Print this page
Sunday, 06 January 2019 00:00

“በራቸውን ሳይዘጉ ሌባ ሌባ ይላሉ” አለች ውሻ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

 አንድ ፅሁፍ የሚከተለውን አስፍሯል፡፡
“አንድ ጉብል አንዲትን ጉብል ለማግባት መንገድ ላይ ነው፡፡
“እንደምወድሽ ታውቂያለሽ?” አላት፡፡
“አዎ በደምብ አውቃለሁ” ብላ መለሰች፡፡
“እንግዲህ የነገ ዕጣ ፈንታችንን ለመወሰን መወያየት መጀመር አለብን”
“ደስ ይለኛል”
“መቼ እንደምንጋባ መወሰን ይኖርብናል”
“ትንሽ አልፈጠነም”
“እንዲያውም! ለገና በዓል ማለቅ ያለበት ነገር ነው”
“ቢያንስ ለሳምንታት ማየት አለብን”
“እሱን አልቀበልሺም”
“እሺ በሶስት ቀን ጊዜ ውስጥ መልስ ልስጥህ?”
“እሱ ጥሩ”
በእነዚህ ሦስት ቀናት ውስጥ አንድ ነገር ተከሰተ፡፡
የሚኖርበት ሆቴል ክፍል አንዲት በጣም ቆንጆ፣ ቅርጿ የሚያማልል፣ ዐይነ - ግቧ የሚስብ ሴት፤ ስስ ቀሚስ ለብሳ፣ ፊቱ ሽንጥና ዳሌዋን እያማታች ትንጎራደድበት ጀመር፡፡
ሁሉ ነገሯ እንዳማረው ገብቶታል፡፡ እሷም ገብቷታል፤ ጓጉቶላታል፡፡ ግን ደግሞ ሊያገባ ጥቂት ቀናት የቀረው ሰው ነውና የቸገረው ይመስላል፡፡ ቆንጆዋ እጮኛው የላከችበት ፈተናም ልትሆን ትችላለች፡፡ ተነስቶ ወጣና ደጅ መኪናውን ወዳቆመበት ቦታ ሮጠ፡፡” ይልና፤ ከግርጌው “ከዚህ ታሪክ የምናገኘው ትምህርት ኮንዶም መኪና ውስጥ ማስቀመጥ እንደሚገባ ነው!!”
*   *   *
 በእቅድ መንቀሳቀስ የህይወታችን መመሪያ ሊሆን ይገባዋል፡፡ የአንድ መስሪያ ቤት መመሪያ ለመቅረፅ ምጥ ያህል አድካሚ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የአንድ ሰው የህይወት መመሪያ ግን እጅግ ውስብስብና መጀመሪያውን እንጂ መጨረሻውን የማንተነብየው የጉዞ ሂደት ነው። ፍፃሜውን አወቅንም አላወቅንም ግን መኖር ይቀጥላል፡፡ የሀገር ጉዳይ ሲሆን ደግሞ የጨዋታው ህግ ይለወጣል፡፡ አንደኛ፤ መመሪያው ከመቀረፁ አስቀድሞ የአቃጁ ቡድን ያየዋል፡፡ ግራ ቀኙን ይመዝነዋል፡፡ ይሰርዛል፡፡ ይደልዛል፡፡ እመጫት ያስገባል፡፡ እዝባር እያደረገ አማራጭ ያስቀምጣል! እንዲህ ተጠንቶና ተጣርቶ የመጣ መመሪያ፤ የስህተት ዕድሉ እጅግ ውሱን ነው፡፡
በዚህ መንገድ ነጥረው ያልወጡ መመሪያዎች ግን የሀገር ዕዳ ናቸው፡፡ የአቅም ግንባታ ሳይሆን አቅመ - ጎዶሎነትን ጠቋሚ ናቸው! ነገር ዓለሙ አልሆን ካለንና የሄድነው መንገድ ሁሉ ወደ ጥፋት እያመራ ከመሰለን ወደ ኋላ ከመመለሳችን በፊት ቆም ብሎ ማውጠንጠን፣ የረገጥነውን ሁሉ መፈተሽ፣ ትርፍና ኪሳራውን ማስላት ያሻል፡፡ ከዚያ እንዳዲስ ሥራ ከመጀመር አንስቶ ችግሩን እየፈተሹ መላ መላውን እስከ ማበጀት መታገል ነው! ለዚህ ጠቃሚው ዘዴ ቀና ቀናውን ማትና ከብዙ መጥፎዎች መካከል እንኳ ተዛማጁ መልካም ነገርን በትዕግሥት መፈልፈልና ማግኘት ነው! መንገዳችን እንዳይምታታ ግን ሶስት ነገሮችን መገንዘብና ማስገንዘብ ይገባናል፡-
1ኛ/ የጊዜ ዕቅድ
2ኛ/ በመለስተኛ ፕሮግራም የመስማማት ዕቅድ
3ኛ/ ከራስና ከወዳጅ ዘመድ ጥቅም ባሻገር፣ አገርንና ህዝብን የማሰብ ዕቅድ
በጊዜ ውስጥ አገርን ማሰብ ይቻላል፡፡ ሁላችን ያለፅንፈኛ የፓርቲም ሆነ የድርጅት አጀንዳ እንደ ኑሮና እንደ ህይወት ህዝባዊ ጠቀሜታ ተግቶ ማገዝና መተጋገዝ ይቻላል፡፡ ከኢኮኖሚና ፖለቲካዊው ሰንሰለት የቱን ቀለበት ብናላላ፣ የቱን ቀለበት ብናጠብቅ ይሻላል? የሚል ዕቅድ ማቀድም ይቻላል፡፡ መነሻችንን እናቅድ፣ መድረሻችንን እንወቅ!
ይህን ለማድረግ ግን በወርቅ አልጋ፣ በእርግብ ላባ ላይ መተኛት የለብንም፡፡ አንችልምም! እንደ ጥንቱ ሶሻሊስታዊ መፈክር፤ “ትግላችን እረጅም ጉዟችን መራራ” ባንልም፣ ብዙ የኢኮኖሚና የፖለቲካ አቀበት ገና መውጣት እንዳለብን አንስትም! የትኛውም ርዕዮታዊ መንገድ ቢታሰብ - (ሀ) የተቃርኖ ህግን (ለ) በአንድነት ውስጥ ልዩነትን እና (ሐ) የአዲሱን አሸናፊነት ማመን ግዴታችን መሆኑን ተግተን እናውቃለን!
“ጥንትም ወርቅ በእሳት፣ እኛም በትግላችን እየተፈተንን፣ እናቸንፋለን!” ብለን እንደነበር ለአፍታም ሳንጠራጠር ዛሬም እንናገራለን!
ኢትዮጵያ ብዙ ያልተዘጉ በሮች አሏት - ለሌቦች ክፍት የሆኑ፣ አያሌ የተከፈቱ በሮች! ሌቦቹ፣ ሌቦቹ ብቻ አይደሉም! ያቀበለ፣ ሀሳቡን የደገፈ፣ “ቢዝነስ ነው” እያለ የሰበከ፣ ሀሳቡን ያስተላለፈ፣ ሚስጥር አድርጎ ያቆላለፈ፣ ደብዛው እንዲጠፋ የደገፈና ያደጋገፈ … ሁሉም ሌቦች ናቸው!
ዛሬ የሌቦቹ ቋንቋ “በራቸውን ሳይዘጉ ሌባ ሌባ ይላሉ” አለች ውሻ፤ የሚለውን ተረት መተረት ሆኗል፡፡ ለማያውቅሽ ታጠኚ ማለት የኛ ፈንታ ነው! እውነቱን ለመናገር ግን በሩን ገርበብ ያደረገውም፣ ያለቁልፍ የተወውም፣ ቁልፍ እንዳይኖረው ያደረገውም፤ …. ሁሉም ሌቦች ናቸው! ወንጀሉ ሙሉው ሰንሰለቱ ላይ ተንጠልጥሎ ያለ መሆኑን አንርሳ! የተንጠለጠለው ወንጀል”  አንድ ቀን ሁሉንም ያንጠለጥላል፤ ብለን እንጠብቃለን!
ለክርስትና አማኞች
እንኳን ለብርሃነ ልደቱ አደረሳችሁ!

Read 4633 times
Administrator

Latest from Administrator