Sunday, 06 January 2019 00:00

ኦፌኮ የሃገር ሽማግሌዎች ግጭቶች እንዲፈቱ ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በመከላከያ ሰራዊትና በተለያዩ ታጣቂ ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ያለው ግጭት በእጅጉ እንዳሳሰበው የገለፀው ኦፌኮ፤ መንግስት ንፁሃንን እየገደሉ ያሉትን እንዲከላከል፤ የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች ደግሞ ለተፈጠሩ ችግሮች መፍትሄዎችን እንዲያመነጩ ጠይቋል፡፡
በመከላከያ ሰራዊትና በታጠቁ ኃይሎች መካከል ያለው ግጭት የንፁሃንን ህይወት እየቀጠረ መሆኑን የጠቆመው ፓርቲው፤ በቅርቡ በምዕራብ ጉጂ ዞን ፊንጫ አካባቢ በተተኮሰ ከባድ መሳሪያ የ13 ሰዎች ህይወት ጠፍቷል ብሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሌሎች ክልሎች ታጣቂ ኃይሎች ወደ ኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች (ወለጋ፣ ቦረና፣ ጉጂና ሐረርጌ ዞኖች) ውስጥ በመግባት ዜጎችን እየገደሉና እያፈናቀሉ መሆኑን ፓርቲው አስታውቋል፡፡
እነዚህ ሁኔታዎች ተባብሰው ህዝብ ለበለጠ አደጋ እንዳይጋለጥ በመንግስትና በኦነግ ግንባር መካከል ያለው ልዩነት በውይይት በአስቸኳይ እንዲፈታ እንዲሁም ሁለቱ አካላት ያደረጉት ስምምነት ለህዝብ ይፋ እንዲደረግና ስምምነቱ ያለመሸራረፍ እንዲተገበር ጠይቋል፡፡
የፌደራል መንግስት ከሌሎች ክልሎች ወደ ኦሮሚያ በመግባት ንፁሃን ዜጎችን እየገደሉ፣ እየዘረፉና እያፈናቀሉ ያሉትን ታጣቂዎች እንዲከላከልም ኦፌኮ በመግለጫው ጠይቋል፡፡
የሃይማት ተቋማት፣ የሃገር ሽማግሌዎች አባገዳዎችና የማህበረሰብ መሪዎች በህዝቡ መሃል በመሰራጨት ህዝብን እያሸበሩ የሚገኙ ኃይሎች ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩና ለተፈጠሩ ችግሮች የመፍትሄና የእርቅ አካል እንዲሆኑ የጠየቀው ኦፌኮ፤ የረድኤት ድርጅቶች ደግሞ ለተፈናቃዮች እርዳታ እንዲያቀርቡ ጥሪ አቅርቧል፡፡
መንግስት ከዚህ በኋላ ህዝብን በኃይል መግዛት እንደማይቻል በመገንዘብ የሃገሪቱን ችግር ብቻውን መፍታት እንደማይችል ተረድቶ ሁሉንም ፓርቲዎች ጨምሮ የሚመለከታቸው ዋና ዋና አካላት ሁሉ የሚሳተፉበት ብሔራዊ የደህንነት መንግስት እንዲቋቋም ኦፌኮ ጠይቋል።

Read 2375 times