Sunday, 06 January 2019 00:00

በአቶ ጌታቸው አሰፋ ጉዳይ የህግና የፖለቲካ ባለሙያዎች ምን ይላሉ?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

    ተጠርጣሪ ወንጀለኛን የደበቁ በህግ መጠየቅ አለባቸው”


    በየትኛውም የኢትዮጵያ መንግስት በከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩትና መቀሌ ተሸሽገዋል የሚባሉት አቶ ጌታቸው አሰፋ ጉዳይ በፓርላማ ጭምር እያነጋገረ ነው፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ሰፊ ማብራሪያ ያቀረቡት ዋና አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ፤ ተጠርጣሪው በትግራይ ክልል እንደሚገኙ ነገር ግን ክልሉ ተጠርጣሪውን አሳልፎ ለመስጠት ፍቃደኛ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሰብአዊ መብት ጥሰት ዋነኛ ተጠርጣሪው አቶ ጌታቸው አሰፋ በትግራይ ክልል ተሸሽገው እንደሚገኙ ፖሊስ በቂ መረጃ እንዳለው የጠቆሙት ጠቅላይ አቃቤ ህጉ፤ በሌሎች ወንጀሎች የተጠረጠሩ የሌላ አካባቢ ተወላጆች ሳይቀሩ በትግራይ ክልል ተሸሽገው እንደሚገኙ ለም/ቤቱ አባላት ገልፀዋል፡፡
የፌደራል መንግስቱ አንድ አካል የሆነው የትግራይ ክልል፣ አንድን የህግ ተጠርጣሪ መደበቁ ከፍተኛ የህገ መንግስትና የህግ ጥሰት ነው ይላሉ - የህግ ባለሙያው አቶ አመሃ መኮንን፡፡
ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን የደበቀ፣ ከለላ የሰጠ፣ ወይም ተጠርጣሪ መሆኑን እያወቀ ወደ ሌላ ቦታ ያሸሸ አካል በግልፅ በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ የወንጀል ተጠያቂነት እንዳለበት ያስረዱት አቶ አመሃ፤ የትኛውም አካል በህግ ፊት እኩል እንደመሆኑ ተጠርጣሪን የሸሸገው የክልሉ አመራር በህግ ተጠያቂ መሆኑ እንደማይቀር ገልፀዋል፡፡
“ግለሰቡ ዝም ብሎ የደረቅ ወንጀል ተጠርጣሪ አይደሉም፤ በከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት ወንጀል የተጠረጠሩ ናቸው” የሚሉት የህግ ባለሙያው፤ በሰው ላይ ስቃይ ወይም “ቶርቸር” የፈፀሙ አካላት በሃገር ደረጃ ብቻ ሳይሆን በአለማቀፍ ደረጃም የህግ ተጠያቂነት አለባቸው ይላሉ፡፡ በሰው ልጅ ላይ ስቃይ (ቶርቸር) የፈፀመ ሰው በየትኛውም የዓለም ሃገራት ከለላ ሊሰጠው እንደማይችል የጠቆሙት ባለሙያው፤ ኢትዮጵያም በሰው ልጅ ላይ የሚደርስን ስቃይ ለመከላከል የወጣውን አለማቀፍ ስምምነት የፈረመች ሃገር እንደመሆኗ በሰብአዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩ ማናቸውንም አካላት ለህግ የማቅረብ ግዴታ አለባት ብለዋል፡፡
በትግራይ ክልልም ሆነ በሌላ ቦታ ያሉ በሰብአዊ መብት ጥሰት ወይም በቶርቸር የሚፈለጉ ግለሰቦችን ለመያዝ የፍ/ቤት ትዕዛዝ በቂ ሊሆን ይገባዋል ይላሉ - የህግ ባለሙያው፡፡
የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤትን ለማቋቋም የወጣው አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀፅ 35 ላይ በሃገሪቱ በየትኛውም ደረጃ የሚገኝ ፍ/ቤት የሰጠውን ትዕዛዝ፣ የክልል ፍ/ቤቶች የማስፈፀም ግዴታ አለባቸው እንደሚል ጠቅሰው፤ ይህ ህግ ህገ መንግስቱን መሰረት አድርጎ የወጣ በስራ ላይ ያለ ህግ እንደመሆኑ የፌደራል ፍ/ቤት የሰጠውን የመያዣ ትዕዛዝ የትግራይ ክልል ፍ/ቤቶችም ሆኑ ሌሎች ተጠርጣሪዎች ያሉባቸው ክልሎች የማስፈፀም ግዴት አለባቸው ሲሉ ያብራራሉ - አቶ አመሃ፡፡
የክልሉ ፍ/ቤቶች ትዕዛዙ እንደደረሳቸው፣ ለክልሉ የህግ አስከባሪ አካል የሚፈለገው ተጠርጣሪ እንዲያዝ ትዕዛዝ መስጠት ግዴታ አለባቸው፤ ይሄን አለማድረግ ህገ መንግስቱን፣ የፍ/ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅን የሚጥስ ተግባር ነው ብለዋል- ባለሙያው፡፡
ተጠርጣሪዎች እንዳይያዙ የሚከላከሉ አካላት ካሉ ራሳቸው በወንጀል ተጠያቂ መሆን አለባቸው የሚሉት አቶ አመሃ፤ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግም በእነዚሁ ከለላ ሰጪ አካላት ላይም የወንጀል ምርመራ እንዲያጣራ ማድረግ ይጠበቅበታል ይላሉ፡፡
ግለሰቦቹ በወንጀል ተጠርጣሪ መሆናቸው ሁሉንም ያግባባ ነው ያሉት የህግ ባለሙያው፤ ሌሎች ካልተያዙ እነሱን አንሰጥም ማለት ግን የህግም የሞራልም አመክንዮ የለውም ብለዋል፡፡ ሌሎች ሊከሰሱ ይገባል የሚባሉ ካሉ ማስረጃና ጥቆማ በማቅረብ የህግ እርምጃ ይወሰድ የሚል ጥያቄ ማቅረብ ነው እንጂ እነ እገሌ ካልታሰሩ… እገሌ እንዲያዝ አልፈቅድም ማለት ከህግ አንፃር በየትኛውም መንገድ የሚያስኬድ አይደለም፤ ግልፅ የህገ መንግስትና ህጎች ጥሰት ነው ሲሉ ይሞግታሉ፡፡
የምስራቅ አፍሪካ ጂኦ ፖለቲክስ ምሁርና የፖለቲካ ተንታኙ ፕ/ር መድህኔ ታደሰ በበኩላቸው፤ ጉዳዩ ከህግ ጋር ሳይሆን ከፖለቲካ ጋር መያያዙ ላይ ነው ችግሩ ያለው ይላሉ፡፡
በለውጡ ሂደት ውስጥ ህውሓትን ጨምሮ ሌሎች የኢህአዴግ ድርጅቶች የተስማሙበት ጉዳይ ሊኖር ይችላል የሚሉት ፕ/ር መድህኔ፤ የዚያ ስምምነት በአንደኛው ወገን መጣስ ለውዝግቡ ምንጭ ነው የሚል እምነት እንዳላቸው ይገልፃሉ፡፡
በኢህአዴግ ደረጃ የተስማሙበት ጉዳይ ግልፅ ቢሆን ብዥታውን ሊያጠራ ይችላል ያሉት ፕ/ር መድህኔ፤ ፌደራሉን ከትግራይ ክልል እያወዛገበ ያለው የህግ የበላይነት ጉዳይ ሳይሆን የፖለቲካ ውላቸው ወይም ስምምነታቸው መከበርና ያለመከበር ነው ብለዋል፡፡
ጉዳዩ የህግ ብቻ ቢሆን ኖሮ ፌደራል መንግስት ተጠርጣሪን ለመያዝ ክልሎችን ጠይቆ መያዝ ይችል ነበር፤ ይሄም ካልሆነ እዚያው በክልሉ ጉዳዩ በህግ እንዲታይ ማድረግ ይቻል ነበር ይላሉ - ምሁሩ፡፡ አሁንም ቢሆን ኢህአዴጎች በለውጡ ሂደት ውስጥ የተስማሙበትን ጉዳይ ለህዝብ በዝርዝር ግልፅ ማድረግ አለባቸው ያን ጊዜ የተዘበራረቀው የፖለቲካ ጉዳይና የህግ የበላይነት ሁኔታ ይስተካከላል፡፡
ጉዳዩ የፖለቲካ ነው በሚለው አልስማማም የሚሉት የፖለቲካ ተንታኙ  አቶ ሙሼ ሰሙ፤ የአቶ ጌታቸውም ሆነ የሌሎች ተጠርጣሪዎች ጉዳይ እንደማንኛውም በህግ ፊት የሚቆም ዜጋ ነው መታየት ያለበት ይላሉ፡፡ “በህግ ፊት ሁሉም ዜጋ እኩል ነው የሚለው የህግ መሰረታዊ ሃሳብ መሰረት፣ ግለሰቡ እንደማንኛውም ዜጋ ለህግ መቅረብ አለባቸው የሚል ፅኑ አቋም ያላቸው አቶ ሙሼ፤ ጉዳዩ የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ እንጂ የፖለቲካ ውሳኔ አይደለም” ብለዋል፡፡
ምናልባት በፌደራል መንግስቱና በክልሉ መካከል በፍትህ ስርአቱ ላይ የእርስ በእርስ አለመተማመንና ጥርጣሬዎች ካሉ፣ በጥርጣሬዎቹ ላይ ውይይት በማድረግ፣ መተማመን ላይ መድረስ አለባቸው ይላሉ አቶ ሙሼ፡፡
የወንጀል ተጠርጣሪን አሳልፎ የመስጠትና ለህግ የማቅረብ ጉዳይ በህግ አግባብ ቢፈታ የሚመረጥ መሆኑን የሚያስረዱት የህግ ባለሙያው አቶ አመሃ፤ በሌላ በኩል ችግሩ ይፈታ ከተባለ በፌደራልና በክልሉ መካከል ውይይት ማድረግ ተገቢ ይሆናል ብለዋል፡፡
ይህ የህግን ጉዳይ በድርድር የመፍታት አካሄድ ግን ነገ ከነገ ወዲያ ለሌሎች ክልሎችም አርአያነቱ አሉታዊ ነው ባይ ናቸው፡፡ መጥፎ አካሄድና ልማድም ነው የሚፈጠረው የሚል ስጋት አላቸው - የህግ ባለሙያው፡፡
ነገ ሌላውም ክልል ተመሳሳይ እርምጃ ወስዶ አጠቃላይ ሀገሪቱን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሊወስድ ይችላል የሚል ስጋት ያላቸው አቶ አመሃ፤ በህግ አግባብ ግለሰቦቹ ቢያዙ ይመረጣል ብለዋል፡፡ የክልሉ መንግስትም ግለሰቦቹን ለህግ አሳልፎ ሰጥቶ በሌላ በኩል የህግ ሂደታቸውንና በማረሚያ ቤት የመብት አጠባበቅና ይዞታቸውን ቢከታተል የተሻለ እንደሚሆን ባለሙያው ይመክራሉ፡፡
በዜጎች ላይ ስቃይ ፈፅመዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎችን ለመስጠት ማንገራገር በራሱ ፖለቲካዊ ኪሳራም ነው የሚሉት አቶ አመሃ፤ ተገቢ አቋምና አካሄድም አይደለም ይላሉ፡፡ የፌደራል መንግስቱ ኃይል ተጠቅሞ ተጠርጣሪውን ማምጣት ቢችልም ወደዚያ መገባቱ ጠቃሚ አይሆንም ብለዋል፡፡
ይህን ጉዳይ የፖለቲካ መፋጠጫ ማድረግ ተገቢ አይደለም የሚሉት አቶ ሙሼ በበኩላቸው፤ አንድን ግለሰብ አሳለፌ አልሰጥም በሚል ወደ ግጭት ውስጥ መግባትም በየትኛውም ሉአላዊ ሃገር የሌለ፣ ፖለቲካዊ ድጋፍ የማይኖረው ተግባር ነው ይላሉ፡፡ በግለሰብ ምክንያት ጦርነት ውስጥ የሚገባ የለም ያሉት ፖለቲከኛው፤ በፌደራልና በክልሉ መካከል ያለው ውዝግብ በሽምግልና ሊፈታ የሚገባ መሆኑን በመጠቆም፣ የሃገር ሽማግሌዎች ለምን ዝምታን መረጡ? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡
በዚህ ጉዳይም የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አጀንዳ ቀርፆ ሊወያይበት ይገባል ይላሉ አቶ ሙሼ፡፡ ግለሰብ ተጠርጣሪዎችን ለህግ አሳልፌ አልሰጥም ያለው ማነው? የትግራይ ክልል ስራ አስፈፃሚ ነው? ግለሰብ አመራሮች ናቸው? የክልሉ ም/ቤት ነው? የሚለው ጥያቄም መመለስ አለበት ብለዋል -ፖለቲከኛው፡፡ የግለሰቦች ለህግ የመቅረብ ጉዳይ የህዝብ መጠቃት አድርጎ ማቅረብ ግን ተገቢ አለመሆኑን አቶ  ሙሼ ያሰምሩበታል፡፡
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ያሉ አለመረጋጋቶችን ወደ መረጋጋት መመለስ ላይ ማተኮሩ የተሻለ ይሆን ነበር የሚሉት ፕ/ር መድህኔ በበኩላቸው፤ በሰብአዊ መብት በኩልም ቢሆን ሰዎች በአደባባይ ተዘቅዝቀው እየተገደሉ፣ ወደ ኋላ መመለሱ ብዙም አራማጅ አይሆንም ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ ችግሩ ፖለቲካዊ እንደመሆኑም በፖለቲካዊ ውይይት መፍትሄ ማግኘት አለበት ይላሉ፡፡ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ባለፈው ማክሰኞ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመሥሪያ ቤታቸውን የአምስት ወራት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት፤ “በዜጐች ላይ አሰቃቂ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲፈፀም በማድረግ የተጠረጠሩትን አቶ ጌታቸው አሰፋን ለመያዝ ጥይት ተታኩሰን የሌላ ሰው ህይወት እንዲጠፋ አንፈልግም” ብለዋል፡፡ ፓርላማው በዚህ ጉዳይ አቋም ይዞ ለጠቅላይ አቃቤ ህግ ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል- ጠቅላይ አቃቤ ህጉ፡፡     

Read 3320 times