Tuesday, 01 January 2019 00:00

“ግንቦት 7”፤ ሁሉም ለሰላም ዘብ እንዲቆም ጥሪ አቀረበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱ ፖለቲካ ከነበረበት አስፈሪ ድባብ ወደ ተስፋ ሰጪ ሁኔታ ተለውጧል ያለው አርበኞች ግንቦት 7፤ ከእንግዲህ አመጽ ለኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ትግል አማራጭ መሆን የለበትም ብሏል፡፡
ንቅናቄው ሰሞኑን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጠው መግለጫ፤የህዝቡ ትግልና በኢህአዴግ ውስጥ የተፈጠሩ የለውጥ ሃይሎች ጥምረት፣ የሃገሪቱን ፖለቲካ ከአስፈሪ ድባብ ወደ ተስፋ ሰጪ ሁኔታ እንዳሸጋገሩት ጠቁሞ፤ ይህን ተስፋ ሰጪ ሁኔታ ለማጨለም ያቀደ አመጽ ከእንግዲህ ተቀባይነት እንደሌለው አስገንዝቧል፡፡
በለውጡ ተስፋ አድርጐ ማንኛውንም የአመጽ መንገድ በማቆም ወደ ሠላማዊ ትግል መመለሱን የጠቆመው አርበኞች ግንቦት 7፤ ሌሎች የፖለቲካ ሃይሎችም ተመሳሳይ መንገድ እንዲከተሉ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ቀደም ሲል በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ታጥቀው ይንቀሳቀሱ የነበሩ አባላቱ በምንም አይነት የትጥቅና የአመጽ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዳይሳተፉ ግልጽ መመሪያ ማስተላለፉን ያስታወሰው ንቅናቄው፤ እስካሁን ድረስ አባላቱ ለሠላም መስፈንና ለህግ የበላይነት መከበር ቀናኢነት ማሳየታቸውንና ምንም አይነት የአመፃና የትጥቅ እንቅስቃሴ ውስጥ አለመሳተፋቸውን አረጋግጧል፡፡
“ለወደፊትም ምንም አይነት አመፃ ውስጥ አባሎቼ እንደማይሳተፉ እርግጠኛ ነኝ” ያለው ንቅናቄው፤ ሌሎች ሃይሎችም በዚህ መንገድ የሀገሪቱ ለውጥ የማይደናቀፍበትን ሁኔታ እንዲፈጥሩ ጠይቋል፡፡  
አመጽ ከሀገራችን ፖለቲካ ተወግዶ ፖለቲካ በሠላማዊና በሰለጠነ መንገድ የሚካሄድበትን ጊዜ ሲናፍቅ መኖሩን የጠቆመው ግንቦት 7፤በሀገሪቱ የተፈጠረው ሠላማዊና ህጋዊ የፖለቲካ ድባብ እንዳይቀለበስ በመንግስት ውስጥ ካሉ የለውጥ ሃይሎችና ለሰላምና ለህግ መከበር ከሚታገሉ ፓርቲዎች ጋር በጽናት እንደሚቆም አስታውቋል። ሁሉም ዜጋ ለሠላም ዘብ እንዲቆምም ንቅናቄው ጥሪውን  አስተላልፏል፡፡      

Read 952 times