Tuesday, 01 January 2019 00:00

የሙያ ማህበራትና ፓርቲዎች ምነው ተዳከሙ?

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(3 votes)

 ይህ ጽሁፍ በሁለት ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደርጋል። አንደኛው ጉዳይ የሙያ ማህበራትን የሚመለከት ሲሆን፤ ሁለተኛው ጉዳይ
ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ይመለከታል፡፡ እነዚህ ሁለት ተቋማት ማህበረሰባዊ ጥያቄዎች የሚመከርባቸውና የሚዘከርባቸው ተቋማት ናቸው፡፡ ተቋማቱ በአሁኑ ወቅት ምን ሁኔታ ላይ ነው ያሉት? ምንስ ማድረግ ነበረባቸው? ታሪካዊ ዳራቸውን በአጭሩ በማመላከት ተራ በተራ እንያቸው፡፡
    
     የሙያ ማህበራት
የሙያ ማህበራት ማለት የተለያዩ ዓላማን በማንገብ፣ የአባላቶቻቸውን መብትና ጥቅም ለማስከበር የሚመሰረቱ ማህበረሰባዊ ተቋማት ናቸው፡፡ በሀገራችን የተለያዩ ዓላማዎችን መሰረት አድርገው የተቋቋሙ በርካታ የሙያ ማህበራት አሉ፡፡ በዚህ ጽሁፍ ትኩረት የተደረገው ግን በሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽንና በኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ዙሪያ ነው፡፡
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር (ኢመማ) የጣሊያን ወራሪ ኃይል ከተባረረ በኋላ በየካቲት 1941 ዓ.ም በ32 መምህራን የተቋቋመ ማህበር መሆኑን የታሪክ ድርሳናት ይነግሩናል፡፡ በዚህም ምክንያት “ኢመማ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካም ደረጃ አንጋፋ ማህበር ነው” ይላሉ የታሪክ ምሁራን፡፡
እንደኔ እንደኔ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አንጋፋ ማህበር ብቻ አይደለም፡፡ የመምህራንን መብትና ጥቅም ከማስጠበቅ ጎን ለጎን፣ ማህበረሰባዊ ጉዳዮችን በማንሳት መጠነ ሰፊ ትግል በማድረግም አንጋፋ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ በዚህ ረገድ በንጉሡ ዘመን የነበረው የሀገሪቱ የትምህርት ፖሊሲ እንዲለወጥ ኢመማ ያደረገው ጥረት ለአብነት የሚጠቀስ ነው።  በ1966ቱ አብዮት ዋዜማ ወጥቶ የነበረው፣ ነገር ግን ስራ ላይ ያልዋለው በተለምዶ “ሴክተር ሪቪው” እየተባለ የሚጠቀሰው የትምህርት ፖሊሲ ማሻሻያ እንዲዘጋጅ ኢመማ ሚና ነበረው የሚሉ ወገኖች፤ ራሳቸውን በእማኝነት ያቀርባሉ፡፡ በዚያው ወቅት ሲቀጣጠል የነበረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ይበልጥ እንዲጠናከር መምህራን የነበራቸው ሚና ላቅ ያለ እንደነበርም ይነገራል፡፡
በደርግ ዘመን ኢመማ የህዝብን ጥያቄዎች በማቀጣጠል የጎላ ሚና ነበረው ለማለት አያስደፍርም።  ይሁን እንጂ ኢህአዴግ ደርግን ካስወገደ በኋላ በሰኔ ወር 1983 ዓ.ም በተደረገው የሽግግር ኮንፈረንስ ላይ የኢመማ ተወካዮች ተካፋይ እንደነበሩ ይታወሳል። በተለይም አንጋፋው ቀዳጅ ሐኪም ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ፣ በዚያ ኮንፈረንስ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህራን ማህበርን በመወከል ተገኝተው ያደረጉት ታሪካዊ ንግግር የማይረሳ ነው፡፡ ፕሮፌሰሩ በኮንፈረንሱ ላይ በያዙት አቋም ብቻ ሳይሆን፤ መምህራን ለኢህአዴግ ፖሊሲዎች በነበራቸው አሉታዊ አመለካከትና በየመድረኩ በሚያቀርቡት ትችት የተነሳ ኢመማ ግንባር ቀደም የኢህአዴግ “የጥቃት ዒላማ” ሆነ፡፡ መንግስትም (ይለይላቸው በሚል መንፈስ) 42 የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህራንን ያለ ምንም ምክንያት፣ ህግን ባልተከተለ መልኩ በማባረር ኢመማ ዒላማ ውስጥ መግባቱን ይፋ አደረገ፡፡
በዚያ ወቅት አንጋፋው ኢመማ 120 ሺህ አባላት ነበሩት፡፡ ማህበሩ የእነዚህን አባላቱን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ ያደረገውን ጥረት በበጎነት ያላየው መንግስት ብዙም ሳይቆይ ፕሬዚዳንቱን ፕሮፌሰር ታዬ ወ/ሰማያትን አሰረ፡፡ ቢሮዎቹ ተዘጉ፡፡ አፍታም ሳይቆይ ለኢህአዴግ ታዛዥ የሆነ “አሻንጉሊት” ማህበር በማቋቋም የኢመማን እንቅስቃሴ ሽባ አደረገው፡፡
ባለፉት 27 ዓመታት የነበረው ማህበር “መምህራኑን የማይወክል ነው” ይላሉ አስተያየት ሰጪዎች።  በመቀጠልም፤ “በሀገሪቱ ያሉ በርካታ መምህራን የ‘አሻንጉሊቱ’ ኢመማ አባል መሆንን አልመረጡም።  ለምሳሌ፤ … በአሁኑ ወቅት በዲላ ዩኒቨርስቲ ከሁለት ሺህ በላይ መምህራን ቢኖሩም የማህበሩ አባል የሆኑት መምህራን ግን 257 ብቻ ናቸው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ብዙዎቹ ከዩንቨርስቲው የለቀቁ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት አባላቱ ከ100 አይበልጡም፡፡ … ‘አሁን ያለው ኢመማ ለስም ያህል የቆመ ነው’ እየተባለ የሚታማው በዚህ ምክንያት ነው…” በማለት ይደመድማሉ አስተያየት ሰጪዎቹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ስልጣን በያዙ ማግስት ትኩረት የሰጡት ቀዳሚ ጉዳይ ትምህርት ነው። አሁን ያለው የትምህርት ፖሊሲ “ትውልድ ገዳይ” መሆኑን በመገንዘባቸው፣ ይህንን ፖሊሲ የመለወጥ እርምጃ ወስደው፣ አዲስ የትምህርት ፖሊሲ ፍኖተ ካርታ በመዘጋጀት ላይ ይገኛል፡፡ የጉዳዩ ባለቤት የሆነው ኢመማ ግን ኢህአዴግን ሎሌ ሆኖ ከማገልገል ባሻገር “ትውልድ ገዳይ” እየተባለ በብዙዎች የሚብጠለጠለውን የትምህርት ፖሊሲ በተመለከተ የአንድ ተራ መምህር ያህል እንኳ ድምጹን አሰምቶ አያውቅም፡፡
ይህንን በተመለከተ አስተያየታቸውን የጠየቅኳቸው ምሁራን፤ “ኢመማ፤ 27 ዓመት ሙሉ ስለ ትምህርት ፖሊሲው ምንም ነገር አለመናገሩ ብቻ አይደለም የሚገርመው፡፡ አሁንም ከዝምታው አለመላቀቁ እንጂ፡፡ የሚገርመው፤ ባለፉት 27 ዓመታት ሲታሰሩና ሲንገላቱ የነበሩና አሁንም በስደት ላይ ላሉ ቀደምት አመራሮቹ ጥሪ በማድረግ፣ ራሱን ማጠናከርና ለአዲሱ የትምህርት ፖሊሲ ፍኖተ ካርታ ዝግጅት በንቃት መሳተፍ ሲገባው አሁንም በዝምታ ማንቀላፋቱ ነው” ይላሉ በቁጭት፡፡
“መምህሩ በጠንካራ ማህበር ስር አለመደራጀቱ በሀገር ደረጃ ልኂቃዊ አስተዋጽዖ እንዳይኖረው አድርጎታል... ከእንግዲህ መምህሩ ሀገርን በሚገነባ የትምህርት ፖሊሲ አመንጪነት እንጂ የፖሊሲ አስፈጻሚነት ሚና ብቻ መጫወት የለበትም፡፡ መምህሩ ከጉዳዩ ባለቤትነት ወደ ጉዳይ አስፈጻሚነት መውረድ የለበትም፡፡” የሚል አስተያየት ይሰነዝራሉ፤ በጉዳዩ ላይ ያነጋገርኳቸው መምህራን፡፡
ወደ ሠራተኛው ማህበር እናምራ… በአውሮፓ የሙያ ማህበራት እንቅስቃሴ የተጀመረው በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው፡፡ ይህ ወቅት ኢንዱስትሪዎች ማቆጥቆጥና መስፋፋት የጀመሩበት ወቅት ነበር፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በፋብሪካ ባለቤቶችና በሰራተኛው መካከል ያለው ግንኙነት መሻከር ሲጀምር ሰራተኞች ተደራጅተው መታገል ጀመሩ፡፡ የትግሉም ውጤት በየሀገሩ የአሰሪና ሰራተኛ ህግ እንዲወጣ አድርጓል፡፡
በአውሮፓ ያሉ ሌበር ፓርቲዎች የተመሰረቱትም በጠንካራ የሰራተኛ ማህበር መሪዎች ነበር፡፡ ለምሳሌ፤ በእንግሊዝ ሀገር የመጀመሪያው የ“Independent Labor Party” ዋና ጸሐፊ ቶም ማን (Tom Mann) ይባላል፡፡ ይህ ሰው የሌበር ፓርቲን ከመመስረቱ በፊት የሰራተኛ ማህበር መሪ ነበር፡፡ በሰራተኛ ማህበር መሪነት ዘመኑ በርካታ የሥራ ማቆም አድማዎች እንዲካሄዱ አድርጓል፡፡ የሰራተኛው ጥያቄ እየጨመረ ሲመጣ የሌበር ፓርቲን በማቋቋም የፖለቲካ ትግል መጀመሩ ይነገራል፡፡
በአሁኑ ወቅት በብዙዎቹ የአውሮፓ ሀገሮች የሌበር ፓርቲዎች አሉ፡፡ በየሀገሩ ያሉት የሰራተኛ ማህበራትም ከእነዚህ ፓርቲዎች ጋር የጠበቀ ግንኙነት አላቸው። የሌበር ፓርቲዎች ቀዳሚ አጀንዳም የሰራተኛውን መብትና ጥቅም ማስጠበቅ ነው፡፡ ወደ ሀገራችን እንመለስ…
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰራተኛ ማህበር የተመሰረተው በሚያዝያ 1955 ዓ.ም ነበር፡፡ በ1966 ዓ.ም አብዮቱ ሲፈነዳ ማህበሩ 80 ሺህ ገደማ አባላት ነበሩት፡፡ ይህም በሀገሪቱ ከነበሩት ሰራተኞች ውስጥ ሰላሳ በመቶ (30%) የሚሆኑት የማህበሩ አባል እንደነበሩ ያመለክታል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ያቀፋቸው ማህበራት 300 ሺህ አባላት እንዳላቸውና ይህም በሀገሪቱ ካሉ ሰራተኞች ውስጥ አስር በመቶ (10%) የሚሆኑትን ብቻ ያቀፈ መሆኑን ያመለክታል፡፡
ኢሠማኮ በተመሰረተ በአጭር ጊዜ (በ1957 እና በ1964 ዓ.ም) የሥራ ማቆም አድማ በማድረግ በአፄ ኃ/ስላሴ መንግስት ላይ ተጽእኖ በመፍጠር በሀገሪቱ መንግስታዊ ለውጥ እንዲመጣ ብርቱ ግፊት አድርጓል። ይሁን እንጂ በደርግ ዘመን የማህበሩ አመራር አባላት በመታሰራቸውና ማህበሩም እንቅስቃሴ እንዳያደርግ ለተወሰኑ ጊዜያት በመታገዱ ጉልበቱ ተዳክሞ ነበር፡፡ በአጠቃላይ በደርግ ዘመን የነበረው የሰራተኛ ማህበር አመራር “የመንግስት ጉዳይ አስፈጻሚ በመሆን የሰራተኛውን እንቅስቃሴ አፍኖ በመያዝ፣ ታሪካዊ ስህተት ፈጽሟል” ይላሉ አስተያየት ሰጪዎች፡፡
በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ያሉ የኢሠማኮ አባል የሆኑ የሰራተኛ ማህበራት፤ በመንግስትና በግል የንግድ ተቋማትና በፋብሪካዎች ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞችን በአባልነት በማቀፍ የተደራጁ ናቸው።  በ2006 ዓ.ም በተደረገ ጥናት መሰረት በኢትዮጵያ የሰራተኛ ማህበር አባል የሆነው ሰራተኛ ብዛት በሀገሪቱ ካለው አጠቃላይ ሰራተኛ አስር በመቶ (10%) የሚሆኑት ብቻ ናቸው፡፡ ይህም ማለት ዘጠና በመቶ የሚሆኑት በልዩ ልዩ ስራ ላይ የተሰማሩ ዜጎች፤ የማህበሩ አባል አይደሉም ማለት ነው፡፡
ይሄ ቁጥር ከአፍሪካ አገሮች ጋር ሲነጻጸር በጣም ትንሽ ነው፡፡ ለምሳሌ፤ በኒጀር፣ ግብጽ፣ ሴኔጋል፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ዛምቢያ፣ ታንዛኒያ፣ … ያሉ የሰራተኛ ማህበራት በሀገራቸው ካሉ ሰራተኞች ከ20-43% የሚሆኑትን በአባልነት አካትተው ይዘዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የእኛ ሀገር የሰራተኛ ማህበር፣ የሰራተኛው “ምሉዕ” ወኪል ነው ብሎ ለመውሰድ አስቸጋሪ ነው፡፡
እንደኔ እንደኔ ከቤት ሰራተኛ ጀምሮ በስራ ላይ የተሰማሩ ዜጎች ሁሉ የሰራተኛ ማህበር እንዲያቋቁሙ ቢደረጉ መልካም ነው፡፡ ኢሠማኮ፤ እንኳን የቤት ሰራተኞችን እንዲደራጁ በማገዝ መብትና ጥቅማቸውን ሊያስከብር፣ በኩባንያዎች የሚሰሩ አባላቱን መብትና ጥቅም በአግባቡ የማስጠበቅ ስራ ሲሰራ አይታይም፡፡ የአባላቱን መብትና ጥቅም ማስጠበቁ ይቅርና አባላቱ መብትና ግዴታቸውን ተገንዝበው ስራቸውን እንዲሰሩ ባለመደረጋቸው ከአሰሪዎቻቸው ጋር በሚፈጠር ውዝግብ በየፍርድ ቤቱ ፋይል ይዞ መንከራተት እጣ ፈንታቸው ሆኗል፡፡
ኢሠማኮ ጠንካራ ቢሆን ኖሮ፤ ዜጎቻችን በዐረብ ሀገራት ከሚደርስባቸው ግፍና መከራ ባልተናነሰ መልኩ እዚሁ በሀገራችን የቤት ሰራተኞች በአሰሪዎቻቸው ሲደፈሩ፣ በቀን ሃያ ሰዓታት እንዲሰሩ ሲደረጉ፣ ደመወዛቸውን ሲቀሙ፣… ዋስ ጠበቃ በሆነላቸው ነበር።  ዋስ ጠበቃ መሆኑ ቢቀር እነዚህን ዜጎች በተመለከተ መብትና ጥቅማቸውን የሚያስከብር ህግ እንዲወጣ ጥረት ባደረገ ነበር…  
የፖለቲካ ፓርቲዎች
ፓርቲዎች በተለያዩ ደረጃዎች ሀገርን የሚያስተዳድሩ መሪዎችን የምናፈራባቸው ተቋማት ናቸው - በኛ ሀገር ግን የመነታረኪያ መድረኮች ሆነዋል።  ፓርቲዎች የህብረተሰብ ጥያቄዎች ተሰብስበው፣ መልክና ቅርጽ ይዘው በአጀንዳነት የሚቀረጹባቸው መድረኮች ናቸው - በኛ ሀገር ግን የህብረተሰብ ጥያቄዎች ይበልጥ እንዲበተኑ የሚደረጉባቸው የልዩነት መፈልፈያ ጎሬዎች ሆነዋል፡፡ ፓርቲዎች በህዝብ መብትና ፍላጎቶች ዙሪያ ዜጎች ሃሳባቸውን የሚያዋጡባቸው የምክክር፣ የውይይትና የድርድር መድረኮች ናቸው - በኛ ሀገር ግን ሸርና ተንኮል፣ ጠልፎ መጣል፣ ሴራና ደባ የሚጠነሰስባቸው መድረኮች መሆናቸው ይስተዋላል፡፡
በእነዚህ ምክንያቶች በሀገራችን በተለያዩ ጊዜያት ብቅ ብቅ ያሉ አቅም ያላቸው የፖለቲካ ሰዎች በአሉባልታና በሴራ እየተጠለፉ ከፖለቲካው መድረክ ተገፍትረዋል፡፡ የሚያሳዝነው ነገር፤ ገፍታሪዎቹ ሴራ ከመጎንጎን የዘለለ ብቃት የሌላቸው በመሆኑ ፓርቲዎቹን ለመምራት አልቻሉም፡፡ በዚህም ምክንያት ፓርቲዎቹ ተሽመድምደው ከእድር የተሻለ ስራ ሊሰሩ  አልቻሉም፡፡ ፓርቲዎቹ በሁለት እግራቸው መቆም ባለመቻላቸው ገዢው ፓርቲ እገዛና ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ሲማጸኑ እየተስተዋለ ነው፡፡
ባለፈው ሰሞን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ሰማንያ ከሚሆኑ የፓርቲ መሪዎች ጋር ያደረጉትን ስብሰባ በቴሌቪዥን ተከታትያለሁ፡፡ የስብሰባው ዓላማ በአንድ በኩል የመመካከሪያ አጀንዳዎችን በጋራ ለመቅረጽ ሲሆን፤ በተቀረጹት አጀንዳዎች ዙሪያ በጋራ ለመምከር የሚረዳ ደንብ በማዘጋጀት በቀጣይ ጊዜያት ከተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎቹ ጋር ለመወያየት ነው። በዚያ ስብሰባ ላይ ከተገኙ የፓርቲ መሪዎች ንግግር የተረዳሁት ነገር፤ የቀጣይ ዘመን “ዕጩ መሪዎቻችን” በማያውቁት አጀንዳ፤ ምንም ዝግጅት ሳያደርጉ ለስብሰባ መምጣታቸውን ነው፡፡ ለዚህ አባባል ማሳያ የሆነኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰማንያ ፓርቲዎች ጋር ለመነጋገር እንደሚያስቸግራቸው በመግለጽ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንደየ ርዕዮተ-ዓለማቸው በሦስት ወይም በአራት ቡድን እንዲደራጁ (እንዲጠቃለሉ) ሲነግሯቸው፤ አንዳንዶቹ “ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እርስዎ እንድንቧደን ያግዙን…” ዓይነት ሃሳብ ሲያቀርቡ መስማቴ ነው፡፡
ነገ ሀገር ይመራሉ፣ ሕዝብ ያስተዳድራሉ ብለን የምናስባቸው “የፓርቲ መሪዎች”፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲያቋቁሟቸው ከመማጸን በላይ ምን ውርደት ይኖራል? ሀገር የሚመራ ገዥ ፓርቲ ሊቀ መንበር የሆነ ሰው፤ ነገ በምርጫ የሚፎካከሩትን ፓርቲዎች እንዴት ሊያደራጅና ሊያጠናክር ይችላል? ግዴታስ አለበት? እንደኔ እንደኔ የገዥ ፓርቲ ግዴታ ሊሆን የሚገባው በያዘው መንግስታዊ ኃላፊነት የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የሚመሩት ኢህአዴግ ባለፉት 27 ዓመታት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሲያነሷቸው የነበሩ አጀንዳዎችን ጥርግ አድርጎ በመውሰድ፣ የራሱ አጀንዳ አድርጎ ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ያዩ ብዙዎቹ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች፤ ኢህአዴግ የራሳቸው ፓርቲ፣ የኢህአዴግ መሪ የእነርሱም ፓርቲ መሪ ሳይመስላቸው አልቀረም፡፡ እንዲያ ከሆነ ደግሞ አንድ ፊቱን ተቃዋሚነቱን ትቶ ጥቅልል ብሎ “ኢህአዴግ” የሚባለው የፓርቲዎች ስብስብ (ግንባር) ውስጥ መግባት ነው፡፡ አሊያም አጋር ፓርቲ ሆኖ መሰለፍ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ “አደራጁን” እያሉ መወትወት ትዝብት ላይ ይጥላል፡፡
በዚህ ወቅት ጠንካራ፣ ራዕይ ያለው ፓርቲ የለም እንጂ ቢኖር ኖሮ ማድረግ የነበረበት በሀገሪቱ ያሉ ፓርቲዎችን ዝርዝር ከምርጫ ቦርድ በመውሰድ፣ ዓላማዎቻቸውን በመፈተሽ፣ እንደየ ርዕዮተ-ዓለማቸው በሦስት፣ በአራት፣… ቡድን ደልድሎ የመነሻ ሃሳብ ያቀርብ ነበር፡፡ በድልድሉ ያልተስማማ ፓርቲ “የለም እኔ ከምከተለው ርዕዮተ-ዓለም አንጻር በዚህኛው ቡድን ሳይሆን በዚያኛው ቡድን ውስጥ ነው መሆን ያለብኝ…” ብሎ የድልድል ሽግሽግ እንዲያደርግ ወይም አዲስ ቡድን እንዲመሰርት ማድረግ ይቻላል፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አሁንም በዚህ መንገድ ራሳቸውን ቢያደራጁ የተሻለ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡
በአጠቃላይ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሰራተኛ ማህበራት፣ የመምህራን ማህበርና በተለያየ አደረጃጀት የተቋቋሙ የሙያ ማህበራት በሀገራቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት ውስጥ የጎላና የላቀ ሚና መጫወት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለይም አሁን ሀገራችን እንዳለችበት ባለ ፈታኝ የሽግግር ወቅት ፓርቲዎችና የሙያ ማህበራት የህዝብን ፍላጎቶች መልክ በማስያዝና በመምራት ብቻ ሳይሆን፤ ከመለኪያ በላይ የወጣውን የህዝብ ስሜት (ቁጣ) ማቀዝቀዝ ይገባቸዋል፡፡
የሙያ ማህበራት በተጠናከሩ ቁጥር የሙያቸውንና የአባላቶቻቸውን መብትና ጥቅም ከማስከበር አልፈው በየሙያቸው ሀገራዊ አጀንዳዎችን አንጥረው በማውጣት ለፓርቲዎች የመታገያ አጀንዳ የማዘጋጀት ሚና ሊኖራቸው እንደሚችል ብዙዎች ይስማማሉ፡፡
በ1941 ዓ.ም የተቋቋመው፣ በአፍሪካ አንጋፋው የሆነው የኢትዮጵያ መምሕራን ማኅበር፤ የመምሕራንን መብት ከማስከበር ባሻገር ለትምሕርት ጥራት የበኩሉን አስተዋጽዖ ማድረግ ቢጠበቅበትም ባለፉት 27 ዓመታት ይህን ታሪካዊ ኃላፊነቱንና ግዳጁን ለመወጣት አልቻለም:: ባለፉት 27 ዓመታት አንድ ለአምስት ተጠርንፈው፣ መፈናፈኛና መላወሻ አጥተው የነበሩት መምህራን፤ የ“እኔ” የሚሉት ማህበር አልነበራቸውም።  አሁንም “አላቸው” ብሎ በድፍረት ለመናገር የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ይሁን እንጂ፤ ሁሉም ነገር ዳግም ላይመለስ አልፏል፡፡ መምህራንም ሆኑ ሰራተኞች ወይም ሌሎች የሙያ ማህበራት አባላት ማህበራቸውን እንደገና ማደራጀትና ለወቅቱ የሚመጥን ቁመና እንዲኖረው ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ከሁሉም በላይ፤ የክቡር ሙያ ባለቤትና ትውልድን የመቅረጽ ኃላፊነት የተሰጠው መምህር፤ በሀገሩ ጉዳይ አዎንታዊ ሚና እንዲጫወት እድል ሊሰጠው ይገባል።  በዚህ ረገድ በመንግስት በኩል በስደት ላይ ላሉ መምህራንና የኢመማ አመራሮች ጥሪ ተደርጎላቸው እንዲመጡ ቢያደርግ፣ በትምህርት ፖሊሲ ቀረጻውም ሆነ በአተገባበሩ ሂደት ላይ የላቀ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ አስባለሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡-ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.   ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 702 times