Sunday, 06 January 2019 00:00

የመጪው ምርጫ ስጋትና ምትሃት!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)

 ዕረፍት የማያውቀው - ፈጣን ሰረገላ፣
መንቃት በማያውቁ፣ - ተጓዦች ሲሞላ
የመገለጥ ወይን በአፍጢሙ ተደፋ
“ወራጅ አለ” የሚል - ተሳፋሪ ጠፋ
(“የመንፈስ ከፍታ”፤ በረከት በላይነህ)
በዚህች ሃገር ላይ “ምርጫ” ተብሎ ይካሄድ የነበረውን ሁነት በዘግናኝ ገፅታው፣ በአሳዛኝ ትርዒቱ እናስበዋለን። የሌላውን ባላውቅም በኔ አእምሮ ግን፣ በየአምስት ዓመቱ ሰዎች የሚታሰሩበትና የሚጉላሉበት፣ በሚሊዮን የሚቆጠር የሕዝብ ሀብት የሚባክንበት ጨለማ ጊዜ ነበር፡፡ ይህንን ምስልና መልክ የፈጠርኩትም እኔ አይደለሁም። ይህን የተፈጠረው የዴሞክራሲ ጭንብል ያጠለቀውና በጠመንጃ ታግዞ ጫንቃችን ላይ የተከመረው መንግስት ነበር፡፡ ስለዚህም ብዙ ጊዜ “ምነው ይሄ ምርጫ ቢቀር!” እላለሁ፡፡ እውነት ይሁን ውሸት ባይጣራም በአንድ ወቅት የኤርትራው ፕሬዚዳንት፤ አንዴ “እንደ ኢትዮጵያ ያለ የውሸት ምርጫ በዓመት አስሬ ማካሄድ እንችላለን” ብለዋል ይባላል፡፡ እኔ ግን እል የነበረው “ቢቀርስ?” ነው፡፡ ነገሩ ግን እንዲያ አይደለም፤ መንግስት ብር የሚመዠርጠው፣ የምርጫ ቦርድም እየተላከ፣ ቴሌቪዥን  ላይ የሚያላዝነው፣ ጋዜጠኛውም አቧራ እያቦነነ ሰነድ የሚፈትሸውና ዶክመንተሪ የሚሰራው በነፃ አይደለም፡፡ እነዚያን የፈረደባቸውን መፅዋች ፈረንጆች “በዴሞክራሲያዊ ጉዞ ላይ ነን” ብሎ ለመሸንገል ነው፡፡
ብቻ እንደ ሀገሬ እያሰብኩ “ምርጫ” ሲባል እፈራለሁ፡፡ ልቤ ለምርጫ ድክ ድክ የምትለው የአሜሪካንና የአውሮፓን ምርጫ በቴሌቪዥን ባየሁ ቁጥር ነው፡፡ ቅናቱም ምኞቱም ይፈናጠጥብኛል፡፡ ግን ምን ያደርጋል! ምራቅ እየዋጥን እዚህ ደርሰናል! በደም የተለወሰ ትዝታችን፣ በለቅሶ የተዋጠ ሙሾዋችን፣ በእንባ የተወለወለ ስቃያችን ዛሬም በልባችን  ይገላበጣል፡፡
ታዲያ አሁንም በዶክተር ዐቢይ የሚመራው የለውጡ መንግስት ወደ ምርጫ መግባቱ የግዴታ ውዴታ ነው። በዚህ የመግባት ጉዞው ውስጥ ያሳያቸው የዴሞክራሲ አቅጣጫ ምልክቶች፣ የሰለጠነውን ዓለም የሚመስሉና በእኛ ዐውድ የማይታመኑ ናቸው፡፡ በተለይ ያ ቁማርተኛ ምርጫ ቦርድ፣ የመንግስት ጨካኝ ካድሬዎችን ሰግስጎ እንዳላፌዘብን፣ ዛሬ ቁንጮዋ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የአመራር መንበሩ ላይ ጉብ ማለቷ ትልቅ እመርታ ነው፤ ይህ በእኛ ሀገር ፖለቲካ በአጭር ጊዜ ሊሆን የማይችል ነገር ነበር፡፡ ግን እንደ ተዐምር ሆኗል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላት ከእሥር ተፈትተዋል፤ ስደተኞቹም ሀገራቸው ገብተዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ተንኳሾች ላይ እንኳ የኃይል እርምጃ ለመውሰድ፣ መንግስት የቀድሞውን ታሪክ መድገም አልፈለገም፡፡
ስለዚህ ምርጫው ፍትሃዊና ዴሞክራሲዊ እንዲሆን መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን በዚህና በመሰል ድርጊቶች አሳይቷል፡፡ ይሁንና ምርጫው በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ እንዲካሄድ የሚያበቁ ሁኔታዎች የተመቻቹ አይመስሉም። የተለያዩ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሳይቀሩ፣ አሁን ባለው ያልሰከነና ያልተረጋጋ ከባቢ፣ ምርጫው ይካሄድ ቢባል፣ የሀገሪቱ እንጭጭ የለውጥ ጉዞና አንድነት ሊናጋና ሊጨነግፍ ይችላል የሚል ስጋት ይዟቸዋል፡፡ ሰሞኑን በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ቃለ ምልልስ ያደረጉት የአርበኞች ግንቦት ሰባት መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋም፤ ሌላው ቀርቶ የክልል ልዩ ኃይሎች ተጠናክረው ባሉበት ሁኔታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ገብተው እንደልባቸው መንቀሳቀስና ምርጫ ማካሄድ እንደሚከብዳቸው ተናግረዋል፡፡
ይህ ሀሳብ የፕሮፌሰሩ ሃሳብ ብቻ አይመስለኝም፤ የብዙ የኢትዮጵያውያን ስጋት ነው፡፡ ስጋታችን ደግሞ ከዚህም ያለፉ ምክንያቶች ይኖሩታል፡፡ እነዚህን ስጋቶች ለመቀነስና በተረጋጋ ሁኔታ ለማካሄድ የሀገሪቷ ሁኔታ መስከንና መረጋጋት እንዳለበት ለማንም ግልፅ ይመስለኛል። አለበለዚያ ነገሩ የተገረፈችን ልጃገረድ ቁስሏ ሳይደርቅ፣ ህመምዋ ሳይታገስ ወደ ጫጉላ ቤት እንደመውሰድ የሚቆጠር ነው፡፡
በምክንያት የሚያምኑት፣ በሳል ቀናና፣ ለሀገር የሚቆረቆሩት ኢትዮጵያዊ ምሁር ዶ/ር መረራ ጉዲና (በጣም የማከብራቸውን የምወዳቸው ምሁር) ሳይቀሩ ምርጫው በወቅቱ መካሄድ እንዳበት ያሳስባሉ፡፡ እኒህ ፖለቲከኛ ፍርሃታቸውና ስጋታቸው የዚህ ዓይነተ መንሸራተቶች በቀጣዩ የፖለቲካ  ስርዓት ግንባታ ላይ ችግር ይፈጥራል የሚል ነው፡፡ እውነታቸውን ነው፣ ሌሎችም የዓለም ፖለቲከኞች የዚህ አይነት ስጋት እንደነበራቸው፡፡ የታሪክ ገፆች ያስነብቡናል ለምሳሌ ከነዚህ ስጉዎች አንዱ የነበረው ታላቁ መሪና ሳይንቲስት ቶማስ ጀፈርሰን ነበር፡፡ ጀፈርሰን ለሶስተኛ ጊዜ ፕሬዚዳንት እንዲሆን በጥብቅ ሲጠየቅ “በፍፁም አላደርገውም” ያለው፤ በቀጣይ ትውልድ የዚያ ዓይነት ሽንቁር እንዳይከፈት በማሰብ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ በዚያ ጊዜ ጀፈርሰን ስልጣን ቢለቅም አሜሪካንን አደጋ ላይ የሚጥላት የተለየ ችግር አልነበረም። ሌላ ሰው ተተክቶ ሊመራ፣ ሌላ ሰው ጉዞዋን ሊያስቀጥል ይችል ነበር፡፡   
የእኛ ጉዳይ ግን ከእነርሱ ይለያል፡፡ ይህንን ዶክተር መረራና መሰሎቸው ሊረዱት ይገባል፡፡ በእርግጠኝነት ዶክተሩ ይቀበሉታል ብዬ አምናለሁ፡፡ ከዶክተሩ ትይዩ ተመሳሳይና የከረረ አቋም ያላቸው ሰዎችና ወገኖችም አሉ። እነዚህ ወገኖች ምናልባት ምርጫው ባልተረጋጋ ሁኔታ ቢካሄድ የድምፅ ሎተሪ የጠበቁ ይመስለኛል፡፡ ሀገሪቱ ያለችበትን ሁኔታና ይህን ሃያ ሰባት ዓመታት የተከተፈ ብትንትን ልብ በፍቅር፣ በትዕግሥትና በጥንቃቄ ለመስፋት የሚያስፈልገውን ጥንቃቄ ያወቁ አይመስልም፤ አልያም ግድ የላቸውም፡፡ ስለዚህ ስልጣን ለመናጠቅ ያሰፈሰፉ ይመስላሉ፡፡ ለመሆኑ ሀገር ከሌለች ሹመቱስ እምን ላይ ነው? ደግሞ እማን ላይ?
በተለይ አንዳንዶቹ ፓርቲዎች አሁን የሃገሪቱ ችግር ጫንቃው ላይ የወደቀውና ለለውጡ አንገቱን ገመድ ውስጥ አስገብቶ የተፋለመው “ኦዴፓ”፤ በብሔራዊ መሪነት በሚባትልበት አጋጣሚ የክልሉንና የፓርቲውን ስራ ሳይሰራ በምርጫው ደካማ አሰላለፍ እንዲኖረው ለማድረግና ለመናጠቅ እንደሚያስቡ የሚያመለክቱ ሁኔታዎች አሉ፡፡ እናም ምርጫው “አሁኑኑ መደረግ አለበት” ብለው ዓይኖቻቸውን አፍጥጠው ጠብቀዋል፤ እልህም የገቡ የሚመስሉ አሉ፡፡
ይሁንና ዲሞክራሲ በራሱ የሀሳብ ልዩነትን ማስተናገድ ነውና መልካም ነው ተብሎ ሁሉም እየተብላላና በየአደባባዩ እየተናገረ ነው፡፡ ቶማስ ጀፈርሰን እንደሚለው፤ “In every country where man is free to think and to speak, differences of opinion will arise from difference of perception, and the imperfection of reason;”
ምክንያቱ ተገቢና ትክክለኛ ቢሆንም - ባይሆንም ሁሉም ፓርቲዎችና ግለሰቦች በጉዳዩ ላይ የራሳቸውን ሃሳብና እምነት መግለጥ እንዲችሉ የለውጡ መሪዎች አመቻችተውታል፡፡ ይህ የዲሞክራሲያዊ ጉዞ መገለጫ በመሆኑም ደስተኞች እንሆናለን ብዬ አምናለሁ፡፡ ግን የሀገሪቱስ ጉዳይ ለዚህ የተመቻቸ ነው? ምርጫው ባልሰከነ - የህዝብ ስሜት፣ በብሔር ግጭቶች በቆሠለ ልብ፣ ተንኮለኞቹ፣ ከለውጡ በፊት የነበሩ ገዢዎች፤ ቦንቦቻቸውን ከእጃቸው፣ ሃሳባቸውን ከሰዎች ልብ በሚገባ ባላፀዳንበት ሁኔታ ዘው ብሎ መግባት ወደ ሌላ ግጭትና ግርሻት አያስገባንም ወይ? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡
ለምሳሌ ያህል “ኦዴፓ” ከላይ እንደጠቀስኩት ከጭንቅላቱ እንጂ ከወደ እግሮቹ ገና የታጠበና የፀዳ አይመስልም፡፡ ይህንንም ለማድረግ በክልሉ ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ የተፈጠረውን አለመረጋጋት ለማስከን አባላቱ ላይ ታች እያሉ ናቸው፡፡ ሌላ ተአምር ካልተፈጠረ በስተቀር ለምርጫው ቅስቀሳ እንኳ ህዝብን ለማግኘት የማያስችል ውጥረት ውስጥ ናቸው፡፡ እንደዚህ ባሉበት ሁኔታ ምርጫውን አካሂደው ሥልጣናቸውን ገና ለማናውቀው፣ ገና ብዙ ላልተዋወቅነው ፓርቲስ መስጠት አደጋ እንደማያመጣ ምን ማረጋገጫ አለን? ገና ጡት ያልጣለውን አራስ ለውጥ፣ ለጡጦ እንኳ ሣደርሱ በዚህ ውጥንቅጥ ውስጥ መጣል አደጋው ቀላል አይመስለኝም፤ ደግሞ ደጋግሞ ሊታሰብበት የሚገባ የህልውና ጉዳይ ነው። ህጐችም ሀገርን ዘአደሃ ካላደኑ ሌላ የማርያም መንገድ ያስፈልገናል፡፡
ከላይ የጠቀስኩት የቶማስ ጀፈርሰን ሀሳብ ጥንቃቄ ትክክል የነበረበት ጊዜ ነበር፡፡ ምክንያቱም “ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል” እንዲሉ ጀፈርሰን ለሦስተኛ ዙር ቢመረጡ ሌሎቹም ያንኑ ተጠቅመው ከህግና ከሥርዓት ውጭ ሊያደርጉ ይችላሉና ተቃውሞዋቸው የሚገባ ነበር፡፡
በኋላ ግን ከሁለኛው የዓለም ጦርነት ማግስት፣ ሌላ ታሪክ አሜሪካንን አፍንጫዋን ሰንጐ ይዟት ነበር፡፡ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በሚያስደነግጥ ሁኔታ አሽቆልቁሎ በጠፈር ላይ በወደቀች ጊዜ “Newdeal” በሚል ፖሊሲያቸው እጅዋን የያዙት ዲላኖ ሩዝቬልት ሁለተኛው የፕሬዚዳንትን ዘመናቸውን ቢጨርሱም ሀገሪቱን ከሞት መታደግ ነበረባቸውና ሦስተኛውን ዙር በዚያው እንዲቀጥሎ ተወስኗል፡፡ ያ - ባይሆን ህጉን ታቅፈው ዐይናቸው እያየ ሀገራቸውን ማጣታቸው ነው፡፡ የሀገሬ ሰው “እዬዬ ሲዳላ” ነው የሚለውም ለዚህ ይመስለኛል፡፡
አሁን ያለው የእኛም የምርጫ ጥድፊያ የሚያሰጋው ለዚህ ነው፡፡ ሀገሪቱ ሳትረጋጋ፣ ያልጠገጉ ቁስሎች ገና ዘይት ሳይጠግቡ፣ የፊታችን ላይ እምባ ሳይደርቅ፣ ወደ ምርጫ ድንኳን መግባቱ ሌላ አሰቃቂና የባሰ መከራ እንዳያመጣ ያስፈራል፡፡
በጥድፊያ በሁለት ጉንጭ የታኘከ ምግብ ዞሮ መግቢያው አንድ ጉሮሮ ስለሆነ መታነቅ ያመጣልና የሰከነ አእምሮ፣ ለሀገርና ለሕዝብ የሚራራ ልብ ቆም ብሎ ሊያጤነው ይገባል፡፡
አለበለዚያ “የሲቲዝን ፖለቲክስ” ደራሲ እንዳሉት፤ “The Political Fanatic who wants a perfect world, and expects now” እንደሚል ይሆንብናል፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ፍፁም የሆነና ያለ ሂደት የሚፈፀም ነገር ስለሌላ አክራሪዎችም ብንሆን ትኩረታችንን በዚህም አቅጣጫ ብናደርግ የሚለው ሃሳብ የሚያስማማን ይመስለኛል፡፡
አሁን ሀገራችን ፊቷ ላይ ሁለት ምርጫዎች ተደቅነዋል። ባንድ ወገን ሀገሪቱን ወደተሻለ ዲሞክራሲና ፍትህ ለመምራት፣ የሀገሪቱን አንድነት በፍቅር አስጠብቆ፣ የተሻለ የምርጫና ሌሎች ዲሞክራሲያዊ መብቶችን በቀጣይነት ለመገንባት የተዘጋጀና በሥራ ላይ ያለው መንግሥት ሀገሪቱን ለጥቂት ጊዜያት እንዲመራ፣ ነገሮችን በተቀናጀ መልኩ ፈር እንዲያስይዝ ጊዜ መስጠት፣ ሕዝቡ ሥነ ልቡናዊ ማህበራዊና ሞራላዊ ዝግጅት አድርጐ፣ ምርጫው ፍትሀዊና  የተሳካ እንዲሆን ማመቻቸት፡፡ ካልሆነ ደግሞ “የነቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ” እንዲሉ፤ በጥድፊያና በስልጣን ምኞት፣ ቀውሱ ሣይረጋጋ፣ ማዕበሉ ሳይሰክን፣ ሰዎች ቀልባቸው ሳይሰበስብ፣ ቂምና በቀላቸው ጠፈፍ ሳይል ምርጫው ይደረግ ብሎ እሳት ውስጥ መግባት! ከዚያም ሀገሪቱን አፍርሰን መፍረስ አሁን ያሉን ዕድሎች እነዚህ ብቻ ናቸው፡፡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሊንደን ቢ ጆንሰን እንዲህ እንዳሉት ማድረግ ብቻ!
“There are two courses open four us, we can meet the challenge, or we can turn away from it. We can master the problem or we can leave it to master us”
ፊታችን የቆመው ዕጣ ይህና ይህ ነው፡፡ መንግሥትም ሜዳውን ማመቻቸት ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱን ከአደጋና ከጥፋት ለመታደግ፣ ያለ ይሉኝታ ከሕዝቡ ጋር መምከር አለበት፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም እንደዚሁ!
“የመንፈስ ከፍታ” የሚለው የበረከት በላይነህ መጽሐፍ፤ ይህንን ጠቃሚ ግጥም አስፍሯል፡፡ እንዲህ፡-
ትርጉም እያዛባ፣ ቃል እያናናቀ፣
ፍቺ እያጣረሰ፣
ከበሽታ ሁሉ የደሃ ኩርፊያ ነው
ሀገር ያፈረሰ
እናንተ ብልሆች
ተስፋ ተስፋ የሚሸት ዕቅድ ስታቅዱ፣
ንቁ ፍኩ እንዲሆን የለውጥ መንገዱ፣
“ካኮረፈ ደሃ” ሃሳብ አትውሰዱ!
ነገሩ እንዲህ ይመስለኛል፡፡ መገናኛ ብዙሀን፣ የፖለቲካ የጥበብ ሰዎች በቸልታ ሊያዩት የማይገባ፣ አስፈሪ ተግዳሮት ነውና፡፡ ከመዝሙርና ቅኔ ያለፈ ጩኸት ልንጮህ፣ ነጋሪት ልንጐስም፣ መለከት ልንነፋ… ሕዝቡን ልናወያይ ይገባል፡፡

Read 956 times