Tuesday, 01 January 2019 00:00

እነ ዶ/ር ብርሃኑ አዲስ ብሔራዊ ፓርቲ ሊመሰርቱ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 በዜጋ ፖለቲካ የሚያምን ሁሉ ሊቀላቀል ይችላል ተብሏል


    በፓርቲ ጥምረት ታሪክ ውስጥ ጉልህ ቦታ የነበረውን የ1997ቱን ቅንጅት የፈጠሩ ፖለቲከኞችና ፓርቲዎች በድጋሚ ሊሰባሰቡ መሆኑ ተሰምቷል፡፡ የሚሰባሰቡት ደግሞ እንደከዚህ ቀደሙ በ“ቅንጅት” ወይም በጥምረት ሳይሆን በውህደት ነው፡፡ ውህደቱም የአመራሮችን በጎ ፍቃድ ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡ ዋነኛው የውህደቱ ፈፃሚዎች የየፓርቲዎቹ አባላት ይሆናሉ ተብሏል፡፡
ፓርቲዎቹ የሚዋሃዱት በአመራር ደረጃ ሳይሆን ከስር ጀምሮ ባሉ አባላት ነው፡፡ የዚህ ውህደት ፈፃሚዎች ደግሞ አርበኞች ግንቦት 7፣ ሰማያዊ፣ ኢዴፓ፣ የቀድሞ አንድነት ፓርቲ አባላት ናቸው፡፡ ሌሎችም በዜግነት ፖለቲካ የሚያምኑ የዚህ ውህደት አካል መሆን ይችላሉ ተብሏል፡፡
ሠማያዊ ፓርቲ ላለፉት ሁለት አመታት በአላማ ከሚመሳሰሉት ጋር ለመዋሃድ ሌት ተቀን ባለመታከት ሲሰራ መቆየቱን የጠቆሙት ሊቀመንበሩ አቶ የሸዋስ አሠፋ፤ “ጥረታችን ፍሬ አፍርቶ አሁን ለኢትዮጵያ ህዝብ የቆመ፣ ጠንካራ ስረ መሠረት ያለው ፓርቲ በጋራ ለመመስረት በዋዜማው ላይ እንገኛለን” ብለዋል፡፡
አዲሱን ፓርቲ ለመመስረት ነባር ፓርቲዎች ህልውናቸው ሙሉ ለሙሉ እንደሚከስም የሚገልፁት አቶ የሸዋስ፣ ሊቀመንበሩን ጨምሮ በተለያየ ደረጃ ያሉ አመራሮችም ወደ የወረዳቸው ሄደው ከህዝብ ጋር ተወያይተው፣ በአባሎቻቸው በድጋሚ ከተመረጡ ብቻ አዲስ በሚመሠረተው ፓርቲ ውስጥ የማዕከላዊ ኮሚቴም ሆነ የአመራርነት ቦታ ያገኛሉ እንጂ ቀድሞ አመራር ስለነበሩ አሁንም ይሆናሉ ማለት አይደለም፡፡
ይህ አካሄድም በሀገሪቱ የፓርቲ ፖለቲካ ታሪክ፣ ህዝባዊ መሠረት ያለውን የመጀመሪያ ድርጅት ለመመስረት የሚያስችል ነው ይላሉ - አቶ የሸዋስ፡፡
የአርበኞች ግንቦት 7 ዋና ፀሐፊ አቶ እንዳርጋቸው ጽጌ በበኩላቸው፤ የሚዋሃደው ፓርቲ ምን ዓይነት ቅርፅና አደረጃጀት ይኖረዋል? የሚለውን እንደሚከተለው ያብራራሉ፡፡
ውህደቱን የምንፈጽመው በቀድሞ “ቅንጅት” ውስጥ የነበርን አካላት ነን፡፡ እነዚህ አካላት በየፊናቸው ለዲሞክራሲ እውን መሆን ሲታገሉ ቆይተዋል፡፡ በመሠረታዊ የፖለቲካ ፕሮግራምና  አላማ ላይ ልዩነት የለንም፡፡ ድርጅቶቹ እንደ ድርጅት፣ በመጀመሪያ ራሳቸውን ካጠፉ በኋላ ነው የሁላችንም አባላት ተቀላቅለው፣ በአንድ ላይ በወረዳ ደረጃ፣ የወረዳ የድርጅት መዋቅር እንፈጥራለን፡፡ ሁሉም ድርጅቶች እንደገና ተበትነው፣ እንደገና ተቦክተው፣ ተጋግረው፤ መሪዎቹ ሲጣሉ የማይበተን ፓርቲ ነው የሚመሠረተው፡፡
የሚፈጠረው ፓርቲ ከዚህ ቀደም እንደተፈጠሩት መሰል ፓርቲዎች በአመራር ቦታ ሽሚያ መልሶ እንደማይከስም ምን ማስተማመኛ አለ ለሚለው ጥያቄ አቶ አንዳርጋቸው ሲመልሱ፤ “የሚመሠረተው ፓርቲ ሁሉም አሁን ያለውን ህልውናውን አፍርሶ፣ እንደገና ተጠፍጥፎ ከስር ጀምሮ የሚፈጠር በመሆኑ፣ የመፍረስ ስጋት አይኖርበትም” ብለዋል፡፡
“አሁን ውህደት ሊፈጥሩ ያቀዱ ፓርቲዎችን በሊቀመንበርነትና በተለያየ አመራር እየመሩ ያሉ ግለሰቦች እንደ ማንኛውም አባል ወደ ወረዳ ወርደው፣ በወረዳቸው ይወክሉን ተብለው ከተመረጡ ብቻ ወደ ከፍተኛው አመራር መምጣት እንደሚችሉ መተማመን ላይ ደርሰን ነው ስራውን የጀመርነው ያሉት አቶ አንዳርጋቸው፤ የሚመሠረተው ፓርቲ ተመልሶ እንዳይበተን ሆኖ የሚሠራ ነው ይላሉ፡፡
በዜግነትና በህብረ ብሔራዊ አንድነት የሚያምኑ ፖለቲከኞች በሙሉ አባል መሆን የሚችሉ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም እንደነበረው መንግስት በሚያሠርፃቸው ሠላዮች የሚቋቋመው ድርጅት ይፈርሳል የሚል ስጋት እንደሌለም አቶ አንዳርጋቸው ይገልፃሉ፡፡ አሁን ሸፍጠኛ መንግስት አለ ብለው እንደማያምኑ የተናገሩት ፖለቲከኛው፤ ከዚህ አንፃር የሚመሠረተው ፓርቲ በጠንካራ መዋቅር የተዋሃደ ነው የሚሆነው ብለዋል፡፡
የምርጫ መራዘም አለመራዘም ጉዳይ ከኛ ዝግጅት ጋር አይገናኝም የሚሉት አቶ አንዳርጋቸው፤ አገሪቱ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጁ ከሆነች እኛ ባንዘጋጅም ቢካሄድ ይቅር አይለንም ብለዋል፡፡ ሃገሪቷ ሠላምና፣ የህግ የበላይነት የሰፈነባት፣ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ነፃ ተቋማት የፈጠረች ስትሆን ብቻ ነው ነፃና ገለልተኛ፣ በህዝብ ተአማኒ የሆነ ምርጫ ማካሄድ የሚቻለው የሚል እምነት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡
ታች ያሉ የወረዳ ተቋማትና የፀጥታ አካላት፣ ሚዲያዎች፣ ፍ/ቤቶች ባልተጠናከሩበት ሁኔታ የሚካሄድ ምርጫ ከሆነ ግን ሀገሪቱን ወደ ባሰ ቀውስ ይመራታል የሚሉት አቶ አንዳርጋቸው፤ በዋናነት በክልል ደረጃ ያሉ የፀጥታ አካላት ነፃና ገለልተኛ መሆናቸው መረጋገጥ አለበት ይላሉ - አርበኞች ግንቦት 7 በተለያዩ ክልሎች አላማውን ለማስረዳት በተንቀሳቀሰበት ወቅት ከፀጥታ አካላት እየገጠመው ያለውን ፈተና በመጥቀስ፡፡
አሁን ብዙዎች ትኩረት ያደረጉት በፌደራል ደረጃ ስላለው ለውጥ ነው ያሉት ፖለቲከኛው፤ የክልሎች የፀጥታ መዋቅር ግን አድራጊ ፈጣሪ ሆኖ፣ በወንጀል የተጠረጠረን አካል እንኳ ለህግ አላስረከብም የተባለበት ደረጃ ተደርሷል ይላሉ፡፡ ይህ አይነት የፀጥታ ሃይል ባለበት ሁኔታ፣ ፓርቲዎች በነፃነት ተንቀሳቅሰው፣ ለምርጫ ለመዘጋጀትና በምርጫው ለመሳተፍም ይቸግራቸዋል ባይ ናቸው - አቶ አንዳርጋቸው፡፡
አሁን በሀገሪቱ ዲኤንኤ እየተመረመረ በሚመስል መልክ የዘር ፖለቲካ ሠፊውን ቦታ ይዟል የሚሉት ፖለቲከኛው፤ የዚህን በዘር ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ ጉዳት አሁን ሁሉም እየተረዳው የመጣ ይመስላል የሚል ግምት አላቸው፡፡
ህዝቡ የዜግነት ፖለቲካን እንደሚፈልግ መረዳት ችለናል ያሉት የግንቦት 7 ዋና ፀሐፊ፤ ህዝቡ ዛሬም ነባሩ የኢትዮጵያዊነት እሴት አብሮት ነው ያለው፤ የዘር ፖለቲካ በሽታው ያለው ልሂቃኑ ዘንድ ነው ይላሉ፡፡ “በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምን፣ ዘር መቁጠር የማይፈልግ ህዝብ ቁጥሩ ከፍተኛ ነው” የሚሉት አቶ አንዳርጋቸው፤ የህዝቡንና የልሂቃኑን አካሄድ ለይቶ ማስቀመጥ ያስፈለጋል ይላሉ - ትግላቸውም በዚህ መንገድ እንደሆነ በመግለጽ፡፡ ርዕዮተ አለምን በተመለከተ ያብራሩት አቶ የሸዋስ አሰፋ፤ ለጊዜው “የማህበራዊ ፍትህ” ርዕዮተ አለም አዋጪ ነው የሚል መግባባት እንዳለ ነገር ግን ቀጣይ ውይይት እንደሚደረግበት አስረድተዋል፡፡
“ማህበራዊ ፍትህ” ርዕዮተ አለም፤ ማህበራዊ ዲሞክራሲና ሊበራል ርዕዮት አለምን ታሳቢ ያደረገ ሲሆን በዋናነት ያልተመጣጠነውን የዜጐች ኑሮ ለማስተካከል፣ የእኩል ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነትን እውን የሚያደርግ ርዕዮተ አለም ነው ብለዋል፡፡
በመጋቢት መጨረሻ ውህደቱ እውን ይሆናል ተብሎ ለሚጠበቀው ለዚህ የዜግነት ፖለቲካ አራማጅ አዲስ ፓርቲ ምስረታ፤ ከወዲሁ በአዲስ አበባና በተለያዩ የክልል ከተሞች ህዝባዊ ውይይቶችም እየተደረጉ መሆኑ ታውቋል፡፡
የአዲሱ ፓርቲ ስያሜ የሚታወቀው ከመስራች ጉባኤ በኋላ ሲሆን፤ የፓርቲው መዋቅርም በመላ ሀገሪቱ ይዘረጋል ተብሏል፡፡

Read 4060 times