Monday, 24 December 2018 08:23

ዘረኝነትን መግታትና ከጥፋት መዳን፣ ከባድ ስራ ሆኖ ነው? ወይስ እያከበድነው?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(11 votes)

 ኢትዮጵያ ውስጥ፣ በጣም ከባዱ ስራ ምንድነው? ሰላም ማግኘት? ከድህነት መገላገል? ነፃ ምርጫ ማካሄድ?... ምኑ ተጠርቶ ምኑ ይቀራል! አብዛኛው ስራ እንደ ትልቅ ሸክም ሆኖ የሚታየንና መከራ የሚሆንብን ግን፣ በተፈጥሮው ከባድ ስራ ስለሆነ አይደለም። ስራው ከባድ ባይሆን እንኳ፣... በዚህም በዚያም ብለን፣ ከላይም ከታችም ተረባርበን፣ ከኋላም ከፊትም ተብትበን ለማወሳሰብ እንሯሯጣለን። ወይም ደግሞ፣ ሲተበትቡትና ሲያወሳስቡት፣ የመከራከርም ሆነ የመከላከል አቅም አጥሮን በተስፋ ቢስነት እንደነዝዛለን። ዘረኝነትን መከላከልና ከጥፋት መዳን ሲያቅተን እያያችሁ!
ከዘረኝነት በሽታ የሚገላግልና ከመዘዙ የሚያድን ሁነኛው መፍትሄ ምን እንደሆነ ጠፍቶን ነው? የዘረኝነት በሽታ፣ በራሱ ጊዜ የሚስፋፋ እርግማንና በራሱ ጊዜ የሚከስም የነፋስ ሽውታ ሳይሆን፣ ሳቢያና መዘዝ፣ መንስኤና መፍትሄ ያለው በሽታ መሆኑን መገንዘብ ከባድ አይደለም (እውነታውን አይቶ የመገንዘብ ፍላጎትና የመገንዘብ ጥረት ካልጎደለን ወይም ካላጎደልን በቀር ማለቴ ነው)።
“የጋርዮሽ ሕይወት” እንደሌለ፣... እያንዳንዱ ሰው፣ “የግል ሕይወት ባለቤት” እንደሆነ፣ እውነታው አልታይ ብሎን ነው? ወይስ ይሄን ዘላለማዊና ሁለንተናዊ እውነት፣ እንደተራ ነገር ቸል ስለምንለው ወይም ቸል ለማለት ስለምንፈልግ? እያንዳንዱን ሰው የእንደየግል ብቃቱ፣ ተግባሩና ባሕርይው መመዘንስ፣... ቀና የፍትሃዊነት መርህ እንደሆነ፣ ጨርሶ አልታይ ብሎን? እያንዳንዱን ሰው፣ የግል ብቃቱን ያህል ለማድነቅ የሚሻ ንፁህ ሰብዕናን መቀዳጀትስ፣ የተቀደሰ የግብረገብ ሃላፊነት እንደሆነ መገንዘብ ተስኖን ነው?
የሰው አእምሮና አካል፣ የግል አእምሮና አካል እንደሆነ፣... የሰው ሕይወትና ማንነት፣ የግል ሕይወትና ማንነት እንደሆነ፣... እውኑን ተፈጥሮ አይተን በቀላሉ ማረጋገጥና መገንዘብ የምንችለው በጣም ግልፅ እውነታ ነው።
ይሄውም ነው የዘረኝነት በሽታ ሁነኛ መፍትሄ። ግን፣ የበሽታ መድሃኒት ብቻ አይደለም። የጤንነትን ጎዳና የሚጠርግና የሚያበራ አስተማማኝ መፍትሄውም፣ ይሄው ነው። ይሁነኛው መፍትሄ፣ የዚህን ያህል በግልፅ የሚታይ ቢሆንም፣ ጨርሶ መፍትሄው የሌለ እየመሰለንና እያስመሰልን፣ ከዘረኝነት የጥፋት ቁልቁለት መውጣት ያቃታቸው፣ “እያዩ የሚያልቁ” አቅመቢሶች መሆን አለብን? ግን እየሆንን ነው።
“እያዩ የማለቅ ቁልቁለት”
ከብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ ጋር በዘር የመቧደን በሽታ፣ እንደ “ኖርማል” እስከመታየት ሲደርስ፣ የጅምላ ፍረጃ ጎራዎች እንደአሸን እየተፈለፈሉ፣ በየቦታውና በየእለቱ የበርካታ ሰዎች ሕይወት ሲጠፋ፣ ብዙዎች ሲሰደዱና አገር በግጭት ሲታመስ፣ በአቅመቢስነት ከመፍዘዝና በጭንቀት ከመመልከት ውጭ፣ ሁነኛውን መፍትሄ ተጠቅመን የፈጠርነው መላ አለ? እስካሁን ሁነኛውን መፍትሄ ለመጠቀምና መላ ለመፍጠር አልቻልንም፤ ወይም አልፈለግንም። “እያዩ የማለቅ ቁልቁለት” ይሉሃል ይሄው ነው።
ዙሪያችሁን ተመልከቱ - ከከተማ እስከ ገጠር፣ ከጎዳና እስከ ፌስቡክ፣ ከስታዲዬም እስከ ዩኒቨርስቲ፣... ከመሃል እስከ ዳር፣ በጣም የሚሳፍር፣ የሚያሳዝንና የሚያስጨንቅ የጥፋት ቁልቀለትን ታያላችሁ።
ምርጥ ብቃትን በእውን በማሳየት፣ የሰውን ሕያው መንፈስ አድሰው ማነቃቃት የሚገባቸው የስፖርት ስታዲዬሞች፣... የጭፍን ስሜትና የብሽሽቅ መናሃሪያ፣ የዘረኝነት መፈንጫ፣ የክፉ ጥላቻ መራቢያ፣ የፀብና የጥፋት አውድማ እየሆኑ ነው። ነገር ግን፣ የዘር የመቧደንና የጅምላ ፍረጃ መዘዞችን በእውን እያየንም እንኳ፣ አይተን እንዳላየን ለመሆን ስንሞክር፣ “የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል” እያልን ብቻ እናወራለን። ወይም ደግሞ፣ በጭፍን የዚህና የዚያ ቲፎዞ እያልን፣ ወይም የእከሌ ከተማ ወጣቶችና የእከሊት ከተማ ወጣቶች ያልን በጅምላ ፍረጃ እያሞጋገስን፣ የእንትና ብሔርና ብሔረሰብ እያልን በጅምላ እያወደስን፣...  “እርስበርስ ተዋደዱ” ብለን ፍቅር ለመፍጠርና ሰላም ለማውረድ የምንችል ይመስለናል፤ እናስመስላለን። ግን፣ ፍቅር ለመፍጠር በሚልም ሆነ እርቅ ለማውረድ በሚል ሰበብ፣ በጅምላ ፍረጃ እያሞገስን ቁጥር፣ በዘር መቧድንን እንደዘበት በይሁንታ ባስተጋባን ቁጥር፣... ውሎ አድሮ፣ የዘረኝነትን በሽታ ከማባባስና የቁልቀለት ውድቀትን ከማላመድ ያለፈ ውጤት አይኖረውም።
ዩኒቨርቲዎች እንኳ፣... ከእውነትና ከእውቀት ጋር በሚያጣላ በሽታ ይሸነፉ?
የእውነትና የእውቀት ቅዱስ ስፍራ መሆን የሚገባቸው ዩኒቨርስቲዎች፣... የዘረኝነት “ማሰልጠኛና ቤተሙከራ” እስኪመስሉ ድረስ፣ ለጭፍን ስሜት፣ ለግርግር ግጭትና ለዘረኝነት ክፋት ሲሸነፉ እያየን ነው። የዘረኝነት በሽታውና ቁልቁለቱ የምር የሚታየን፣ የበሽታው መዘዞች ገንፍለው አፍጥጠው ሲመጡብንና፣ ነውጥ ተፈጥሮ ጥፋት ከደረሰ በኋላ ነው። ነገር ግን ከዚያ በፊት ነው በሽታው የጠናብን፣ ቁልቁል ለመውደቅ የተመቻቸነው። አስርም ይሁኑ መቶ ተማሪዎች በዘር ሲቧደኑና፣ “የእንቶኔ ብሔር ተማሪዎች”፣ “የእንቶኔ ብሔረሰብ ተማሪዎች” የሚሉ የጅምላ ፍረጃ አባባሎች እንደ “ኖርማል” አባባል የተቆጠሩ ጊዜ ነው፣ ቁልቁል እየተንደረደርን መውረድ የጀመርነው።
ይህንን የጥፋት ቁልቁለት ከመነሻው ለመግታትና ከስረመሠረቱ ለማስተካከል የሚችል ትክክለኛ አስተሳሰብ፣ ቀና መርህ፣ ንፁህ የሰብዕና ብቃት ከሌለን፣... የበሽታውን መንስኤ በቸልታም ይሁን በይሁንታ እያስተናገድን፣ በዘር የመቧደን አባዜ ከተለመደ በኋላማ፣... “የዚያ ብሔር ተማሪዎች፣ የዚህ ብሔረሰብ ተማሪዎች”... የሚል የዘረኝነት አባባል እንደዘበት ከተዘወተረ በኋላማ... የጥፋት መዘዝ መከተሉ አይቀሬ ነው። አምና በጭፍን ሲስቡ መክረም፣ ለዘንድሮ የከፋ ጥፋት መምዘዝ የመሆኑን ያህል፣... ቁልቁል ተንደርድረን ስናበቃ፣... እየተላተምን መፈጥፈጥ መች ይቀርልናል! ግጭቱ፣ ፀቡ፣ ግርግሩ፣ ጥፋቱ፣ ሞትና መፈናቀሉ ሁሉ፣... የቁልቁለት ጉዞው አይቀሬ መዘዝ ነው።
መፍትሄውም፣ እለት በእለት፣ በእልፍ ቦታዎች፣ እልፍ መዘዞችን ለማለዘብ መፍጨርጨር ሳይሆን፣ ከስረመሰረቱና ከመነሻው፣ ዋናውን በሽታ ማከም ነው። በዘር መቧደን አስፀያፊ መሆኑን በመገንዘብ፣ “የኦሮሞ ተማሪ፣ የአማራ ተማሪ፣ የትግራይ ተማሪ፣ የሲዳማ ተማሪ...” የሚሉ የጅምላ ፍረጃ አባባሎች ለዘረኝነት የሚያመቻቹ ነውሮች መሆናቸውን በመረዳት ወደ ጤንነት ማምራት ነው። መፍትሄው፣ ከመነሻውና ከጅምሩ ከቁልቁለት ጉዞ መቆጠብና ወደ ቀናው ጎዳና ማቅናት ነው።
የዘረኝነት በሽታና የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ
የሰው ማንነት ማለት፣... የግል ማንነት ማለት እንደሆነ ተዘንግቶ፣... ማንነት ማለት፣... “በዘርና በብሔር ብሔረሰብ የሚተላለፍ አንዳች የጋራ ትዝታ ወይም በሽታ” መስሏል። የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ ደግሞ፣ ከዚህ የተሳሳተ አጥፊ አስተሳሰብ ጋር የተቆራኘና የሚያባብስ የፖለቲካ ቅኝት ነው።
በእርግጥ፣ “አገራዊ፣ ሕብረብሔራዊ፣ አንድነታዊ”... በሚሉ ስያሜዎች የሚደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የፖለቲካ ቅኝቶችም፣... ፋይዳ የሚኖራቸው፣ “የሰው ማንነት፣ የግል ማንነት ነው” የሚለው እውነት ላይ ከተመሰረቱ ብቻ ነው። አለበለዚያ፣... አንድም ዘረኝነትን መከላከል የማይችሉ አቅመቢስ ከንቱዎች ይሆናሉ። አልያም፣ በለዘብታም ሆነ በግለት፣ በፈረቃም ሆነ በሙሉ ጊዜ፣... ዘረኝነትን በመስበክ ድጋፍ ለማግኘት የሚሯሯጡና የሚደናበሩ ቀሽም አጥፊዎች ሲሆኑ የምንመለከተውም በዚሁ ምክንያት ነው።
በሌላ አነጋገር፣... የሰው ማንነት ማለት፣... የግል ማንነት ማለት እንደሆነ፣ የአገራችን ፖለቲካ ውስጥ ተዘንግቷል፤ ወይም እውነታው ተጠልቷል። እውነታው ግን፣ በዝንጋታም ሆነ በጥላቻ አይቀየርም። እንዴት ሊቀየር ይችላል? የአንድ ሰው እዋቂነትም ሆነ አላዋቂነት... የሁሉም ሰው አዋቂነት ወይም አላዋቂነት ማለት አይደለም። ይሄ እውነት ይቀየራል?
“የአንድ ሰው እውነተኛነትና እውቀት” ማለት፣ “ሙሉ ለሙሉ የራሱ እውነተኛነትና እውቀት” ማለት ነው እንጂ፣... የአገር፣ የብሔረሰብ፣ የቤተሰብ... የጋርዮሽ እውነተኛነትና እውቀት ማለት አይደለም። የአንድ ሰው ውሸትና አላዋቂነትም፣... የጋርዮሽ ውሸት አይሆንም፣ ሁሉንም ሰው አላዋቂ አያደርግም። እውነትና ውሸት፣ እውቀትና አለማወቅ፣... በትውልድ አገርና በመንደር፣ በዘርና በብሔረሰብ ይቅርና፣... ከወላጅ ወደ ልጅ የሚተላለፍ፣ በወንድም እህትነት የሚወረስ አይደለም።
አባት የሂሳብ ስሌትና ቀመር ስላላወቀ፣ ልጅም “በትውልድ የሚተላለፍ አላዋቂነት”ን የመጋራት ፍርጃ አለበት? የለበትም። ተፈጥሮ እንደዚያ አይደለችምና። እውነታው እንደዚያ አይደለምና። እውቀትም ሆነ አላዋቂነት፣ በዘርና በትውልድ የሚተላለፍ ውርስና ፍርጃ ሲሆን አይታይም፤ ይሄ ደግሞ የምኞትና የፍላጎት ጉዳይ አይደለም። ተፈጥሮን የማስተዋልና እውነታውን የመገንዘብና ያለመገንዘብ ጉዳይ ነው።
እውነታው፣... በተቃውሞና በዓመፅ፣ በድጋፍና በአዋጅ፣ የብሔረሰብ ማንነት እያሉ በዘር በማቧደን አይቀየርም።
የሰው አእምሮ፣... በተፈጥሮው፣... የግል አእምሮ ነው። ይሄ እውነት፣... በምኞትና በስሜት፣ በስብከትና በአዋጅ አይቀየርም። በስምምነትና በብሽሽቅ፣ በውይይትና በመፈክር፣ በሰላማዊ ሰልፍና በዓመፅ፣ በተቃውሞና በድጋፍ... አማካኝነት እውነታው አይቀየርም። ፀሐይዋ ብርሃን መፈንጠቋን የምድር ዑደቷን፣ በውይይትና በሕዝብ ጥያቄ፣ በምርጫና በመንግስት ውሳኔ ለመቀየር እንደመሞከር ይሆናል። በቃ፣... የሰው አእምሮ፣ የግል አእምሮ ነው።
እህት በተመራመረች፣ ወንድሟ ዝምድናውን በመቁጠር ብቻ “በአውቶማቲክ” የእህቱን እውቀት መጋራት አይችልም። አእምሮ የግል ነውና። በእርግጥ፣ ለዚህ ሃቅ ደንታ የሚኖረን፣... ለእውነት፣ ለአእምሮና ለእውቀት ክብር ሲኖረን ብቻ ነው። እውነትን ከሀሰት፣ ትክክልን ከስህተት እየለየን፣... ቅጥ ያለው እውቀት ለማዳበር የምንፈልግ ከሆነ ብቻ ነው።    
የአንድ ሰው የአካል ብቃትና ጉድለት፣ ጥንካሬና ድክመትም፣... የአገርና የአህጉር፣ የብሔር ብሔረሰብ፣ የዘመድ አዝማድ፣ የሰፈር የመንደር፣ የሰው ሁሉ “የጋርዮሽ ብቃትና ጉድለት” አይደለም። የአንድ ሰው ሕይወትና ሞትም፣ የአንድ ሰው “100% ሕይወት” ወይም “100% ሞት” ማለት ነው። የጋርዮሽ ሕይወትና ሞት፣... ክፍልፋይ ሕይወትና ክፍልፋይ ሞት የለም። መቶ ሰዎች 1% ሕይወት አውጣጥተው የአንድ ሰው 100% ሕይወት፣... አይፈጥሩም። የአንድ ሰው ሞትስ? መቶ ሰዎች ሆነን፣ “1% ሞት” ተከፋፍለን እንጋራለን ብሎ ነገር የለም። አለበለዚያ በሰው ሕይወት ላይ እንደመቀለድ ይሆናል።
ስኬትና ጥፋትም እንዲሁ፣ እንደየሰውዬው የግል ጥረትና ስንፈት፣ ስኬትና ጥፋት እንጂ፣... በዘርና በብሔረሰብ የሚመጣ ውርስና ውርጅብኝ አይደለም።
ስኬትን ነጥቆ የመጋራት ሙከራና ጥፋትን ተጋርቶ የመሸከም መከራ
አንድ ሰው በጥረቱ ያፈራውን ስኬትና ትርፋማነት፣ የተቀዳጀውን ኩራትና ሽልማት በአቋራጭ ልንነጥቀው ስንሞክር ምን እናደርጋለን? “የጋርዮሽ ስኬት” እንዲመስል እናደርጋለን። “የብሔር ብሔረሰብ ውጤት፣ የአገር ኩራት፣ የጋርዮሽ ትርፋማነት፣ የጋርዮሽ የክብር ሽልማት”... ምናምን እያልን የታታሪዎችን ውጤትና ሽልማት፣ የትጉሃንን ስኬትና ክብር ነጥቀን ለመውረስ እንሞክራለን።
በሌላ በኩልስ? አንድ ብኩን ሰው፣ ስንፍናውንና እርባና ቢስነቱን፣ ስህተቱንና መጥፎነቱን፣ በዚህ ሳቢያ የሚመጣ ውድቀቱንና መዘዙን፣ ኪሳራውንና ጥፋቱን ሁሉ፣... “የጋርዮሽ” ብሎ እንዲጭንብንና እንዲያሸክመን እንመቻችለታለን። እንዴት? በዘር፣ በብሔር ብሔረሰብ፣ በትውልድ ቦታና በሰፈር... “የጋራ ማንነት” በሚል መፈክር እያቧደነ፣ የሌላ ሰው ስኬትን ለመንጠቅና የራሱን ጥፋት ለሌላ ሰው ለማሸከም ሲያመቻቸን፣... “አይሆንም” ብለን የመከላከል አቅም የማይኖረን ለምንድነው?
የዘረኝነትን በሽታና መዘዙን የመከላከል አቅም ሊኖረን የሚችለው፣... “የጋራ ማንነት” የሚለው መፈክር፣ ከእውነትና ከሕይወት ጋር የተጣላ መፈክር መሆኑን ከተገነዘብን ብቻ ነው። ያኔ፣ “የጋርዮሽ ብቃትና ጉድለት፣ የጋርዮሽ ትጋትና ስንፍና፣ የጋርዮሽ ስኬትና ጥፋት የለም። እያንዳንዱ ሰው፣ እንደየግል ብቃቱና ትጋቱ እየመዘንን የመዳኘት ቅንነትና ንፁህ ሰብዕና ያስፈልገናል። የታታሪውን ስኬት ለጋርዮሽ መንጠቅና የሰነፉን ጥፋት በጋርዮሽ መሸከም፣ ከፍትህ ጋር የተጣላ ክፋት ነው” ብለን ዘረኝነትን የመግታት አቅምና እያንዳንዱን ሰው በቅንነት መዝነን የየብቃቱን ያህል የማድነቅ ቅዱስ ሰብዕና ይኖረናል። ከዚህ ውጭ ሌላ መፍትሄ የለም።    
“የጋራ ማንነት፣ የብሔር ብሔረሰብ ማንነት” ከሚለው የጥፋት መፈክር ሳንላቀቅ፣ ዘረኝነትን የሚያስፋፉ እነዚያኑን መፈክሮች እንደያዝን መቀጠልና በአንዳች ተዓምር ዘረኝነትን ተከላክለን ከጥፋት መዳን የምንችል እየመሰለንና እያስመሰልን፣ ራሳችንንና ሌሎችን ብናታልል፣ ዋጋ የለውም። የማይበጅ፣ የማያዋጣና የማያዛልቅ እንደሆነ በየእለቱና በየአካባቢው በሚከሰቱ ጥፋቶች እያየን!
እያንዳንዱን ሰው በግል ብቃቱ፣ በተግባሩና በባሕርይው እየመዘንን በግል የመዳኘትና የማድነቅ የሞራል ሃላፊነትን እንደ ከባድ ሸክም እየሸሸን፣... በጅምላ፣... አቶ እንቶኔ ብሔረሰብ፣ ጋሼ እንትና ብሔር... ብለን በደፈናው ማሞገስና በደምሳሳው ማወደስ፣... ጭፍንነትን፣ የመጠፋፋትና የክፋት ጥላቻን የሚያበርድ፣... ከዚህ የተሻለ ሌላ ትክክለኛ መፍትሄ የሌለ እየመሰለን፣... ሁነኛ መፍትሄ ቢኖርም እንኳ ብዙ ጥረትን የሚጠይቅ ከባድ ስራ ሆኖ እየታየን፣... ልንታለል ወይም ልናታልል እንችላለን።
አሳዛኙ ነገር፣... እያንዳንዱን ሰው እንደየግል ብቃቱ፣ ተግባሩና ባሕርይው መዳኘትን ቸል እያልን፣... በበጎ ምኞት ብቻ ተገፋፍተን፣ የሚያዋጣ መስሎን፣... “እከሌ ብሔር፣ እንትና ብሔረሰብ” እያልን በጅምላ ስናሞግስ፣... በጅምላ የመፈረጅ ቅኝትንና የዘረኝነት በሽታን ከማስፋፋት ያለፈ ደህና ውጤት አያመጣልንም። ጭፍን የጅምላ ሙገሳ፣ ጭፍን የጅምላ ፍረጃን፣ የመጠፋፋትና የክፋት ጥላቻን ለሚዘሩ መጥፎ የዘረኝነት ሱሰኞች፣ የጥፋት መንገድ ከማመቻቸት የዘለለ ፋይዳ አያስገኝልንም። ለምን? ብሔር ብሔረሰብ ላይ በመመስረት በጅምላ ማሞገስ ትክክል ከሆነ፣... “የብሔር ብሔረሰብ ወዳጅነትና እርቅ” እያሉ መቧደን ትክክል ከሆነ፣... እንዲህ አይነት የጅምላ ፍረጃ ተገቢ ከሆነ፣... እንዴት የጅምላ ፍረጃን የመከላከል አቅም ይኖረናል?
የብሔር ብሔረሰብ ማንነት በሚል መፈክርና በጅምላ ፍረጃ አማካኝነት፣ በጥላቻ የመቧደን የዘረኝነት በሽታ ሲስፋፋብን፣ በየአካባቢውና በየጊዜው በርካታ ሰዎች ለሞት፣ ለጉዳትና ለስደት ሲዳረጉ እያየንም እንኳ፣... በሽታውን ለመግታትና ከእልቂት ለመዳን የሚያቅተንም፣ “በጎ የጅምላ ፍረጃ”፣ ለ”መጥፎ የጅምላ ፍረጃ” እንደሚዳርግ በደንብ አለመገንዘባችን ነው። ለዚህም ነው፣ አብዛኛው ሰው፣... ቅንነትንና መልካምነትን የሚመኝ ቢሆንም፣... ጥቂት ሰዎች በዘረኝነት ሲያቧድኑ፣ ጥላቻን ሲያስፋፉ፣ ጥፋትን ሲያስከትሉና የእልቂት ትርምስን ሲለኩሱ፣... አብዛኛው ሰው፣... ይህንን መከላከል ሲያቅተው የምንመለከተው።


Read 6332 times