Tuesday, 01 January 2019 00:00

የሁለት ጉዞዎች ማስታወሻ!

Written by  አብይ ተስፋዬ አሳልፍ/አተአ/
Rate this item
(3 votes)


“--በተለይ ፖሊሶችና ሌሎች ቁጥጥር ላይ የሚሰሩ ግለሰቦች፤ ጉቦ ለመቀበል አሰፍስፈው ይጠብቃሉ፡፡ እናም እንዲህ አስብ ነበር … ‹እዚህ አገር ብቻ የተለየ ነገር የለም፡፡ የእኛ የአፍሪካውያን የጋራ እርግማን ሳይሆን አይቀርም፡፡ ዘረፋም ይሁን ጉቦ እኛስ አገር ሞልቶ የለ! ›”
        ክፍል - 2-
ወደ ጉራጌ ዞን ስንጓዝ ….
ፀጥተኛው ዶክተር እንዲህ የሚል አስተያየት ሰጠ … ‹‹…በደርግ ጊዜ በስኮላር ወደ ጀርመን ተልኬ ከመሄዴ በፊት አዋሳ ኮሌጅ ነበርኩ፡፡
ትምህርታችንና የተማሪዎች ዲሲፕሊን እጅግ ጥብቅ ነበር፡፡ ጀርመን ከመሄዴ በፊት አንድ አመት ነበር የተማርኩት፡፡ ኬሚስትሪ ነበር የምማረው፡፡ እናም
በዓመቱ መጨረሻ ከኮሌጁ አንደኛ ወጣሁ፡፡ እያንዳንዱን ቲዎሪ ሸምድጄ ልያዘው እንጂ ትምህርቱ ውስጥ ግን አንዲትም የተግባር ትምህርት ወይም
የላብራቶሪ ሙከራ አልነበረም፡፡ ሁሉም ነገር ሽምደዳ ነበር፡፡ ስንጠየቅ እንኳ ከጠፋብን ለመጀመር … ‹እስኪ ጫፉን አስይዘኝ…› ነበር የምንባባለው፡፡
ጀርመን ስገባ ግን ሁሉም ተቃራኒ ሆኖ ጠበቀኝ፡፡
በዚያን ወቅት አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የሚማር አንድ ጓደኛዬ ሲያወራኝ፣ ያስተማረው ታዋቂው ጌታቸው ቦሎዲያ ነበር፡፡ መቼም ስለርሱ ብዙ ሰምታችሁ ይሆናል፡፡ አንድ ቀን ተማሪዎች ለገና ፈተና ተሰብስበው ሲሄዱ ፈተናው እንደተለመደው የፅሁፍ መሆኑ ቀርቶ የቃል ነው ይባላሉ፡፡ ከዚያ ሁሉንም ተማሪዎች በየተራ እያስገባ፣ ይህንን አብራራ፣ ያንን ተናገር፣ ዘርዝር፣ እያለ ያፋጥጣቸዋል፡፡ አብዛኛው ተማሪ ሸምዳጅ ነው፣ የሸመደዳትን ነገር ጫፍ ሲያገኝ በቃሉ ያንበለብላል፡፡
ጓደኛዬ ተራው ደርሶ ገባ፡፡ እንኳን ጥያቄውን ሰውየውን በጣም ይፈሩታል፡፡ እንደተቀመጠ አንድ ሰፋ ያለ ማብራሪያ እንዲሰጠው ጠየቀው፡፡ ጓደኛዬም ትንሽ ካሰላሰለ በኋላ፣ በደንብ ተዘጋጅቶ ስለነበር የደብተሩን አምስት ገፅ ፅሁፍ በቃሉ፣ እስከ ምልክቶቹ አንበለበለለት፡፡ ያው ሸምድዶ እየነገረው እንደሆነ አስተማሪው አውቋል፤ ስለዚህ ጥቂት አሰበና እንዲህ አለው፤
‹‹…እስኪ አሁን ያንበለበልከውን ነገር ምን ያህል እንደተረዳኸው አብራራልኝ፡፡ ማለቴ እንዴት፣ ለምን፣ መቼ፣ የት፣…›› እያለ ያፋጥጠዋል፡፡ እጅግ ደንግጦ ሰውነቱ ይርድ ጀመር፡፡ አይኑ ተጎልጉሎ ፀጥ አለ። ነገርየው አልገባውም፣ በግልፅ አልተረዳውም ነበር። ማስረዳት አልቻለም፣ ምክንያቱም በወቅቱ ሁሉም ተማሪ ያደርግ የነበረው አብዛኛውን ትምህርት መረዳት ሳይሆን መሸምደድ ነበር፡፡ እናም ያን ቀን ያጋጠመውን ሲነግረኝ እንዲህ ነበር ያለኝ፤ ‹‹…በህይወቴ እንደዛን ዕለት ደንግጬም ተርበትብቼም አላውቅም፡፡ ነፍስ ካወቅሁ ጀምሮ ለመጀመሪያ ግዜ በውስጥ ሱሪዬ ላይ እርጥበት ተሰማኝ፡፡ ስወጣ
ኮቴን እንደ ሽርጥ አድርጌ ሄድኩ፡፡ ከዩኒቨርሲቲው እስክመረቅ ድረስ ጌታቸው ቦሎዲያን ሳይ ሽንቴ ይመጣብኝ ነበር፡፡ ከተመረቅሁ በኋላ እንኳ በዚያ ዩኒቨርሲቲ አጥር አጠገብ አልሄድም። አራት ኪሎ አልደርስም፡፡ ትምህርቱም ፖለቲካውም አይመቸኝም!›› ሁኔታው ለእኔ በአዕምሮዬ ሰሌዳ ቁልጭ ብሎ ይታየኝ ነበር፡፡ እናም የትምህርት ፖሊሲውንና የተማሪውን ድክመት እያነሳን መንጫጫታችን የአሁን ብቻ ሳይሆን መሰረታዊ ችግራችንም ነበር ብዬ እገምታለሁ፡፡ጉዞውን ቀጥለናል፤ ወደ ፊት በፍጥነት ስንገሰግስ፣ በድንገት ከመንገዱ መሃል ላይ የተኮለኮሉ ድንጋዮች፣ በሩቁ መንገዱን እንደዘጉት ተመለከትን፡፡ ሾፌሩ
የመኪናውን ፍጥነት እየቀነሰ ዙሪያውን በጥንቃቄ ሲቃኝ ፣ ሁላችንም በስጋት ተቁለጨለጭን፡፡ ወዲያው ከየጥሻዎቹ መሃል እየተግተለተሉ ተሰልፈው ወጡ፡፡
***
ፕሪቶሪያ!
ከሁለት ሚሊዮን አይልቁም የሚባሉ ነዋሪ ዜጎች የሰፈሩባት ንፁህ ከተማ ናት ፕሪቶሪያ፡፡ ከሶስቱ የመንግስት መቀመጫ ዋና ከተሞች አንዷ፡፡ ከኬፕታውን (የፓርላማው ከተማ) እና ብሉምፎንቴን (የከፍተኛው ፍርድ ቤት መቀመጫ) ለጥቆ ፡፡ ከግማሽ በላይ ጥቁር ነዋሪዎች እንደሚገኙ ቢታወቅም ብዙ ነጮች ይታያሉ፡፡ የትምህርትና የምርምር ከተማ ነች ይሏታል (ፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ፣ እኛ አገር የምናውቀውን ዩኒሳንና ቪስታን የመሳሰሉ ዩኒቨርሲቲዎቿን ያስታውሷል)፡፡ ዘምባባ ባህርዳርን እንደሚያስታውሰን፣ በጃካራንዳ ዛፎቿ ትታወቃለች፡፡  
በቀድሞው ሾውማን ጎዳና፣ አርኬዲያ ጎጥ ካረፍኩባት ሆቴል 224 (የሆቴሉ የመኝታ ክፍሎች ብዛት 224 ስለሆነ ይመስለኛል!) በማለዳ ስነቃና ሰዓቴን ስመለከት፣ ከሌሊቱ 12፡00 ይላል፣ ኤሲውን ስላላበራሁ በላብ ተዘፍቄያለሁ፡፡ ክፍሉ በሙቀት ታፍኗል፡፡ ወደ መስኮቱ ተጠግቼ ባስተውል ወለል ብሎ ነግቶ ፀሃይ ወጥታለች፡፡ ግራ እንደገባኝ እየተጨናበስኩ ጥቂት ተንጎራደድኩና ልዩነቱን ለማስላት ሞከርኩ፡፡ ተገለጠልኝ፡፡ ሰዓቴ በአገሬ አቆጣጠር እየሰራ ሲሆን የነሱ ሰዓት ግን በአንድ ሰዓት ወደ ኋላ ይቀራል፡፡ ስለዚህ እዚህ ከማለዳው 11፡00 ሰዓት ነው ማለት ነው፡፡ ቢሆንም እንዲህ ወለል
ብሎ መንጋቱ እያስገረመኝ ገላዬን ተለቃልቄ ተመልሼ ተጋደምኩ፡፡ (እዚያ በነበርኩባቸው ቀናት ሁሉ የሻወር ውሃ የሚጠፋ እየመሰለኝ፣ በየሰዓቱ ቼክ
አደርግ እንደነበር ሳልነግራችሁ አላልፍም፡፡)
ሲነጋ፣ ቁርስ ከአልጋው ጋር ስለተከፈለበት ወደ ምግብ አዳራሹ ስገባ፣ አብረን የተጓዝናቸው ጓዶች የተለያዩ ጠረጴዛዎችን ሞልተው በፀጥታ ይመገባሉ፡፡ ወደ ተደረደሩት የቁርስ ብፌዎች ተጉዤ መቁለጭለጭ ጀመርኩ፤ አንድም የማውቀው የምግብ አይነት አላገኘሁም፡፡ የተቆራረጠ ዳቦ ከማር ጋር አንስቼ፣ ከአንድ ብርጭቆ ጭማቂ ጋር መመገብ ጀመርኩ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በተለያዩ ጠረጴዛዎች ላይ የተቀመጡትን የአገሪቱን ህዝቦች ለማየት ቻልኩ፡፡ ጥቁሮች፣ ነጮች፣ ህንዶች፣ ክልሶች … ሁሉም አመጋገባቸው የሚገርም ሆነብኝ፡፡ ለእኔ እስከ እራት ብዬ የማስበውን መጠን በየሰሃናቸው ደርድረው ይቀጠቅጣሉ፡፡ አይ አመጋገብ! አይ ፍላጎት! … አይ ሰውነት፡፡ በአብዛኛው ግዙፋን ናቸው፡፡
ከአገሬ ሰምቼው የሄድኩት በተራመድኩ ቁጥር እንድጠነቀቅ ስለነበር መጀመሪያ ከሆቴሉ ግቢ ለመውጣት ፍርሃት ወሮኝ ነበር፡፡ አጥሮች፣ መንገዶችና በሮች ሁሉ በካሜራ ውስጥ ናቸውና ይጨንቃል፡፡ ቀስ በቀስ ተበረታትቼ ከተማውን ማየት ስጀምር እጅግ ውብ ነበር፡፡ መንገዶቹና ብዙዎቹ መንደሮች ፅዱ ናቸው፡፡ ግንባታዎቹና ህንፃዎቹ ከመስተዋት ድርድር የተለዩ፣ አብዛኞቹ በጡብ የተሰሩ ቆንጆዎች፡፡ (በፊልም እንደማያቸው የአውሮፓ ከተሞች ይመስላሉ!) የመንገድ አጠቃቀማቸው ከእኛ በተቃራኒ ስለነበር ግራ ተጋብቼ ነበር፡፡ እንደለመድኩት የግራ መንገዴን ተከትዬ፣ ሰከም ሰከም ስል መኪኖቹ ድንገት ከኋላዬ እየመጡ ያስደነግጡኛል (ቀኝ መሪዎች መሆናቸውን ልብ ይሏል!)፡፡
የሚነዷቸው መኪኖች እጅግ ዘመናዊ ሲሆኑ አብዛኞቹ እኛ አገር አንደ ብርቅ የምናያቸው ናቸው፡፡ እዚህ እንደ ጉድ የፈሰሱት አሮጌና ሳልባጅ መኪኖች፤ እዚያ ለላንቲካ አይታዩም፡፡ ከተማችንን ያስጨነቀችው ቪትዝማ እዚያ ጨርሶ የለችም፡፡ ፖርሽ፣ ፌራሪ፣ ኦዲ፣ ማርቸዲስ … የመሳሰሉ ቅንጡ መኪኖች ይንሸረሸራሉ። መንገዶቹ ላይ ብዙም እግረኞች ስለማይታዩ መኪኖች እጅግ ይፈጥናሉ፡፡ ጥቂት የጎዳና ተዳዳሪዎች በየፓርኩ (ነጮችም ጥቁሮችም)ይታያሉ፡፡ አንድ ትራፊክ መብራት ላይ ደግሞ ‹መስራት ስለምችል ስራ ቅጠሩኝ፣ መለመን ያሳፍራል!› የሚል የካርቶን ላይ ፅሁፍ የለጠፈ ለማኝና
ልጆች ይዘው በመንገዱ ጠርዝ የተቀመጡ እናቶችም አጋጥመውኛል፡፡ የመኪና አነዳዳቸው ግን የውድድር አነዳድ ይመስላል፣ ፍጥነትና የሞተር ድምጽ ሲያስደነብረኝ ከረምኩ፡፡ ለከተሞች የደም ስራቸው መንገድ መሆኑን የተገነዘብኩት በዚያ ያለውን የመንገድ መሰረተ ልማትና የመኪና ብዛት ሳይ ነበር፡፡
ምንም አይነት በትራፊክ የመቆም ችግር የለም፡፡ቤተሰብ ለመጠየቅ ስልክ ስላልነበረኝ ለመደወል አልቻልኩም፡፡ ጓደኛዬ ስልኩን ይዞ ስለነበረ ወጣ ብለን ሲም ካርድ አገኘን፡፡ ብዙ የስልክ አገልግሎት ሰጪ
ካምፓኒዎች ስላሉ ሲም ካርዱን በነፃ ተቀብሎ መደወል ይቻላል፡፡ የአየር ሰዓት ለመሙላት ቫውቸሮችን እንደ ኤ.ቲ.ኤም በሆቴላችን ከቆመው ማሽን ገንዘቡን እየሰጠን የምንፈልገውን የካርድ መጠን በመጫን መግዛት ነበር፡፡ መጀመሪያ አካባቢ በትክክል ለመግዛት ተቸገርን፡፡ ችግራችን በትክክል አንብቦ ከመስራት ላይ ነበር፡፡ ማሽኑን ስናዘው የአገልግሎት ሰጪውን ካምፓኒ ካርድ መርጠን መግዛት ሲገባን፣ እኛ እናዝ የነበረው የገንዘብ መጠኑን ብቻ ነበርና የምንገዛው የሌላ ካምፓኒ የአየር ሰዓት መሆኑን ያወቅነው ከስህተቶችና ከኪሳራዎች በመማር ነበር፡፡ የመጠየቅና አላውቀውም አሳዩኝ የማለት መሰረታዊ ችግር
አለ፡፡
ትልልቅ ሞሎችን አየሁና ተገረምኩ! (አገሬ ያሉትን ሞሎች - (የገበያ አዳራሾች!) በልቤ አሰብኩ፡፡) ተረከዜ ወደ ውስጥ የሰመጠ እስኪመስለኝ ድረስ በአተርቤሪ ጎዳና የሚገኘውን ሜንሊንና አካባቢዬ ያለውን ሰኒ ፖርክ አዳራሾችን ዞርኩ፡፡ በተለይ ሜይሊንን ስዞርና ስቃኝ ብውልም አልጨረስኩትም፡፡ ከደቡብ አፍሪካ ሞሎችም ትልቁ እርሱ ይመስለኛል፡፡ በ177ሺ ሜትር ስኩየር ቦታ ላይ የተዘረጋ የገበያ ህንጻ፣ 500 ያህል የገበያ ሱቆችና አዳራሾች፣
16 የፓርኪን መግቢያና 12 መውጫዎች፣ 8250 የፓርኪንግ ቦታዎች .. ወዘተ የያዘ ቦታ እንዴት ሊያልቅ ይችላል፡፡ በዚያም ላይ ገባ እያሉ መቃኘትና ዋጋ ማየት አለ፣ በተጨማሪ ደግሞ አንዳንዶቹን ሱቆች ጎብኝቶና አይቶ ለመጨረስ በራሱ ሰዓት አይበቃም፡፡ ከጓዶች ጋር በዚህ ሰዓት ጨርሰን እዚህ ቦታ እንገናኝ ተባብለን ሞሉ ውስጥ ከተለያየን በኋላ አንድም ቀን በሰዓቱ የተመለሰ ሰው የለም፡፡ ብዙዎቻችን የቀጠሮውን ቦታ መልሶ ማግኘት በራሱ አልቻልንም ነበር፡፡
እቃዎች በገፍና በተመጣጣኝ ዋጋ ከእነዚህ ማዕከሎች ማግኘት ይቻላል፡፡ አብዛኞቹ ግብይቶች በኤሌክትሮኒክ ካርድ የሚፈፀሙ ሲሆኑ የወረቀት ገንዘብ የሚይዘው እንደኔ አይነቱ እንግዳ መሆን አለበት፡፡ የያዝኩትን የአሜሪካ ዶላር ወደ አገሬው ራንድ ለመቀየር ወደ ባንኮች ጎራ ብልም ግማሾቹ በዚህኛው ባንክ እንገዛም ሲሉኝ፣ ግማሾቹ ወደ ሌላኛው ባንክ ይጠቁሙኛል፡፡ እንደ አገሬ ባንኮች ለዶላር የሚንሰፈሰፉ ሆነው አላገኘኋቸውም፡፡ እያንዳንዱ ባንክ የተለያየ የመግዢያ ዋጋ ያለው ሲሆን ዶላሩን ሲገዛኝም የራሱን ኮሚሽን ያስከፍለኛል፡፡ በጥቅሉ ዝርዝር ማግኘት ከብዶኝ ነበር፡፡ ዶላሬን ተሸክሜ ምንም
መግዛት ሳልችል ብዙ ተንከራትቼአለሁ፡፡  
ለመጠየቅም ትፈራለህ ፣ ደፍረህ ፍለጋ ለመዞርም አትችልም፡፡ በመጨረሻም እንደምንም ከአንዱ ባንክ በርካሽ ጥቂት ራንዶችን ገዝቼ መገበያየት ቻልኩ።
ሲርበኝ ማክዶናልድ ወይም ኬ.ኤፍ.ሲ ጎራ እያልኩ በርገርና የዶሮ ስጋ እገነጥላለሁ እንጂ ሌላ ምግብ መመገብ አልቻልኩም፡፡ አላውቀውማ፡፡ (የዝርዝሩን ነገር በኋላ ከሆቴሌ አካባቢ አንዱ ጓደኛዬ በጥቁር ገበያ በጥሩ ዋጋ የሚገዛ አንድ ጠረንገሎ ባለ ፀጉር ቤት አገኘና እዚያ መሸጥ ቻልኩ፣ መቼም ሁሌም የሚነጥቀኝ እየመሰለኝ እስከ መጨረሻው እንደበረገግሁ ነበር፡፡)
ደግሞ በማግስቱ ብዙ ኢትዮጵያውያን በብዛት ወደሚገኙበት ማራባስታድ (አስያቲክ ባዛር) ገባሁ። ከቀድሞው ማራባ መንደር አጠገብ ይገኛል። የማራባ መንደር መስራችና መሪ ቺፍ ማራባ ይባሉ ነበር አሉ። ማራባስታድ በአፍሪካንስ ማራባ ከተማ ማለት ነው። የእኛ ልጆች መርካቶ ይሉታል! እዚያ
እንድንሔድ የጠቆመን የሆቴሉ ሸትል ሾፌር ነበር። እንደኛው መርካቶ ሱቆች ተደርድረዋል፣ ጥሩም መጥፎውም የሞላበት የገበያ ስፍራ ነበር፡፡ የሱቅ ባለቤቶች፣ እንደ መርካቶ በየበረንዳው ላይ ደርድረው የሚሸጡ እንዲሁም እዚያም እዚያም የሚሯሯጡ ብዙ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ ስንተላለፍ በመልክ ስለምንተዋወቅ፣ ሰላም ሰላም መባባሉ አልቀረም፡፡  
ከጓደኛዬ ጋር ወደ አንዱ ሱቅ ጎራ ብለን ካልሲዎችንና ከረባቶችን መምረጥ ስንጀምር ገንዘብ ተቀባዩን (ባለቤትም ነው) ኢትዮጵያዊ ሆኖ አገኘነው። ቀይና ሰልካካው አሊ፤ አዲስ አበባ ኳስ ሜዳ አካባቢ ያደገ ሲሆን እዚህ ከመጣ አስር አመት እንዳለፈው አጫወተኝ፡፡ (ካልዘነጋሁ!) መድንን ጨምሮ
በፕሪሚየር ሊግ እንደተጫወተ አስረዳኝ፡፡ ሆኖም ጉልበቱ ላይ በደረሰበት ጉዳት ምክንያት ከጨዋታው ሲወጣ ምንም ጥሪት አልነበረውም፡፡ ሰፈር ውስጥ ህመሙን ችሎ ለወራት በመቀመጥ ካሳለፈ በኋላ ወደዚህ የሚሰደድበትን አማራጭ ሲያገኝ አይኑን አላሸም፣ አንገቱንም ቀለስ አላደረገም፡፡ እኛን በማግኘቱ የተነሳ በጣም ስለተደሰተ የመረጥናቸውን እቃዎች (ከ300 ራንድ በላይ የሚያወጡ ናቸው) በነፃ እንድንወስድ ፈቀደ፡፡ ካልከፈልን ብለን ስንከራከር፣ አሊ በፈገግታ እያስተዋለን እንዲህ አለ፤ ‹‹ወንድሞቼ … ገንዘብ ይዘን ስንከራክር የአገሬው ወጣቶች ካዩን ጥሩ አይደለም፡፡ ብዙ ጊዜ ገንዘብ
ስለማያገኙ እኛ ያለን ይመስላቸዋል። እናም ለሌላ ነገር ራሳችንን እንጋብዛለን፡፡ አሁን ዝም ብላችሁ በሰላም ሂዱልኝ፡፡ ኢትዮጵያንም፣ ሸገርንም ሰላም በሉልኝ…›› እናም ስጦታውን ተቀብለንና አመስግነን ወጣን፡፡
በየቦታው የምናገኛቸው ያገራችን ልጆች በሙሉ እንድንጠነቀቅና የአገራችንንም ልጆች ቢሆን እንዳናምን የሚመክሩን ቢሆንም ከተማዋን ሰላማዊ ሆና ነበር ያገኘኋት፡፡ እንዲያውም አንዱ የዚህ ሰፈር (የማራባስታድ) ነጋዴ እንዲህ ነበር ያለን፤ ‹‹12 ሰዓት ካለፈ በኋላ እኛ ራሱ እዚህ አካባቢ አንገኝም፡፡
ሱቆቻችንን ዘጋግተን በጊዜ እንሔዳለን፤ አለበለዚያ በግሩፕ መጥተው የሰራናትን ይነጥቁናል፡፡››
እኛም እንደ እንግድነታችን በጊዜ ወደ መኖሪያችን መግባት ለምደናል፡፡ ሲመሻሽ ከሻወር በኋላ ሆቴላችን ከሚገኘው ባር ብቅ እልና፤ ካስቴል ድራፍቴን እየጠጣሁ አመሻለሁ፡፡ እዚህም የአገሬን ሰዎች ማግኘቴ አልቀረም፣ ክብሮም ባንኮኒ ላይ ተቀምጦ ጥቂት ዝም ዝም ከተባባልን በኋላ ቀጥታ መጥቶ ተዋወቀኝ፡፡ ደቡብ አፍሪካ ከገባ 15 አመት አልፎታል፡፡ ህክምና ውስጥ ነው የምሰራው ያለኝ ቢሆንም ደላላ መሆኑን ከቀናት በኋላ ተረድቻለሁ፡፡ ጥቂት አብረን ከጠጣን በኋላ ሴቶች ከፈለግሁ ሊያመጣልኝ እንደሚችል ነገረኝ፡፡ ‹‹…እዚህ እንደኛ አገር እንዳይመስልህ…የተመቸህን ማግኘት ትችላለህ፡፡
ትጋብዛለህ፣ ትደሰታለህ፡፡ የተሰረቁ ኦሪጅናልና እርካሽ ሞባይሎችንና ላፕቶፖችንም ከህንዶችና ናይጀሪያውያን አካባቢ አመጣልሃለው፣›› አለኝ ዘና ብሎ፡፡
በማግስቱ ጀምሮ ፈራሁትና ራቅ ማለት ጀመርኩ፡፡
አንድ ምሽት ባልኮኒ ተደግፌ ስቀመቅም፣ ለስለስ ያለው ሙዚቃ አስደነገጠኝ፡፡ በቀስታ የተከፈተው የአገሬ ዘፈን ነበር፡፡ ብዙ ጥቁሮችና ነጮች ያሉ ቢሆንም ዘፈኑን ልብ ያሉት አይመስልም፣ ቢራቸውን እየተጎነጩ ግማሾቹ በየመለኪያ የቀረበላቸውን ተኪላ በትንፋሽ ይጨልጡና ይጯጯሃሉ፡፡ ኤፍሬም ታምሩ በቴፑ እያዜመ ነበር፡፡ ደንግጬ ባሬስታውን ሳስተውለው፣ በደበዘዘው መብራት ውስጥ ነጭ አይኑና ጥርሱን እንደ ባትሪ እያብለጨለጨ እንዲህ አለኝ፤ ‹‹ እዚህ የሚመጣ አበሻ ደንበኛ አለኝ … ከሱ የወሰድኩት ነው፡፡ ቴዲ አፍሮንም አውቃለሁ፡፡ … ቆሎ ይዘህ አልመጣህም ወይ! … በጣም
እወዳለሁ!›› ከመሳቅ ውጪ አማራጭ አልነበረኝም፡፡
በማግስቱ የአማርኛ ዘፈን እንዲከፍትልኝ ግን ጥቂት ራንድ ጉቦ መስጠት ነበረብኝ፡፡ ለሙዚቃው ብቻም አልነበረም፤ ቆየት ሲል የማዝዘውን ትዕዛዝ ማዘግየት ጀመረ፡፡ መጀመሪያ አልገባኝምና ደጋግሜ እጠይቀዋለሁ፤ በኋላ ከኋላዬ የመጡትን ሰዎች እያስተናገደ ረሳኝ፡፡ ሳፈጥበት እነሱን ቶሎ ቶሎ የማስተናግደው ሒሳብ ቅድሚያ ስለሰጡኝ ነው ይለኝ ጀመር፡፡ ተገለጠልኝና ጥቂት ራንድ ጣል ሳደርግለት በፈገግታ ያፈጥነው ጀመር፡፡ እግዚኦ! ፈጣሪ፡፡ ለነገሩ ጉዳዩ ብዙ ቦታ የሚታይ ተግባር መሆኑን ተረድቻለሁ። በተለይ ፖሊሶችና ሌሎች ቁጥጥር ላይ የሚሰሩ ግለሰቦች፤ ጉቦ ለመቀበል አሰፍስፈው
ይጠብቃሉ፡፡ እናም እንዲህ አስብ ነበር … ‹እዚህ አገር ብቻ የተለየ ነገር የለም፡፡ የእኛ የአፍሪካውያን የጋራ እርግማን ሳይሆን አይቀርም፡፡ ዘረፋም
ይሁን ጉቦ እኛስ አገር ሞልቶ የለ!›


Read 677 times