Tuesday, 01 January 2019 00:00

“ምናለ ጠጋ ብትይ!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(7 votes)


     እንዴት ሰነበታችሁሳ!
አንድ ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ ነው... እንደ አብዛኛዎቹ የከተማችን ታክሲዎች ውስጡ የስዕል ኤግዚብሽን ግድግዳ አይመስልም፡፡ አንድ ብቻ ብዙም ባልጎሉ ፊደላት የተጻፈ ጥቅስ ነገር ተለጥፏል፡፡
‘ፍጥነት ለአትሌት እንጂ ለሾፌር ወርቅ አያስገኝም’ ይላል፡፡ አሪፍ አይደል! ያውም ከፍጥነት በላይ በማሽከርከር የእርግማን መአት በምናወርድባቸው ሚኒባሶች ላይ እንዲህ አይነት ቁም ነገር ማንበብ ደስ ይላል፡፡ ማህበራዊ ሀላፊነት የሚሰማን ዜጎች ቁጥር እንደ ቀይ ቀበሮ በተመናመንበት ጊዜ፣ የዚህ አይነት አነቃቂ ነገሮች ያስፈልጉናል፡፡
አሁንም ለተሳፋሪ ክብር የማይሰጡ ጥቅስ የሚመስሉ ነገሮች እያየን ነው፡፡
እንበልና…ሴትየዋ፤ ከሰውየዋ ጋር አንድ፣ ሁለት ተባብለው፣ ተበጣብጠው ነው ጠዋት ከቤት የወጣችው፡፡ ሚኒባስ ገብታ አራት ብሯን ከፍላ፣ መልስ የሚሠጣት የለም፡፡
“መልስ ስጠኝ?”
“ዝርዝር የለኝም፡፡”
“እሱ የአንተ ችግር ነው…!”
እናላችሁ… ቀና ብላ ስታይ ምን የሚል ጥቅስ ታያለች… “የቤትሽን አመል እዚያው!” በነጠላ ሰውየዋ በማለዳ ሲጨቀጭቃት ቆይቶ፣ ሚኒባስ ታክሲ ላይ በጋራ ትዘለፋለች፡፡
ታዲያማ… ከዚህ በፊት እንዳወራነው፤ “ምናለ ጠጋ ብትይ!” ምናምን እያሉ…በሰው መብት እንጀራቸውን ለማብሰል የሚሞክሩ ሰዎች አያበሽቋችሁም!
“እሙ ቅርብ ወራጅ አለ፣ ጠጋ በይ…” ሲላት አትጠጋም…ረዳቱ ወይ ይሰድባታል ወይ አጉረምርሞ ሌላ ሰው ይጠይቃል፡፡ ይሄኔ ምንም የማያገባት ሌላ ተሳፋሪ፤ “ምን አለ ጠጋ ብትይለት!” ትልና ነገሩን ታባብሰዋለች፡፡
እንዲህ ባይዋ እኮ ፈረሱላ ሙሉ በርበሬ ጓዳዋ ድብቃ ጎረቤቷ፣ “አንድ ስኒ በርበሬ ታበድሪኝ!” ስትላት “ውይ ብታይው እኮ የበርበሬ እቃው ሸረሪት አድርቶበታል” የምትል ነች፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… የምር ግን ከተሳፋሪዎች አካባቢ የሚታዩ ጣልቃ ገብነቶች ችግር እየፈጠሩ ነው፡፡ የሌላው ሰው መብት ተገፎ ተወዳጅነት ለማግኘትና ለመመስገን ስንል አንዳንዶቻችን የምናደርገው ነገር ትክክል አይደለም፡፡ በተለይም ለከፈላችሁበት ወንበር (ያውም ሽልንጋችሁ ሳይመለስላችሁ!) ለትርፍ ሰው፣ “ምን አለ ጠጋ ብትል!” የሚባለው ነገር ቅጥ ያጣ  ይመስላል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ በቀደም ተፈጠረ የተባለ ነገር ነው፡፡ የሆነ ሚኒባስ ላይ ረዳቱ ትርፍ ሰው ለመጫን አንዱን “ጠጋ በል” ይላል፡፡ በወጣትነት እድሜ ላይ ያለው ተሳፋሪ፣ “አልጠጋም‹” ይላል አሉ፡፡ ይሄኔ መልስ የሚሰጠው ረዳቱ አይደለም፡፡ ተሳፋሪው ፊት ነበርና ራሱ ተስፋፍቶ ተቀመጠ፤ ሌላ ወጣት “ምን አለ ጠጋ ብትልልት!” ይላል፡፡ (ምን አገባው! ምን ጥልቅ አደረገው!) ጠጋ አልልም ያለው ወጣትም፣ የሰጠው መልስ ይህንኑ ነው አሉ… “አንተ ምን አገባህ?” ይለዋል። ይሄኔ አንድ፣ ሁለት ይባባሉና ተናነቁ አሉ፡፡ ታክሲው ቆሞ በስንት መከራ ነው የተላቀቁት አሉ፡፡
የሆነ የትራፊከ ህግ ያፈረሰውን ሰው፣ የትራፊክ ፖሊስ ያስቆመውና የቅጣት ወረቀት ሊጽፍለት ይጀምራል፡፡ ይሄኔ ሌላ ምንም የማይመለከተው ሰው ይመጣና፣ “ምን አለ ብትተወው!” ይላል፡፡ የትራፊክ ፖሊሱ እኮ  ሥራውን ነው እየሠራ ያለው፡፡
በነገራችን ላይ በዘንድሮውም ፖለቲካ፣ በዚህኛው ወይም በዛኛው ወገን ለመወደድ ሲባል የሙገሳ መአት መደርደር፣ ወይም የእርግማን ናዳ ማውረድ እየተለመደ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ በማያገባን ነገር ጣልቃ እየገባን ነገሮችን የምናባብስ ሰዎች፣ ነገር ገደድ ማለት የጀመረ ጊዜ ቀድመን መሸሸጊያ ዋሻ ዘለን የምንገባው እኛ ነን፡፡ (እናማ…በፖለቲካችን የነፋሱን አቅጣጫ በማየት “ምናለ ወንበር ብትለቅለት!” አይነት የራስን ‘ፕሮፋይል’ የማሳመር ነገር እየበዛብን ነው፡፡ የምር ግን….ፖለቲካችን ውስጥ የምናየው ስካር፣ ለዞረ ድምር ሳይበቃ በዛው እልም ብሎ ቢጠፋ እንዴት ደስ ይል ነበር!)
የስካር ነገር ካነሳን አይቀር፣ ይቺን ስሙኝማ…ከረጅም ጊዜ በፊት በአንድ የሚዲያ ተቋም ውስጥ የሆነ ነው፡፡ አና አንዱ እዛው የሚሠራ ባለሙያ፤ ቀን የለ፣ ሌሊት የለ…በሥራ ሰዓትና ከሥራ ሰዓት ውጪ የለ… ኪሱ ገንዘብ እስካለ ድረስ ደም ስሩ ውስጥ ሎካል ጂን ወይ ብራንዲ አለ፡፡ ሁልጊዜ እንደቀማመሰ ነው፡፡ በዚሀም የተነሳ ከቅርብ አለቆቹ ጋር ብዙ ጊዜ ይጋጫል። በኋላ መሥሪያ ቤቱን እንዲመሩ አዲስ ‘ቢግ ቦስ’ ይመጣሉ፡፡ እሳቸው ደግሞ በ‘መጨለጥ ውድድር ቢኖር ወርቋን ማንም የማይወስደባቸው አይነት ነበሩ። በጣም ጠዋት መጡ ቢባል እንኳን ከሦስት ተኩል ወይም አራት ሰዓት በፊት የማይታሰብ ነው፡፡
እናላችሁ…እሳቸው እንደተሾሙ አጅሬያችን ምን ቢል ጥሩ ነው… “ከአንግዲህ አንድ ሰው እንዳይናገረኝ!” ብሎ ማስጠንቀቂያ ሰጠ፡፡ ልክ ነዋ… “ተከተል አለቃህን” የሚባል ነገር አለ አይደል! ቢሯቸው ሄዶ “ጌታዬ ትጠጣለህ፣ ትጠጣለህ እያሉ ሥራዬን እንዳልሠራ እያስቸገሩኝ ነው” ብሎ ቢያነካካ ምን ሊፈጠር ነው፡፡ ሰውየው “አንተን ሳይሆን በአሽሙር እኔን መናገራቸው ነው” ብለው ጥርሳቸውን ቢነክሱስ!
እኔ የምለው...እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ይቺ ‘ኮንፊደንስ’ የሚሏት ነገራችን…አለ አይደል…አንዳንዴ ሞልታ ትፈስና የሆነ ሥራ ሠርተን፣ በቃ “የወርቅ ሜዳሊያ የእኔ ብቻ ነው” አይነት ውሳኔ ላይ እንደርሳለን፡፡ በራስ መተማመኑ አሪፍ ሲሆን ለራሳችን ያጨበጨብነውን ያህል ከሰዉ ጭብጨባ ስናጣ “ድሮሰ እዚህ አገር የበሰለ ሥራ የሚያውቅ ማን አለና!” ምናምን ብለን ራሳችንን ከጨዋታው ሜዳ እናወጣለን፡፡
“የእኔ ወንድም ሥራህን ብትነግረኝ…”
“ጸሃፊ ነኝ፡፡”
“ኦ ደስ የሚል ነው፡፡ በምን አይነት ቦታ ስትጽፍ ይስማማሃል?”
“ለመሆኑ ተሳክቶልኛል ትላለህ?”
“መሳካት ብቻ! እውነት ለመናገር ራስህን ካብክ አትበለኝና በአሁኑ ጊዜ ከሚወጡ ሥራዎች በስነጽሁፍ ደረጃም፣ በርእሰ ጉዳይም የተለየ ሥራ ይዤ መጥቻለሁ እላለሁ፡፡ ዋናው ግቤ ጥቅም ማግኘቱ ሳይሆን የአገራችንን ስነጽሁፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ ነው፡፡”
“እሰይ!” ነው እንጂ ሌላ ምን ይባላል፡፡ ግን የኖቤል ሽልማት ተሸልሞ…ሰዎች ከማድነቃቸው በፊት፣  መጀመሪያ እኛ እናድንቀውማ፡፡
የምር ግን…ህልም፣ ምኞት ምናምን ነገሮች አሪፍ ናቸው፡፡ ግን ሊሆን የሚችለውንና ‘የጊዜ ማሳለፊያ’ ህልምን መለየቱ አሪፍ ነው፡፡ “እንደው አሁን እንደሜሲ ኳሷን ማንከባለል ብችልበት…” ለማለት መጀመሪያ ኳሷ ክብ መሆኗን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ (ቂ…ቂ…ቂ…)
“ስማ ያንን ባለሦስት መቶ ገጽ መጽሀፍ አነበብከው?”
“እንደምንም ወደ ሠላሳ አካባቢ ደርሻለሁ፡፡ ለዛውም ጎበዝ ነኝ፡፡ አንተስ?”
“እኔ ትናንት ማታ ገጽ አስራ ሦስት ደርሻለሁ፡፡”
“ጀመርኩት ካልከኝ ሀያ ቀን አያልፈውም እንዴ! መቼ ልትጨርሰው ነው?”
“ቃል የምገባልህ መካከለኛ ገቢ ከመድረሳችን በፊት እኔ መጨረሻ ገጽ እደርሳለሁ፡፡”
እናማ… ጎረቤት ከማሰብ በፊት ቀደም ብሎ የቤታችንን አስተያያቶች መስማቱ መልካም ሳይሆን አይቀርም!
“ለመሆኑ አዲሱ ፊልም ምን ላይ ያተኩራል?”
“ፊልሙ አንገብጋቢ በሆኑ አገራዊ ጉዳች ላይ የሚያተኩር ነው፡፡”
“ጥሩ ሥራ ሠራን ትላላችሁ?”
“በጣም የተጨነቅንበት ነው፡፡ ይህን ፊልም ለመስራት ከፍተኛ መስዋእትነት ከፍለንበታል፡፡”
“አሁን በአገራችን እየተሠሩ ካሉ ፊልሞች ምን የተለየ ነገር አለው ትላላችሁ?”
“ብዙ የተለየ ነገር አለው፤ በምስሉ ጥራት፣ በድምጽ፣ በትወና… በሁሉም ነገር የተሻለ ሥራ ይዘን መጥተናል፡፡”
እኛም ፊልሙን ለማየት እንሄዳለን፡፡ ሀያ ደቂቃ፣ ሠላሳ ደቂቃ፣ አርባ ደቂቃ… ሹክክ ብለን እንወጣለን። በሆነ ሚዲያ ላይ ግን በአንድ (ከአንድም በላይ ሊሆን ይችላል) አስተያየት ሰጪ፤”በአይነቱ እጅግ ልዩ የሆነና የፊልም ኢንዱስትሪያችንን በአንድ ደረጃ ከፍ የሚያደርግ ፊልም!” ሲባል ስንሰማ፣ “ምናልባት እኔ ፊልም የመመዘን ችሎታዬ ገና ያልበሰለ በመሆኑ ይሆናል” ብለን አርፈን እንቀመጣለን፡፡ እናም… ይቺ “ምናለ ጠጋ ብትይ!” አይነት ነገር ብዙም እያራመደችን አትመስልም፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 4351 times