ ደርሷል፡፡ ተጨነቅሁ፡፡ ‹‹በመውጫ ሰዓቴ አጉል ኬዝ ይዘህብኝ መጣህ!…›› አለና ተነጫነጨ። ገለል ካለች ወንበር እንድቀመጥ አደረገኝና ወደ ሃላፊው ቢሮ ገባ፡፡ ብዙ ነገር እያወጣሁና እያወረድኩ፣ ረሃቤንና ራስ ምታቴን አስታምም ጀመር፡፡ ከደቂቃዎች በኋላ ሃላፊው አብሮ መጣና ተመሳሳይ ጥያቄዎች አቀረበልኝ። መለስኩለት፡፡ የልብ ምቴ ጨምሮ ነበር። ሰዓቴን በማሰብ ተጨንቄያለሁ፡፡ ጥቂት ቆይቶ በሃላፊው ፈቃድ ወደ ውስጥ እንድዘልቅ ተፈቀደልኝና እፎይ አልኩ፡፡
ከደቂቃዎች በኋላ በቦይንግ 787 ላይ እንደ ስብሰባ አዳራሽ ከሞላው ተሳፋሪ መሃል ራሴን አገኘሁት፡፡ መስኮት ስር ባለች መስኮት ውጪውን እየተመለከትኩ ተከዝኩ፡፡ የአዲስ አበባን እንደ እንጉዳይ የፈሉ መንደሮች ለደቂቃ ቃኝተን፣ ከደመናው በላይ ተንሳፈፍን፡፡ እንደ ጥጥ ከተባዘቱት ደመናዎች ውስጥ በፀጥታ፣ ምንም የማይጓዝ በሚመስል ሃይለኛ ፍጥነት፣ በቀበቶዬ ታስሬ የደህንነት መልዕክቱን በድጋሚ በልቡናዬ አሰብኩት …
‹‹…በአደጋ ጊዜ የሚያገለግል ጀልባ ከፕሌኑ ኮርኒስ ውስጥ…መንሳፈፊያ ኮቶች ከወንበራችሁ ስር ይገኛል፤ የመተንፈሻ ማስኮች ከኮርኒሱ ቁልቁል ከወረዱ … እንዲህና እንዲያ አድርጉ…›› በመስኮቱ ቁልቁል እንደ ጉንዳን የሚታዩትን መንደሮችና መልክዓ ምድር አየሁ። እግዚኦ! ለማንኛውም መሬት ትርቃለች ወዳጄ። ትኩረቴን ሰብስቤ ፕሌኑ ውስጥ የሚታየውን ፊልም ለመከታተል ሞከርኩ፡፡ እናም ሳላስበው ከአምስት ሰዓት በረራ በኋላ፣ ሁለተኛውን ፊልሜን ሳጠናቅቅ፣ እንደ እንቁ ከፈሰሱት የጆሃንስበርግ መንደሮች መሃል በኢትዮጵያ አየር መንገድ በሰላም አረፍኩና ተነፈስኩ። ለአብራሪው አስተራረፍ እንደ ሲኒማ/ ወይም ካምቦሎጆ ሲጨበጨብ ሰምቼ፣ ዙሪያዬን መቃኘት ስጀምር፣ በድካም ውስጥ እፎይታ የሚነበብባቸው ብዙ የወዳጆች ፊት ተመለከትኩ፡፡ ዕቃዬን ሸካክፌ እግሬን አፍታትቼ፣ የመጀመሪያውን እርምጃ ቀኝ እግሬን በማስቀደም ጀመርኩት፡፡
ደግሞ እዚህም ካሉ የደካከሙና የሰለቹ የአገሬው የጉምሩክ ሰዎች ጋር ጥቂት ንግግር ከተደረገ በኋላ፣ በመንገደኞች ተርሚናል ወደ መውጫው ሻንጣችንን እየገፋን ስንወጣ፣ የፍተሻ ሰዎች በሰፊው መንገድ መሃል እየተንጎራደዱና የፈለጉትን ሰው ወደ ዳር እየጠሩ ሻንጣ መበርበር ያዙ፡፡ እንደዚህ ደክሞኝ እንዳያንገላቱኝ በልቤ እየፀለይኩና ፊቴ ላይ በራስ መተማመኔን ለማሳየት እየሞከርኩ ዘለቅኩ፡፡ በተለይ አረቦቹንና ህንዶቹን እየለዩ እንደሚፈትሹ ሳስተውል ተገረምኩ። የፍተሻውን መስመር እንዳለፍኩ ደስ ከሚለው የእንግዶች መጠበቂያ ተከሰትኩ፤ ከዚህ በምሽቱ ወደ ማረፊያዬ የሚወስደኝ የአገሬው ሰው ዴሪክ ፊት ለፊት በፈገግታ ቆሟል፡፡ ቀጫጫው ዴሪክ ‹ዌል ካም ቱም ሙዛንሲ!› (ሙዛንሲ - በአገሬው ቋንቋ ደቡብ እንደማለት ሲሆን የደቡብ አፍሪካ ሌላ ስም ነው፡፡) እያለ ተቀበለኝና በሌሊት ወደ መኪናው ወሰደኝ፡፡ በጣም ስለደከመኝ ማረፍ ፈልጌ ነበር፡፡ ግና ወደ ፕሪቶሪያ የጨለማ ጉዞ ይጠብቀኛል፡፡ ከከተማው በደቂቃዎች ወጥቶ በጣም ሰፊ ከሆነው የቀለበት መንገድ ውስጥ እንደ ጀት ሲበር ደነገጥኩ፤ በመስኮት ሌሎቹንም ሳስተውል እንዲሁ የሚበሩ መኪኖች ነበሩ፡፡ ከሰፊው መንገድ ላይም መኪኖች በ120 ኪሜ በሰዓት እንዲጓዙ የሚያሳይ ምልክት ስመለከት፣ የቅድሟን የአውሮፕላን ላይ መልዕክት አሰብኩና ወደ ኮርኒሱ ተመለከትኩ። ‹‹…ለአደጋ ጊዜ የሚያገለግል ጀልባ ከፕሌኑ ኮርኒስ ውስጥ … መንሳፈፊያ ኮቶች ከወንበራችሁ ስር ይገኛል፤ የመተንፈሻ ማስኮች ከኮርኒሱ ቁልቁል ከወረዱ…›› የፈጣሪ ያለህ፡፡ አይኔን ዘጋሁ፡፡
***
ደግሞ ወደ ጉራጌ ዞን!
ነጯ ፒከአፕ መኪናችን ትፈጥናለች፡፡ ሾፌራችንም እንዲሁ፡፡ በወጉ በወጉ የተሰደሩ ጨዋታዎች ለተዳከሙ መንገደኞቹ ያቀርባል፡፡ በአፋር ክልል ከውጪ ባለሞያዎች ጋር የጥልቅ ውሃ ቁፋሮ ስራና የመስኖ ስራ ላይ ተሳትፏል፣ እናም ከነርሱ ጋር ከአስር አመታት በላይ አብሮ በመኖሩ እጅጉን የተቀየረ ሰው ነው፡፡ ስፖርተኛ፣ ጠንቃቃ፣ ታታሪ፣ ይቅርታና አመሰግናለሁን አብዝቶ የሚጠቀም፣ ተጨዋች ነው፡፡ ትንሽ እንደተጓዝን በተንጣለለው ሜዳ ላይ የተለቀቀ እሳት አየን፣ ይንቦገቦጋል፡፡ ሜዳው ላይ ያሉትን የሳር ዘሮች እያሻመደ ይፈጥናል፡፡ ጭሱ አገር ምድሩን ሞልቶት ወደ ነፋሱ አቅጣጫ ይበታተናል፡፡ ሁላችንም በመስኮት ወደ ውጪ አተኮርን፣ (ከሾፌሩ ውጪ ሶስት ነን፡፡ አንድ ጀርመን የኖረ ኢትዮጵያዊ የእርሻ ስራ ዶክተር፣ አንድ የእርሱ ወዳጅ፣ አሁን የምንሔድበትን ቦታ አብሮት የሚያለማ የነበረ፡፡  እና ጋቢና የተቀመጥኩ እኔ፡፡ በጥንቃቄ ቀበቶ ታስሬ በርሃብና በቡና ጥማት እያዛጋሁ የማንጎላጅ...)
ሾፌራችን እንዲህ አለ … ‹‹ወዳጆቼ እሳት’ኮ የሚያስፈራ ነገር አይደለም፡፡ በእውነት ነው የምላችሁ የሚያስፈራ ነገር ውሃ ነው፡፡  ውሃ በእርግጥ ሞኝ ነው፡፡ ወደምትፈልገው ስፍራ በዘዴ ልትመራውና ልትወስደው ትችላለህ … ሆኖም ከአቅም በላይ ከሆነ ደግሞ እንደ ውሃ አጥፊ የለም፣ እሳት’ኮ ከተነሳ የሆነውን አካል የማትረፍ እድል ይኖርሃል፤ ውሃ ግን ጠራርጎ ነው የሚወስደው፡፡ አንዲት አያስቀርም! … ይገርማችኋል አፋር ውስጥ አንድ የስኳር ፕሮጀክት ላይ ግድብ እየተሰራ ነበር፡፡ አማካሪዎቹ የኔ ቀጣሪዎች ሲሆኑ፣ ኮንትራክተሩ ደረጃ አንድ የአገር ውስጥ ድርጅት። ባለቤቱ ደግሞ መንግስት ነበር፡፡ አሁን’ኮ በቅርብ አመታት ውስጥ ነው፡፡ ታዲያ ከግድቡ በላይ ለሚገኘው ወንዝ ማስቀየሻ ተገንብቶ ነበር ስራው የሚሰራው። እናም አማካሪው የማስቀየሻ ግንባታው ቁመትና መጠን ማነሱን ደጋግሞ ይወተውታል፡፡ ኮንትራክተሩና ክሊየንቱ ግን እየሳቁ አለፉት፡፡ በቂ ነው አሉ!
የግድቡ ዋናው የመሰረት የኮንክሪት ግንባታ ተፋጠነ፡፡ ሚሊየን ብሮችን እየዋጠ ግድቡ ከፍ ማለት ጀመረ፡፡ ታዲያ አንድ ፀሃያማ ቀን በድንገት ወንዙ ጎርፍ ሆኖ መጣ፡፡ ለካ በላይኛው አካባቢ ሃይለኛ ዝናብ ዘንቦ ኖሯል፡፡ እናም ጎርፉ እጅግ ሃይለኛ ስለነበር የማስቀየሻ ግንባታዋን በቀላሉ አለፋትና ወደ ዋናው ግድብ ገባ፡፡ ለወራት የተገነባው ግንባታ ለሰዓታት ብቻ በቆየ ደራሽ ጎርፍ ጥርግ ተደርጎ ተወሰደ፡፡ ከአንድ ሰዓት ተኩል ጎርፍ በኋላ በቦታው ምንም ያልነበረ ያህል አድርጎት ጠፋ፡፡ ሁላችንም እጅግ አዘንን፡፡ ከሁሉም ያንገበገበኝ የባለሙያዎቻችን ቀድሞ ለተሰጡ ሀሳቦች ያን ያህል ዝግ መሆን ነበር፡፡ እዚያ ከነበርነው ውጭ ዜናው እንኳ ለኢትዮጵያ ህዝብ አልደረሰም፡፡ በበረሃው ለወራት የተደከመበትና ሚሊዮኖች የፈጀውን ግድብ፣ ሰባራ ሳንቲም ሳያስቀርና ምልክት ሳይተው አጠፋው፡፡››
ታሪኩ እውነት ይሁን ሃሰት አላወቅሁም፡፡ ብቻ ለደቂቃዎች በሃሳብ ተወሰድኩ፡፡ እዚህም እዚያም ብቅ ጥልቅ የሚሉ ትዕይንቶች ላይ ትኩረት ባደርግም ድንገት በተነሳው ሀሳብ ላይ በሚቀርበው አስተያየት መንጫጫት ጀመርን፡፡ የባለሙያዎቻችን የአቅም ማነስ፣ የትምህርት ጥራታችንን፣ ሙስናውን የመሳሰሉ ነገሮችን አንስተን እየተጯጯህን ነበር፡፡ በመሃል ፀጥተኛው ዶክተር እንዲህ የሚል አስተያየት ሰጠ…
ይቀጥላል

Read 1080 times