Print this page
Tuesday, 01 January 2019 00:00

የዓለማችን የስፖርት ኢንዱስትሪ በ2018 ላይ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

• በዓመት እስከ 620 ቢሊዮን ዶላር መዋዕለንዋይ፤ ከ62 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ፤
   • ከ8000 በላይ የስፖርት ውድድሮች፤ ከ3.5 ቢሊዮን በላይ ተመልካች፤ ስፖርተኛ እና ፕሮፌሽናል አትሌት
   • ከ60 በላይ ቢሊየነሮች፤ ከ22.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዓመታዊ ደሞዝ


    በዓለማችን የስፖርት ኢንዱስትሪው በየዓመቱ ከ480 እስከ 620 ቢሊዮን ዶላር እንደሚንቀሳቀስበት በጥናት ተረጋግጧል፡፡ በስፖርት ምርቶች፣ አልባሳት፣ ትጥቅና ቁሳቁሶች፤ በስፖርተኞች ደሞዝ፣ ቦነስ ፣ የሽልማት ድርሻና የዝውውር ገበያ ክፍያዎች፤ በተለያዩ የብሮድካስትና የንግድ መብቶች፤ በስፖርት ሚዲያና አማካሪ ኤጀንሲዎች፤ በስፖርት ኢንቨስተሮችና ስፖንሰሮች፤ በስፖርት መሰረተልማት፤ በስፖርት ብሮድካስተሮች፤ በስፖርት አወዳዳሪ ተቋማት…ባለድርሻነት የስፖርት ኢንዱስትሪው  እስከ 1.3 ትሪሊዮን ዶላር እንደሚያስተዳድርም  ይገመታል፡፡
በመላው ዓለም ከ8ሺ በላይ የስፖርት ውድድሮች በየዓመቱ እንደሚካሄዱ የሚያመለክት አንድ ጥናት ከኢንዱስትሪው ከፍተኛውን የገበያ ድርሻ በ43 %  የያዘው እግር ኳስ መሆኑን ይጠቅሳል፡፡ አሜሪካን ፉትቦል በ13%፤ ቤዝቦል 12%፤ ፎርሙላ 17%፤ ቅርጫት ኳስ 6%፤ ሆኪ 4%፤ ቴኒስ 4% እንዲሁም ጎልፍ 3%  ድርሻ ሲኖራቸው የተቀሩት ሌሎች ስፖርቶች እና ውድድሮቻቸው ቀሪውን 8 % ገበያ ይዘዋል፡፡
በፕሮፌሽናል የስፖርት ውድድሮች በዓለም ዙርያ የሚገኘው ገቢ በ2018 እኤአ ላይ ዕድገት እያሳየ ቀጥሏል፡፡  በሚዲያና የብሮድካስት መብት፤ በስፖንሰርሺፕ እና በተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች በየዓመቱ በስፖርት ኢንዱስትሪው እስከ 62 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚሆንም እየተገለፀ ነው፡፡ በዓለማችን የስፖርት ኢንዱስትሪ ከሚገባው ገቢ  ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው  እግር ኳስ ሲሆን በተለይ  ባለፉት 10 ዓመታት አጠቃላይ ገቢው  በ3 እጥፍ  ጭማሪ ማሳየቱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በእግር ኳስ ስፖርት ከቲቪ የስርጭት መብት፣ ከስታድዬም ትኬት ሽያጭ እና በተለያዩ የንግድ ውሎች ባለፈው 2018 እኤአ ከ25.5 ቢሊዮን ዩሮ በላይ ገቢ ሆኗል፡፡ ከአውሮፓ እግር ኳስ ባሻገር በዓለም የስፖርት ኢንዱትሪ ላይ ከፍተኛው ገቢ የሚንቀሳቀሰው በሰሜን አሜሪካ በሚካሄዱ የተለያዩ ፕሮፌሽናል ስፖርት ውድድሮች ሲሆን በተለይ ትልቁን የስፖርት ገበያ በሚቆጣጠረው NFL (National football league) በየዓመቱ የሚንቀሳቀሰው መዋዕለንዋይ ከ14 ቢሊዮን ዶላር በላይ መሆኑ ይጠቀሳል፡፡
21ኛው የዓለም ዋንጫ የፈጠረው መነቃቃት
2018 እኤአ የዓለም ዋንጫ ዓመት ስለነበር በተለይ በዓለም እግር ኳስ ላይ ከፍተኛ የገቢ መነቃቃትን ፈጥሯል፡፡ ራሽያ ያስተናገደችው 21ኛው የዓለም ዋንጫ እስከ 2020 እ.ኤ.አ ድረስ በእግር ኳሱ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በስፖርት ኢንዱስትሪው ተፅእኖ መፍጠሩን ይቀጥላል፡፡ በፊፋ ስር የሚንቀሳቀሰው (PMSE) ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው ሪፖርት 21ኛውን የዓለም ዋንጫን በተለያየ መንገድ የተከታተለው ከዓለም ጠቅላላ የህዝብ ብዛት ግማሹ ይሆናል፡፡ 21ኛው የዓለም ዋንጫን ዕድሜያቸው 4 ዓመት እና ከዚያም በላይ የሚሆናቸው 3 ቢሊዮን 262 ሚሊዮን የዓለማችን ህዝቦች ቢያንስ 1 ደቂቃን ሊከታተሉት በቅተዋል፡፡  በተለያዩ የዲጂታል ሚዲያ አውታሮች፣ ለህዝብ መመልከቻ ስፍራዎች፣ ለባርና ሬስቶራንት ዓለም ዋንጫውን የታደሙት ደግሞ ከ309.7 ሚሊዮን በላይ ናቸው፡፡ ይህም ብራዚል አስተናግዳ ከነበረው 20ኛው የዓለም ዋንጫ  በ9.5% ጨምሯል፡፡
በሞስኮው ሉዚሂንኪ ስታድዬም ፈረንሳይ ከክሮሽያ ያደረጉትን የ21ኛው የዓለም ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ቢያንስ ከ1 ደቂቃ በላይ የተከታተሉት ደግሞ ብዛታቸው 1.12 ቢሊዮን ሆኗል፡፡ 884.37 ሚሊዮን ተመልካች የዋንጫ ጨዋታውን በቀጥታ የቴሌቭዥን ዙር ብቻ ሲመለከተው፡፡ በተለያዩ ዲጂታል የሚዲያ አውታሮች፤ በህዝብ መመልከቻ ስፍራዎች፤ በባር፣ በሬስቶራንትና በተለያዩ የመዝናኛ ስፍራዎች  ፍፃሜውን የተመለከቱት ከ231.82 ሚሊዮን በላይ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ የ21ኛው የዓለም ዋንጫ በአማካይ 191 ሚሊዮን ተመልካች በዓለም ዙርያ ነበረው፡፡ ፊፋ በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ከቲቪ መብት 3 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም ከስፖንሰርሺፕ 1.65 ቢሊዮን ዶላር የሚያገኝ ሲሆን በ2022 ኳታር እስከምታስተናግደው 22ኛው የዓለም ዋንጫ የሚያገኘው ትርፍ 100 ሚሊዮን ዶላር ይሆናል፡፡ የዓለም ዋንጫው በዓለም የስፖርት ኢንዱስትሪ ከማስተዋወቂያ ጋር በተያያዘ ወጭ የሚሆነውን ገንዘብ ከፍ የሚያደርግ ሲሆን በ2018 ብቻ ለስፖርት ማስታወቂያዎች ከ2.4 ቢሊዮን ዶላር ወጭ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ሙካሽ አምባኒና ከ60 በላይ ቢሊየነሮች
በዓለማችን በስፖርት ክለቦች እና ቡድኖች ባለቤትነት፤ ባለድርሻነትና ኢንቨስትመንት የሚንቀሳቀሱ ከ60 በላይ ቢሊየነሮች በ2018 የተነዘገቡ ሲሆን የሃብታቸው መጠን ከ375 ቢሊዮን ዶላር በላይ ነው፡፡ በ78 የስፖርት ቡድኖችና ክለቦች ከፍተኛ የባለቤትነት ድርሻ ያላቸው የዓለማችን   ቢሊዬነሮች በተለይ በእግር ኳስ ላይ ማተኮራቸው የስፖርቱን ትርፋማነት ያመለክታል፡፡ ከዓለማችን የስፖርት ኢንቨስተሮች በከፍተኛ ሃብት አንደኛ ደረጃን የሚወስደው ደግሞ ህንዳዊው ሙካሽ አምባኒ ነው፡፡ የህንዱ ክሪኬት ክለብ “ሙምባይ ኢንድያንስ” ባለቤት ሲሆን ከስፖርት ክለቦች ባለሀብቶች በሃብቱ አንደኛ ደረጃ የወሰደው ከ3 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነና ያስመዘገበው ሃብትም 47.7 ቢሊዮን ዶላር ነው ተብሏል፡፡  ሙካሽ አምባኒ ሙምባይ ኢንድየንስ የተባለውን ክሪኬት ቡድን በ2008 እ.ኤ.አ ላይ በ100 ሚሊዮን ዶላር ገዝቷል፡፡
 ፍሎይድና ከፍተኛ ዓመታዊ ገቢና ሃብት ያላቸው ስፖርተኞች
በ2018 በከፍተኛ ገቢው የዓለም ስፖርተኞችን የሚመራው አሜካዊው ቦክሰኛ ፍሎሮድ ሜይ ዌዘር ነው፡፡  የፎርብስ ሪፖርት እንዳመለከተው “መኒ” በሚል ቅጽል ስሙ የሚታወቀው ፍሎይድ ሜይዌዘር በ275 ሚሊዮን ዶላር የዓመቱን ከፍተኛ ገቢ አስመዝግቧል፡፡ በቦክሰኝነት ዘመኑ ከ50 በላይ ውድድሮችን ያሸነፈው እና እስከ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ የሰበሰበው ፍሎይድ ሜይዌዘር እስከ 560 ሚሊዮን ዶላር ሃብት እንዳለው የሚገለፅ ሲሆን በዓመታዊ ከፍተኛ ገቢ በፎርብስ የሚዘጋጀውን የደረጃ ሰንጠረዥ በ1ኝነት ሲመራ ባለፉት 7 ዓመታት ለ4ኛ ጊዜ ነው፡፡
ፎሎይድ ሜይዌዘር ዘንድሮ ከፍተኛ ገቢ ሊያስመዘግብ የቻለው ሌላው አሜሪካዊ ቦክሰኛ ኮነር ማክሪጐር በማሸነፉ  ነበር፡፡ እንደፎርብስ ትንታኔ ባለፈው 1 ዓመት ከስፖንሰርሺፕ እና ከተለያዩ የንግድ ውሎች ፍሎይድ 10 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አድርጓል፡፡  የባርሴሎናው ሊዮኔል ሜሲ በ111 ሚሊዮን ዶላር  ማለትም 84 ሚሊዮን ዶላር በደሞዝና 27 ሚሊን ዶላር በስፖንስርሺፖ እና በተለያዩ የንግድ ውሎች በማስገባት ሁለተኛ ደረጃ አግኝቷል፡፡ በጁቬንትስ የሚገኘው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከስፖንሰርሺፕ ማስታወቂያ እና የተለያዩ የንግድ ውሎች ከ47 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ በማድረግ ከዓለም ስፖርትኞች የሚስተካከለው ባይኖርም በደሞዝ ከሰበሰበው 61 ሚሊዮን ዶላር ጋር በ108 ሚሊዮን ዶላር ዓመታዊ ገቢው  3ኛ ደረጃ ላይ ነው፡፡
ቦክሰኛው ኮነር ማክሪጐር በ99 ሚሊዮን ዶላር፣ ኔይማር በ90 ሚሊዮን ዶላር ፤የቅርጫት ኳስ ኮከቡ ሌብሮን ጀምስ በ85.5 ሚሊዮን ዶላር ፤የሜዳ ቴኒስ ስፖርተኛው ሮጀር ፌደረር በ77.2 ሚሊዮን ዶላር፣ የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ስቴፈን ኩሪ በ76.9 ሚሊዮን ዶላር፣ የአሜሪካ ፉትቦል ተጨዋቾች ማት ሪያን በ67.3 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ማቲው ስታንፎርርድ በ59.5 ሚሊዮን ነበር ዓመታዊ ገቢያቸው እስከ 10ኛ ደረጃ አከታትለው ይዘዋል፡፡ ፎርብስ በዓመታዊ ገቢያቸው ለዓለማችን ፕሮፌሽናል ስፖርተኞች ከ1-100ኛ ባወጣው ደረጃ 18 የአሜሪካን ፉትቦል ሊግ  አትሌቶች፣ 14 የቤዝቦል ተጨዋቾች፣ 9 ኳስ ተጨዋቾች፤ 5 ጐልፈኞች 4 የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች ይገኙበታል፡፡
በስፖርት ዓለም ከደሞዝ፣ ከተለያዩ የሽልማት ገንዘብ ድርሻዎች፣ ከስፖንሰር ሺፕ እና ከተለያዩ የንግድ ገቢዎች ከፍተኛውን ሃብት በማካበት የተሳካላቸው በኦሎምፒክ ሜዳልያዎች የተሽንቆጠቆጡ ኦሎምፒያኖች አይደሉም። ለምሳሌ ያህል 28 የኦሎምፒክ ሜዳልያዎች በዋና ስፖርት የሰበሰበው አሜሪካዊው ዋናተኛ ማይክል ፊሊፕስ 55 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም በአጭር ርቀት 8 የወርቅ ሜዳልያዎችን በኦሎምፒክ መድረኮች የተጎናፀፈው ጃማይካዊው ዩሴያን ቦልት እስከ 100 ሚሊዮን ዶላር ማግኘታቸውን መጥቀስ ይቻላል፡፡
በስፖርተኛነት ዘመናቸው ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ ካጋበሱት መካከል የሜዳ ቴኒሱ ሮጀር ፌደረር፤ የቅርጫት ኳሶቹ ሌብሮን ጄምስ እና ሻክ ኦኒል እንዲሁም የእግር ኳሱ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ይገኙበታል፡፡ ከቅርጫት ኳስ ጡረታ በኋላ በስፖርት ኢንቨስትመንቱ በመሰማራት ማይክል ጆርዳን ከ1 ቢሊየን ዶላር እንዲሁም ማጂክ ጆንሰን ከዓጃናፍን ከ1.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ  አግኝተዋል፡፡
አምስቱ የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች
ፕሪሚዬር ሊግ፤ ላሊጋ፤ ቦንደስሊጋ፤ ሴሪ ኤ እና ሊግ 1
በአውሮፓ እግር ኳስ ባለፈው 1 ዓመት በተለይ በ5ቱ ታላላቅ ሊጐች በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ፤ በስፔን ላሊጋ፤ በጀርመን ቦንደስ ሊጋ፤ በጣሊያን ሴሪኤ እና በፈረንሳይ ሊግ 1 እስከ 14.7 ቢሊዮን ዩሮ ገቢ ተገኝቷል፡፡ ከአውሮፓ 5ቱ ታላላቅ ሊጐች ውጭ ከ4.9 ቢሊዮን ዩሮ በላይ፤ እንዲሁም ከሌሎች የአውሮፓና የፊፋ አባል አገራት  የሊግ ውድድሮች 2.4 ቢሊዮን ዩሮ በላይ የዓመቱ ገቢ  ነው፡፡
በአውሮፓ 5 ታላላቅ ሊጎች የሚንቀሳቀሱ፤ የቢሊዬነሮች ኢንቨስትመንት የሚፈስባቸውና በየዓመቱ ከፍተኛ ገቢ እና ትርፍ የሚያስመዘግቡ 32 ትልልቅ ክለቦች የዋጋ ግምታቸው 39.15 ቢሊየን ዶላር በላይ እንደሚገመት ሪፖርቶች ያመለክታሉ። በዴሊዮቴ አማካኝነት በተዘጋጀው የአውሮፓ እግር ኳስ ዓመታዊ የክለሳ ሪፖርት ላይ እንደተጠቆመው የአውሮፓ እግር ኳስ ገበያ በየዓመቱ ከ29.75 ቢሊዮን ዶላር በላይ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን  እስከ 20ኛ ደረጃ የተሰጣቸው ክለቦች ከ145.5 ሚሊዮን እስከ 820 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በየዓመቱ እያስመዘገቡ ናቸው።  የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ 5.83 ቢሊዮን ዶላር፤ የጀርመን ቦንደስ ሊጋ 3.213 ቢሊዮን ዶላር፤ የስፔን ፕሪሚዬራ ሊጋ 2.86 ቢሊዮን ዶላር፤ የጣሊያን ሴሪኤ 2.26 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም የፈረንሳይ ሊግ1 1.79 ቢሊዮን ዶላር ባለፈው የውድድር ዘመን ገቢ አድርገዋል፡፡ በአምስቱ የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች በየዓመቱ ከቴሌቭዥን የስርጭት መብት 7.85 ቢሊዮን ዶላር፤ በስፖንሰርሺፕ እና ሌሎች የንግድ ገቢዎች 5.47 ቢሊዮን ዶላር፤ በስታድዬም ገቢ 2.62 ቢሊዮን ገቢ እንደሚሆን የዴሊዮቴ ሪፖርት አመልክቷል፡፡
የዓለማችን 10 ሃብታም ክለቦች እና የዋጋ ተመናቸው
በዓለም ዙሪያ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ የዋጋ ግምት ያላቸው የተለያዩ የስፖርት ቡድኖችና ክለቦች ብዛት ከ81 በላይ እንደደረሰ ታውቋል፡፡ ከዚህ በታች የቀረበው የዓለማችን ሃብታም ክለቦች በአጠቃላይ የዋጋ ተመን ያላቸው ደረጃ ነው፡፡
1. ማንችስተር ዩናይትድ $4.12 ቢሊዮን ዶላር
2. ሪያል ማድሪድ $4.09 ቢሊዮን
3. ባርሴሎና $4.06 ቢሊዮን
4. ባየር ሙኒክ $3.06 ቢሊዮን
5. ማንችስተር ሲቲ $2.47 ቢሊዮን
6. አርሰናል $2.24 ቢሊዮን
7. ቼልሲ $2.06 ቢሊዮን
8. ሊቨርፑል $1.94 ቢሊዮን
9. ጁቬንቱስ $1.47 ቢሊዮን
10. ቶትንሃም ሆትስፕርስ $1.24 ቢሊዮን
ከ22.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የስፖርተኞች ደሞዝ
በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፖርት መስክ በተለያዩ የስፖርት አይነቶችና ውድድሮች ለስፖርተኞች የሚከፍለው ዓመታዊ ደሞዝ ከ22.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ መሆኑን ያመለከተው ‹‹ግሎባል ስፖርት ሳለሪ ሰርቬይ 2018›› የተባለ  ሰነድ ነው፡፡  በስፖርት ኢንተለጀንስ አማካኝነት በተዘጋጀው GSSS 2018 ሰነድ በዓለም ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ የስፖርት ቡድኖች፣ ክለቦች በሚወዳደሩባቸው ስፖርተኞች እና የቋሚ ቡድን ዓመታዊ እና አማካይ ክፍያዎች ተሰልተዋል፡፡
በዓለም ዙሪያ በ13 አገራት የሚገኙ 349 የስፖርት ቡድኖችና ክለቦች፤ 18 የሊግ  ውድድሮች፣ 8 የስፖርት ዓይነቶች እንዲሁም 10889 ስፖርተኞች ላይ የደሞዝ ስሌቱ እንደተሰራ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በመላው ዓለም ዙሪያ በሚካሄዱት የስፖርት እንቅስቃሴዎች በዓመት 22.2 ቢሊዮን ዶላር ለደሞዝ ክፍያ ወጭ እንደሚሆን በግሎባል ስፖርት ሳለሪስ ሰርቬይ ሲመለከት ከፍተኛውን የደሞዝ ወጭ በማውጣት የአውሮፓ እግር ኳስ ቀዳሚ ነው፡፡ በተለይ በዓመት ከ9.76 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለደሞዝ ወጭ የሚያደርጉት አምስቱ የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡በዓመታዊ የደሞዝ ወጭ ከ5ቱ የአውሮፓ ታላላቅ ሊጐች ግንባር ቀደም ስፍራ የሚይዘው የእንግሊዙ ፕሪሚዬር ሊግ በ2.5 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ የስፔን ላሊጋ 1.7 ቢሊዮን ዶላር፣ የጀርመን ቦንደስ ሊጋ 1.5 ቢሊዮን ዶላር፤ የጣሊያን ሴሪኤ 1.4 ቢሊዮን ዶላር እና የፈረንሳይ ሊግ 1 1.1 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ደሞዝ ለተጨዋቾች ይከፍላሉ፡፡
በስፖርተኞች ዓመታዊ ደሞዝ በሁሉም ስፖርቶች ያሉትን ክፍያዎች በማወዳደር በወጣው ደረጃ የስፔኑ ክለብ ባርሴሎና 1.373 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ደሞዝ በመክፈል አንደኛ ደረጃ ላይ ነው፡፡ ሪያል ማድሪድ 1.0644 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ደሞዝ ወጭ በሁለተኛ ደረጃ ይከተላል፡፡ የሰሜን አሜሪካ ቅርጫት ኳስ ቡድኖች ኦክላሃማ ሲቲ ተንደር 1.0327 ቢሊዮን ዶላር፤ ጎልደን ስቴት ዋርየርስ 1.0289 ቢሊዮን ዶላር፤  ዋሽንግተን ዊዛርድስ 1.044 ቢሊዮን ዶላር፤ ቶሮንቶ ራነርስ 997.03 ሚሊዮን ዶላር፤ ሂውሰተን ሮኬትስ 985.29 ሚሊዮን ዶላር እና ማያሚ ሂት 926.09 ሚሊዮን ዶላር ከ3 እስከ 8ኛ ያሉትን የዓመታዊ ደሞዝ ወጭ ደረጃዎች ይሸፍናሉ፡፡ የጣሊያኑ ጁቬንትስ በ885 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም የእንግሊዙ ማን ዩናይትድ በ859 ሚሊዮን ዶላር ዓመታዊ የደሞዝ ወጭ 9ኛ እና 10ኛ ደረጃዎችን ይዘዋል፡፡
ትርፋማው የሰሜን አሜሪካ ዞን
በሰሜን አሜሪካ የስፖርት ኢንዱስትሪ በየዓመቱ ከ73 ቢሊዮን ዶላር በላይ ይንቀሳቀስበታል፡፡ ከአሜሪካ አመታዊ የስፖርት ውድድሮች የቅርጫት ኳስ፤ የአሜሪካን ፉትቦል እና የቤዝ ቦል ሊጎች ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡ የአሜሪካ የቅርጫት ኳስ ሊግ በዓመት ከ22 ሚሊዮን በላይ ድምር ተመልካች የሚያገኙ ሲሆን በሊጉ በሚወዳደሩ 30 ክለቦች የሚገኙ ተጨዋቾች ከ3.44 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዓመታዊ ደሞዝ ይከፈላቸዋል፡፡ የአሜሪካን ፉትቦል ሊግ በዓመት ከ17.3 ሚሊዮን በላይ ድምር ተመልካች ያለው እና ከ4.94 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዓመታዊ ደሞዝ ለስፖርተኞቹ የሚከፈልበት ሲሆን የአሜሪካ ሜጀር ቤዝቦል ሊግ እስከ 4 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ደሞዝ ለስፖርተኞቹ የሚከፍል ነው፡፡
ትርፋማ የስፖርት ብራንዶች
Football 50/2018 በሚል ርዕስ ውድ የብራንድ ዋጋ ያላቸውን የስፖርት ብራንዶች ዓመታዊ ሪፖርት ለ13ኛ ጊዜ የተሰራ ሲሆን ማንቸስተር ዩናይትድ በ1.895 ሚሊዮን ዶላር አንደኛ ደረጃ ላይ ነው፡፡ በደረጃ ሰንጠረዥ ላይ ውድ የብራንድ ዋጋ ካላቸው ትርፋማ የስፖርት በተለይ የእግር ኳስ ክለቦች ይበዛሉ፡፡ የውድ ብራንዶች የደረጃ ሰንጠረዥ ላይ የእንግሊዝ ክለቦች በብዛት የሚገኙት በብሮድካስት ገቢ እና በስታድዬም የተሟላ አገልግሎት በሚያገኙት ትርፍ በየጊዜው ብራንዶቻቸውን ስለሚያሳድጉ ነው፡፡ ስለዚህም በፉትቦል 50/2018 ላይ የውድ የብራንድ ዋጋቸው እስከ 10 ባለው ደረጃ 6 እስከ 50 ባለው ደረጃ 18 የእንግሊዝ ክለቦች ተካትተዋል፡፡ የስፔኖቹ ባርሴሎና እና ሪያል ማድሪድ በኤልክላሲኮ የደርቢ ጨዋታዎቻቸው፣ በጣሊያን ሴሪኤ ደግሞ ጁቬንስት እና ኢንተር ሚላን በቻይና ባለሃብቶች በመያዛቸው በብራንድ ዋጋቸው ላይ እድገት እያሳዩ ናቸው፡፡  ከማንችስተር ዩናይትድ በመቀጠል ሪያል ማድሪድ 1.573 ቢሊዮን ዶላር፣ ባርሴሎና 1.511 ቢሊዮን ዶላር፣ ባየር ሙዚክ 1.406 ቢሊዮን ዶላር፣ ማንቸስተር ሲቲ 1.381 ቢሊዮን ዶላር፣ ሊቨርፑል 1.204 ቢሊዮን ዶላር ቼልሲ 1.095 ቢሊዮን ዶላር፣ አርሰናል 1.081 ቢሊዮን ዶላር፣ ባየር ሙኒክ 981 ሚሊዮን ዶላር እና ቶትንሃም ሆትስፕርስ 764 ሚሊዮን ዶላር የብራንድ ዋጋ በማስመዝገብ እስከ 10ኛ ደረጃ ያገኛሉ፡፡
የተለያዩ ዓለም አቀፍ ብራንዶች በማልያ ስፖንሰርሺፕ እና በስፖርት ትጥቅ አቅራቢነት ከአውሮፓ እግር ኳስ ክለቦች ጋር እየሠሩም ናቸው፡፡ ፉትቦል 50/2018 ላይ እንደተገለፀው የአየር መንገድ ኩባንያዎች 216 ሚሊዮን ዶላር፣ የአውቶሞቲቭ ኩባንያዎች 199 ሚሊዮን ዶላር፣ የፋይናንስ ተቋማት 140 ሚሊዮን ዶላር፣ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች 70 ሚሊየን ዶላር፣ የአቋማሪ ድርጅቶች 60 ሚሊዮን ዶላር፣ የቴሌኮም ኩባንያዎች 50 ሚሊዮን ዶላር በየዓመቱ በአውሮፓ እግር ኳስ ላይ ያወጣሉ።
ከስፖረት ትጥቅ አቅራቢዎች መካከል ከ10 በላይ ታዋቂ ኩባንያዎች በአውሮፓ እግር ኳስ እየሠሩ ናቸው፡፡ ናይኪ ከ18፣ አዳዲስ ከ15፣ ፑማ ከ10 አምብሮ ከ8፣ ክሮን ከ8… የአውሮፓ ክለቦች እየሠሩ ናቸው፡፡

Read 3123 times