Tuesday, 01 January 2019 00:00

በቤኒሻንጉል - ወለጋ ግጭት ሩብ ሚሊዮን ዜጎች ተፈናቅለዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የእርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር ወደ 8 ሚሊዮን እንደሚያሻቅብ ተጠቆመ

     በቤኒሻንጉልና በምዕራብ ወለጋ አዋሳኝ ሰሞኑን የፀጥታ ኃይሎች የወሰዱትን የህግ ማስከበር እርምጃ ተከትሎ አንፃራዊ መረጋጋት በመስፈኑ ለተፈናቃዮች እርዳታ ማቅረብ መጀመራቸውን የረድኤት ድርጅቶች አስታወቁ፡፡
ቀደም ሲል በግጭቱ ምን ያህል ሰዎች እንደተፈናቀሉ ለማወቅ አስቸጋሪ እንደነበር የጠቆመው የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ፅ/ቤት፤የተፈናቃዮች ቁጥር ሩብ ሚሊዮን መድረሱን አስታውቋል፡፡ ለእነዚህ ተፈናቃዮች አስቸኳይ እርዳታ ለማቅረብም 25.5 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ተብሏል።
ከተፈናቀሉት 255 ሺ ያህል ዜጎች መካከል 57 ሺህ የሚሆኑት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ አሶሳና ከማሺ ዞን ውስጥ የሚገኙ ሲሆን 200 ሺ ያህሉ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ተፈናቅለው፣ በምስራቅና ምዕራብ ወለጋ ውስጥ የሰፈሩ መሆናቸውን ጽ/ቤቱ በሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡
ከሰሞኑ ተፈናቃዮች ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅ የረድኤት ድርጅቶች ምልከታ ያደረጉ ሲሆን ተፈናቃዮቹ አስቸኳይ የህክምና፣የተመጣጣኝ ምግብና የመጠለያ አቅርቦት እንደሚያስፈልጋቸው አስታውቀዋል፡፡ ተማሪዎችም ትምህርት ማቋረጣቸውም በሪፖርታቸው ተመልክቷል፡፡   
ይህን እርዳታ በአስቸኳይ ለማቅረብም 25.5 ሚሊዮን ዶላር ለህክምና ቁሳቁስ፣ለምግብ፣ ለህፃናትና እናቶች አልሚ ምግብ እንዲሁም ለዘይት መግዣ እንደሚያስፈልግ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ፅ/ቤት ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡  
በአጠቃላይ በግጭት ምክንያት በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር በህዳር ወር ከነበረበት 2.2 ሚሊዮን ወደ 2.4 ሚሊዮን ከፍ ማለቱን የጠቆመው ጽ/ቤቱ፤በአዲሱ የፈረንጆች ዓመት 2019 የአስቸኳይ እርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር ወደ 8 ሚሊዮን እንደሚያሻቅብ አስታውቋል፡፡ ለእነዚህ ዜጎች እርዳታ ለማቅረብ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ብሏል፤የመንግስታቱ ድርጅት፡፡

Read 1337 times