Print this page
Tuesday, 01 January 2019 00:00

ዝክረ ጋዜጠኛ ደምስ በለጠ (የመጨረሻው ቆይታ ከአዲስ አድማስ ጋር)

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

በተረጋጋ አንደበት ነገሮችን የማስረዳት ችሎታውና ገለፃው ትኩረትን የመሳብ አቅም አለው፡፡ አንደበተ ርቱዕ ነው፡፡ ምናልባት የሬዲዮ ጋዜጠኛና የሥነ ፅሁፍ ባለሙያ መሆኑ ሳይጠቅመው አልቀረም፡፡ “ስለ ኢትዮጵያ ክፉ ክፉውን ሳይሆን ቀናውን ማሰብ ይበጃል” የሚል ፅኑ እምነት አለው፡፡ በእድሜም በእውቀትም መብሰሉ ያመጣው ድምዳሜ ይመስላል። መንፈሰ ጠንካራ እንደሆነ ሁለመናው ይመሰክራል፡፡ ጋዜጠኛና መምህር ደምስ በለጠ፤ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የአገሩን መሬት የረገጠው ከ32 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ በገባ በሳምንቱም በአዲስ አድማስ ቢሮ ተገኝቶ፣ ሰፊ ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡ የስደት ህይወቱን፣ የወደፊት ህልሙንና ራዕዩን፣ ለአገሩ ያለውን በተስፋ የተሞላ ምኞት አውግቶናል - በቃለ ምልልሱ፡፡ በሳምንቱ ድንገተኛ ህልፈቱ ተሰማ፡፡ ለብዙዎች እጅግ አስደናጋጭና አሳዛኝ ነበር፡፡
ለ7 ዓመታት ያህል በሩሲያ በትምህርትና በተለያዩ የሚዲያ ስራዎች የቆየው ጋዜጠኛ ደምስ፤ በሰሜን አሜሪካ በሬዲዮ ጋዜጠኝነትና በመምህርነት ስራ ላይ ተሰማርቶ ለ25 ዓመታት ኖሯል፡፡ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የኢንተርኔት የአማርኛ ሬዲዮ መስራቹ ጋዜጠኛ ደምስ፤ ወደ አገሩ የተመለሰው ባዶ እጁን አልነበረም፡፡ ብዙ ተስፋና ራዕይ ሰንቆ ነበር፡፡ በሚዲያው ኢንዱስትሪ በርካታ ተግባራትን ለማከናወን፣ በሃገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ለማገዝና የህዝብ አንደበት ለመሆን እንዲሁም በኢትዮጵያ ጠንካራ ሚዲያ ለማቋቋም እቅድ እንደነበረው አውግቶናል፡፡ ለአዲስ አድማስ በቋሚነት ለመጻፍ እንደሚፈልግም  ነግሮን ነበር፡፡  
አዲስ አበባ ተወልዶ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ያደገው ደምስ በለጠ፤ ከአሜሪካ ከመጣ በኋላ ከባህር ዳር በመጀመር በርካታ የኢትዮጵያ ከተሞችን የመጎብኘት ዕቅድ ነበረው፡፡ “ኢትዮጵያዊነት ፅኑ ማንነት ነው” የሚለው ደምስ፤ ላለፉት በርካታ ዓመታት በአማራ ህዝብ ላይ ሲደርስ የነበረውን ግፍና በደል፣ ስደትና መፈናቀል---ሳይታክት በሬዲዮ ፕሮግራሙ ሲያጋልጥ የቆየ ሲሆን በሃገር ቤትም  የጀመረውን ትግል በሚዲያው ለመቀጠል ዓላማ ነበረው፡፡
ከመንግስት ጋር በነበረው የፖለቲካ ልዩነት ሳቢያ ሶስት ወንድሞቹ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ወደ አገሩ መጥቶ መቅበር ባለመቻሉ በእጅጉ እንደሚያስቆጨው የነገረን ጋዜጠኛ ደምስ፤ በሌላ በኩል ፈጣሪ እድሜ ሰጥቶ ያቆየለትን ወላጅ እናቱን በ92 ዓመታቸው ለማግኘት በመቻሉ የተሰማውን ደስታ አጋርቶን ነበር። የሚያሳዝነው ይሄን ደስታውንና ናፍቆቱን በቅጡ ለመወጣትና ለማጣጣም በቂ ጊዜ ሳያገኝ ድንገት ማለፉ ነው፡፡   
የዚህ ባለ ብዙ ህልም መምህርና ጋዜጠኛ ድንገተኛ ዜና እረፍት ሲሰማ ብዙዎች ተደናግጠዋል፤ ተረብሸዋል። ደምስ እንዴት ሞተ? በምን ምክንያት ሞተ? እስካሁን ምላሽ ያላገኘ ጥያቄ ነው፡፡ ፖሊስ ጉዳዩን በትኩረት መርምሮ የአሟሟቱን መንስኤ ይፋ እንዲያደርግ፣ ቤተሰቦቹ የቅርብ ወዳጆቹና የሙያ አጋሮቹ እየጠየቁ ነው፡፡
በብዙ ናፍቆት ወደ ሀገሩ የተመለሰው፣ በብዙ ተስፋ ነገን ሲያልም የነበረው፤ ነገር ግን በአጭሩ የተቀጨው ጋዜጠኛ ደምስ፤ ከአዲስ አድማስ ጋር በነበረው ቆይታ፣ የዛሬ 25 አመት ከሩስያ ቋንቋ ወደ አማርኛ የመለሰውን የአሌክሳንደር ፑሽኪንን ግጥም በቃሉ ተወጥቶት ነበር። እንዲህ  በጽሁፍ አስፍረነዋል፡፡  
“አስታውሳለሁ የአንድን ቅጽበት
ፊት ለፊቴ አንቺ የተደቀንሽበት
እንደ አጭር ጊዜ እይታ
እንደ ብሩህ ንፁህ ውበት
ያለ ተስፋ በሚያሰቃይ ንዴት
በግርግር በስጋት በጩኸት
ለረጅም ጊዜ ለስላሳ ድምጽ ተሰማኝ
እና በአይነ ህሊናዬ ውብ ድምጽሽ ታየኝ
አመታት አለፉ
የአውሎ ነፋስ መንፈስ ሽብርም
አጠፋው የቀድሞውን ህልም
እና ረሣሁት ያንቺን ድምጽ ለስላሳውን
ሩቅ ሀገር በጨለማው ግባት
ተዘርግተው የኔ ፀጥተኛ ቀናት
ያለ አምላክ ያለ እምባ ያለ ፍቅር ያለ ህይወት
በነፍሴ መነሳሳት ንቃት
እንደገና ይኸው መጣሽብኝ ወዴት
እንደ አጭር ጊዜ እይታ
እንደ ብሩህ ንፁህ ውበት
አምላክም ጥልቅ ስሜትም
ህይወትም እምባም ፍቅርም
እና ልቤ ይመታል በፍንደቃ
ህያውነት ተሰማው እንደገና ነቃ”
ደምስ የአሌክሳንደር ፑሽኪን ግጥሞችን ከሩስኪ  ወደ አማርኛ መተርጎሙን አውግቶናል፤ ነገር ግን ለህትመት አልበቁም፡፡ የራሱም በርካታ ግጥሞችም አሉት፡፡ ሥራዎቹን ለህትመት ማብቃት ቢቻል የደምስ ነፍስ ጮቤ ትረግጣለች፡፡ ልፋቱም ለፍሬ ይበቃል። ቤተሰቦቹና የቅርብ ወዳጆቹ ትኩረት ቢሰጡት መልካም ነው፡፡  
“ህይወት አጋጣሚ ነች” የሚለው መምህሩና ጋዜጠኛው፤ “ሰዎች አጋጣሚያቸውን መኖር አለባቸው” ብሎ ያምናል፡፡ እርሱም አጋጣሚውን ኖሯል፡፡ ነፍሱ በሰላም ትረፍ!!
የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል፣ በጋዜጠኛና መምህር ደምስ በለጠ ድንገተኛ ህልፈት የተሰማውን መሪር ሃዘን እየገለፀ፣ ለቤተሰቦቹ፣ ለወዳጅ ዘመዶቹና ለአድናቂዎቹ መፅናናትን ይመኛል፡፡

Read 2487 times