Tuesday, 01 January 2019 00:00

ትናንትን በዛሬ ሀሁ... (የተውኔት ቅኝት)

Written by  ኃይሌ ሲሳይ ገበየሁ
Rate this item
(0 votes)

ነገረ መግቢያ
ጠቢብ ወትሮም ለትንቢት የቀረበ ለጥበብ ያደረ ነው፡፡ እናም ዘመን ተሻግሮ አመታት ቆጥሮ፣ ቃሉ በተግባር፣ ትንቢቱ በአካል ይገለፃል፡፡ የጸጋዬ ገብረ

መድህን “ሀሁ በስድስት ወር” ተውኔትም የዘመናችን የአስተሳሰብ ልሽቀትን፣ የትምህርት ውድቀትን፣ የሰብዕና ድቀትን በድኩማን ገፀ ባህሪያቱ የተነበየ ነው

ማለት ይቻላል፡፡ ስለሆነም የሀገራችን ኢትዮጵያን የችግር መንስኤ ለመረዳት የጠቢቡን አንኳር አንኳር ሥራዎች መርጠን፣ መልሰን ከልሰን፣ ከዘመናችን ጋር

እየዋጀን መፈተሽ፣ ለሰብዕናችን ዝቅጠትና ልሽቀት መፍትሄ ለማግኘት ሳይበጀን አይቀርም፡፡
ተውኔቱን በወፍ በረር እየነቀስን፣ በምዕራፍ እየቆረስን፣ በትናንት ትንቢት ዛሬን እንዳስሳለን። የውድቀታችንን ጅማሮ፣ የችግራችንን መንስኤ እናስሳለን፡፡ ከዚያ

በፊት ግን  ትዝታችንን ለአንዳፍታ ወደ ‹‹የካቲት 1966 ዓ.ም›› እንመልስ፡፡ “ሀሁ በስድስት ወር” ተውኔት በአጣዳፊ ተደረሰ ይላል -

ደራሲው፤  በትሁት አስተያየት፡፡ ቀድሞ ከነበረው የህዝባዊ የፖለቲካ ሞት ወደ ሥርዓት፣ ከሲቃ ወደ ትንሳኤ፣ ከቅዥት ወደ እውነት የምናንሰራራበት

የተስፋ ‹‹ሀሁ››ን በሃምሳ አለቃ ጣሴ፣ ወታደርን በጥዱ ናደው፣ የመገናኛ ብዙኃኑን  በሰሙ ንጉሡ፣ ጣሴ አስተማሪን በህፃኗ ጢቅሌ፣ ረሃብንና

ስደትን በአያያ ቃሌ፣ ባሕታዊነትን በደራ አጋኖ፣ የልመናን ጥበብ በጌኔ አምበርብር፣ አስለቃሽን በግራ ጌታ (ባፈረሱት ካህን)፣ የሐይማኖት አባትን

በአዲሱ ጥሩባም ነፊ  እናያለን፡፡
የ“ሀሁ በስድስት ወር” ተውኔት ዘውግ ባይተዋር ነዉ፡፡ ብትውርና ተውኔት ደግሞ እንደ በርቶልት ብሬሽት እምነት፤ ማንኛውም ነባራዊ እውነታ ላይ

ተመስርቶ ተውኔት ማቅረብ ያለበት ተመልካችን ለማሳወቅ እንጂ ስሜት ውስጥ ከትቶ ለማስዋኘት መሆን የለበትም፡፡ ብትውርና ተውኔት በዋናነት

የሚያተኩርበት ርዕሰ ጉዳይ ፖለቲካ ሲሆን አምርሮ በመንቀፍ ታዳሚውን ያሳውቃል፡፡ አለማመንን ማስተጓጎል (Illusion of reality)

እንዳይፈጠር ይጠነቀቃል፡፡ የምክንያትና ውጤት ውህደት ሳይሆን የርዕሰ ጉዳዩ መተላለፍም ያስጨንቀዋል። በተጨማሪም የቃለ ተውኔቶቹ መነሻና ማጠንጠኛ

ሃሳብ የሚመነጨው ከእውነታውና ከማህበራዊው ዓለም ገጠመኝ ነው፡፡ “ሀሁ በስድስት ወር” ሴራ አልባ ተውኔት ነው፡፡ መነሻውም ሁለንተናዊው

የየካቲት አብዮት ዋዜማ ታሪካዊ ክንዋኔዎች ናቸው፡፡ ድርቅ፣ አመፅ፣ ሰላማዊ ሰልፍ፣ እሥራት፣ ግዞት፣ ሥራ አጥነት፣ ሙስና… ወዘተ ናቸው፡፡ እነዚህን

እየነቀሰ ይተቻል፡፡
የ“ሀሁ በስድስት ወር” ተውኔት ታሪክ ምንድን ነው? ቢባል አንድ ነጠላ ሀረግ መሳይ ታሪክ መዘን ማውጣት አንችልም፡፡ በሴራ አልባ ተውኔት፣

አቀንቃኝና ፀረ-አቀንቃኝ የምንላቸው ወጥና አስተኔ ገፀ ባህሪያት ለይቶ ማውጣትና ስለነሱ መናገርም እንዲሁ አስቸጋሪ ነው፡፡ መቼቱን በተመለከተ

በአብዛኛው ኢ-ምናባዊ በመሆኑም የሴራ አልባ ተውኔት ጊዜ፣ ቦታና ማህበራዊ እውነታ በዘመኑ ከነበረው ማህበረሰባዊ፣ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ

እውነታዎች ነቅሶ ያወጣል፡፡ ከዚህ አንፃር የ2010 ‹‹አብዮት›› መነሻውም፤ ሁለንተናዊው እሥራትና ግዞት፣ ሥራ አጥነት፣ አመፅና ሰላማዊ ሰልፍ

እንዲሁም ሙስና… ነው ብንል አልተሳሳትንም፡፡  
ልክፍት…
ኢትዮጵያ በሌት ጨለማ በአዲስ ፍልስፍና እየተናወጠች ነው፡፡ በለውጥ ማዕበሉ ጎሕ እንደሚቀድ ተስፋ አድርጋለች፡፡ ጸጥ ባለው ጨለማ ድንገት አሚናዎች

ሹመት ያዳብር ዜማና ግጥም ያወርዳሉ። ‹ሌሎች በህብር መደመር ሲጀምሩ› “ሀሁ በስድስት ወር” /ገጽ 2/ በኑሮ የተበደለ፣ አካሉ የጎደለ ሰው

እየተሽመደመደ መጥቶ፣ አሚናዎችን ልክፍት እንዳይጠሩ ያባርራል፡፡ በድጋፍ የቆመችው ቤት፤ የኢትዮጵያን ተምሣሌት ናት፤ እንዳያፈርሷት በአዲሱ ቅያስም

እንዲሄዱ ያሳስባል፡፡ ይሁንና ‹የፈሩት ይደርሳል የጠሉት ይወርሳል› እንዲሉ፣ የሰሙን ልክፍቱን ቀስቅሰው ይሄዳሉ፡፡ የሙያዎች አባት፣ የእውቀት ብርሃን

የሚወክለውን ገፅ ባህሪ፣ ሰሙ ንጉሱን በመጀመሪያ እንመልከት፡፡
ሰሙ ንጉሱ፤ አስተማሪን የሚወክል ገፀ ባህሪ፣  ነው። በመሆኑም የትናንቱን አይተን፣ የዛሬን አስተማሪ፣ ትምህርትና ማህበረሰብ ህይወት እንድናገናዝብ

ይረዳናል፡፡ ሰሙ ከመጀመሪያው እውነት የተነጠቀ፣ ፍትሕ ያጣ በመሆኑ፣ ህይወቱም በልክፍት ፍርሃት- ንዴት፣ ሀዘን፣ ፀፀት መጠራጠር እልህ መግባት …

በጥቅሉ የጤና ቀውስ ውስጥ ይገባል፡፡ መንፈሱ ይሞታል፡፡ በዚህም ጊዜ  ኮሌጅ ገብቶ ተመርቆ፣ ለማስተማር ወደ ማህበረሰቡ ሲገባ፣ ያጣውን ፍትህ

የተነጠቀውን እውነት ከማህበረሰቡ ይነጥቃል። ያለበትን የሥነ ልቦና ቀውስ፣ የኑሮ ልክፍት ወደ ማህበረሰቡና ተማሪዎቹ እንደ ወረርሽኝ ይረጫል። በመበደሉ

ይበድላል፤ በመሰረቁ ይሰርቃል፡፡ አብዶ ማህበረሰብን ያሳብዳል፡፡ ይህ የሀሁ ትንቢት፣ በዛሬው አስተማሪና ማህበረሰብ ላይም የሚታይ ነው፡፡ ይህም

የልክፍቱን መስፋፋት፣ የውድቀታችንን ፍጥነት አጉልቶ ያሳያል፡፡ የሰው ንቃተ ሕሊና፣ የሚባለውን የአእምሮ አስተሳሰብ እየተጠቀመ፣ ነገሩን አገናዝቦ የሚያስብ

ሲሆን ነው፡፡ ይሁንና ህሊናውን የተቀማው ግን የውድቀቱን መንገድ ያፋጥናል፡፡
ድግምት…
አስተማሪው ለምን ልክፍተኛ ሆነ? ካልን በደረሰበት የፍትህ እጦት፣ በተሰረቀው እውቀትና እውነት ሲሆን እሱም የጨለመበትን ተስፋ በተማሪዎቹ ላይ

ሲያጨልም እናያለን፡፡ ሰሙ መጀመሪያ ያልወደቀውን ወድቀሃል መባሉ፣ የአዕምሮ መቃወስ የጤና መታወክ ያሳድርበታል፡፡ ልክፍቱም የሚጀምረው በዚህ ጊዜ

ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የሀገር መሰረት የሙያና የዕውቀት አባት የሆነው መምህር፤ በወደቀና በታወከ ተስፋ ቢስ ሰው ሲወክል ይታያል፡፡ እንግዲህ የአንድ

ሀገር የትምህርት ተቋም ሲታወክ ምን እንደሚከሰት ግልጽ ነው!! ምንም እንኳን ሰሙ በፈተና ያልወደቀ ቢሆንም እውቀቱን በመሰረቁ የሥነ ልቦና

ቀውስ ውስጥ ነዉ። ስለሆነም ያለውን ለማካፈል ፊደል ለማስቆጠር፣ ብርሃን ለማሳየት፣ እውቀት ለማብራት፣ ነፃነትን ለመስበክ ወሎ ቦረና ቢሄድም፣

በልክፍቱና በተከሰተው ረሃብ ሳቢያ ለረሃባቸው ምግብ፣ ለጥማቸው ውሃ መስጠት ባለመቻሉ ተስፋው ይመነምናል። ልጆቹንና ማህበረሰቡን ይዋሻል፡፡

የቀረቻቸውን ንብረታቸውን አንዲት ግማሽ ሙት ግመል፣ ምግብና ውሃ ይዞ ለመመለስ ቃል ገብቶ ወደ ከተማ ሲሄድ፣ ግመሏ በመሞቷ የነበረው

እንጥፍጣፊ እምነትና ተስፋ ይጨልማል፡፡ በዚህም ምክንያት የአፋር ግመል ይሰርቃል፡፡
እውቀትን … ተስፋን … ነፃነትን… አንድነትን ለመስበክና ለማስተማር የተላከው አስተማሪ፤ ስርቆትና ውርደት ውስጥ ይገባል፡፡ ገጠር ውስጥ ሲያስተምር

ማህበረሰቡ ያደረገለትን ትብብር፣ ቅንነት ሲያስታውስ ግን ሕግ መጣሱ ሰላምና ደስታ ያሳጠዋል። ይህን የምንገነዘበው በሚያስተምርበት ማህበረሰብ ገረድ

አምጡልኝ ሲል ሲያመጡለት፣ ዲቃላ አስይዞ ሲያባርራቸው፣ ምሽት አምጡልኝ ሲል ልጆቻቸውን ሲሰጡት ዲቃላ አስታቅፎ ሲልክላቸው፣ ልጆቹን ተስፋ

እያሳጣ፣ ነፃነታቸውን እየነፈገ እንደነበር ሲያስታውስ ይፀፀታል፡፡ ልክፍቱም ይባባሳል፤ እሱ የተቀማውን ተስፋና እውነት ከሌሎች ይቀማል፡፡ ምንም እንኳን

እውቀትን ለማጋራት ነፃነትን ለመፈንጠቅ፣ ብርሃን ለማሳየት ወደ ገጠር ቢሄድም፣ ልክፍቱንም አስተላልፎ፣ የልጃገረዶቹን ሥነ ልቦና አጨልሟል፡፡ በመከራና

ረሃብ ዘመናቸውም እግሬ አውጭኝ  ብሎ ልጆቹን ትቶ፣ ንብረታቸውን ዘርፎ፣ ትቷቸው ከተማ ገብቷል፡፡ ማህበረሰቡ በረሃብ በፍትሕ እጦት፤ በተስፋ

መነጠቅ ይጎዳል፡፡ ይህ ደግሞ የተፈጸመው በእውቀት አባታቸው  በመሆኑ ተስፋ ቢስ ያደርጋቸዋል፡፡
ውርስ…
የዛሬውም አስተማሪ ሕይወቱን፣ እውቀቱንና ገቢውን የተሰረቀ ነው፡፡ በእኩል ደረጃ ካሉት የሙያ ዘርፎች ዝቅተኛ ገቢም ክብርም ያለው አስተማሪ ነው፡፡

በመሆኑም እውቀት ያላቸው በሥነ ምግባር የተወደሱ፣ ባህልና ትውፊታቸውን ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ ማህበረሰብን የሚረዱ፣ በራሳቸው የሚተማመኑ ሥራውን

የሚወዱና የሚያከብሩ አይገቡበትም። የገቡበትም ሙያውን ወደ ሌላ ሙያ መሸጋገሪያ ድልድይ ያደርጉታል እንጂ በእውቀት እየበቁ፣ በልምድ እየዳበሩ

እስኪሄዱ አይቆዩም፡፡ ስለሆነም ‹‹ተምረዉ›› ስማቸውን የማይፅፉ፣ ፊደል የማይለዩ ተማሪዎች በዝተዋል፡፡ አንድ አንጋፋ አስተማሪ እንደነገሩኝ፤

‹‹ከ10ኛ ክፍል የወደቁ፣ መሰናዶ መግባት ያልቻሉ፣ በእውቀትም በምግባርም ደካሞች ተማሪዎች፤ በኮሌጅ የመምህርነት ኮርስ ወስደው፣

‹‹ያልተማሩትን›› እንዲያስተምሩ ተደርገዋል››፡፡ የአስተማሪ ደመወዝና ክብር በመነጠቁ ሙያው እየጎፈየ ሄዷል፡፡
ሰሙ ንጉሱ የተነጠቀውን ፍትህ ያዩ ሰዎች ሙያውን ጠልተውታል፡፡ አሁንም ሰሙ ፍትህ አላገኘም፡፡ እጓለ ገ/ዮሐንስ (የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ)

በተሰኘው መጽሐፋቸው ትልቁ ፈላስፋ ፕላቶን እንዳለው ‹‹ሰው ትክክለኛውን ትምህርት ያገኘ እንደሆነ ለስላሳና (ኖብል) እግዜርን የሚመስል ፍጡር

ነው፡፡ ትምህርት ያላገኘ እንደሆነ ግን በምድር ላይ ካሉት አራዊት ሁሉ የባሰ ነው፡፡›› አውሬነቱ በሀገራችን ኢትዮጵያ ተከስቶ በመንጋ ፍርድ ታይቷል፡፡

የሰሙን እውነት መልሰን የፍትህ ህክምና ማድረግ እስካልቻልን ድረስ  የውድቀትን አውራ ጎዳና እየጠረግን እንደምንቀጥል “ሀሁ” ይጠቁመናል፡፡ የሰሙ

ንጉሱ ፍትሕ ከተመለሰ ግን ሙያውን የሚወዱ፣ ሀሳባቸው ያልተሰረቀ፣ ብቃት ያላቸው፣ ብርሃንን ከአፅናፍ አፅናፍ የሚረጩ፣ ለፍትህ የሚቆሙ፣

ማህበረሰቡንና ልጆቹን ከልክፍቱ የሚያወጡ ሰዎች እንደሚፈጠሩ በተውኔቱ እናያለን፡፡


Read 830 times