Print this page
Tuesday, 01 January 2019 00:00

ቃለ ምልልስ “በመጀመሪያው ቀን የዘፈንኩት መብራት አስጠፍቼ ነው”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

 ከዋሽንት በስተቀር አብዛኛውን የባህላዊና ዘመናዊ ሙዚቃ አሳምሮ ይጫወታል፡፡ ዋናው ሙያው ግን ድምፃዊነት ነው፡ ፡ በጎንደር በሚሰራባቸው

የባህል ምሽት ቤቶች የአንጋፋ ድምጻውያንን ሥራዎች በማቀንቀን ይታወቃል፡፡ በድምፁ ሲዘፍን አይተውና ተደንቀው ሳይጨርሱ ኦርጋን ላይ ቁጭ ብሎ

ሲያሳልጠው ይመለከታሉ፡፡ ኦርጋኑን ሲጨርስ የመሰንቆውን አሊያም የክራሩን ክር ሲቃኝ መመልከት ያስደንቃል፡፡ የዛሬው
እንግዳችን ሁለገቡ የሙዚቃ ባለሙያ ሔኖክ አበባው፤ደብረታቦር ነው ተወልዶ ያደገው፡፡ የሙዚቃ አጀማመሩ ፈገግታን ያጭራል፡፡ በቅርቡ የለቀቀው

“ተነስ” የተሰኘ ነጠላ ዜማው ከፍተኛ ተቀባይነት እንዳገኘለት የሙዚቃ አድናቂዎቹ ይመሰክራሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ለሥራ
ጎንደር በተጓዘችበት ወቅት አርቲስት ሔኖክ አበባውን አግኝታ በሙዚቃ ህይወቱ ዙሪያ አነጋግራዋለች፡፡


    ሙዚቃ የጀመርክበት አጋጣሚ ትንሽ ፈገግ ያሰኛል። እስኪ አጫውተኝ ---
10ኛ ክፍልን እንደጨረስኩ አካባቢ፣እኛ ሰፈር ውስጥ ከሰፈር ልጆች ጋር ቁጭ ብለናል፡፡ እናም የሆነች በግ ጠፍታ ትመጣለች፡፡ ያቺን በግ ባለቤቷ

እንዲያገኛት ይዘናት ወደ ቀበሌ ስንሄድ፣ የቀበሌው ኪነት ቡድን አባላት ሲዘፍኑ አገኘናቸው፡፡ በጓን አስረክበን ልንወጣ ስንል፣ ”እስኪ እንግባ፤ አንተ ዝም

ብለህ ቤት ለቤት ከምታንጐራጉር እንግባ” አሉኝ፡፡ ከዚያ በፊት እኔ ባላውቀውም፣ በውስጤ የነበረ ነገር ነው ማለት ነው፡፡ ለጓደኞቼ እዘፍንላቸው

ነበር፡፡ ከዚያ ወደ አዳራሹ ገብተን፣ ፍላጐታችንን ነገርናቸው፡፡ በመጀመሪያው ቀን የዘፈንኩትም፣ የአዳራሹን መብራት አስጠፍቼ ነው፡፡
ለምንድን ነው መብራቱን ያስጠፋኸው?
አሃ ፈርቼ ነዋ፤ አፍሬ መብራቱን አስጠፋሁት። እዛ ይለማመዱ የነበሩትም እኮ ገና ልጆች ናቸው፡፡ ግን መድረክ ላይ ወጥቶ በሰው ፊት መዝፈን

ያስፈራል። ሌሎች አዳራሹ ውስጥ ቁጭ ይላሉ፡፡ አንድ አንድ ሰው እየወጣ ነው የሚዘፍነው፡፡ ለልምምድ ነበር የሚዘፈነው፤ያንን ፈርቼ ነው መብራቱን

ያስጠፋሁት፡፡
የዚያን ዕለት የማንን ዘፈን እንደዘፈንክ ታስታውሳለህ?
አዎ አስታውሳለሁ፡፡ የጋሽ ጥላሁንን ነበር የዘፈንኩት፡፡ “ሰላምታዬ ይድረስ ናፍቆቴን ያስረዳ/ በትዝታ ጭነት ስንቱ እንደሚጐዳ” (በድምፁ እየዘፈነ)

የሚለውን ነበር የዘፈንኩት፡፡
የጥላሁንን ዘፈን ትወደው ነበር?
አዎ እወደዋለሁ፤አዳምጥም ነበር፡፡ የአስቴር አወቀንም ጭምር እንዴት እንደማዳምጥ ልንገርሽ። ደብረታቦር ቤታችን አውቶቡስ መናኸሪያ አካባቢ ስለሆነ፣

ህዝብ የሚያመላልሱ መኪኖች ሲወጡና ሲገቡ በማይክራፎን ሙዚቃ ይለቁ የለ፡፡ በዛ መልኩ ነበር ሙዚቃ የምሰማው፡፡
ቤታችሁ ውስጥስ ዘፈን አይከፈትም እንዴ?
አይከፈትም ነበር፤ ምክንያቱም እኛ ቤት ቴፕ አልነበረንም፡፡ መናኸሪያ በሚመጡና በሚሄዱ መኪኖች የሚለቀቀውን ሙዚቃ ግን በደንብ አዳምጥና፣ ዜማና

ግጥሙን በደንብ እይዝ ነበር፡፡
ከዚያስ ሙዚቃን እንዴት ህይወትህ አደረግኸው?
እዛ የቀበሌ አዳራሽ መጀመሪያ መብራት እንዳስጠፋሁት ሁሉ፣ በሁለተኛውም ቀን አስጠፍቼ ልዘፍን ስል፣ “አሁን መድፈር አለብህ፤ መብራት ይብራ”

ተባለና እንደምንም ዘፈንኩኝ፡፡ ከዛ በአማተር ደረጃም ቢሆን አሰልጣኞች ስለነበሩ፣ እንዲህ አድርግ ይሄንን አስተካክል አሉኝ፡፡ እኔም አስተያየታቸውን

ተቀብዬ የድምጽ ልምምድ ለማድረግ ጫካ ውስጥ ሄጄ፣ድምፄን እስከ መጨረሻው በማጮህ፣ በማውጣትና በማውረድ ልምምዴን ተያያዝኩት፡፡ በዚህ መልኩ

አይኔን ከገለጥኩ በኋላ የምሽት ክበብ ለመስራት ወደ ባህርዳር ሄድኩኝ፤ በ2001 ዓ.ም ይመስለኛል፡፡ ከዚያም “ጃሎ በል” የሚባል የባህል ምሽት

ቤት መሥራት ጀመርኩኝ። ይገርምሻል፤ እኔ “ጃሎ በል” ስጀምር ፋሲል ደሞዝም ነበር፡፡ ቤቱም የዛን ቀን ነበር የተከፈተው፡፡ እነ ፋሲል የመክፈቻ ስነ

ስርዓቱ ላይ ተጋብዘው ነበር የተገኙት፡፡ ከዚህ ቤት በፊት ግን ለትንሽ ጊዜ ሌላ የምሽት ክበብ፣ በ300 ብር ደሞዝ ሰርቼአለሁ፡፡ በወቅቱ 17 ዓመቴ

ነበር፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁህ በቆብ አስጥል የባህል ምሽት ቤት ነው፡፡ ትዘፍናለህ፣ ከዚያ ኪቦርድ፣ ቀጥሎ ደግሞ ማሲንቆ ከዛ ክራር ስትጫወት አይቼሃለሁ፡፡

ይህን ሁሉ የሙዚቃ መሳሪያ መጫወት እንዴት ቻልክ? ሙዚቃ ት/ቤት ገብተህ ነበር?
እንዳልኩሽ ባህርዳር “ጃሎ በል” መስራት ጀመርኩ፤ በምሽት፡፡ ቀን ቀን ደግሞ ለምን ያለ ስራ እቀመጣለሁ ብዬ “ቢዝራ” የተባለ የፀረ-ኤድስ ክበብ

እሄድ ነበር፡፡ ይህ ክበብ በደንብ የተደራጀና የራሱም የባህል ቡድን የነበረው ነው፡፡ ዘመናዊ ቡድንም ነበረው፡፡ ክራር የሚጫወተው ኪቦርድም

ይጫወታል። ጊታር ተጫዋቹ  ከበሮ ይመታል፡፡ ዋሽንት የሚነፋው ተወዛዋዥም ነው። ማሲንቆ የሚጫወተው ቤዝ ጊታር ይጫወታል፡፡ እነሱን ሳያቸው በቃ

መልመድ አለብኝ አልኩኝ፡፡ ቀደም ሲል ደብረ ታቦር ልምምድ ላይ በአማተርነት ስገባ፣ ከሌላ ቦታ ክራር ተውሼ ነበር። አለማማጅ አልነበረም፤ ዝም ብዬ

ክራሩን እገርፈው ነበር፡፡ አልችልበትም፤ ልክም አልነበርኩም፡፡ ወደ “ቢዝራ” ፀረ ኤድስ ክበብ ስመጣ፣ ልጆቹ በትንሹ ሁለትና ከዚያ በላይ ሙያ

አላቸው፡፡ እነሱን ሳይ እኔም እችላለሁ የሚል መንፈስ በውስጤ አደረና መለማመድ ጀመርኩኝ፡፡ ክራሩን እየቃኙ ይሰጡኛል፤ ቀስ በቀስ እጫወት ጀመር፡፡

በኋላ እራሴም መቃኘት ጀመርኩኝ፡፡ ሌሎች የሙዚቃ መሳሪያዎችን ለመልመድ፣ መጀመሪያ ክራር መልመድ ነገሮችን ያቀላል፤ ቢያንስ ባለ አምስቱን ክር

ክራር ማለት ነው፡፡ እኔ አሁን ከአምስቱም ክር አልፌ ባለ ሰባቱን ነው የምጫወተው፡፡
አሁን ጨጨሆ ነው ያለኸው፡፡ የቆብ አስጥል ቆይታህና ተሞክሮህ ምን ይመስል ነበረ?
ቆብ አስጥል ብዙ ልምድና ተሞክሮን የወሰድኩበት ቤት ነው፡፡ መቼም ከእያንዳንዱ ህይወትሽ ትምህርት እየወሰድሽ ነው የምትሄጂው፡፡ ቆብ አስጥል ሳለሁ፣

ክፍተት በነበረበት ቦታ እየሸፈንኩ እሰራ ነበር፡፡ ለምሳሌ ለአንድ ወር መሰንቆ ሸፍኜ ሰርቻለሁ፡፡ ይሄ ለቤቱም ለእኔም ጠቅሞናል፡፡ ከኪቦርድ ተጫዋቾች

ጋር ሆኜ የተለያዩ የሙዚቃ ቁጥሮችን እንዳውቅና እንድይዝ የረዳኝ የቆብ አስጥል ቆይታዬ ነው፡፡ የምሰራቸው ሙዚቃዎችም በአንድ ዘፋኝ ላይ የተወሰኑ

አይደሉም፤ የብዙ ድምፃዊያንን ስራዎች እጫወታለሁ፡፡
ለምሳሌ የእነ ማንን ትጫወታለህ?
የፀጋዬ እሸቱን፣ የጋሽ ማህሙድን፣ የአረጋኸኝን፣ የጋሽ ጥላሁንን፣ የማዲንጎንና የሌሎችንም በጥሩ ሁኔታ እሰራለሁ፡፡ ይሄን ሁሉ በስፋት እንድሰራና ልምድ

እንዳዳብር ቆብ አስጥል እድል ሰጥቶኛል፡፡ አሁን ጨጨሆ የባህል ምሽት ደግሞ ሌላ የህይወት ልምድ፣ ሌላ ተሞክሮ እያገኘሁ ነው፡፡
በቅርቡ ከ90 ሰው በላይ የተሳተፈበት “ተነስ” የተሰኘ የጎንደር ዘፈንህን ለአድማጭ አቅርበህ ጥሩ ተቀባይነት ማግኘትህን ሰምቻለሁ፡፡ እኔም “ሆፕ

ኢንተርቴይንመንት” ላይ ተመልክቼዋለሁ፡፡ እስኪ ስለዚህ ስራህ ትንሽ አጫውተኝ----
እንዳልሽው ከ90 በላይ ሰው የተሳተፈበት “ተነስ” የተሰኘ ነጠላ ዜማ ሰርቼ፣ ተቀባይነቱ አበረታች ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ይህንን ስራ እውን እንዳደርግ

ሲገፋፋኝና ሲጎተጉተኝ የነበረው፣ ጓደኛዬም ወንድሜም የሆነው፣ የቆብ አስጥል የባህል ምሽት ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ወንደሰን ብዙዓለም ነው። በዚህ

አጋጣሚ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ ይህንን ዘፈን ስሰራው ወደ 97 ያህል ሰው ነበር የተሳተፈው። የተሰራው ሰሜን ፓርክ ላይ ነው፡፡ ብዙ ፈተናዎችን

አልፈናል፡፡ ወቅቱ ክረምት ስለነበር በጉምና በዝናብ ምክንያት ለቀረፃ ሁሉ ተቸግረን ነበር፡፡ ቀረፃው ሁለትና ሶስት ቀናት ፈጅቶብናል፡፡ በቪዲዮው ላይ

97 ሰው ያሳተፍኩት፣ በጥቂት ሰው ሲሰራና በብዙ ሰው ሲሰራ ልዩነት ስላለው ነው፤ የውበትም የድምቀትም። በተለይ የጀግንነቱን ክፍል ልብ ብለሽው

ከሆነ፣ በብዙ ሰው መከወኑ ይበልጥ ከመልዕክቱ ጋር ውበትና ድምቀት ሰጥቶታል፡፡ ሌላው ቀርቶ “ተነስ” የሚለው ፅሁፍ፣ ፊደሉ ራሱ በሰዎች ነው

የተሰራው፡፡ ሰዎች ተደርድረው ነው “ተ”ንም “ነ”ንም “ስ”ንም የሰሩት፡፡ በጣም ጥሩ አድርገን ነው የሰራነው፡፡ ከወጪም አንፃር ልጆች በየሙያቸው

በትብብር ከሰሩልኝ ውጪ 90 ሺህ ብር ወጥቶበታል፡፡ የተባበሩኝና ያለ ክፍያ ሙያቸውን ያበረከቱልኝ ልጆች ባይኖሩ፣ ወጪው ከዚህ በእጅጉ ይጨምር

ነበር፡፡ ግጥምና ዜማውን የድሮ የፖሊስ ኪነት ቡድን የሳክስፎን ተጫዋች የነበረው “ጮማ” የተባለ ባለሙያ ነው የሰራልኝ፡፡ እንደነ ማዲንጎና ፍቅር

አዲስ ያሉ በርካታ ታዋቂ አርቲስቶችን፣ በሳክስፎን ያጀበ ሙዚቀኛ ነው፡፡
ወደፊት ምን አቅደሃል? አልበምስ መቼ እንጠብቅ?
እንግዲህ ወደ አልበም ከመምጣት በፊት በተደጋጋሚ ነጠላ ዜማዎችን በመስራት፣ ከአድማጭና ተመልካች ጋር መገናኘት ያስፈልጋል፡፡ ከዚያ ግብረ መልሱን

ማየት፣ ራስን በግብረ መልሱ መቃኘት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ሂደት ላይ ነኝ፡፡ ከዚህ ቀጥሎ አንድ አራት ነጠላ ዜማዎችን ሰርቼ፣ ከህዝብ ጋር በደንብ

ከተገናኘሁ በኋላ አልበም መስራቴ አይቀርም። ከወዲሁም አንዳንድ ዝግጅቶች አሉኝ፡፡ እንግዲህ ሙዚቃ ህይወቴ ነው፡፡ ሙያውን ማክበር፣ በሙዚቃ በደንብ

መስራትና እስከ መጨረሻው በሙያዬ ማገልገል ነው ህልሜ፡፡
አዲስ በተዋቀረው የፋሲለደስ የኪነት ቡድን ውስጥ አባል ነህ፡፡ የቡድኑ አጠቃላይ እንቅስቃሴ እንዴት ነው?
 ጥሩ እንቅስቃሴ ላይ ነው፡፡ በጥሩ ሁኔታ የተደራጀ ቡድን ነው፡፡ ለእኛም ብዙ ኤክስፖዠር እየሰጠን ነው። ከከተሞች ቀን ጀምሮ ትልልቅ የመድረክ

ስራዎችን እንሰራለን፡፡ በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ በስፋት እንሳተፋለን፡፡ ይሄ ሦስት ጥቅሞች አሉት፡፡ አንደኛ በገቢ እንጠቀማለን፡፡ ሁለተኛ ብዙ በሰራን ቁጥር

የሙያ አቅማችንን እናሳድጋለን፡፡ ሦስተኛ እውቅናንና እይታን እናገኛለን፡፡ አሁን በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ያለነው፡፡ እኔም በዚህ ደስተኛ ነኝ፡፡ በስራዬ ከጎኔ

ሆነው የሚያበረታቱኝንና የሚያግዙኝን በሙሉ በዚህ አጋጣሚ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡  

Read 786 times