Tuesday, 01 January 2019 00:00

የማንነትና የድንበር አጣሪ ኮሚሽን ህገ መንግስቱን አይጥስም ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 “ኮሚሽኑ የተቋቋመው በህገ መንግሥቱ ፍልስፍና ላይ ተመስርቶ ነው”


     ባለፈው ሳምንት የፀደቀው የማንነትና የድንበር ጉዳዮች አጣሪ ኮሚሽን፤ በየትኛውም መንገድ ህገ መንግስቱን እንደማይጥስ የገለፁት የህግ ባለሙያዎች፤ በፓርላማ አባላት የተነሳው ክርክርም የህግ መሰረት የሌለው ነው ብለዋል፡፡
የትግራይ ክልል ተወካዮች በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አዋጁ ህገ መንግሥቱን ይፃረራል ሲሉ የሞገቱ ሲሆን ተመሳሳይ ተቃውሞና ሙግትም በትግራይ የፖለቲካ ልሂቃን ሲስተጋባ ሰንብቷል፡፡
የትግራይ ክልል የህገ መንግስት ተርጓሚ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሰሞኑን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ ኮሚሽኑ ህገ መንግስቱን የሚጥስና ለክልሎች የተሰጠውን ሥልጣን የሚጋፋ መሆኑን በመግለፅ ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም መምህሩ ሜ/ጀነራል አበበ ተ/ሃይማኖትም፤ የኮሚሽን አዋጁ ህገ መንግስቱን ይጥሳል ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ ህገ መንግሥቱ የማንነትና የድንበር ጉዳይን የመፍታት ብቸኛ ስልጣን የሚሰጠው ለፌዴሬሽን ም/ቤት ነው የሚሉት ጀነራሉ፤ የኮሚሽኑ መቋቋም ህገ መንግስቱ በግልፅ ለፌዴሬሽን ም/ቤት የሰጠውን ስልጣን መጋፋት ነው ብለዋል፡፡
የድንበር ወይም የማንነት ጥያቄ ሲቀርብ፣ የፌዴሬሽን ም/ቤት በህገ መንግስቱ በተሰጠው ስልጣን አጣሪ ጉባኤ ያቋቁማል የሚሉት ሜ/ጀነራል አበበ፤ መሆን የነበረበትም በፌዴሬሽን ም/ቤት ስር ያለውን አጣሪ ጉባኤ ሰፋና ጠንከር አድርጎ ማደራጀት ነው እንጂ ሌላ ኮሚሽን ማቋቋም ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡
የህግ ባለሙያና ጠበቃው አቶ አዲሱ ጌታነህ በበኩላቸው፤ የተቋቋመው አጣሪ ኮሚሽን በየትኛውም መመዘኛ ህገ መንግስቱን የሚነካ አይደለም ይላሉ፡፡ ህገ መንግስቱን ይፃረራል የሚለው መከራከሪያ፣ የኮሚሽኑን ኃላፊነትና ተግባር ካለመረዳት እንዲሁም የፌዴሬሽን ም/ቤትን ስልጣንና ኃላፊነት በአግባቡ ካለመገንዘብ የሚመጣ ነው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
የተቋቋመው ኮሚሽን ተግባርና ኃላፊነቱ የውሳኔ ሰጪነት ሳይሆን ለውሳኔ ግብአት የሚሆን ጥናት አጥንቶ ሪፖርት የማቅረብ ብቻ ነው ያሉት የህግ ባለሙያው፤ ይህ አሰራርም ህገ መንግስታዊ ድጋፍ አለው ይላሉ፡፡
“ህገ መንግስት ጥሷል፤ የፌዴሬሽን ም/ቤትን ኃላፊነት ተጋፍቷል ሊባል የሚችለው ውሳኔ የመስጠት መብት ቢኖረው ነበር” ያሉት አቶ አዲሱ፤ ከዚህ ቀደምም የተለያዩ ጉዳዮችን ለማጥናትና የመፍትሄ ሃሳብ ለማቅረብ የተቋቋሙ መሰል ኮሚሽኖችና አጣሪ ኮሚቴዎች መቋቋማቸውን አስታውሰዋል፡፡
“ጉዳዩ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ካልተጫኑት በስተቀር “አዋጁ ህገ መንግስቱን ይጥሳል” የሚለው መከራከሪያ ውሃ የሚቋጥር አለመሆኑን የሚናገሩት  የህግ ባለሙያው፤ ኮሚሽኑ መቋቋሙ እንዲያውም በህግ ሽፋን የሚፈጠረውን የአሰራር ክፍተትና ድክመት በተቀላጠፈ መልኩ ለማረምና ውሳኔ ለመስጠት የሚያግዝ በመሆኑ በቀና ልቦና መታየት ያለበት ነው ይላሉ፡፡
ለዚህ ሁሉ ቀውስ የዳረገን የፌዴሬሽን ም/ቤት ስራውን በተቀላጠፈ መልኩ አለመስራቱ ነው የሚሉት አቶ አዲሱ፤ ኮሚሽኑ ችግሩን እንዲያጠና መደረጉ የተጓተተን ጉዳይ ለማፋጠን ጠቃሚ ነው ብለዋል፡፡
የአቶ አዲሱን ሃሳብ ሙሉ ለሙሉ የሚጋሩት የቀድሞ የፓርላማ አባልና የህግ ባለሙያው አቶ ወንድሙ ኢብሳ፤ ኮሚሽኑ መቋቋሙ እንዲያውም ህገ መንግስቱ የበለጠ ስራ ላይ እንዲውል ያደርጋል ባይ ናቸው፡፡ ኮሚሽኑ የተቋቋመው በህገ መንግስቱ ፍልስፍና ላይ ተመስርቶ ነው የሚሉት አቶ ወንድሙ፤ አጥኚ ኮሚሽን በየትኛውም ደረጃ ማቋቋምን የሚከለክል ወይም ለአንድ አካል ብቻ የሚሰጥ የህገ መንግስት አንቀፅ ሲሉ ያስረዳሉ፡፡  
ኮሚሽኑ መቋቋሙ ትክክለኛ ጥናት አድርጎ የህገ መንግስቱን ፍልስፍና ስራ ላይ ለማዋል ያግዛል የሚል አቋም የሚያንፀባርቁት የህግ ባለሙያው፤ የፌዴሬሽን ም/ቤት አጣሪ ጉባኤ አቋቁሞ ያጥና ማለት ዜጎች የተሰላቹበትን በሙያ ያልተደገፈ፤ የፖለቲካ ጥናትና ውሳኔን ለማስቀጠል ካለ ፍላጎት ነው ይላሉ፡፡
“የፌዴሬሽን ም/ቤት የባለሙያዎች ሳይሆን የካድሬዎች ስብስብ ነው” የሚል እምነት እንዳላቸው የገለፁት አቶ ወንድሙ፤ የሚቋቋመው ኮሚሽን ግን በተለያየ ዘርፍ ያሉ ምሁራንና ባለሙያዎች የጥናት ሙያቸውን ተግባራዊ የሚያደርጉበት በመሆኑ ህገ መንግስቱን የማይጋፋ የችግር መፍቻ መንገድ ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡
በ1997 የተቋቋመው የምርጫ ጉዳይ አጣሪ ኮሚሽን መሰል ተአማኒነት አጥቶ በርካታ ቀውስ መፈጠሩን ያስታወሱት አቶ ወንድሙ፤ አሁን በገለልተኛ አካል ጉዳዩ እንዲጣራ መደረጉ መተማመንን ሊፈጥር ይችላል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡
የህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ በዚህ ኮሚሽን በህግ የተወሰደበት ስልጣን ወይም እንዲፈርስ የተላለፈበት ውሳኔ እስከሌለ ድረስ የጉባኤው መብት ተጥሷል የሚለው መከራከሪያም መሰረት የሌለው ነው ብለዋል - የህግ ባለሙያዎቹ፡፡         


Read 4185 times