Sunday, 06 January 2019 00:00

የእርስበርስ ግንኙነቶችና ግጭቶች (ይቅርታ ምንድነው? ምንስ አይደለም?)

Written by  ወንድወሰን ተሾመ (የማህበራዊ ሳይንስና የስነልቦና ባለሙያ)
Rate this item
(0 votes)

ክፍል 2
ባለፈው ሳምንት፣ ሶስት ዓይነት የእርስበርስ ግንኙነት አይነቶችን በመጥቀስ፣ ልዩነታቸውንና ጉድለታቸውን ለማሳየት ሞክሪያለሁ፡፡ በእርስበርስ ግንኙነት ሁለት ሰዎች ወይም አካላት በጋራ የሚስማሙበትና አንዱ ከሌላው የሚለይበት ነገር እንዳለ አውቆ፣ በጋራ ጉዳዮች መስማማት እንዲሁም በሚያለያያቸው ነገር አንዱ ሌላውን አክብሮና ተቀብሎ መኖር ተገቢ እንደሆነ በምሳሌ ለማስረዳት ሞክሪያለሁ። በዚህ ውስጥ አንዱ ሌላውን ተቀብሎ ሲኖር በልዩነቱ እየተቸውና እያዘነበት መሆን እንደማይገባ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም  ግንኙነቱን ለመቀጠል የሌላውን ድክመት ወይም ከእኛ የተለየው ማንነቱን ልንሸከመው የምንችለው (bearable weakness or difference) ሊሆን ይገባል፤ ልንሸከመው የማንችለው ድክመት ወይም ልዩነት (unbearable weakness/ difference) እንዳለም ማወቁ አይከፋም፡፡  በዛሬው ፅሑፌ የእርስበርስ ግንኙነትን የሚያዳብሩ ሶስት ምሰሶዎችን (እሴቶችን) ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡
1ኛ ፡ ፍቅር፡- ፍቅር ምንድነው?
“ፍቅር”ን ከታች ከተጠቀሱት ከሶስቱ ዓረፍተ ነገሮች የትኛው በደንብ ይገልፀዋል ብለው ያስባሉ?
ፍቅር ስሜት ነው
ፍቅር ስሜት ያለው ውሳኔ ነው
ፍቅር ውሳኔ ያለው ስሜት ነው
አንዳንድ መምህራንና አሰልጣኞች ከሶስቱ አንዱን ጠቅሰው ሲያስተምሩ ሰምታችሁ ወይም አንብባችሁ ይሆናል፡፡ እኔም በተለያዩ ጊዜያት “ፍቅር ስሜት ነው”፤ “ፍቅር ስሜት ያለው ውሳኔ ነው” ሳልል አልቀረሁም፡፡ ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጉዳዩ ላይ ሳሰላስል፣ እነዚህ ሁለቱም ፍቅርን የሚገልጹት ሆነው አላገኘኋቸውም። ፍቅር ስሜት ብቻ አይደለም። ፍቅር ስሜት ያለው ውሳኔም አይደለም፡፡ ለኔ ፍቅር “ውሳኔ ያለው ስሜት ነው”፡፡ ለምን? ቢባል ፍቅር በተፈጥሮው ስሜት ተብለው ከሚዘረዘሩት እንደ ንዴት፣ ሃዘን፣ ተስፋ ወዘተ መካከል የሚጠቀስ ነው። ፍቅር ስሜት ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል እንደሆነ በስነልቦናና በማህበራዊ ግንኙነቶች ዙሪያ በሚሰሩ ምሁራን አካባቢ ስምምነት አለ፡፡ ስለዚህ ተፈጥሮው ማንነቱን ሊገልፀው ይገባል፡፡ ሆኖም ፍቅር ስሜት ብቻ አይደለም፤ በውስጡ ውሳኔን መያዝ ይገባዋል፡፡ ስለዚህም ፍቅር ስሜት ነው፤ ነገር ግን ውሳኔ አለው፡፡ ውሳኔ አለው ስል ምን ማለቴ ነው? ፍቅር ሊዘልቅ፣ ሊፀና፤ በጊዜ ውስጥ ተፈትኖ ሊያልፍና በሁኔታዎች ላይደናቀፍ ይወሰናል ማለቴ ነው፡፡ ፍቅር ስሜት ብቻ ነው ካልን በመፅሐፍ ቅዱስ ላይ አምኖንና ትዕማር የሚባሉትን ሁለት ሰዎች ያስታውሰናል (2ኛ ሳሙኤል 13፡1-15)፡፡ አምኖን የተባለ ሰው ትዕማርን ከመውደዱ የተነሳ ተከዘ፣ ታመመ፣ አካላዊ ክሳትም (ጉስቁልናም) እንዳጋጠመው እንመለከታለን፡፡ ትዕማርን በዘዴ ቤቱ እንድትመጣ ካደረገ በኋላ በግድ ደፈራት፡፡ ስሜቱ ሲበርድለት ወዲያውኑ “ጠላሁሽ” አላት፡፡ ይህ በስሜት ላይ ብቻ የተመሰረተ መውደድ ነው፡፡ ፍቅር ስሜት ብቻ ሲሆን “ወደድኩሽ” ብሎ ወዲያው ደግሞ “ጠላሁሽ“ ማለት ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል የያዕቆብና የራሄልን ግንኙነት (ዘፍጥረት 29፡18) ያነበበ ሰው ፍቅር እንደማይቸኩል፣ ፍቅር ሁኔታዎችን አልፎ እንደሚሄድ፣ ዋጋ እንደሚያስከፍል ጭምር ያሳያል፡፡ “---ያዕቆብም ራሔልን ለማግኘት ሲል ሰባት ዓመት አገለገለ፤ አጥብቆ ይወዳትም ስለነበረ ሰባት ዓመት እንደ ጥቂት ቀን ሆኖ ታየው፡፡” ይላል፡፡ በመሆኑም ፍቅር ውሳኔ ያለው ስሜት ነው፡፡
በመሆኑም በሁለት ሰዎች መካከል ያለ ግንኙነት፤ አንዱ ሌላውን የሚታገስበት፣ አንዱ ለሌላው ቸርነት የሚያደርግበት፣ አንዱ በሌላው ላይ የማይቀናበት፣ አንዱ ሌላውን የሚያከበርበት፤ አንዱ በሌላው ላይ ሆን ብሎ ጉዳት የማያደርስበትና አንዱ ሌላውን እንዲያድግ፣ እንዲበረታ፣ አቅሙን እንዲያወጣ የሚኮተኩትበት ሊሆን ይገባዋል፡፡ ፍቅር የእርስበርስ ግንኙነትን ውበት ከሚሰጡትና ውጤታማ ከሚያደርጉት ምሰሶዎች አንዱ ነው፡፡
2ኛ፡ ይቅርታ፡- ይቅርታ ምንድነው? ይቅርታስ ምን አይደለም?
ይቅርታ የሚደረገው አንድ ሰው አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት (ምክንያታዊነት በጎደለው ድርጊት) በሌላው ሰው ስምና ክብር ላይ፤ ስሜት ወይም አካል ላይ ጉዳት ሲያደርስ ነው፡፡ አንድ ሰው ያደረገው ነገር ምክንያታዊነት ሲያጣ ይቅርታ መጠየቅ ያስፈልገዋል።
ይቅርታ ሌላው ሰው ባይጠይቅም ለሌላው ሰው የሚሰጥ እሴት ነው፡፡ C.S.Lewis የተባለው እንግሊዛዊ ፀሐፊ በአንድ ወቅት በደል አድርሶበት  ከሞተ ሰላሳ ዓመት የሞላውን ሰው ይቅር ማለቱን ተናግሯል፡፡ ይቅርታ በአብዛኛው ከይቅርታ አድራጊው እርካታ፣ የአዕምሮ ሰላምና ጤንነት እንዲሁም ሃይማኖታዊ እሴት ጋር የሚገናኝ ነው። በዳዩ ሰው ይቅርታ መጠየቅ ሲገባው ይቅርታ ባይጠይቅም፣ ተበዳዩ ይቅርታ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ዶክተር ዳንኤል አሚን የተባለውና በአሜሪካን አገር በአዕምሮ ህክምና ማዕከልነቱ የሚታወቀው የአሚን ክሊኒክ ባለቤት ቀደም ሲል ይቅርታ በሃይማኖታዊ ጉዳይ እንደሚታወቅ (ለምሳሌ መፅሐፍ ቅዱስ “ይቅር ብትሉ የሰማዩ አባታችሁ ይቅር ይላችኋል’’ እንደሚለው) ገልፆ፣ አሁን ግን ኒውሮ ሳይንቲስቶች ይቅርታ የአዕምሮ ጤንነት ጉዳይም ጭምር እንደሆነ በጥናታቸው እንዳረጋገጡ  በስነ-አዕምሮ ዙሪያ በፃፈው መፅሐፉ ላይ አስነብቧል፡፡
በቤተሰቦቻቸውና በራሳቸው ላይ ከፍተኛ ቅሬታ ይዘው ለስነልቦና ምክር ወደ ቢሮዬ (የዚህ ፅሑፍ አቅራቢ ቢሮ) የሚመጡ ሰዎችን ይህንኑ ሳይንሳዊ እውነታ ገልጬላቸው፣ ራሳቸውንና ሌሎችን ሰዎች ይቅር ማለት የሚሰጠውን ጠቀሜታ በማሳወቅ ይቅር እንዲሉ አበረታታቸዋለሁ፡፡ ራሳቸውን ይቅር የሚሉት ማድረግ ሳይገባቸው ላደረጉትና ማድረግ ሲገባቸው ሳያደርጉት ለቀሩት ጉዳይ ነው (ስለሚፀፅታቸውና ስለሚቆጫቸው ጉዳይ ማለት ነው)፤ ሌሎቹን ይቅር የሚሉት ደግሞ ስላደረሱባቸው ስነልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም አካላዊ ጉዳት ነው። ይቅርታ ማድረግ የሚከብዳቸው በርካታ ሰዎች አጋጥመውኛል፤ ይቅርታ ከማድረጋቸው በፊት የበደላቸውን ሰው ቢያንስ አንዴ እንኳን ቢሆን ሊጎዱት ይፈልጋሉ፡፡ ጉዳቱንም ካደረሱ በኋላ ይቅር ለማለት እንደሚችሉ ያስባሉ፡፡ ይህ ግን የበቀል ስሜትና ሌላ ጥፋት ነው፡፡ ይቅርታ፤ የተበደለውንም ሆነ በዳዩን ሰው ነፃ የሚያወጣ ትልቅ መሳሪያ ነው፡፡
በይቅርታ ዙሪያ በርካታ የሃይማኖት ሰዎችና ሌሎች ፀሐፍት ትንተና ሰጥተውበታል፡፡ ከእነዚህ መካከል ጆን ኦርትበርግ የተባለ ፀሐፊ  በግንኙነት ዙሪያ ባተኮረው መጽሐፉ ያስቀመጣቸው ነጥቦች መልካም ሆነው አግኝቻቸዋለሁ፡፡  እነሱን ነጥቦች ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ስለ ይቅርታ የተወሰኑ ጉዳዮችን ለማንሳት እሞክራለሁ፡፡
ይቅርታ የሚከተሉትን ማለት አይደለም፡-
ይቅር ማለት መርሳት ማለት አይደለም፡- መርሳት የማስታወስ ችሎታ ከማጣት ጋር የሚያያዝ ነው። በተለይ መርሳት የማንችላቸውን በደሎች የምናሸንፋቸው ይቅር በማለት ብቻ ነው፡፡ ይቅር ስንል ጉዳዩን እንተወዋለን እንጂ አንረሳውም፤ ይቅር ስንል ጉዳዩን እያነሳን አናወራም፣ አንኮንንም፤ ሌላውን ሰው አናሳቅቅም ማለታችን ነው፡፡
ይቅር ማለት እንደገና አብሮ መቀጠል ላይሆን ይችላል፡፡ በአብዛኛው ይቅርታ ከተደረገ በኋላ ግንኙነቶች ይቀጥላሉ፡፡ በዳዩ በተፀፀተበትና ባህርዩን ባስተካከለበት ሁኔታ ይቅርታ ግንኙነቱ እንዲቀጥል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ሆኖም ይቅር ማለት አንድን መጥፎ ባህርይ ያለበትን ሰው ባህርዩን ሳያሻሽል እየታገሱት አብሮ መቀጠል ማለት ላይሆን ይችላል፡፡ በምሳሌ ለማየት እንሞክር፡-
አንድ የንግድ አጋር በተደጋጋሚ ታማኝነትን ቢያጎድል፣ ይቅር ብለኸው ግንኙነቱን ግን ልታቋርጥ ትችላለህ፡፡
አንዲት ሴት በእጮኝነት አብሯት የነበረ ሰው የግብረሰዶም ተለማማጅ ሆኖ በመገኘቱ፣ አንድ ቀን ያስተዋወቀችውን ታናሽ ወንድሟን በዚሁ የጾታዊ ትንኮሳ ውስጥ በተደጋጋሚ ሊያስገባው ሲሞክር በማየቷና እርግጠኛ በመሆኗ ግንኙነቱን አቋርጣለች፤ ነገር ግን ይቅር ብለዋለች፡፡
ይቅር ማለት ፍትህን መተው ማለት አይደለም። የተደፈረች ሴት የደፈራትን ወንድ ይቅርታ ልታደርግለት ትችላለች፡፡ የደፈራት ሰው ግን እዳውን ለማህበረሰቡ ሊያወራርድ ይገባል። ይህም ማለት ክስ ተመስርቶበት ፍርዱን ሊያገኝ ይገባል፡፡ ፍትህ ሲኖር የሌላውን ባህሪ ያቃናል፤ ጤናማ ማህበረሰብ እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡
ስለዚህ ይቅርታ ጉዳቱን መርሳት አይደለም፣ ፍትህን መተው ማለት አይደለም፤ግንኙነቱንም የግድ መቀጠል ማለት አይደለም፡፡ ሆኖም በይቅርታ የሚቀጥሉ ግንኙነቶች በርካታ ናቸው፡፡ ተጣልቶ መታረቅ የበሳሎች ችሎታና ድርጊት ነው፡፡ ታርቀው ግንኙነቱን ሲቀጥሉ ግን ያጋጫቸውን ጉዳይ በመፍታት ሊሆን ይገባል፡፡
ይቅርታ የሚከተሉትን ማለት ነው፡-
ይቅርታ የጎዳህን ሰው በጎዳህ መልክ ለመጉዳት አለመፍቀድ ነው፡፡ ይቅርታ ስታደርግ ሌላውን ሰው መልሰህ ላለመጉዳት መወሰንህ ነው። በሌላው ሰው መክሰር፣ መዳከም፣ መዋረድ ወዘተ ከመደሰት መታቀብ ነው፡፡ ይቅርታ በጎዳህ ሰው ላይ ስነልቦናዊም ይሁን አካላዊ በቀል ለማድረግ ጊዜ ከመጠበቅ መቆጠብ ነው። አንዳንድ ሰዎች የበደላቸውን ሰው ለመበቀል ጊዜና ሁኔታን እየጠበቁ ይኖራሉ። እነዚህ ሰዎች የበዳያቸው እስረኛ ሆነው መኖራቸውን አይረዱም፡፡
ይቅርታ አዲስ ስሜትና አዲስ እይታ/አስተሳሰብ/ መጎናፀፍ ነው፡፡ ይቅርታ ከጉዳታችን በላይ ከፍ ያለን ነገር ማየት ነው። ሰው መሆንን፣ በእግዚአብሔር አምሳል መፈጠርን ወዘተ--
በእርስበእርስ ግንኙነት ውስጥ ግጭቶች ይኖራሉ፤ አንዱ ሌላውን የሚያሳዝንበት ጉዳይ ይፈጠራል። በመሆኑም ይቅርታ ማድረግ ግጭቶችን ለማርገብ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ ይቅርታ የሌላውን ሰው ግለት ማብረጃ ነው፣ ይቅርታ “ደግመህ ተመሳሳይ ነገር አታድርግ” ብሎ መልዕክት ማስተላለፊያ ነው። በመሆኑም ይቅርታ ለእርስበእርስ ግንኙነት አንዱ ሌላው ምሰሶ ነው፡፡
3ኛ፡- እምነት መጣል (Trust)፡- አንዱ ሌላውን ማመን ነው፤ መጠራጠር የሌለበት ግንኙነት ሲኖር ማለት ነው።
አንዳችን ሌላችንን የምናምንበት መጠን ምን ያህል ይሆን? በአንድ ግንኙነት ውስጥ ምንም መተማመን ከሌለ ግንኙነቱ ዋጋ የለውም፡፡ በአንድ ወቅት አንዲት ሴት ከትዳር አጋሯ ጋር በተፈጠረ ችግር “ለዚህ ሰው (ባለቤቷን ማለቷ ነው) ፍቅር አለኝ፤ ይህን ሰው ይቅርታም አድርጌለታለሁ፤ ነገር ግን ከእንግዲህ ይህንን ሰው እንዴት አምነዋለሁ?”  የሚል ጥያቄ ጠየቀችኝ (የዚህን ጽሁፍ አቅራቢ)፡፡ የመለስኩላት መልስ በትዳር አጋሯ በኩል እምነት መጣል የሚያስችሉ የባህሪ ለውጦች እያየች ስትሄድ፣ በትዳር አጋርዋ ላይ እምነት መጣል እንደምትጀምር፤ እምነት መጣል ህይወት እንዳለው፤ እንደሚያድግና እንደሚጎለብት አስረድቼያት፣ ይህንን ታሳቢ በማድረግ እሷም ሆነች የትዳር አጓሯ ግንኙነታቸውን ለማሻሻል በአዲስ እይታ መቀጠል እንደሚገባቸው መክሬያታለሁ። ከትዳር አጋሯም ጋር ባሳለፍኩት የካውንስሊንግ ጊዜ፣ በእሱ በኩል ለመሻሻል ቁርጠኝነት እንዳለ በማስረዳት አመለካከቷ ላይ ሰርቻለሁ፡፡ ከአመታት በኋላም ተሳክቶላት አይቼአለሁ፡፡ በመሆኑም እምነት መጣል በግንኙነቱ ውስጥ አንዱ ለሌላው በሚያሳየው እውነተኛነት፣ ግልጽነትና ቅንነት ሊያድግና ሊበለፅግ እንደሚችል መረዳቱ አስፈላጊ ነው፡፡  በመሆኑም በእርስበርስ ግንኙነት ውስጥ መተማመን ሌላው ምሰሶ ነው፡፡
በሁለት ተከታታይ ጽሁፎች ስለ እርስበርስ ግንኙነት የፃፍኩትን ፅሁፍ ከማጠናቀቄ በፊት በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚታዩ ችግሮች መካከል ምናልባትም አንዱና ዋነኛው፣ የእርስበርስ ግንኙነት መርህ አለመኖርና አንዱ ከሌላው የተለየ አስተሳሰብ ሲያንጸባርቅ በሌላው የሚሰጠው አሉታዊ ምላሽና ፍረጃ ነው፡፡ ይህ ከቤተሰብ ይጀምርና እስከ ማህበረሰብ፣ ሚዲያ ወዘተ ይዘልቃል። ይህም በመሆኑ በርካታ ግጭቶች በየቦታው ይስተዋላሉ። ስሜትን መሰረት አድርገው የሚፈጠሩ ግጭቶች በርካታ ናቸው፡፡ ሰው ግን ስሜት ብቻ አይደለም ያለው፡፡ ቆም ብሎ የሚያስብ አዕምሮም አለው፡፡ የስሜቱ መኖር አዕምሮን እንዲያስብ፣ እንዲያመዛዝንና አርቆ እንዲመለከት ሊያደርገው ይገባል፡፡ በመበቃቀል፣ በፍረጃና በራስ ወዳድነት ውስጥ የሚያልፍ የእርስበእርስ ግንኙነት ለኢትዮጵያ ራስ ምታት ነው፡፡ በመሆኑም ፍቅርን፣ይቅርታንና እርስበርስ መተማመንን የሚፈጥሩ ትምህርቶች፣ ስልጠናዎች፣ ፊልሞች፣ ድራማዎችና ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች በብዛት ያስፈልጉናል፡፡ በአንድነት ውስጥ የጋራ ነገር አለ፤ ሆኖም አንድ አይነት ነገር እያደረግንና አንድ አይነት ነገር እያሰብን እንኑር ካልን፣ የእርስበርስ ግንኙነታችን ላይ ከፍተኛ ችግር ስለሚፈጥርብን በጋራ እየኖርን፣ ልዩነቶችን ማክበር መልካም ነው እላለሁ፡፡
መልካም የገና በዓል!!
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡-  This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 371 times