Print this page
Sunday, 06 January 2019 00:00

የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ውህደት እያመሩ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 ጠ/ሚር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ወደ ውህደትና ህብረት እንዲመጡ ያስተላለፉትን ጥሪ ተከትሎ 12 ያህል ፓርቲዎች በተለያየ አግባብ ለመዋሃድ በሂደት ላይ ናቸው፡፡
የአራት ፓርቲዎች ጥምረት የሆነው “የኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት መድረክ” ሰሞኑን ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤው፣ የግንባሩን አባል ፓርቲዎች አቋም በማጠናከር፣ ጠንካራ ግንባር ሆኖ ለመውጣት የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ነድፎ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩ ተገልጿል፡፡
በውህደት ሂደት ላይ የሚገኙትና የዜግነት ፖለቲካ እንደሚያራምዱ የገለፁት አርበኞች ግንቦት 7፣ ኢዴፓ፣ ሠማያዊ እና የቀደሞ አንድነት አመራሮችና አባላት እስከ መጋቢት መጨረሻ ውህደታቸውን ለማጠናቀቅ ያቀዱ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም ፓርቲው እንዴት ይመስረት፣ የሀገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ምን ይመስላል?... የሚሉ ጉዳዮችን የሚያጠና 50 አባላት ያሉት የኤክስፐርቶች ቡድን ተቋቁሞ ስራ መጀመሩ ታውቋል፡፡
የታለመውን ውህደት እውን ለማድረግ ከተመሠረተ 7 አመት ያስቆጠረው ሰማያዊ ፓርቲ ባለፈው እሁድ ሙሉ ለሙሉ ህልውናውን አፍርሷል፡፡ በተመሳሳይ ኢዴፓ እና አርበኞች ግንቦት 7 ራሳቸውን የማክሰም እርምጃ እንደሚወስዱም ይጠበቃል፡፡
በሌላ የውህደት ስብስብ ውስጥ የተካተቱት 8 ፓርቲዎች በበኩላቸው፤ ተግባራዊ የውህደት እንቅስቃሴ መጀመራቸውን የገለፁ ሲሆን በቅድሚያ ከሁለት ሳምንት በኋላ በሁለት ፓርቲዎች ውህደት ይፈፀማል ተብሏል፡፡ የሁለቱ ፓርቲዎች ማለትም የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ እና የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ህብረት ውህደትን ተከትሎም፣ በውጭ ሀገር ሆነው ሲታገሉ የነበሩ ስድስት ፓርቲዎች ውህደቱን እንደሚቀላቀሉ ተጠቁሟል፡፡
በውጭ ሀገር የነበሩት ስድስት ፓርቲዎች ማለትም በፕ/ር ስዩም ገላዬ የሚመራው የኢትዮጵያ መድህን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (መድህን፣) በአቶ ስለሺ ጥላሁን የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ም/ቤት (ሽግግር)፣ በዶ/ር አክሎግ ቢራራ የሚመራው ብሩህ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብሩህ) በአቶ በርገና ባሣ የሚመራው ቱሳ የኢትዮጵያ ትንሣኤ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት (ቱሳ)፣ በአቶ ነሲቡ ስብሃት የሚመራው ኢትዮጵያችን ህዝባዊ ንቅናቄ (ኢትዮጵያችን)፣ እንዲሁም በአቶ ሽመልስ ኮታንች የሚመራው የደቡብ ኢትዮጵያ አረንጓዴ ኮከቦች ህብረት በአሁን ወቅት ወደ ሀገር ቤት ተመልሰው ለውህደቱ አስፈላጊ የሆኑ ተከታታይ የእርስ በእርስ ውይይቶችን እያካሄዱ ነው ተብሏል፡፡
ይህ ውህድ ፓርቲ ሲመሠረት ህብረ ብሔራዊ እንደሚሆን የተገለፀ ሲሆን ለዜግነትና ለብሔር መብቶች በእኩል እንደሚቆምም ተነግሯል፡፡
ባለፈው እሁድ ታህሳስ 21 ቀን 2011 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤውን ያካሄደው የአራት ፓርቲዎች ስብስብ የሆነው መድረክ በበኩሉ፤ በሊቀመንበርነት ፕ/ር መረራ ጉዲናን መርጦ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጠንካራ ግንባር ለመሆን አቅዷል፡፡ የመድረክ አባል ድርጅቶች አረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ሉአላዊነት፣ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ፣ የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ንቅናቄና የሲዳማ አንድነት ንቅናቄ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
በመድረክ ውስጥ የተሰባሰቡ ፓርቲዎች እስካሁን የጋራ ርዕዮተ አለም የላቸውም፡፡ በፕ/ር በየነ ጴጥሮስ የሚመራው ኢሶዴፓ፤ ሶሻል ዲሞክራሲ ርዕዮት አለም የሚከተል ሲሆን አረና በበኩሉ፤ የሊበራል ርዕዮተ ዓለም ይከተላል፡፡

Read 3018 times