Print this page
Sunday, 06 January 2019 00:00

የኢዴፓ አመራሮች ፓርቲውን ለማክሰም ፈተና ገጥሟቸዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

የኢዴፓ አመራርነት ይገባኛል ጉዳይ እልባት ሳያገኝ ፓርቲውን አፍርሶ ከሌሎች ጋር ውህደት ለመፈፀም የሚደረግን እንቅስቃሴ እንደሚቃወሙ የገለፁት እነ አቶ ልደቱ አያሌው፤ የመጨረሻ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
የኢዴፓ የቀድሞ ፕሬዚዳንትና ከፍተኛ አመራር አቶ ልደቱ አያሌው ቀደም ብሎ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጋር በፓርቲው ውስጥ በተፈጠረው ውዝግብ ዙሪያ ውይይት አድርገው እንደነበር ለአዲስ አድማስ ያስረዱት አቶ አዳነ ታደሰ፤ ጠ/ሚኒስትሩም ምርጫ ቦርድ ጉዳዩን አጣርቶ እንዲፈታ እማከራለሁ የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው አስታውሰዋል፡፡
የቀድሞ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ አምባሳደር ሳሚያ ዘካሪያም ጉዳዩን እየመረመሩና እንደነበርና መፍትሄ ያበጃሉ ተብለው እየተጠበቁ ሳለ ከኃላፊነታቸው ተነስተው በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ መተካታቸውን የጠቀሱት አቶ አዳነ፤ አሁን አዲሷ የቦርድ ሰብሳቢ ጉዳዩን ተመልክተው የመጨረሻ እልባት እንዲሰጡ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረውል፡፡ የፓርቲው እጣ ፈንታ ባልለየበት ሁኔታ አፍርሰነው ከሌሎች ጋር እንዋኃዳለን የሚለው ተቀባይነት እንዳያገኝም በደብዳቤያቸው መጠየቃቸውን አስታውቀዋል፡፡ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ከተሸሙ በኋላ ውሳኔ የሚሰጡበት የመጀመሪያ ውዝግብ የኢዴፓ ጉዳይ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
የፓርቲያችን መተዳደሪያ ደንብ ውህደትን ያበረታታል ያሉት አቶ አዳነ፤ ትልቁ ተቃውሟችን ውህደቱን ሳይሆን የፓርቲውን ደንብና መርህ የተከተለ ባለመሆኑ ነው፤ የፓርቲው ህልውና ባልለየበት ሁኔታ ወደ ውህደት ማምራት ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡
በፓርቲው ዕጣ ፈንታ ላይ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን የመጨረሻ መፍትሄም እየተጠባበቁ መሆኑን አቶ አዳነ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡  

Read 1016 times