Print this page
Wednesday, 02 January 2019 00:00

የእርስ በእርስ ግንኙነቶችና ግጭቶች

Written by  ወንድወሰን ተሾመ (የስነልቦና እና የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያ)
Rate this item
(0 votes)

የእርስ በእርስ ግንኙነት አንዱ ወገን ከሌላው ጋር በጋራ ጉዳይ ይስማማል፤ አንድኛው ከሌላኛው ተለይቶ የራሱን ማንነት ያንፀባርቃል፤ ፍላጎቱንና ስሜቱን እንዳቅሙ በማሟላት ይኖራል። ለሌላው ተጣማጅ ግን የግሉ የሆነውን ባህሪ እንዲያንፀባርቅ አይፈቅድለትም፡፡

     ክፍል 1
ላለፉት ጥቂት ዓመታት በእርስበርስ ግንኙነት ዙሪያ በርካታ ሰዎችን አማክሬያለሁ፡፡ በወላጆችና በልጆች፣ በጓደኛሞች መካከል፣ በባልና ሚስት እንዲሁም በቤተዘመድ መካከል ባሉ ግንኙነቶች ዙሪያ ሰርቻለሁ። ከዚህ ተሞክሮ በመነሳት ከዚህ በታች የተጠቀሱትን የግንኙነት ዓይነቶች በግልፅ ተመልክቻለሁ፡፡ በምስልም (በሁለት መስመሮች) እንደሚከተለው ለመግለፅ ሞክሪያለሁ፡፡ ከአሁን በፊት የመጀመሪያውን የግንኙነት ዓይነት በጾታ ከፍዬ፣ አራት የግንኙነት ዓይነቶችን በናሁ ቴሌቪዥን “እሴት” ፕሮግራም ላይ አቅርቤ ነበር፡፡ ሆኖም በሶስት መጠቃለሉ የበለጠ ግልፅ እንደሚያደርገው ስለተረዳሁ በሶስት ከፍዬ ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡
አንዱ የሌላውን ማንነት የሚጨፈልቅበት፤ ነገር ግን የራሱን የግል ማንነት የሚያንፀባርቅበት፡-
በዚህ አይነት የእርስ በእርስ ግንኙነት አንዱ ወገን ከሌላው ጋር በጋራ ጉዳይ ይስማማል፤ አንድኛው ከሌላኛው ተለይቶ የራሱን ማንነት ያንፀባርቃል፤ ፍላጎቱንና ስሜቱን እንዳቅሙ በማሟላት ይኖራል። ለሌላው ተጣማጅ ግን የግሉ የሆነውን ባህሪ እንዲያንፀባርቅ አይፈቅድለትም፡፡ በዚህም ምክንያት አንዱ ሌላውን ይጨቁናል፤ አንዱ በሌላው ላይ ይሰለጥናል፡፡ አንዱ አምባገነን በመሆን ያሻውን ያደርጋል፤ ለሌላው አካል ግን እሱ ከሚያምንበት ውጪ እንዲፈናፈን አይፈቅድለትም፡፡ በዚህም ምክንያት የግል ማንነቱን እንዳያንጸባርቅ የተገደበው አካል ፍላጎቱና ስሜቱ ተጨቁኖ እንዲኖር ይገደዳል፡፡ (መስመሮቹ እኩል ይጀምሩና አንዱ ይቀጥላል፤ ሌላው ጥቂት ከሄደ በኋላ ያቆማል)
ይህንን ግንኙነት በባልና ሚስት ምሳሌ እየሰጠን ብናየው፣ በዚህ ግንኙነት አንዱ ወገን ቤተሰቡን ወይም ጓደኛውን ይረዳል፤ ሌላው ወገን ለመርዳት ሲሞክር ግን ይቃወማል፡፡ አንዱ በየሰዓቱ ዜና ማዳመጥ ይፈልጋል፤ ሌላው ግን ለአንድ ሰዓት ያክል የሚቆይ ተከታታይ ድራማ ልመልከት ሲል ይቃወማል፡፡ አንዱ በየዕለቱ ከጓደኞቹ ጋር ከበርቻቻ ይላል፤ ሌላው በሳምንት አንድ ቀን ጓደኛዬን ላግኝ ሲል ይተቻል፡፡ አንዱ የመጣበትን ቤተሰብ (Family of orientation) ዓመት በዓል በመጣ ቁጥር ልጆቼን ይዥ ልጎብኝ ይላል፤ ለሌላው ግን ዕድሉን ይነፍጋል፡፡ አንዱ ደሞዙን በግልፅ ይናገራል፤ ሌላው ግን ስለ ደሞዝ ሲጠየቅ ጨርቁን ይጥላል፡፡
በዚህም ምክንያት ይህ ግንኙነት ጠብና ሃዘን አይጠፋውም፡፡
አንዱ ከሌላው ጋር ተመሳሳይ የሚሆንበትና የግል ማንነቶች የሚጨፈለቁበት፡-
በዚህ አይነት የእርስበርስ ግንኙነት አንዱ ለሌላው የራሱን ማንነት እንዲያንፀባርቅ እድል አይሰጠውም፡፡ ራሱም የራሱን የግል ማንነት አያንፀባርቅም፡፡ ሁለቱም ተጠባብቀው ነው የሚኖሩት፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች የሚያለያያቸው ነገር ቢኖርም፣ አንዱ ለሌላው ልዩነቱን እንዲያንፀባርቅ አይፈቅድለትም፡፡ የጋራ ከሆኑ ጉዳዮች ውጪ የሚደረጉ የግል የማንነት መገለጫዎች በሁለቱም አካላት እንደ አደጋ ስለሚቆጠሩ ራሳቸውን ነፃነት ነፍገው ይኖራሉ፡፡ (መስመሮቹ እኩል ይጀምሩና እኩል ያቆማሉ፡፡)
ይህንን ግንኙነት በምሳሌ ማየቱ ጥሩ ነው፡፡ ሚስት ወይም ባል የሚያምንበት የፖለቲካ መስመር ሲኖር፣ ሌላው ደግሞ ከዚህኛው ተፃራሪ የሆነ የፖለቲካ እምነት ቢኖረው በግንኙነቱ ዙሪያ የፖለቲካ ጉዳይ አይነሳም፤ ከተነሳ ደግሞ ግንኙነቱን ከመጉዳቱ ባሻገር ሊንደው ይችላል፡፡ ይህ ጉዳይ ከሃይማኖታዊ ጉዳዮች ጋርም ግንኙነት አለው፡፡ አንዱ ወገን ሃይማኖት ቢቀይር ሌላው ከሰማ ግንኙነቱን ሊንደው ይችላል፡፡ በሁለቱም ምክንያቶች የፈረሱ ትዳሮች አሉ፡፡ ይህንን በሚመስሉ ግንኙነቶች አንዱ ከሌላው ጉዳት እንዳይደርስበት ወይም ደግሞ ግንኙነቱ እንዳይፈርስ በማስመሰልና የራስን ማንነት በመደበቅ የሚኖርበት ሁኔታ ይታያል፡፡
በዚህም ምክንያት በዚህ አይነቱ ግንኙነት አንደኛው ከሌላው የተለየ ፍላጎትና ባህርይ ማንፀባረቅ እንዳይችል አንዱ ሌላውን ይገድባል፡፡ በመካከላቸው መፈራራት አለ፡፡ በአብዛኛው አስተሳሰባቸውንና እምነታቸውን ከእነሱ ግንኙነት ውጪ ካሉ ሰዎች ጋር ሲገልጡት ይታያሉ፡፡ ለአጋራቸው ግን ሚስጥር ሆኖ አንዲቀጥል የተቻላቸውን ያደርጋሉ፡፡ ይህንን የመደባበቅ ጉዳይ የጀመሩት በአንድ ወቅት ዳር ዳር ብለው ነገሩን ለመግለፅ ሞክረውት፣ ከአጋራቸው ከተሰጠ አስተያየት አለያም አንዱ በያዘው አስተሳስብና እምነት ላይ ሌላው አካል ያለውን አቋም በማወቃቸው ነው፡፡ ሁለት አካላት አንድ አይነት ሊሆኑ አይችሉም፡፡ አንድ ለመሆን በሚያደርጉት ትግል በግንኙነቱ እርካታ ሳያገኙና ላለመፎረሽ ሲጠባበቁ  ይኖራሉ ፡፡
አንዱ ከሌላው ጋር በጋራ ጉዳይ ላይ የሚስማማበትና የራሱንና የሌላውን የግል ማንነት እንዲያንፀባርቅ የሚፈቅድበት፡-
በዚህ ግንኙነት ሁለቱ አካላት አንድ በሚያደርጓቸውና ትስስራቸውን በሚያጠናክረው ጉዳይ ላይ የጋራ ማንነት አላቸው፡፡ ሆኖም በተለያዩ ምክንያቶች የሚያለያያቸው ነገር መኖሩን ተገንዝበው፣ አንዱ ለሌላው የግል ማንነቱን እንዲያንፀባርቅ ይፈቅድለታል፡፡ ሆኖም የግል ማንነቱን ሲያንፀባርቅ የጋራ መርሆቻቸውን ወይም እሴቶቻቸውን የማይጎዳ መሆኑን የማረጋገጥ ሃላፊነትን ይወስዳል፡፡ በዚህ መልክ የተጣመረ አካል፣ የግል ማንነቱን ሲያንፀባርቅ፣ ራስን በመግዛት መርህ ይመራል፡፡ በጋራ ጉዳዮች ላይ ደግሞ ለእርስ በእርስ ግንኙነቱ የሚበጅ የሃሳብ ብልጫ በማቅረብ፣ በጎ ተፅእኖ በማድረግ ግንኙነቱን ያዳብራል። በዚህ ግንኙነት ግጭት የለም ማለት አይቻልም፡፡ አልፎ አልፎ በሃሳብ አለመግባባት የሚከሰቱ ግጭቶች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ሆኖም በውይይትና በመከባበር መርህ በቀላሉ ይፈታሉ፡፡ (መስመሮቹ አንዱ ከሌላው ቀድሞ ይጀምራል፤ ዘግይቶ የጀመረው ደግሞ አልፎ ይሄዳል)
ይህንን ግንኙነት አሁንም በባልና ሚስት ግንኙነት ብናየው፣ ለምሳሌ በገንዘብ አጠቃቀም ዙሪያ የጋራ መርህ ያስቀምጣሉ፡፡ በጋራ የሚወስኑበት የገንዘብ መጠን ይመድቡና ለእያንዳንዳቸው በየግል በነፃነት የሚወስኑበት የገንዘብ መጠን ያስቀምጣሉ፤ በዚህን ጊዜ አንዱ ወገን እንደፈለገ በገንዘቡ ላይ የማዘዝ ነፃነት ይኖረዋል፡፡ ለጋራ በተቀመጠው የገንዘብ መጠን ላይ ግን የሌላውን ወገን ፍቃደኝነትና ስምምነት ይጠይቃል። አንዱ ፊልም ማየት የሚወድ ሌላው ደግሞ መፅሐፍ ማንበብ የሚያዘወትር ከሆነ፣ በውይይት  የየግል ፍላጎታቸውን የሚፈፅሙበት ጊዜ በመመደብ፣ የጋራ ጊዜያቸውን እንዳይጎዳባቸው ይስማማሉ፤ አንዱ መማር ቢፈልግ ሌላው ደግሞ መነገድ ቢሻ በጋራ የሚያደርጉትን ዋና ነገር ሳይጎዳ፣ ሌላው ፍላጎቱን እንዲተገብር ይፈቀድለታል፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ አንዱ የሌላውን ልዩነት ተቀብሎ የሚኖረው እየተቸው ወይም እየወቀሰው አለያም ለሌሎች ሰዎች በአሉታዊ መንገድ እያሳጣው አይደለም፤ በመቀባበልና በመከባበር መርህ ነው የሚኖሩት፡፡
አልፎ አልፎ በአገራችን ሶስተኛውን አይነት የግንኙነት አይነት የመሰረቱ ተጣማጆች አጋጥመውኛል፡፡ ሶስተኛው ዓይነት ግንኙነት ለባልና ሚስት፣ ለጓደኛሞች፤ ለቤተሰብ አባላትና ለፌደራልና ለክልል መንግስታት ግንኙነት ጭምር የሚጠቅም የግንኙነት ፎርሙላ ነው እላለሁ፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ሶስቱም የግንኙነት አይነቶች፣በየትኛውም አይነት የሁለትዮሽ ግንኙነቶች የሚታዩ ናቸው፡፡ ሰዎች አውቀውም ሆነ ሳያውቁ በተራ ቁጥር 1 እና 2 የተጠቀሱትን የግንኙነት አይነቶች በብዛት ሲተገብሩ ይታያሉ፡፡ እነዚህ ግንኙነቶች ደግሞ መሠረታዊ የግንኙነት ምሰሶዎችን በጥያቄ ምልክት ውስጥ ያስገባሉ፡፡ እነዚህ ዋና ዋና የግንኙነት ምሰሶዎች በሚቀጥለው ሳምንት ፅሑፌ (ክፍል 2) ይዳሰሳሉ፡፡ ሆኖም አንድ ነገር መጠቆም መልካም ነው፡፡ ማንኛውም አይነት ግንኙነት ውስጥ ያለ ሰው የግንኙነቱ አይነት አሉታዊ ተፅእኖ ማሳደሩን ተገንዝቦ፣ መጀመሪያ በራሱ አስተሳሰብ፣ ስሜትና ባህሪ ላይ በመስራት ቀጥሎም ጥበብ ባለው መንገድ በሌላው ላይ በጎ ተፅእኖ በማሳደር፣ ወደ ሶስተኛው አይነት የግንኙነት ጥምረት ማሻሻል ይችላል፡፡
የእርስበርስ ግንኙነትን አንዳንዶች ልክ እንደ ግንባታ ቀጠና ያዩታል፡፡ በግንባታ ቀጠና ውስጥ ሁልጊዜ ግንባታ አለ፤ ስለዚህም የእርስበርስ ግንኙነት ሁልጊዜ ግንኙነቱን ለማዳበር የሚሰራ ሥራ፣ የሚደረግ  ነገር አለ ለማለት ነው፣ ይህም  በግንኙነቱ ላይ የሚሰራ የግንባታ ስራ፣ ግንኙነቱን ዘላቂ  ያደርገዋል፡፡ በሰዎች የእርስበርስ ግንኙነት ሂደት ውስጥ ግጭቶች ይኖራሉ፡፡ አንዳንድ የግጭት ምክንያቶች ቀላልና ወዲያውኑ የሚፈቱ ናቸው፡፡ እንዳንዶች ደግሞ ከባድ ይሆኑና ለመፍታት ጊዜ ይወስዳሉ፡፡ እንዳንዶቹም ግጭቱ በተፈጠረባቸው ሰዎች መካከል መፈታት ያቅታቸውና በሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ሊፈቱ ይችላሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ጨርሶ ሳይፈቱ ይቀሩና ወደ ህግ ይወሰዳሉ፤ አስከ መለያየትም ያደርሳሉ፡፡ እነዚህን የግጭት ምክንያቶች ለመቀነስ ከላይ ከተጠቀሱት የግንኙነት ዓይነቶች የመጀመሪያዎቹን ሁለቱን የግንኙነት ዓይነቶች ማስወገድና በሶስተኛው ተራ ቁጥር ላይ የተቀመጠውን የግንኙነት አይነት መከተል ተገቢ ይመስለኛል፡፡
ቸር እንሰንብት!
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡-  This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1074 times