Tuesday, 01 January 2019 00:00

ሰማያዊ ፓርቲ የመጨረሻውን ጠቅላላ ጉባኤ ያደርጋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

ፓርቲው ከሌሎች ጋር የመዋሃድ እቅዱ በጉባኤው ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል


    ሰማያዊ ፓርቲ ነገ በሚያደርገው 2ኛ ጠቅላላ ጉባኤ፣ ከአርበኞች ግንቦት 7 እና ከኢዴፓ ጋር ውህደት ለመፈፀም የተያዘውን እቅድ ያፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ የፓርቲው ሊቀ መንበር አቶ የሸዋስ አሰፋ አስታወቁ፡፡
“ተፎካካሪ ፓርቲዎች አንድ ሆነው ተጠናክረው መውጣት አለባቸው የሚል እምነት ከመነሻውም ፓርቲያችን ነበረው” ያሉት ሊቀ መንበሩ፤ “ይህ ጥረቱ ፍሬ አፍርቶ በአሁን ወቅት ከአርበኞች ግንቦት 7 እና ከኢዴፓ ጋር ውህደት በመፈፀም ለኢትዮጵያ ህዝብ የቆመ፣ ጠንካራ መሰረት ላይ የተዋቀረ ፓርቲ ለመመስረት በዋዜማው ላይ እንገኛለን” ብለዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የፓርቲው አመራሮች፤ አዲስ የሚመሰረተው ሁሉን አቀፍ ፓርቲ ግዙፍና ጠንካራ ሆኖ ገዥውን ፓርቲ የሚገዳደር ይሆናል ተብሎ ተስፋ እንደተጣለበት አስታውቀዋል፡፡ መሰረቱን በዜግነት ፖለቲካ ላይ አድርጎ የሚቋቋመው አዲሱ ፓርቲ፤በዋናነት በሃገሪቱ በዜጎች መካከል ያለውን የኑሮ አለመመጣጠን የማስተካከል አላማ ያነገበ ሲሆን ርዕዮተ ዓለሙን በማህበራዊ ፍትህ ላይ ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመራሮቹ ጠቁመዋል።  
ነገ እሁድ ታህሳስ 21 የሚካሄደው የሰማያዊ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ፣ ምናልባትም የመጨረሻው የፓርቲው ጉባኤ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ጉባኤው የውህደት ዕቅዱን ያፀድቃል ተብሎ ሙሉ እምነት እንደተጣለበት አመራሮቹ ገልጸዋል፡፡
ከተመሰረተ 7 ዓመታት ያስቆጠረው ሠማያዊ ፓርቲ፤ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በየጊዜው ከሚሰጣቸው መግለጫዎች ባሻገር በአዲስ አበባና በተለያዩ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፎችን በማዘጋጀት ትግል ሲያደርግ የቆየ ጠንካራ ፓርቲ ነበር ብለዋል፤ አመራሮቹ፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ፣ ኢዴፓ እና አርበኞች ግንቦት 7 አሁን ያላቸውን ህልውና አፍርሰው፣ በአመራር ሳይሆን በአባላት ደረጃ ተዋህደው፣ አዲስ ሃገር አቀፍ የፖለቲካ ድርጅት እስከ መጋቢት ወር ለመመሥረት አቅደው እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡  

Read 2019 times