Tuesday, 01 January 2019 00:00

አዳም ረታና የኤግዚስቴንሻሊዝም ፍልስፍና

Written by  መኮንን ማንደፍሮ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(2 votes)


     “…ትንሽ ፊትና የሚያስደነግጥ ትልቅነት ያላቸው ዐይኖች ነበሩኝ። ይሄ ማንም የሚለው ነው። አንዳንድ ጊዜ እንደውም እጅግ ከማጉላታቸው

የተነሳ ‘ዉሮ’ ያስመስልሻል ይሉኛል። ጠዋት ከእንቅልፌ ስነሳ ዓይኖቼ አይንጮሎጮሉም። ባሌ ከእንቅልፉ እንደባነነ የሚስመው እነዚህን ዓይኖቼን

ነበር--”

    ክፍል ሁለት
በቀዳሚው ክፍል በደራሲ አዳም ረታ የስነ-ጽሑፍ ሥራዎች ውስጥ የሚገኙ መሰረታዊ የኤግዚስቴንሻሊዝም ፍልስፍና ፅንሰ ሐሳቦችን በመዳሰስ  

በፍልስፍና እና በስነ-ጽሑፍ  መካከል ያለውን ቅርብ ቁርኝት ለማሳየት ሞክሬአለሁ፡፡ ይህ ተከታይ ክፍልም  ይህንኑ ጥብቅ ቁርኝት የሚያሳይ ነው፡፡
የአዳም “አለንጋና ምስር” መጽሐፍ ከሌሎቹ የሥነ-ጽሑፍ ሥራዎቹ በአንጻራዊነት በዛ ያሉ የኤግዚስቴንሻሊዝም ፍልስፍና ዐቢይ ርእሰ ጉዳዮች ተዳስሰው  

የቀረቡበት ነው፡፡ የሰው ልጅ ህልውና አሰልቺነት (አሰልቺነቱ በዘወትራዊ ተመሳሳይና ተደጋጋሚ የሕይወት ጉዞ ምክንያት የተከሰተ ስሜት ነው) እና

ትርጉም አልባነት (the absurdity of existence) መጽሐፉ ውስጥ ከሚገኙ ዐቢይ ፅንሰ-ሐሳቦች አንዱ ነው፡፡ ይህ ፅንሰ ሐሳብ

በአልበርት ካሙ የፍልስፍና እና የስነ-ጽሑፍ ሥራዎች ውስጥ በጥልቀት ተዳስሷል፡፡ እንደ ካሙ እሳቤ፤ ፍፁም በሆነ መንገድ የሕይወትን ትርጉም መፍጠር

 የሚችልና የሰው ልጅን የትርጉም አልባነት ስሜት ሊያጠፋ የሚችል (ሃይማኖትን ሳይንስንና ፍልስፍናን ጨምሮ) አስተምህሮ የለም፡፡ ምክንያቱም ሕልውና

ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ሊገለፅ የሚችል ትርጉም ወይም አላማ ፈፅሞ የለውም፡፡ ከሰው ልጅ እሳቤ በተቃራኒው፤ አለሙ ቋሚ የሆነ ሕግና ስርዓትን

ተከትሎ የሚተዳደር አይደለም ፣ ከሰው ልጅ  ጋርም ሕብረት የለውም፡፡ የሰው ልጅ የሕልውና አላማና ትርጉም ራሱ ግለሰቡ የሚፈጥረው እንጂ

ተፈጥሮአዊ መሰረት ያለው አይደለም፡፡ የሕይወት ትርጉም የሚጀምረው የሰው ልጅ  በሚኖርበት ትርጉም አልባና አላማ ቢስ ዓለም ውስጥ ራሱ

በመረጠው መንገድ ግላዊ ትርጉምን ፈጥሮ መኖር እንደሚችል ሲገነዘብና ሲወስን ነው፡፡
የህልውና ትርጉም አልባነት ስሜት የሚፈጠረው እንደ ካሙ አመለካከት፤ የሰው ልጅ በሕይወቱ ውስጥ ሁልጊዜ ደስታን፤ ሰላምን አንድነትንና መረጋጋትን

ስለሚፈልግና ምክንያቱ በማይታወቅ መልኩ የእነዚህም ነገሮች ተቃራኒ ዓለሙ ስለሚለግሰው ነው፡፡ ምክንያቱም ዓለሙ ከሰው ልጅ ግብ፣ አላማና ምኞት

ጋር ሕብረት እንዲፈጥር የሚያደርግን ስርአት አይከተልም፣ ለሰው ልጅ ዘወትራዊ ፍላጐት፣ ምኞትና መከራ ባዳና ግድየለሽ (indifferent)

ነው፡፡ እንደ ካሙ እሳቤ፤ የሕይወት ከንቱነት ስሜት ፍፁም የተገለጠ ሐቅ ነው፡፡
ይህ የኤግዚስቴንሻሊዝም ፍልስፍና ፅንሰ-ሐሳብ፣ “ያ ሐመልማል” በተሰኘው የአጭር ልብወለድ ታሪክ ውስጥ ዋና ጭብጥ ሆኖ ቀርቧል፡፡ እዚህ ታሪክ

ውስጥ በአንድ ባልተጠበቀ አጋጣሚ እጅግ ታፈቅረው የነበረውን ባሏን በሞት በማጣቷ ብቸኝነት ከቧት፣ ቀቢፀ ተስፋ የነገሰበት ሕይወትን የምትገፋ ገፀ-

ባሕሪ እናገኛለን። በገፀ-ባሕሪዋ ባል ሕይወት ውስጥ የተፈጠረው ያልተጠበቀ አሳዛኝ ክንዋኔ (የክንዋኔው አሳዛኝነት ከሰው ልጅ አቀባበልና ልምድ አንፃር

ነው) በሰው ልጅ የምክንያታዊነት አረዳድ አቅም ሊገነዘቡትና ለምን እንደሆነ ትንታኔ ሊቀርብበት  የሚችል አይደለም፡፡ ይህ ክንዋኔ የሰው ልጅ ነባራዊ

ህልውናዊ ሁኔታን ቁልጭ አድርጐ ያሳያል፡፡         
… በዓለም ላይ አንድ ሰው ብቻ ተወዶ፣ ያም አንድ ሲሞት ምን ይደረጋል? ቤት ለብቻው ምን ትርጉም አለው? ዛሬ ማታ ብቻዬን ከምኖርበት ስሙ

የተጠራ ግዙፍ ቤት፣ ሳሎን ውስጥ በባለ መስታወቱ ሠፊ በር በኩል ወደ ውጪ አያለሁ … ያረጁ የፀደይና የኦብዘርቨር መፅሔቶች ከባሌ ጋር አብረን

የምናነባቸው የነበሩ… የምንስቅባቸው፣ የምንወያይባቸው … እነሱን ዛሬ ደግሜ ደጋግሜ አንብቤ አዳክመውኝ፣ ሰልችተውኝ፣ አንዳንዴም አማረውኝ እንደ

አጋጠመኝ ወርውሬአቸው፣ የወለሉ ከፊል በተገላለጠና በተከደነ እነሱ ተሸፍኖአል (አዳም፣ አለንጋና ምስር፣ 2004፣ ገፅ 252)፡፡
…ዛሬ እዚህ ሳሎን ተቀምጬ … ወደ ውጭ ስመለከት… የእኔ ሕይወት አጠወላለጉ እስኪያስደነግጠኝ፣ እስኪያሳብደኝ ድረስ ተዘበራርቆና ወድቆ ሳለ እዛች

አጥሬ ዙሪያ የተንጠለጠለው የሐረግ አትክልት ሐመልማሉ ግን አማረም አላማረም ሳያቋርጥ መድመቁ፣ መተንፈሱ ይገርመኛል (አዳም፣ አለንጋና ምስር፣

2004፣ ገፅ 258)፡፡
ዓለሙ ውስጥ የሚከናወኑና የሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ የሚፈጠሩ ነገሮች ለምን እንደተከናወኑ፣ በምን ዓይነት ሂደት እንደሚከናወኑ… ወዘተ ምክንያታዊ

የሆነ ትንታኔ ሊቀርብላቸው ስለማይችል፣ የሰው ልጅ ህልውና ዓላማ ቢስና ማብቂያ በሌለው የድግግሞች ሕግ የተሞላ (pointless) ነው፡፡

ግለሰቡ ይህን ድግግሞች ሲያስተውል የመሰልቸትና ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ይፈጠርበታል፡፡
የሰው ልጅ በአጠቃላይ ህልውናዊ ሁኔታው ግራ ማጋባትና ትርጉም ማጣት የሚጀምረው በእሱ ዘወትራዊ አወንታዊ ምኞቱና ከዚህ በተቃራኒው ቸልተኛውና

ከእሱ ቅድመ እሳቤ ጋር የሚጣረስ ስርዓት በሚያካሂደው ኢ-ምክንያታዊው ዩኒቨርስ (irrantional universe) መካከል ያለውን ኢ-

መስተጋብራዊ ሁኔታ ሲያስተው ነው፡፡  ይህ ፍልስፍናዊ ፅንሰ- ሐሳብ “ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ” በተሰኘው የአዳም ረታ የስነ- ጽሑፍ

ሥራ ውስጥ “ኩሳንኩስ” በሚለው የአጭር ልብወለድ ታሪክ  ተዳስሶ ይገኛል፡፡
… ለረጅም ጊዜ ያልተለወጡ ልብሶቼ እላዬ ላይ ይንጀላጀላሉ፡፡ ያን አየሁ፡፡ ሥጋዬ ችኩል ሆነ፡፡ ሴትነቴ ተቅበጠበጠች፡፡ ምን ማለቴ እንደሆነ ይገባችኋል፡፡

የክፍሉ ትዝታ ባልታወቁ ኃይሎች እንደ ታዘዘ ሁሉ ከህሊናዬ ጀርባ ደብዘዝ ብሎ ቆመ (አዳም፣ ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ፣ 2003፣ ገፅ፣

225)፡፡
… እንዲህ በቀለለኝ ዕለት ነው በመኪና የተገጨሁት። እንዲህ አንቀዥቅዦኝ የወጣሁ ዕለት ነው አደጋው የደረሰብኝ፡፡ ትልቁ ፖስታ ቤት አካባቢ መንገድ

ስሻገር ውይይት ታክሲ ገጨኝ፡፡ አደጋ ባይመረጥም ሕይወቴ ግን አላለፈችም፡፡ ብዙ አልተጐዳሁም፣ አጥንቴ አልተሰበረም፡፡ የልብ ሞቴ አልቆመም፡፡ እራሥ

ቅሌ አልተሰነጠቀም፡፡ መንገድ መሐል ከቆሙት ደሴቶች ዙሪያ ጥቅሙ ያልገባኝ ጨረራም ሽቦ ግን ግራ ዐይኔ ላይ ወጋኝ፡፡ ሆስፒታል ገብቼ ከወጣሁ

በአስራ አምስተኛው ቀኔ አንድ ዐይና ሆንኩ (ዝኒ ከማሁ)፡፡  
ገፀ ባሕሪዋ በባሏ ሞት ምክንያት ተከስቶባት ከነበረው ቀቢፀ ተስፋ ካጠላበት ስነ ልቦናዊ ሁኔታ አገግማ በጉጉትና በሙሉ ተነሳሽነት አዲስ የሕይወቷን

ምእራፍ በጀመረችበት ወቅት ነበር ፈፅሞ ምክንያታዊ ምላሽ ልታቀርብለት የማትችለው ያልጠበቀችው አደጋ የደረሰባት። ክስተቱ የሰው ልጅን ህልውና

ትርጉም አልባነት የሚያሳይ ነው።
የሰው ልጅ የህልውናን ትርጉም አልባነትና ድግግሞሽ  መገንዘብ ሲጀምር ጥልቅ የሆነ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ስለሚሰማው አለመኖርን (Suicide)

ከዚህ አይነቱ የሰው ልጅ ተጨባጭ ሐቅ ለማምለጥ እንዳማራጭ ሊያቅደው ይችላል። ለካሙ ይህ አይነቱ ተግባር ኢ-ሞራላዊ ስለሆነ የሚወገዝ ነው።

ካሙ ለዚህ መሰረታዊ ህልውናዊ ተግዳሮቶች እንደ መፍትሄ ያቀረበው ሐሳብ የራሱን ትርጉም አልባነትንና በድግግሞች የተሞላ ኑሮን መቀበል

(acceptance) ነው።  እንደ እሱ እሳቤ፤ የሰው ልጅ ህልውና ትርጉም አልባና አሰልቺ (አሰልቺ የሆነው ተመሳሳይ በመሆኑ ምክንያት ነው)

ስለሆነ ከዚህ ቀውስ ለመውጣት ራስን ማጥፋት ብቸኛ አማራጭ አይደለም፤ ምክንያቱም አንድ ግለሰብ ይህን ህልውናዊ ሐቅ ተቀብሎ ኑሮውን  በዚህ

ትርጉም አልባ በሆነ ዓለም ተመሳሳይ ኑሮውን መቀጠል ስለሚችል። እንደ ካሙ እሳቤ፤ ብቸኛው ትክክለኛ መፍትሄ ይሄ ነው። ይህን መሰረታዊ

አስተምህሮ ተገንዝቦና እንደ መመርያ ተቀብሎ በዚህ ትርጉም አልባ ዓለም ውስጥ ህልውናውን ለመቀጠል የወሰነውን ግለሰብ ጀግና (the absurd

hero) ይለዋል። ይህ ፍልስፍናዊ ርእሰ ጉዳይ ከላይ በተገለፀው የአዳም ስራ “ኩሳንኩስ” በተሰኘው ታሪክ ውስጥ ይገኛል።
… ትንሽ ፊትና የሚያስደነግጥ ትልቅነት ያላቸው ዐይኖች ነበሩኝ። ይሄ ማንም የሚለው ነው። አንዳንድ ጊዜ እንደውም እጅግ ከማጉላታቸው የተነሳ

‘ዉሮ’ ያስመስልሻል ይሉኛል። ጠዋት ከእንቅልፌ ስነሳ ዓይኖቼ አይንጮሎጮሉም። ባሌ ከእንቅልፉ እንደባነነ የሚስመው እነዚህን ዓይኖቼን ነበር  

(አዳም ፣ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ፣ 2003፣ ገፅ 222)።
… ታዲያ ለመጀመርያ ዕለት ተዋውቀን በሚቀጥለው ቀን ተቃጥረን ስንገናኝ በሚችላት በጣም ትንሽ አማርኛና ቀላል ቃላት ዐይኖቼ ትልቅና ዉብ እንደሆኑ

ነገረኝ። ዕንቁ እንደሆኑ ነገረኝ (ዝኒ ከማሁ )።
…ከአስራ አምስት ቀን በፊት በልደታ ዓይን ነበረኝ። ለኪዳነ ምህረት አንድ ዓይና ሆንኩ። በፍልስፍናዬ የምጠብቀው አደጋ ነው። አዝናለሁ፣ ይከፋኛል።

ግን ምን ይጠበስ? ቁስሉ ሲድን የላስቲክ ዓይን አስገባሁ (አዳም፣ ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ፣ 2003፣ ገፅ225)።
…ክፍሉ ከሞተ በኋላ ለሁለተኛ ቀን ዓይኖቼን ስኳል የምኩለው ሁለት የተለያዩ ዐይኖቼን ነው።’ የታወረውን እኩላለሁ እንዳትይን ብቻ ‘የሚሉ

ይኖራሉ። በማንም አልፈርድም። ግን እኮ ታወረ አልታወረ የእኔ ዕቃ ነው። የሚገርመኝ ‘ከውሮ’ ወደ ‘ጠንጋራ’ (ገና መባሌን ባልሰማ፣ እንዳማይቀር

የማውቀው) አወዳደቄ ነው። የሚገርማችሁ ግን ኣይሳስበኝም። አዎ ቅር ይለኛል። ግን አሳስቦ፣ አሳዝኖ አያስተክዘኝም ( አዳም፣ የወስዳል መንገድ

ያመጣል መንገድ፣2003፣ ገፅ 225-226)።
… በቀስታ በቀስታ የተበላሸውን ዐይኔን መኳል ጀመርኩ። የሚያስፈራ ነገር አለው። ግን ይሄ አለመታደል እንደምታዩት ፊቴ ላይ የሰፈረውን ፈገግታ

አያጠፋውም (አዳም፣ ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ፣ 2003፣ገፅ 226)።
ሌላኛው እዚሁ ታሪክ ውስጥ የሚገኝ የኤግዚስቴንሻሊዝም ፅንሰ-ሐሳብ የወንጀለኝነት ስሜት (guilitiness) ነው፡፡ እንደ ሳርተር አመለካከት፤

የወንጀለኝነት ስሜት የሚፈጠረው አንድ ግለብ በሚያደርጋቸው ማንኛቸውም ነገሮች ላይ ሙሉ ነፃነትና ሥልጣን እንዳለው መረዳቱና በዚህም ለሚፈፅማቸው

ማንኛቸውም ድርጊቶች ኃላፊነቱ የግሉ መሆኑን ሲገነዘብ ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ገፀ ባህሪዋ ላይ የተፈጠረው የጥፋተኝነትና የፀፀት ስሜት መነሻ፣ በእሷ

ፈቃደኝነት ጉድለት እጅግ ታፈቅረው ከነበረው ባሏ ልጅ ሳትወልድ፣ እሱ ቀድሞ መሞቱና ለሞቱም ዋና መንስኤ መሆኗ ነው፡፡
… ልጅ ለመውለድ ከእኔ ይበልጥ እሱ ይፈልጋል፡፡ ብዙ ጊዜ ባይሆንም ደጋግሞ መውለድ፣ ልጅ መልካም ነገር መሆኑን ያነሳሳል። እኔ ግን ልጅ ማርገዝና

ማጥባት አልፈለግኩም … እሱን ባሌን ብቻ ነበር የፈለኩት፡፡ ከሁሉም ነገር እሱ ይበልጥብኝ ነበር (አዳም፣ አለንጋና ምስር፣ 2004 ፣ ገፅ 253)፡፡
…ያለፈውን ምሽት አስታወስኩ፡፡ አሁን ባገኘው ተመኘሁ፡፡ ይኼ ጊዜ ሳያልፍ እንዲያስረግዘኝ ፈለግኩ። ውስጤን፣ ገንዳዬን በአምሳሉ እንዲሞላው ፈለግሁ።

አልመጣም፡፡ ለዘላለም አልመጣም፡፡ የተቀመጠት ታክሲ ከአንድ አምቡላንስ  ጋር ተጋጭቶ ነው አሉ፡፡ ከሁለት ሰዓት በኋላ ሆስፒታል ተጠርቼ ሄድኩና

ሲሞት አየሁት። ጭንቅላቱን እየነቀነቀ … ለምን እንደነቀነቀ ይገባኛል፡፡ እተጋደመበት ሕይወቱ ሲያልፍ … አንጀቴን አጥፌ ሆስፒታሉ ወለል ላይ እንደ

አበደ ሰው ስፈራገጥ … “ዓለም ከአሁን በኋላ ትጥፋ” ስል ለምወደው ባሌ ብቻ ያለቀስኩ የመሰላቸው ብዙ ነበሩ፡፡ ለእኔ እሱ ብቻ አልነበረም…

መወደዴ ብቻ አልነበረም… አንድ የተመኘውን ነገር ላደርግለት ባለመፈለጌ ቆጭቶኝ ነው (አዳም፣ አለንጋና ምስር፣ 2004፣ ገፅ 257- 258)፡፡
… ያን ዕለት ማታ “እሺ” ብለው ኖሮ፣ በሰላም እናድር ነበር፤ በሰላም ብናድር ኖሮ በሰላም ጠዋቱን አብረን እናረፍድ ነበር … ታክሲ የለ

አምቡላንስ ያለ፡፡ አሁን እዚህ ተቀምጬ እንዳሻቸው በሚሆኑ አበቦች እቀናለሁ … በለውጥ በሚንቦገቦጉ፡፡ እኔ ግን በበቀል ለምለም ማህፀኔን

እያጠወለግሁ ... እግዜር ያበጀለት መረቁን በቁጭትና በተስፋ መቁረጥ በየቦታው እያዝረበረብኩ (አዳም፣ አለንጋና ምስር፣ 2004፣ ገፅ 259)፡፡
…ገላዬ በጊዜ ብዛት እየወፈረ … የመነኮስ ጭኔ ብቻውን እያደገ፣ የወር አበባዬ እየመጣ ሲጠፋ፣ ጡቴ እየወደቀ፣ የሆዴ ቦርጭ እየገፋ … ሽንጤ እያጠረ

ሲሄድ አያለሁ፡፡ መታጠቢያ ቤት መስታወት ፊት ለፊት ቆሜ የብቸኝነት አወዳደቄን ሳይ፣ ወተት ሳይወርደኝ፣ የዕንግዴ ልጅ ሳይጠረገኝ፣ ማህፀኔ ሳይቆስል፣

ለአንድ ለምወደው ሰው ይኼን ሁሉ የማየውን ሥጋና ደም ሥር ሳልሰጠው መቅረቴ አንጀቴን ይበላኝና ከቆምኩበት ወድቄ፣ መሬት በጥፊ እየመታሁ

አለቅሳለሁ፡፡ በጥፊ እየመታሁ፡፡ ይኼ ሁሉ ስቃይ ግን ከእግዜርና ከሰይጣን በስተቀር ማንም ሳያውቀው ባዶ ቤት ውስጥ ይቀራል እየመሰለኝ (አዳም፣

አለንጋና ምስር፣ 2004፣ ገፅ26ዐ)፡፡

Read 1566 times