Tuesday, 01 January 2019 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(2 votes)

  “ገንዘብህም፣ ደስታህም፣ ነፃነትህም ሃሳብህ ነው!!”
            ሰውየው በየዓመቱ ወደ ቁልቢ እየሄደ የመልዓኩ ገብርኤልን ታቦት ያነግሳል፡፡ “እስከ መቼ በድህነት እንኖራለን? … ምናለ አንድ ቀን የገንዘብ
ዝናብ ብታወርድልን … ላንተ ምን ይሳንሃል?” … እያለ ይለማመናል፡፡” “ፀሎቴን ከሰማኸኝ አንድ ባኮ ሻማ አስገባልሃለሁ” በማለት ከአንድም ሁለቴ

ተስሏል፡፡
“ተዓምር አያልቅም” እንደሚሉት ሆኖ ስለቱ ሰመረለት፡፡ አንድ ሌሊት የሰማይ በር ተበረገደ፡፡ የገንዘብ ዝናም ጣለ፡፡ ሰውየው የሚኖርባት ከተማ በገንዘብ
ባህር ተጥለቀለቀች፡፡ ሁሉም ሰው ሃብታም ሆነ፡፡ ሲፈልጉ፣ ሲመኙና ሲያምራቸው የነበረውን ሁሉ እየተጋፉ መሸመት ጀመሩ፡፡ ዳቦ የፈለገ ለባለ ዳቦው
መቶ ብር እየወረወረ፤ “ቶሎ ስጠኝ፤መልስ አልፈልግም” ሲል- ሌላ ዳቦ ፈላጊ ሁለት መቶ ብር ሰጥቶ፣ ዳቦውን ለመውሰድ ይሽቀዳደማል፡፡ ሁሉም ዕቃ
ላይ እንደዛ ሆነ፡፡ ነጋዴዎቹ ሸቀጦቻቸውን አሟጠው፤ ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው የሚፈልጉትን ለመግዛት ወደ ሌላ ቦታ ሲሮጡ፣ ሌላ ቦታ የሚነግዱትም
እንደነሱ ዕቃቸውን ጨርሰው፣ ሱቃቸውን ዘግተው፣ ለራሳቸው የሚፈልጉትን ለመግዛት ወደነሱ ሲመጡ ይተላለፋሉ። ሁሉም ነገር በጥቂት ሰዓታት ተጠናቀቀ፡፡
ከተማው በጁ የገባውን እንዳይነጠቅ፤ በሩን ዘግቶ ተቀመጠ፡፡ አንዱ የሌላውን በር እያንኳኳ “አንድ ዳቦ ወይም ግማሽ ኪሎ ስኳር ካለህ በሚሊዮን ብር
ሽጥልኝ” ሲለው “አንተ ካለህ በአስር ሚሊዮን ብር እገዛሃለሁ” ማለት ተጀመረ፡፡ ከተማዋ ትንፋሿን ዋጠች፡፡ ሰውየው አዘነ። እግዜርን ለማግኘት
ተቻኮለ፡፡
***
 ወዳጄ፡- ገንዘብ ለኑሯችን ያስፈልገናል፡፡ አንዳንድ ሰዎች፤ ገንዘብ ስድስተኛው የስሜት ህዋሳችን ሆኗል ይላሉ፡፡ ከሌለህ የለህም ተብሎ ተዘፍኗል፡፡ አንድ
ብር ቢጎድልብህ በታክሲ መሄድ፣ አውቶብስ መሳፈር፣ መድኀኒት መግዛት፣ ሆቴል መመገብ አትችልም፡፡ አንድ ብር ያለ ምክንያት ቢጠፋብህ ወይም
ከደሞዝህ ቢቆረጥ ትናደዳለህ፡፡ ጥያቄው፡- “ዘርፈህና አታለህ፣ በዝምድናና በፖለቲካ ትስስር የሰበሰብከው ገንዘብ ምቾት ይሰጥሃል ወይ?” የሚል ነው፡፡
እኔ እንደሚገባኝ፤ ያለ ውስጣዊ ደስታ መኖር ሰላም ይነሳል፡፡ ሰው የመሆን ፀጋን ያሳንሳል፡፡ ‹መኖር› ማለት እንደ እንስሳ መብላት፣ መጠጣትና መባዛት
አይደለም፡፡ “ሰውን በአምሳላችን ፈጠርን” ሲባል መልዕክቱ- ንፁህ የሚያስብ፣ የሚያስተውል፣ የማይዳላ፣ ርህሩህና ምክንያታዊ ፍጡርን አፈራሁ ማለት
ይመስለኛል፡፡
ሊቃውንት፡- “ሰው በኪሱ እያሰበ ሲኖር፣ ጭንቅላቱ እየጠበበ፣ እንደ ቪኖ ፋሽኮ ወይም እንደ ውስኪ ጠርሙስ ሆድና አንገት ብቻ ይሆናል” ይላሉ፡፡
… Non ce testate!!
ወዳጄ፡- ስለ ገንዘብ ያልተባለ፣ ያልተፃፈ ምን አለ? ገንዘብ አጋርን እንጂ ፍቅርን፣ መድኀኒትን እንጂ ጤናን፣ መኖሪያን እንጂ ቤትን (House
but not home)፣ መፃሕፍትን እንጂ ዕውቀትን ወዘተ፣ ወዘተ እንደማይገዛ አንብበናል፡፡ ታላቋ ፈላስፋ አያን ራንድም፡- “ገንዘብ ወደ ፈልግህበት
ሊያደርስህ ይችላል፤ አንተን ተክቶ ግን መኪናህን አይነዳልህም፡፡ ፍላጎትህን ያሟላል፣ ፍላጎት (Desire) ግን አይሆንልህም፡፡ ወደ ሱቅ ያስገባሃል፣
ምርጫ ካላወቅህ (test ከሌለህ) ምን ዋጋ አለው፡፡ ገንዘብ ቂሎችን ብልህ፣ ፈሪውን ደፋር፣ ደንቆሮን ሊቅ አያደርገውም፡፡ በኋላ ቀር ማህበረሰብ
ውስጥ ካልሆነ ሰዎች እንዳያስቡ፣ እንዳይጠይቁ፣ እንዳይመራመሩ የማድረግ ዐቅም የለውም፡፡ በገንዘብ የለውጥ ህግ አይሻርም፡፡ የዕቃ ካልሆነ የሃሳብ ሚዛን
በገንዘብ ከፍና ዝቅ አይልም፡፡ ሰዎችን በገንዘብ በመደለል ለክፉ ተግባር ማሰማራት ጊዜያዊ ወዳጅ፣ ዘላቂ ጠላት ማፍራት ነው፡፡” በማለት ፅፋለች፡፡
ወዳጄ፡- መልካምነት በጥቅም ከተለወጠ መጀመሪያም በቦታው አልነበረም፡፡ ፖል ኤርድማን … “ቢሊዬን ዶላርስ ኪሊንግ” በሚለው መጽሐፉ …. “A
good man out of the good treasure of his heart bringth forth that which is
good; and an evil man out of the evil treasure of his heart bringth forth
that which is evil” ይልሃል፡፡
የገንዘብ ዋጋ አንተ በምትገኝበት በዚች ቅፅበት ይወሰናል ይላሉ፤ አዋቂዎች፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከመግዛት ዓቅሙ የበለጠ ወረቀት የመሆኑ ጥቅም ሊበልጥ
ይችላል (Monitary value v use value)፡፡ ምንም በሌለበት በረዷማ ቦታ ወይም በረሃ ውስጥ መኪናህ ቢበላሽ፣ በቦርሳህ
ያጨከውን ገንዘብ አንድደህ ልትሞቀው ወይም አውሬ ለመከላከል እሳት ማቀጣጠያ ልታደርገው ትገደዳለህ፡፡
ወዳጄ፡- የገንዘብ ‹ውል› ሲነሳ፤ የቅዱስ መጽሐፉን ይሁዳና ሰላሳውን ዲናር፣ የሼክስፒር የቬኑሱ ነጋዴን ሻርሎክን እናስታውሳለን፡፡ ይሄ የሚያሳየው፤ገንዘብ
ምን ያህል ከሰው ልጅ አእምሮ ጋር እንደተቆራኘና በትክክል የማሰብና ያለማሰብ ፈተና መሆኑን ነው። በጥንታዊ ትውፊት የምናውቀው፡፡ “የነካኸው ሁሉ
ወርቅ ይሁንልህ” ተብሎ የተባረከለት ሚዳስ (The touch of Midas) ወይም ከዚሁ ጋር የሚመሳሰለው በቶልስቶይ ተረቶች ውስጥ
የሚነበበው … መሬት ሲያካልል፣ አልጠግብ ብሎ ልቡ የፈነዳው ሰው ታሪክም የሚነግረን፤ በትክክል ማሰብ ባለመቻላችን ንብረታችን መጥፊያችን ሊሆን
እንደሚችል ነው። “ያባብዬን ቤት፣የማምዬን ቤት ወርቅ ይዝነብበት!” እያልን ሆያ ሆዬ ስንጨፍር፣ እያሰብን ካልሆነ ዝናቡ የሚያስከትለውን አደጋ
አንቋቋመውም፡፡
ወዳጄ፡- እንደ ጃፓን ዓይነት ሥልጣኔ ባለበት አገር፤ ገንዘብ ‹ገንዘብ› የሚባለው ወደ ቁስነት ተቀይሮ ለዜጎች ጥቅም ሲውል ነው፡፡ ገንዘብህን ባንክ
ብታስቀምጥ፣ ባንኩ ሳይሆን ወለድ የሚከፍልህ፣ አንተ ነህ ለባንኩ የምትከፍለው፡፡ ያስቀመጥከው ገንዘብ እየጨመረ ሳይሆን በየጊዜው እየቀነሰ ይመጣና
‹ዜሮ› ሊሆን ይችላል፡፡ መልዕክቱ፡- አታስቀምጠው ስራበት ነው። ሥራ ሃሳብ ነው፡፡ ሃሳብ የሚሰራው ጭንቅላት ውስጥ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ከቦርሳህ
የምትመዘው ገንዘብ ሳይሆን ሃሳብ ነው፡፡ ሚጢጢ ካርድ ላይ የተጫነ። ቢወድቅብህ የሚያነሳው የለም፡፡ ለፖሊስም አታመለክትም፡፡ ምናልባት እሷም
ላታስፈልግህ ትችላለች፡፡ ኮምፒውተርህን ወይም የእጅ ስልክህን በመነካካት ሃሳብህ ይፈፀማል፡፡ መቁጠር፣ መሸከም፣ ጊዜ ማባከን፣ ስጋት የለም፡፡
የሚያስፈልግህ ‹ማሰብ› ብቻ ነው፡፡ ገንዘብህም፣ ደስታህም ነፃነትህም ሃሳብህ ነው!!
***
ወደ መጀመሪያው ጨዋታችን ስንመለስ፡- ሰውየው እግዜርን ለማግኘት ተቻኮለ ብለን ነበር ያቋረጥነው፡፡ እንደተገናኙም በእጁ የያዘውን የስለት ሻማ
ለጠባቂው መልዓክ አቀብሎ፣ ወደ እግዜር ዞር አለና …
“ምን አደረግንህ? … ምን በደልንህ?” ሲል ጠየቀ፡፡
“ምንም” በማለት መለሰለት፤ እግዜር፡፡
“ታዲያ ለምን ጨከንክብን?”
“አልጨከንኩም፡፡” አለውና ወደ ሻማው እያመለከተ .. “አሁን አንተ ሻማ አመጣህልን፣ በምንፈልግበት ጊዜና ቦታ እያበራን እንጠቀምበታለን፣ ብርሃን

የምንፈጥረው እኛ ነን፣ አንተ የሰጠኸን ሻማውን ነው”
“እና?”
“እኔም ጭንቅላት ሰጥቻችኋለሁ፣ ገንዘብ አዝንቤላችኋለሁ፣ ማሰብና ባግባቡ መኖር የናንተ ፋንታ ነው፡፡” አለው፡፡ ትስማማለህ----ወዳጄ?
ሠላም!!

Read 639 times