Sunday, 06 January 2019 00:00

“ኢትዮጵያዊነት ማንንም አክስሮ አያውቅም”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 • ፖለቲከኞቻችን አለመዘመናቸው ነው ችግር ውስጥ የከተተን
  • የእርቅ ዘመን መጥቷል፤ቁጭ ብለን ልንወያይ ልንማማር ይገባል
  • በአዲስ ዘመን ላይ አሮጌ የፖለቲካ ባህል ነው የምናጫውተው

    ለሃገሪቱ አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ አደረጃጀት እና አመሰራረት ባህልን ያስተዋውቃል የተባለውን ከአርበኞች ግንቦት 7፣ ከሰማያዊ፣ ከኢዴፓ ጋር ሆነው እየመሰረቱ ካሉ ፖለቲከኞች አንዱ አቶ አንዷለም አራጌ እና ከእሳቸው ጋር ያሉ የቀድሞ አንድነት ፓርቲ አመራሮች እና አባላት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ አቶ አንዷለም አራጌ በተለይ ፓርቲው ይዟቸው ስለተነሱ ሃሳቦች እና ስለመጪው የሃገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል፡፡

    የብሔር ፖለቲካ በገነነበት አገር ውስጥ  በዜግነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ ማካሄድ ፈታኝ አይሆንም?
እኔ እንደምረዳው፣ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ብንሄድ፣ ህዝቡ ቀና ህዝብ ነው፤ ሃይማኖተኛ ህዝብ ነው፤ የሚከባበር ህዝብ ነው፡፡ ለራሱ እየራበው ሌላውን ስለመመገብ የሚያስብ ህዝብ ነው፡፡ የሌላው ወገኑ መጨቆን የራሱም መጨቆን አድርጎ የሚያስብ ህዝብ ነው ያለን፡፡ ይሄ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ያለ እውነት ነው፡፡ ህዝባችን ከፍ ያለ ሰብዕና ያለው ህዝብ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ጥቂቶች በስሙ እየጮኹ በጣም ብዙ ይመስላሉ። በተለይ በዚህ የፌስቡክ ዘመን የጥቂቶች ጩኸት የብዙዎች መስሎ ሊታይ ይችላል፡፡ ግን መሬት ላይ ወርደን የህዝቡን ስሜት ስናይ፣ ኢትዮጵያዊነት ከፍ ብሎ ነው የምናገኘው። አሁንም የኢትዮጵያ ህዝብ እድሉ እስካለው ድረስ ኢትዮጵያዊነት ያሸንፋል፡፡ ኢትዮጵያዊነት ማንንም አክስሮ አያውቅም፤ ማንንም አያከስርም፡፡ እነ ዶ/ር ዐቢይ ኢትዮጵያዊነትን ይዘው ሲነሱ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ  ከዳር እስከ ዳር ምን ያህል እንዳቀፋቸው በገሃድ ያየነው ሃቅ ነው። ይሄ ለሚያስተውል ሰው ትልቅ ትምህርት ነው። ስለዚህ አሁን እኛም ኢትዮጵያዊነትን ይዘን መጥተን እንደማናፍር እናምናለን፡፡ ለዚህ እውን መሆን በሃቅ እንሰራለን፤ በሃቅ እንታገላለን፡ ህዝብም እንደሚደግፈን እናውቃለን፡፡ ግን ፈተና አይኖረውም ማለት አይደለም፡፡ ገና ከአሁኑ ወደ በራችንም አትጠጉ፣ ከዚህ ወንዝ እንዳታልፉ የሚሉ፣ ልባቸው እንዲቃና የምንፀልይላቸው ወንድሞችና እህቶች አሉን፡፡ ከዚህ ሃሳብ እንዲፈወሱ የምንፀልይላቸው በርካቶች አሉ፡፡
ይሄ አስተሳሰብ ባለፉት 27 ዓመታት፣ በዘር ፖለቲካ እየተኮተኮቱ ባደጉ ልጆቻችን ላይ ቤት እንደሰራ እናውቃለን፡፡ ሆኖም ግን ይሄን ነገር ማሸነፍ ይቻላል፡፡ እንደሚታሰበው ከባድ ነው ብዬ አላምንም። ኢትዮጵያዊነት ያሸንፋል፤ ሰብአዊነት ያሸንፋል፡፡ ኢትዮጵያዊነት ሲባል ሰብአዊነት ነው። ሰብአዊ የሆነ ነገር ሁሉ አሸናፊ ነው፡፡ ሰውን ሰው የሚያሰኘው ሰብአዊነቱ ነው፡፡ ሰብአዊነት ደግሞ በቋንቋና በሸንተረር የሚከለል አይደለም። እኛም ይሄን ሰብአዊ የሆነ ሃሳብ ይዘን ስንቀርብ ኢትዮጵያውያን ሁሉ እንደሚደግፉን አምናለሁ፡፡
አዲስ የምታቋቁሙት ፓርቲ የማህበራዊ ፍትህ ርዕዮት አለም ይኖረዋል ተብሏል፡፡ እስኪ ያብራሩልኝ--?
ማህበራዊ ፍትህ ዲሞክራሲ ውስጥ ያለ ነው። ግን ዲሞክራሲያዊም ቢኮን እንደ ህዝቡ የእድገት ደረጃ፣ እንደ ህዝቡ የዲሞግራፊ ሁኔታ የተቃኘ ማህበራዊ ፍትህን የሚያሰፍን መፍትሄ ያስፈልጋል። አሁን በኛ ሃገር ሁኔታ 70 በመቶ ወጣት ነው፡፡ ይህ በሆነበት ለዚያ ወጣት ትኩረት አለመስጠት ትክክል አይሆንም፡፡ ወይም አብዛኛው ድሃ በሆነበት ሃገር ላይ ስለ ሊበራሊዝም ብቻ ማውራቱ ትክክል አይሆንም። ምክንያቱም ስራ ሰርቶ ቀን ከሌት ተግቶ፣ ህዝቡን ካለበት ችግር ማውጣት ያስፈልጋል፡፡ በመንግስት ደረጃ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የኢኮኖሚ ፍትህ መስፈን አለበት፡፡ ማህበራዊ ፍትህ የጎደለባቸውን ወገኖች መታደግ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህን ጉድለቶች በጥናት በመለየት በግኝቱ መሰረት ጉድለቶችን የሚመልሱ መፍትሄዎች ማስመቀጥ ማለት ነው፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ጥናት አድርጋችኋል?
አዎ! አሁን 50 ያህል ኤክስፐርቶች የሚሳተፉበት ስራ እየተሰራ ነው፡፡ ጥናቱ እየተጠና ነው፡፡ ህዝቡ ውስጥ ያሉ ጥያቄዎች ምንድን ናቸው? እንዴት ነው እነዚህ ጥያቄዎች የሚመለሱት? በሚለው ላይ ጥናት እየተደረገ ነው፡፡ ጥናቱ ሲጠናቀቅ ዝርዝር ሃሳቦችን ማቅረብ ይቻላል፡፡
ከዚህ ቀደም ጠ/ሚኒስትሩ በሃገሪቱ ያሉ በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ በሃሳብ የበላይነት ገዥውን ፓርቲ እንዲሞግቱ ወደ ሁለትና ሶስት ቢጠቃለሉ ይበጃል የሚል ሃሳብ አቅርበዋል … አሁን ባለው ሁኔታ ይህ ሃሳብ እውን እየሆነ ይሆን?
ይሄ መልካም ሃሳብ እውን እንዳይሆን ትልቁ ፈተና የሚገጥማቸው የብሔር ድርጅቶች የመስሉኛል። የሃሳብ ፖለቲካ ላየ የተሰማሩ ፓርቲዎች ያንን ውህደት ለማድረግ የተሻለ እድል ያላቸው ይመስለኛል። ፕሮግራማቸውና ሃሳባቸው ቢጨመቅ ወደ አንድ የሚመጣ ነው፡፡ እርግጥ ሃሳባችን አንድ ሆኖ እርስበርሳችን ስንወጋገዝና ስንፈራረጅ ኖረናል፡፡ ግን አሁን ጊዜው ደርሷል፡፡ የመሰባሰብ፣ የመግባባት፣ የመከባበር ጊዜው አሁን ደርሷል፡፡ ትልቁ ችግር የሚሆነው የብሔር ፖለቲካው ነው፡፡ ይሄ ኃይል እንዴት ብሎ ወደ አንድነት ሊመጣ ይችላል? የሚለው የኔም ጥያቄ ነው፡፡ ወይ እነዚህ ድርጅቶች በሃገር ደረጃ ማሰብ አለባቸው፡፡ እኔ በሃገር ደረጃ ካላሰብኩ የራሴን እንጂ የሌላውን ብሔር አባል በሰው ደረጃ ላላስብ እችላለሁ፤ ምክንያቱም ብሔሬን ነው የማስበው ማለት ነው፡፡ የሌላው መሞት የሌላው መገፋት አያሳስበኝም ማለት ነው፤ የሌላው መጨቆን መታሰር ግድ አይለኝም ማለት ነው፡፡ ግድ የሚለኝ ከሆነ ግን ለኢትዮጵያዊነት ቆምኩ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ  በብሄር የተደራጁ ከኢህአዴግ ጀምሮ ወይ በኢትዮጵያዊነት ዙሪያ መሳተፍ አለባቸው፤ አሊያ ግን በጋራ ተሰባሰቡ መባሉ ያን ያህል ውጤት የለውም፡፡ ሌሎቹ ግን ወደ አንድነት ሊመጡ ይችላሉ፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ በቅርቡ በኢትዮጵያ በሳል ፖለቲከኛም የበሰለ ፖለቲካም አልተፈጠረም ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡ በዚህ ሃሳብ ትስማማለህ?
በዚህ ላይ እኔም ከእርሳቸው ብዙም አልለይም። እኛ በአሮጌ የፖለቲካ ባህል ላይ ነው እየተጫወትን ያለነው፡፡ በአዲስ ዘመን ላይ አሮጌ የፖለቲካ ባህል ነው የምናጫውተው፡፡ የፖለቲካ ባህላችን አለመለወጡ፣ ፖለቲካችንን ማዳበር አለመቻላችንና አለማዘመናችን እሳቸው እንዳሉት፣ የበሰለ ፖለቲካም ፖለቲከኛም አለመኖሩን ነው የሚሳየን፡፡ የበሰሉ ፖለቲከኞች ቢኖሩ ኖሮ ፖለቲካውን የማዘመን አቅም ይኖር ነበር፡፡ የነበሩት ሰዎች አለመብሰላቸው አለመዘመናቸው ነው፣ ይሄን ያህል ችግር ውስጥ የከተተን፡፡ እርግጥ አልፎ አልፎ ጉልህ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ ግን በአጠቃላይ የፖለቲካ ንጣፉ ባለመሰራቱ እነዚያ ሰዎች አስተዋጽኦ እንዳያደርጉ እንቅፋት የሆነባቸው ይመስለኛል፡፡ እነሱ የሃገሩ ፖለቲካ የሚፈልገውን ያህል ብልህ ቢሆኑ ኖሮ ደግሞ አስቸጋሪውን የሃገሪቱን የፖለቲካ ንጣፍ የሚቀይር ቀመር ይዘው ይመጡ ነበር፡፡ የፖለቲካ ቀመሩን ሰርተው ባህሉን የመለወጥ አቅም ያላቸው ሰዎች አለመኖራቸው ነው ችግር የፈጠረብን ማለት ይቻላል፡፡
ሃገሪቱ ፕሬዚዳንታዊ ስርአትን ብትከተል መልካም ነው የሚሉ ሃሳቦች ይሰነዘራሉ፡፡ የአንተ አቋም በዚህ ላይ ምንድን ነው? የምትመሰርቱት ፓርቲስ ምን ሊሆን ይችላል?
በአጠቃላይ ፕሬዚዳንታዊ ስርአት ቢሮረን ለሁላችንም የተሻለ ነው፡፡ አንድ ጠንካራ ሃገር ለመገንባት ፕሬዚዳንታዊ ስርአት ትልቅ እሴት ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ምክንያቱም አሁን ባለው የኢህአዴግ አሰላለፍ ጉዳዩን ብንመለከተው፣ አንድ የጋምቤላ ተወላጅ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የመሆን ዕድሉ ጠባብ ነው፡፡ አፋሩም፣ ሶማሌውም እንደዚያው፡፡ ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት ከሆነ ግን ማንም ሰው ከየትም ዘር ይወለድ፣ ሃሳቡና እውቀቱ ካለውና የህዝብን ቀልብ ከገዛለት፣ ከትቢያ ተነስቶ ፕሬዚዳንት ሊሆን ይችላል፡፡ የዜጋው በህግ ፊት እኩል መሆን የሚለካው በዚህ ዓይነቱ ሥርዓት ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ግን ዜጋው ሳይሆን ወሳኙ የብሔር ተዋፅኦው ነው፡፡ በብቃት አይደለም ሃገር እየተመራ ያለው፤ በዋናነት በብሔር ተዋፅኦ ነው፡፡ አሁን ግን ይሄ መቀየር አለበት፡፡ በኛ በኩል ጉዳዩን ገና ውይይት እያደረግንበት ነው። በውይይት የምንወስነው ይሆናል። ፕሬዚዳንታዊ ስርአት ለእንደኛ አይነት ሃገር ጠቃሚ መሆኑን ግን አምናለሁ። ጠንካራ አንድነቷ የተረጋገጠ፣ በሃሳብ ልዕልና ላይ የተመሰረተች ሃገር ለመፍጠር ፕሬዚዳንታዊ ስርአት ጠቃሚ ነው፡፡
አሁን በአመዛኙ በፖለቲካ መድረኩ ላይ ገኖ ያለው የብሔር ፖለቲካ በምርጫ እድል ቀንቶት ወደ ስልጣን ቢወጣ ምን ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል? ለምሳሌ “ኦነግ” እና “አብን” ስልጣንን ቢቆጣጠሩ ምን አንድምታ ሊኖር ይችላል?
ይሄ ጉዳይ እኔ ብዙ አያስጨንቀኝም፡፡ ለምሳሌ የአቶ ዳውድ ኢብሣን ንግግር ፈልጌ ነው የማዳምጠው። እስካሁን አቶ ዳውድ ጋ የሚሻክር ነገር አልሰማሁም። ሌሎቹ ጋርም በተመሳሳይ። ስለ ኢትዮጵያ በጎ ነው ሃሳባቸው፡፡ ስለዚህ ያን ያህል አያስጨንቅም፡፡ የሚናገሩትን ነገርን ስሰማ ብዙም የሚያስጨንቅ ነገር አላይም፡፡ ግን አንዳንድ በድርጊት የሚገለፁ ነገሮች አሉ፡፡ እነዚያ ነገሮች የአቶ ዳውድ ሃሳብ ናቸው ወይ ብለን ነው መመልት ያለብን፡፡ ይሄን ብዙ ሳላውቅ ዝም ብዬ ልፈርጃቸው አልፈልግም፡፡ በንግግር ደረጃ እንዳልኩት፤ ስለ ኢትዮጵያ ጥሩ አተያይ እንዳላቸው ነው የተረዳሁት። ግን በዚህ መሃል ህወሓትን ማየት ያስፈልጋል፡፡ ህወሓት፤ ኢትዮጵያ የ100 ዓመት ታሪክ ብቻ ነው ያላት እያለ ሲሰብክ የኖረ ድርጅት ነው፡፡ በኋላ ላይ ደግሞ የ3 ሺህ አመታት ታሪክ አላት ሲል ሰምተናል። ወደ ስልጣን ሲመጣ በፊት ሲላቸው የነበሩ ነገሮችን ቀይሯል፡፡ ከዚህ አንፃር እነዚህ ኃይሎች ኢትዮጵያን ወደ መምራት ቢመጡ የሚረከቡት ኢትዮጵያን እንጂ አንድ ብሔርን አይደለም። ኢትዮጵያን መምራት ሲጀምሩ ከብሔራቸው ወጥተው ስለ ሃገር ማሰብ መጀመራቸው አይቀርም፡፡ ለምሳሌ ዶ/ር ዐቢይ ኦዴፓ ናቸው ግን የኢትዮጵያ መሪ ናቸው። በእሳቸው ልክ ይሆናሉ ወይ የሚለው አጠያያቂ ቢሆንም እነዚህ አካላት ወደ ስልጣን ቢመጡ ለኢትዮጵያ ያን ያህል ስጋት ይሆናሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡ ለኔ ስጋቴ አይደሉም፡፡
ብሔራዊ የእርቅ ኮሚሽን ተቋቁሟል፡፡ ለአገራችን የእርቅ አስፈላጊነት ምን ያህል ነው?
የእነ ዶ/ር ዐቢይ አመራር በታሪክ ከሚጠቀስበት ጉዳይ አንዱ የብሔራዊ እርቅን ማሰባቸው ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ኮሎኔል መንግስቱ፣ አቶ መለስ ሲለመኑ ሲጠየቁበት የነበረ ጉዳይ ነው፡፡ “ተው እንታረቅ፤ ልዩነቶች ተራግበዋል፤ በማወቅም ባለማወቅም የተሰሩ ስህተቶች አሉ” ሲባሉ ሊቀበሉ አልፈለጉም። ይሄን ሃሳብ ስንሰነዝርም ስንወገዝና ስንሰደብ ነበር። አሁን በጎ ፈቃድ ያላቸው መሪ መጥተው፣ ይሄን ሃሳብ ይዘው ስራ ተጀምሯል፡፡ እርቅን የመሰለ ነገር የለም። አሁን የእርቅ ጊዜና ዘመን መጥቷል፡፡ ቁጭ ብለን ልንወያይ ልንማማር ይገባል፡፡ ሃገራችንን እንዴት አድርገን እንስራ? አባቶቻችን በመሰላቸው መንገድ ሰርተዋታል። አሁንስ የኛ ትውልድ እንዴት ሰርቶ ነው ለትውልዱ ማስረከብ ያለበት የሚለውን፣ መቋሰሎችን በእርቅ ሽረን መምከር ትልቅ ነገር ነው። ዶ/ር ዐቢይ ይሄን ሲወስኑ፣ ከአንድ የበሰለ መሪ የሚጠበቀ.ውን ነው ያደረጉት፡፡ ስለዚህ እርቁ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ እስካሁን ያሉብን ደዌዎች የሚፈወሱት በዚህ መንገድ ነው፡፡
እርቁ የሚፈጸመው በማንና በማን መካከል ነው የሚለው በብዙዎች ዘንድ ግልጽ አይደለም?
እሱን በባለሙያዎች ጥናት መለየት ነው የሚያስፈልገው፡፡ ከመቼ እስከ መቼ ያለውን ቅራኔ በእርቅ እንፍታው? በዚህ እርቅ እነማን ይሳተፉ? ማን ከማን ይታረቅ? አስታራቂው ማን ነው? ታራቂውስ? --- የሚለውን ሁላችንም በምናምናቸውና በምናከብራቸው ሰዎች ተዘጋጅቶ መቅረብ አለበት። ከዚያ በኋላ በተዘጋጀው ምክረ ሀሳብ ላይ ህዝብ እየመከረበት፣ ቀሪውን ማዳበር ይቻላል፡፡ ይሄ እርቅ አስፈላጊያችን ነው፡፡ ከዚህ እርቅ ማንም መቅረት የለበትም፡፡ መታረቅ ትልቅ ሰብአዊነት ነው፡፡ ዝም ብሎ ቁስልን እያከኩ ሀገሪቷን ወደ ኋላ መጎተት መቅረት አለበት፡፡ ኢትዮጵያውያን ከዚህ በኋላ እንደ ዘመናዊ አለም ሰዎች፤ መጪውን ብቻ ማሰብ መጀመር አለብን። ስለ ልጆቻችን እንዲሁም የልጅ ልጆቻችን እጣ ፈንታ መጨነቅ አለብን፡፡ ለዚህ መሰረቱ መሆን ያለበት ፍትህ አንድነትና ፍቅር እርቅ ነው፡፡ ሃገራችንን ወደዚህ ሂደት ውስጥ ማስገባት አለብን፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ቀጣዩን ምርጫ ነጻና ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ ከፍተኛ ጉጉት ያላቸው ይመስላሉ፡፡ በተደጋጋሚም፤ “በምርጫ ከተሸነፍን ስልጣናችንን ለአሸናፊው ለማስረከብ ዝግጁ ነን” ሲሉ ተናግረዋል።  ቃላቸውን ይፈፅሙ ይሆን?
እንደሚፈፅሙት አምናለሁ፡፡ እኔ ዶ/ር ዐቢይ የገባቸው ነገር ያለ ይመስለኛል፡፡ በትውልድ ልብ ውስጥ የምትኖረው ለህዝብ ፍቃድ በመገዛት ነው የሚለው ገብቷቸዋል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ይሄን ቃላቸውን ቢያከብሩ “የኢትዮጵያ ዲሞክራሲ መስራች አባት” ተብለው በታሪክ እንደሚታወሱ በሚገባ ተረድተዋል፡፡ ይሄ ከፍ ያለ አስተሳሰብ ነው። አቶ መለስ የተቻላቸውን ያህል ስልጣናቸውን ላለማስነካት ሞክረዋል፡፡ አሁን ግን ለትውልድ የሚቀር፣ በትውልድ የሚታወስ መልካም ነገር ማቆየት አልቻሉም፡፡ ኮሎኔል መንግስቱ የቻሉትን ያህል ጨፍጭፈዋል ግን በዚያ የሚያስከብራቸውን ነገር አላገኙም፡፡
አለም የምታከብረው ቀናዎችን ነው፡፡ ኔልሰን ማንዴላን፣ ማሃተመ ጋንዲን መጥቀስ ይቻላል። ለመሪ የሚያስከብረው ትልቁ ነገር፣ የህዝብን ሉአላዊነት የስልጣን ባለቤትነት መቀበል ነው፡፡ እሱን አክብሮ ለህዝብ ፍቃድ መገዛት ነው፣ በትውልድ ውስጥ የከበረ ቦታ የሚያስገኘው፡፡ የሃገርህ ምሰሶ ሆነህ ለመታወቅ በታሪክ ለመታወስ፣ ህዝብን ሉአላዊ የስልጣን ባለቤት መሆኑን መረዳት ነው፤ ትልቁ ቁልፍ፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ይሄን በሚገባ የተረዱ መሪ ናቸው፡፡ ከዚህ በፊት ልማት ተብሎ ህንፃ እየተሰራ፣ ነገር ግን ህዝብ እየተረገጠ ነው የኖርነው፡፡ በህንፃ ስር በልመና የሚተዳደሩ ዜጎች የሚኮለኮሉበት አለም መፍጠር ተችሏል፡፡ ነገር ግን ማወቅ ያለብን በመጀመሪያ የህዝብን ሉአላዊ የስልጣን ባለቤትነት ያልተቀበለ እድገት ዋጋ የለውም። ዜጋው የሉአላዊ ባቤት መሆኑን ያከበረ እድገት ግን ትክክለኛ ነው፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ይሄን መስመር እየተከተሉ ነው፡፡ ስለዚህ እንደሚሳካላቸው አልጠራጠርም። ከብዙ መከራ ከብዙ ሰቆቃ በኋላ ጊዜው የደረሰው የዲሞክራሲ ሃሳብ ቦታውን እየያዘ እንደሆነ አምናለሁ። ለእሳቸውም ለእኛም ይሳካልናል ብዬ አምናለሁ። መሸነፍ በዲሞራክሲ ውስጥ ክብር ነው፤ ስለዚህ ሁላችንም በዲሞክራሲ ውስጥ ለማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ለመሸነፍም ዝግጁ መሆን አለብን፡፡   

Read 3237 times