Print this page
Tuesday, 01 January 2019 00:00

የጐሳዬ ተስፋዬ “ሲያምሽ ያመኛል” አዲስ አልበም ሊወጣ ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ፈጅቷል ተብሏል
               
     በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የተወዳጁ ድምፃዊ ጐሳዬ ተስፋዬ አምስተኛ የሙዚቃ አልበም የሆነው “ሲያምሽ ያመኛል”፤ የፊታችን አርብ ታህሳስ

26 ቀን 2011 በኢትዮጵያና በመላው አለም በገበያ ላይ እንደሚውል ተገልጿል፡፡
አራተኛ አልበሙን “ሳታመሃኝ ብላ”ን ካወጣ ከ11 ዓመታት በኋላ ለአድናቂዎቹ ያቀረበው ይህ አዲስ አልበም፤ ከ1.ሚ ብር በላይ ወጪ

እንደተደረገበት አከፋፋዩ “ሪቮ ኮሚዩኒኬሽንና ኢቨንት” ለአዲስ አድማስ አስታውቋል፡፡ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሚባሉት ድምፃዊያን አንዱ

የሆነው የድምፃዊ ጐሳዬ ተስፋዬ አዲስ አልበም፣ ለረጅም ጊዜ በጉጉት ሲጠበቅ የቆየ ሲሆን፤ ደረጃውን የጠበቀና የተዋጣለት አልበም ለማድረግ ሲባል 11

ዓመታትን መፍጀቱንና ግጥምና ዜማቸው ተሰርተው ከተጠናቀቁ ከ40 በላይ ስራዎች ውስጥ 15ቱ ተመርጠው በዚህ አልበም መካተታቸውን አከፋፋዩ

ጨምሮ ገልጿል፡፡
በዚህ አዲስ አልበም ላይ ከተሳተፉ እውቅ የሙዚቃ አቀናባሪዎች መካከል አበጋዝ ክብረ ወርቅ ሺዎታ፣ ካሙዙ ካሳ፣ አቤል ጳውሎስ፣ መኮንን ለማ

(ዶክተሬ)፣ ሚካኤል ኃይሉ (ሚኪ ጃኖ) እና ሱልጣን ኑሪ (ሶፊ) እንደሚገኙበት የገለፀው አከፋፋዩ፤ በግጥምና ዜማውም ከዚህ ቀደም በሰሩት ስራ

አንቱታን ያተረፉት አለምፀሐይ ወዳጆ፣ ይልማ ገ/አብ፣ ሀብታሙ ቦጋለ፣ ቢኒያም መስፍን (ቢኒባና)፣ አለማየሁ ደመቀ፣ መሰለ ጌታሁንና ራሱ ጎሳዬ

ተስፋዬ ተሳትፈውበታል ተብሏል፡፡
በአገራዊ፣ በማህበራዊ እና በፍቅር ዙሪያ የሚያጠነጥኑ 15 ሙዚቃዎችን ያካተተው አልበሙ፤ ሪከርድ የተደረገው በአሜሪካ ኒው ዮርክ ሲቲ ሲሆን

ጥራትና ደረጃውን የጠበቀና ዘመኑ ያፈራው የሪከርዲንግ ቴክኖሎጂ አሻራ ያረፈበት መሆኑም ታውቋል፡፡
ጎሳዬ ተስፋዬ ከዚህ ቀደም “ሶፊ”፣ ከሌሎች ድምፃዊያን ጋር “ቴክፋይቭ”፣ ከአለማየሁ ሂርጶ ጋር “ኢቫንጋዲ” እና በ1999 ዓ.ም ለብቻው

የሰራውን “ሳታመሃኝ ብላኝ” የተሰኙ የሙዚቃ አልበሞችን ለአድናቂዎቹ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

Read 1394 times