Monday, 24 December 2018 08:20

የፕሬዚዳንቱ ሽኝት ላይ ሜትሮ ቢኖር…

Written by  መሐመድ ኢድሪስ
Rate this item
(2 votes)

አዲስ አድማስ ቢሮ ማቅናት ነበረብኝ፡፡ ነገሩ ግን እንዳሰብኩት ቀላል አልነበረም፡፡ ዕለቱ ረቡዕ ነበር። መንገዱ ቀይ የማዕረግ ልብስ በለበሱ የወታደራዊ ማርሽ ሙዚቀኞች ተሞልቷል፡፡ የሚቀመስ ነገር ባፌ አደረግኩና ታክሲ ለመያዝ ሞከርኩኝ፡፡ የማታይሰብ ነበር፡፡ ለታክሲ ወረፋ የሚጋፋው ህዝብ ቁጥር ህልቆ መሣፍርት የለውም፡፡ በፊንፊኔ የምግብ አዳራሽ፣ በቤተመንግስት በኩል አቋርጬ ወደ ካዛንቺዝ ለማምራት ሞከርኩኝ፡፡ መንገዱ በፌደራል ወታደራዊ መኪናና የፌደራል ወታደሮች ተዘግቷል፡፡ ያለኝ እድል በሸራተን አዲስ ወደ መናኸሪያ በሚወስደው መንገድ፣ በዚያ በጠራራ ፀሐይ ዳገቱን መውጣት ነበር፡፡ ትንሽ እንደተጓዝኩ ድካሙ ከአቅሜ በላይ ሆነና፣ እዚያው ሸራተን ባንክ ስር ጥላው ላይ ለመቀመጥ ተገደድኩ፡፡ ስልክ የመጐርጐር ሐሳብም የመጣልኝ በዚያ ቅጽበት ነበር፡፡
ከስልኬ ጋር የተጫወትኩት እንዲህ ነበር፡፡ 2,739,551 የህዝብ ቁጥር ያላት አዲስ አበባ፤ 527 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ስፋት አላት፡፡ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ የተባበሩት መንግስታት ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በአፍሪካ (ECA) ዋና መ/ቤት፣ የዲፕሎማቲኮች መናኸሪያ ናት፡፡ ያሏት የሚኒባስ ታክሲዎችና ኮንትራት ታክሲዎች፣ 730 አውቶቡሶችና 500 ቢሾፍቱ አውቶቡሶች ያሉት አንበሳ አውቶቡስ ሸገር ሲቲ ባስ ዘመንና አልያንስ አውቶቡሶች ከቀላል ባቡሩ ጋር ይህንን ሁሉ ህዝብ ለማጓጓዝ በቂ አይደሉም። ከሜክሲኮ ጀሞ ለመሄድ ግማሽ ሰአት የአውቶቡስ ወረፋ መጠበቅ ሲያስፈልግ፣ አንድ ሙሉ ሰአት መንገድ ላይ መጓዝ ይጠይቃል፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያቱ የመንገድ ላይ ትራፊክ ጭንቅንቅ ነው፡፡
ይህንን ስል አዲስ አበባ ልክ እንደ ኒው ዮርክ ሲቲ ሜትሮ (የምድር ውስጥ ባቡር) ያስፈልጋታል እያልኩኝ ነው፡፡ ኒውዮርክ ሲቲ ሰብ ወይ በመባል የሚታወቀው ሜትሮ የተመሰረተው በ1904 ሲሆን አዲስ አበባ በ2018 ይህንን የመንገድ መጨናነቅ ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም እስከ 70 በመቶ ሊያስወግድ የሚችል ፕሮጀክት መጀመር የሚያቃትት ለምንድነው? ይህ የኒው ዮርክ የአለማችን ግዙፍ ሰብዌይ በቀን 5.525.481 ሰዎችን ያጓጉዛል፡፡ ቅዳሜና እሁድ ደግሞ 2,525,481 ሰዎች፡፡ 245 ማይልስ የሚጓዝ ሲሆን አማካይ ፍጥነቱ ሃያ ሰባት ኪሎ ሜትር በሰአት፣ በጣም ከሮጠ ደግሞ 89 ኪሎ ሜትር በሰአት ይጓዛል፡፡ ብሮኪልን፣ ማንሃተን፣ ኩዊንስን የሚያክስ ሲሆን 472 መዳረሻዎች ወይም ጣቢያዎች አሉት፡፡
የዚህ አይነት ሜትሮ ከተማችን ስለሌላት እንደ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በእግሬ መጓዝ ግዴታ ሆነብኝና ሽቅብ ወደ አራት ኪሎው ቤተ መንግስት አቀናሁ። አንድ ቀይ የወታደራዊ ማርሽ ልብስ የለበሰ ሰው አገኘሁና፤ “ዛሬ ምን አዲስ ነገር ተገኝቷል?” ስል ጠየቅኩት፡፡
“ቀብር ነው” አለኝ፡፡
“ወዲያው ትዝ አለኝ፡፡ የቀድሞው የኢህፌዲሪ ፕሬዚዳንት ዜና እረፍት መሰማቱ፡፡ ቀብሩ የሚፈፀመው ቅዳሜ መስሎኝ ነበር፡፡ ለካ ዛሬ ኖሯል። ታህሳስ 28 ቀን 1924 ዓ.ም ተወልደው፣ ዲሴምበር 15 ቀን 2018 ያረፉትን፣ ከ2001-2013 የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት የነበሩትን፣ ግርማ ወልደጊዮርጊስ የምወድበት ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ ዋናው ለደን የነበራቸው ፍቅር ነው፡፡
“የዛፉ ፀሎት” የተሰኘው ድርሰቴም ከሳቸው አስተሳሰብ የተወሰደ ነበር፡፡ እኚህ የፓርላማ አፈጉባኤና የአየር ሃይል ፐርሶናል የነበሩ ታላቅ ሰው፤ ሌላው ሁሉ ኤርትራን አይንሽን ላፈር ባለበት ዘመን፣ እሳቸው ግን ለሁለቱ ህዝቦች ሰላም ማግኘትና አብሮነት ይታገሉ ነበር፡፡ ከህልፈታቸውም በኋላ አይናቸውን ለአይን ባንክ የተናዘዙ፣ በጣም የሰለጠነ አስተሳሰብ የነበራቸው፣ ሰብአዊነትና በጐነትን የታደሉ ሰው ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ የእምነት ሰዎች እንደሚሉት ከቀብር በኋላ በሶስተኛው ቀን ለሚፈሰው አይን፤ ሌላው አይነስውር ወንድሙ እንዳይበራበት ይዤው እሞታለሁ ማለት ምን አይነት አስተሳሰብ ነው!? ግርማ ወልደጊዮርጊስ፤ የዚህን ኋላ ቀር አስተሳሰብ ከንቱነት ያሳዩ ናቸው፡፡
ሸራተንን አልፌ ዳገቱን ወጣሁና በአራት ኪሎና በመናኸሪያ መሃል ያለው አስፋልት ላይ ደረስኩ። ይገርማል፡፡ አሁንም መንገዱ ተዘግቶ፣ በየመንገዱ ዳር ወታደሮች ቆመዋል፡፡ አባት አርበኞች ተሰልፈዋል። የቀብር መኪና በአበባ አጊጦ በዝግታ ይጓዛል፡፡ ወዲያው አንድ የደንብ ልብስ የለበሰ ወታደር፤ “አባት አርበኞች ከሰረገላው በኋላ” ሲል ጮኸ፡፡ ሰረገላው ፕሬዚዳንቱ የቴክሳስ ባርኔጣ አድርገው የተነሱት ፎቶግራፍ ተለጥፎበታል፡፡ ሳጥኑን ከመኪናው አውጥተው ወደ ሰረገላው አዟዟሩት፡፡ ፈጣሪ በዚህ መንገድ ያመጣኝ እሳቸውን እንድሸኝ መሆኑን አወቅኩና፤ ሰላምታ ሰጥቼ ወደ ጉዳዬ አቀናሁ፡፡ ስመለስ ትራንስፖርት ስላልነበረ፣ እኔም እንዳብዛኛውም ሰው በእግሬ እየተጓዝኩ ነበር። ይሄኔ ነው የፕሬዚዳንቱ ሽኝት ላይ “ሜትሮ” ቢኖር የሚል ሃሳብ ብልጭ ያለልኝ፡፡

Read 1362 times