Tuesday, 01 January 2019 00:00

በወቅታዊ አወዛጋቢ ጉዳዮች ላይ ሜ/ጀነራል አበበ ምን ይላሉ?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 በወቅታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በየጊዜው ትንተና በመስጠት የሚታወቁት አንጋፋው የህወሓት መሥራችና የቀድሞው የአየር ሃይል
አዛዥ ሜ/ጀነራል አበበ ተ/ ሃይማኖት፤ በትግራይ “ህገ መንግስቱ ይከበር” እንቅስቃሴ፣ በሰሞነኛው የአቦይ ስብሃት አወዛጋቢ ንግግር፣ በፓርማ
በጸደቀው የማንነትና ድንበር ኮሚሽን --- ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡


    “ህገ መንግስቱ ይከበር” በሚል በትግራይ ሰፊ እንቅስቃሴ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ የዚህ እንቅስቃሴ ባለቤት ህዝቡ ነው ማለት ይቻላል? ብዙዎች ህወሓት ነው ይላሉ --
በኔ አመለካከት ህገ መንግስቱ ይከበር የሚለው መፈክር ተገቢ ነው፡፡ ይሄ አጀንዳ የህወሓት ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም ትግራይ ውስጥ ልክ  እንዴ ሌሎች ክልሎች ህገ መንግስቱ ተግባራዊ መሆን አልቻለም፡፡ ህወሓት ራሱ ህገመግስቱን እየጣሰ የህዝቡን መፈክር ሲጠቀምበት እናያለን፡፡ በሰላማዊ ሰልፍ የተሳተፉ የተወሰኑትን አነጋግሬ ነበር፡፡ በአንድ በኩል ከትግራይ ውጭ ብዙ መፈናቅሎች አሉ፡፡ የትግራይ ተወላጆችም ከአማራ ክልል እየተፈናቀሉ ነው፡፡ ሁሉም መፈናቅል ሕገ-መንግስቱ የሚፃረር ነው። በሌላው በኩል ፌደራል መንግስት በአለፉት 27 ዓመታት የነበሩት የሙስና እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት አንድ ድርጅትና ጥቂት ሰዎች እንደሆነና ብአዴን፤ ኦህዴድ እና ደህአዴን ከፍተኛ አመራር ሳይጠየቁ የኅውሃት ብቻ እንዲጠየቁ ማድረግ ፍትሃዊ አይደለም ማለታችን ነው እንጅ መቀለ ላይ ያሉት አመራሮች የሚያስጠይቃቸው ካለ አይጠየቁም ማለታችን አይደለም፡፡ ከትግራይ ውጭ ያለው ትግራዊይ ተሸማቆ እንዲኖር በሰላማዊ ሰልፍም አንዳንድ አመራሮች የሚሉትም ለመቃወም ጭምር ነበር ያሉኝ፡፡
ህገ መንግሥት ይከበር ማለት፤ የሰው ህይወት ጥበቃ ይደረግለት፤ ሰብአዊና ዴሞክራሲ መብተቶች ይከበሩ፤ የዜጎች ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ የመኖር፣ ሃብት የማፍራት፣ የመስራት መብት ይከበር ማለት ነው፡፡   ነገር ግን ይህቺ ሃገር፣ ሃገር ሆና እንድትቀጥል ከተፈለገ፣ ህገ መንግስቱ መከበር አለበት፡፡ የምንቀይረውና የምናሻሽለውም ከሆነ፣ በህገ መንግስቱ መሰረት መሆን አለበት፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ ይህቺ ሃገር አንድ ገዥ ህግ የግድ ያስፈልጋታል፡፡ ያም ህገ መንግስቱ ነው፡፡ ስለዚህ እንዲያውም መፈክሩ፣ የሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች ነው መሆን ያለበት፡፡ ይሄ ህገ መንግስት የኔ አይደለም የሚል ካለ እንኳ በምን መንገድ ሌላ ህገ መንግስት ይውጣ? ይህቺ ሃገርስ እንዴት ትቀጥል? የሚለውን መመለስ አለበት፡፡ ስለዚህ ህገ መንግስቱ ይከበር የሚለው ተገቢ መፈክር  ነው፡፡ የሚሻሻል ከሆነም በራሱ በህገ መንግስቱ መሰረት መሆን ነው ያለበት፡፡ ህገ መንግስቱ ለማሻሻል አንቀፆቹ የማይቻል አድርገውታል የሚል ሃሳብ ካለ  ማሻሻል አንቀፆቹ  ራሳቸው ለህዝበ ውሳኔ ቀርበው ሊሻሸሉ ይችላል፡፡ የዜጎች ተፈጥራዊ (inherent) መብት ነው እና ፡፡
በህወሓት አመራሮችና በፌደራል መንግስቱ መካከል ውጥረቶችና አለመግባባቶች ይታያሉ፡፡ እርስዎን አላሳሰብዎትም?
ያው በሁለቱ መካከል ፍጥጫው አለ፡፡ እኔ የህወሓትንም ሆነ እዚህ ያሉ የፌደራል አመራሮችን አላገኛቸውም፡፡ ግን እንደማንኛውም ሰው ሁኔታውን ስመለከተው፣ የማጥቃትና የፀረ ማጥቃት አይነት እንቅስቃሴ እታዘባለሁ፡፡ የአንድ ኢህአዴግ ድርጅት አባላት የማይመስሉበት ሁኔታም ይታያል፡፡ በእርግጥ ሃዋሳ በነበረው ጉባኤ ዶ/ር ዐቢይ በሙሉ ድምፅ ሲመረጡ፣ እኔ በጣም ነበር የተደሰትኩት፡፡
ከሳምንት በፊት  በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ የህወሓት መሥራቹ አቶ ስብሃት ነጋ፤ ”ዶ/ር ዐቢይ የተመረጡት በአሜሪካ መንግስት ጣልቃ ገብነት ነው” ማለታቸው አነጋጋሪ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ ለእርስዎስ?
አቶ ስብሃት ያንን ማለታቸው በጣም ገርሞኛል፡፡ ሃዋሳ ላይ ሙሉ በሙሉ በሚባል ድምፅ የተመረጠን ጠቅላይ ሚኒስትር፣ አሜሪካኖች ናቸው የመረጡልን ሲባል እኔ አፍሬያለሁ፡፡ በእርግጥ አቶ ስብሃት በጉባኤው ውስጥ አልነበሩም፡፡ ስለዚህ በጉባኤው የነበሩ የህወሓት አመራሮችንም ጭምር “የአሜሪካ ተላላኪዎች ናችሁ፤የአሜሪካ መንግስት የሰጣችሁን ትዕዛዝ ነው የፈፀማችሁት” እያሏቸው ነው፡፡ የሌሎቹን ድርጅቶች አመራሮችም እንዲሁ፡፡ ይሄ በጣም አሳፋሪ ነው፡፡ ስለዚህ እኚህ ሰው ከእነ ዶ/ር ደብረፂዮን ጋር ጠብ አላቸው ማለት ነው፡፡ የአሜሪካ  መንግስት ነው የመረጠልን ካሉ፣ ይህ ሲሆን እነሱ የት ነበሩ? ዶ/ር ዐቢይ በመጀመሪያም ሲመረጡ ሁሉም ነበሩ፡፡ የአሜሪካ መንግስት መረጠልን ሲሉ ተሸንፈናል እያሉ ነው፡፡ ተሸናፊዎች ከሆኑ ደግሞ አርፈው ቢቀመጡ ነው የሚሻላቸው፡፡ እንደኔ አተያይ የእነ አቶ ስብሃት ፍላጎት ግን ሌላ ነው፡፡ ፖለቲካውን ማካረር ይፈልጋሉ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ የትግራይ ህዝብ የሚፈልገው ፖለቲካው ረግቦ፣ ቀስ በቀስ ወደ ውይይት እንዲገባ  ነው፡፡ እነሱ ፖለቲካው እንዲካረር የሚፈልጉት፣ በግርግሩ የራሳቸውን ተገቢ ያልሆነ ክብር ለማስጠበቅ ነው፡፡ ሌለም ሊሆን የችላል፡፡  እሳቸውም ሆኑ ይሄን የሚያደርጉ ሌሎች አመራሮች፣ በህወሓት ውስጥ ያሉ ለውጥ ፈላጊዎች እና ለእነ ዶ/ር ዐቢይ አንድ ወጥመድ እያዘጋጁ ነው፡፡ ለውጥ ፈላጊዎቹ በእልህ የልሆነ እርምጃ እንዲወስድ ማድረግና በኋላም “አላልናችሁም የትግራይ ህዝብ እየተጠቃ ነው” ለማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይሄን ወጥመድ በጥንቃቄ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ሰውየው ያንን ማለታቸው በጣም አሳፋሪ ነው፡፡ እሳቸው አባል የሆኑበት ህወሓትም ተላላኪ መሆኑን ነው የተናገሩት። ስለዚህ እዚያው ድርጅታቸው ውስጥ ቢወያዩበትና የአሜሪካ መንግስትን ተልዕኮ የፈፀሙትን ቢያባርሩ ነበር የሚሻላቸው፡፡
አሁን ህወሓት እያራመደ ያለውን ፖለቲካ እንዴት ያዩታል?
እንደ ሌላው ፓርቲ ህወሓት ውስጥም ለውጡን የሚፈልጉ አሉ፡፡ በሌላ በኩል፤እኛ ከሌለን ስርአት አይኖርም የሚሉ ኋላቀሮችም አሉ፡፡ ትልቁ ነገር የለውጡ ፕሮግራም ነጥሮ ተዘርዝሮ የመቅረቡ ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች ፀረ-ዲሞክራሲያዊ አገዛዝ አንፈልግም ብለው አምፀዋል፡፡ ትግራይ ውስጥ ይህን አገዛዝ በመቃወም በ2007 ሰፊ ሰለማዊ እንቅስቃሴ  ነበር፡፡ ህዝበች ለውጥ ፈልገዋል ፡፡ ህዝብ እናከብራለን የምንል ሌላ አማራጭ የለንም፡፡ ለውጥ መደገፍ ብቻ ነው፡፡ እኔ ለውጥ የምለው፣ የነበረውን ፀረ-ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ና ተግባር መቀየር ነው። ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ፡፡ ህገ መንግስታዊ ተቛሞች ግዴታቸውን እንዲወጡ ሁላችንም የመሰለንን ሃሳብ በመሰለን መንገድ እየገለጽን መሄድ መቻል አለብን፡፡ ምናልባት በለውጡ አቅጣጫ ላይ ልንለያይ እንችል ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ለውጡ ህገ መንግስቱን መሰረት ያደረገ መሆን አለበት የሚል ሊኖር ይችላል፡፡ ሌላው ደግሞ ለውጡ ህገ መንግስቱን ሽሮ ሊሆን ይገባል ሊል ይችላል፡፡ ለውጥ ጭራሽ አያስፈልገንም፤ በነበረው እንቀጥል የሚልም ይኖራል። ድሮ ከኢህአዴግ ውጪ ሁሉም የጥፋት መንገድ ተደርጎ ነበር የሚታየው፡፡ አሁንም በዚሁ ልማድ፣ ከለውጥ ውጪ ሌላው የጥፋት መንገድ ነው ብለን፣ ሃሳብ ማፈን ከጀመርን አደገኛ ነው፤ ፀረ ዲሞክራሲ ነው፡፡ ለውጡን በሰላማዊ መንገድ የሚቃወም ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን ህግን መፃረር አይችልም። ሃሳቡን የማቅረብ መብቱ ግን ሊከበር ይገባዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትራችንን የለውጥ አካሄድ የሚተች አስተያየት ሲቀርብም መስተናገድ መለመድ አለበት፡፡ ብዙ ሰው ከዚህ አንፃር የሚያተኩረው ህወሓት ላይ ነው፡፡ እዚህስ? ለምሳሌ ፕሬዚዳንቱ የለውጡ ደጋፊ ነኝ ካሉ አስቸጋሪ ነው። ፕሬዚዳንቱ የሁሉም ርዕሰ ብሔር ናቸው፡፡ ፖሊስ “ለውጡን ለማደናቀፍ-” እያለ መናገር የለበትም፡፡ ይህን የሚል ከሆነ ከበፊቱ በምን ተለየን? ፖሊስ ማለት ያለበት “ህግን ስለጣሱ” ነው፡፡ የለውጥ ደጋፊዎችም ህግ ሲጥሱ ፖሊስ በህግ ይጠይቃል፤የለውጥ ተቃሚዎችም ህግ ሲጥሱ በእኩል ይጠየቃሉ፡፡ አካሄዱ መሆን ያለበት እንደዚህ ነው፡፡ ሚዲያዎች ሁሉንም እኩል ነው ማስተናገድ ያለባቸው፤ያለበለዚያ የቀድሞውን መድገም ነው፡፡ ለምሳሌ ቀደም ሲል ቴዲ አፍሮ በኢቴቪ ቃለ ምልልስ ተደርጎለት፣ እንዳይተላለፍ ተከልክሏል፡፡ አሁንም እንዲህ ያለ አፈና ካለ፣ ለውጡ ምኑ ላይ ነው ታዲያ? እነዚህን ጉዳዮች ማገናዘብ ያስፈልጋል፡፡
የድንበርና የማንነት ኮሚሽን ተቋቁሟል፡፡ ይህ ኮሚሽን በትግራይ ክልል እንደራሴዎችና ፖለቲከኞች ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡ እርስዎ ስለ ተቋቋመው ኮሚሽን ምን አስተያየት አለዎት?
እኔ ኮሚሽኑ  ይቋቋማል ሲባል ህገ መንግስቱን እንደአዲስ ወደ መፈተሽ ነው የሄድኩት፡፡ ከሁሉም በላይ ይሄ የማንነትና የድንበር ጉዳይ አፋጣኝ እልባት ማግኘት አለበት እላለሁ፡፡ በኮሚሽንም ይሁን በሌላ እነዚህ ጥያቄዎች በተጠናከረ መልኩ መፈታት አለባቸው፡፡ ችግሮቹ እልባት የማግኘታቸው ጉዳይ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ለምሳሌ በደቡብ የማንነትና የክልል ጥያቄ ይነሳል፡፡ ይሄ ለኔ ጥሩ ነው፤ መብትን መጠቀም ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ የወልቃይትና የራያ ጉዳይ አለ። ይሄ ጉዳይ እየተንከባለለ ቆይቶ፣ አሁን የውጥረት ምንጭ ሆኗል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ሲፈቱ በየትኛው አግባብ ነው የሚለው ደግሞ ለመፍትሄው ወሳኝ ነው፡፡ ይሄ ችግር የሚፈታው በዚህ ህገ መንግስት ነው  ካልን፣ እንዲህ ያሉ ችግሮችን የመፍታት ስልጣን ህገ መንግስቱ የሚሰጠው ለፌዴሬሽን ም/ቤት እንጂ ለተወካዮች ም/ቤት አይደለም፡፡ የህገ መንግስት ጉዳይ አጣሪ ጉባኤ አወቃቀር፤ ህገ መንግስቱን ስለመተርጎም እና ሥልጣን እና ተግባር በዝርዝር ነው ህገ መንግስቱ ያስቀመጠው። አጣሪ ጉባኤው የውሳኔው ሃሳብ ለፌዴሬሽን ም/ቤት የቀርባል ይላል፡፡   አጣሪ ጉባኤ ሰፋና ጠንከር አድርጎ አደራጅቶ፣ ስራውን እንዲሰራ ማድረግ የቻላል፡፡
የድንበር ጉዳይን በተመለከተ ስልጣን ያለው የፌዴሬሽን ም/ቤት ነው፡፡ የኛ የፌዴሬሽን ም/ቤት ስልጣን ቀደም ሲልም አከራካሪ የነበረ ነው፡፡ ይሄ አካል ከ አሜሪካ ጠቅላይ ፍ/ቤት እና ከአንዳንዶቹ የአውሮጳ ህገ መንግስታዊ ፍርድ ቤቶች  በላይ ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ይሄ አከራካሪነቱ እንዳለ ሆኖ፣ የህገ መንግስቱ ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ይሄ የወልቃይትና የራያ ጉዳይ አፋጣኝ እልባት ማግኘት አለበት፡፡ ይሄ መሆን የሚችለው በፌዴሬሽን ም/ቤት ነው፡፡ በአዋጅ ሌላ አካል ማቋቋም፣ ሃብት ማባከንና ትርፉ፡፡ የፌዴሬሽን ም/ቤትን ቀርፋፋ አካሄድ ነው ማስተካከል የሚያስፈልገው፡፡ ህገ መንግስቱን የሚፃረር ማናቸውም ህግ ተቀባይነት የለውም፤ ይላል ህገ መንግስቱ፡፡ የህገ መንግስቱ ጉዳዮች ላይ ብይን የሚሰጠው ደግሞ የፌዴሬሽን ም/ቤት ስለሆነ፣ ይሄን በአዋጅ የተቋቋመ ኮሚቴ ም/ቤቱ ውድቅ ሊያደርገው የሚችልበት እድል አለ፡፡ የህገ መንግስቱ የመጨረሻ ተርጓሚ አካል ጠቅላይ ፍ/ቤት ወይም የተወካዮች ም/ቤት ሳይሆን የፌዴሬሽን ም/ቤት ነው፡፡
አንዳንድ ወገኖች የወልቃይትና የራያ መሬቶች የተወሰዱት በፖለቲካዊ ውሳኔ ስለሆነ መመለስ የሚችሉትም በፖለቲካዊ ውሳኔ ነው በሚል ይሞግታሉ፡፡---
ጥያቄው የማንነትና የድንበር ነው፡፡ የህዝብን ማንነት በፖለቲካ መወሰን አይቻልም፡፡  የሚመለከተው ህዝብ  ብቻ ነው ማንነቱን መወሰን የሚችለው። ስለዚህ ይሄን ውሳኔ ህዝቡ ይጠየቅ፤ ውሳኔው ለህዝብ ይተው። የድንበር ጉዳይ ከሆነ በአለማቀፍና በኢትዮጵያ ህግ መሰረት፣ ታሪካዊ ሁኔታን መሰረት አደርገን፣ የሚስተካከል ይስተካከላል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የድንበርና የማንነት ጥያቄ በግልፅ ተለይቶ መቅረብ አለበት፡፡ ራያ ትግራዋይ ነኝ ወይም አማራ ነኝ ካለ መብቱ ይጠበቅለት፡፡ ሁለቱም አይደለሁም፤ “ራያ” ነኝ ካለ መብቱ መከበር አለበት፡፡ የወልቃይትም እንዲሁ። ነገር ግን ይሄ ችግር በኃይል ሊፈታ አይችልም፤ የሚሆንም አይደለም፡፡ በሰከነ መንገድ ነው መፈታት ያለበት፡፡
የፖለቲካ መካረርን አለዝቦ መረጋጋት መፍጠር የሚቻለው እንዴት ነው ብለው ያስባሉ?
አንደኛ፤ ህዝብና ድርጅትን መለየት ነው፡፡ አሁን የፖለቲካ ቁማሩ፤ ህዝብና ድርጅትን አንድ ማድረግ ነው፡፡ ይሄ አደገኛ ነው፡፡ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል። ትግራይከ ህወሓት፣ ኦነግ ና ኦዴፓ ከኦሮሚያ ወ.ዘተ ህዝብን መለየት ያስፈልጋል፡፡ ህዝቡ በእነሱ እሳት ውስጥ እንዳይገባ ሁሉም ኃላፊነቱን መወጣት አለበት። የመጀመሪያው የማለዘቢያ መንገድ ይሄ ነው። ሁለተኛው፤መንግስት ለማካረር ለሚፈልጉ ኃይሎች ተጨማሪ ቤንዚንና ማዳበሪያ ከመስጠት መቆጠብ አለበት፡፡ ሁሉም ኃይሎች ወደ ውይይትና የሰከነ ድርድር ነው መግባት ያለባቸው፡፡ ይሄ ሲሆን ህዝቡም ይረጋጋል፡፡ ሥስተኛ መንግስትና ፓርቲ እየተቀላቀሉ ነው ይህ ራሱ መካረሩን ያጤዞዋል፡፡ ይሄ መታረም አለበት፡፡ ለምሳሌ በኦሮሚያ ከኦነግ ጋር የተፈጠረው የፀጥታ ችግር ፌዴራል ወይም የክልሉ መንግስት ነው ለኢትዮጵያ ህዝቦች መግለጫ መስጣት ያለበት። የኦዴፓ ፅ/ቤት ኃላፊ  እንደ ማናቸውም ፓርቲ እስተያየት ነው መታሰብ ያለበት፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ በመጪው ዓመት አገራዊ ምርጫ ማካሄድ ይቻላል?
አንዱ ችግር ተቃዋሚዎች እስካሁን የጠራ የፖለቲካ አቋም አላንፀባረቁም፡፡ አሁንም የ60ዎቹ ትውልድ ነው ፓርቲዎችን የሚመራው፡፡ አዲሱ ኢህአዴግም እስካሁን ግልፅ አካሄድ የለውም፡፡ ሁሉም የተካረረ ነገር እንጂ ብዙ አጥጋቢ፣ ነጥሮ የወጣ ገዥ ሃሳብ የላቸውም። ስለዚህ ይሄ ምርጫ ይራዘም አይራዘም የሚለውን ለማወቅ፣ በፓርቲዎች መካከል መግባባት ላይ መደረስ አለበት፡፡ በምርጫው እኔ አሸንፋለሁ ሳይሆን ከምርጫው በኋላስ ሃገር ትቀጥል ይሆን? የሚለውን ነው ማሰብ፡፡ ከአሸናፊነት በላይ የሃገር ህልውናን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ በፓርቲዎች መካከል ስለ ምርጫው ጊዜ መግባባት ላይ መደረስ አለበት፡፡ እኔ ይህ ቢሆን ለማለት ይከብደኛል፤ ቀጣይ ሂደቱ ነው የሚወስነው፡፡    

Read 3287 times