Sunday, 06 January 2019 00:00

መጪዎቹን ዓመታት ማሳመር እንችል ይሆን?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)


   • “ነፃነት” - ያለ ግል አእምሮ፣... ያለ እውነትና እውቀት?
   • “መብት” - ያለ ግል ንብረት፣... ያለ ትጋትና ምርታማነት?
   • “ፍትህ” - ያለ ግል ማንነት (ያለ እኔነት)፣... ያለ ብቃትና የራስ ሃላፊነት?
           

     1. ነፃነት፣... ያለ እውነትና ያለ እውቀት አይዘልቅም!
የታፈነ አፍ ከልጓሙ ስለተገላገለ ብቻ፣... “በአውቶማቲክ” እውነትን የሚመሰክር እውቀትን የሚያስተምር አንደበት ይሆናል? ይሄንን ጥያቄ ጨርሶ የዘነጋነው ይመስላል።
ባለፉት ጥቂት ወራት፣ በተለያዩ አጋጣሚዎች፣ ጠ/ሚ አብይ አህመድ፣... ለ”እውነት” ትልቅ ትኩረት መስጠት፣ እጅጉን አስፈላጊ እንደሆነ በተደጋጋሚ ለመግለፅ ሞክረዋል። በእርግጥም፣ “እውነት”፣ የሁሉም ነገር መሠረት ነው። አንዴ ወይም ሁለቴ ብቻ ሳይሆን፣ ደጋግመው እውነት ላይ እንድናተኩር ቢናገሩ እንኳ፣... ትኩረት የመስጠት አዝማሚያ ብዙም አይታይም።
ተራው ዜጋ ብቻ ሳይሆን፣... የተማሩ፣... ከዚያም በላይ፣... ትምህርትን የመምራት፣ “የትምህርት ፍኖተካርታ” የተሰኘውን ሰነድ የማዘጋጀት አልያም የመቀየር ስልጣን የተሰጣቸው ምሁራን እንኳ፣... ለ”እውነት” ቀዳሚ ትኩረት የመስጠት አስፈላጊነትን የሚደግፉ ሳይሆን የሚቃወሙ ነው የሚመስሉት።
ለ”እውነት” ቀዳሚ ትኩረት ከመስጠት ይልቅ፣... (ማለትም፣... “መረጃን ከእውኑ ተፈጥሮ ጋር በማመሳከር እውነትን ማረጋገጥ፣... እውነትን በማገናዘብ ደግሞ እውቀትን በቅጡ መጨበጥ”፣... ዋነኛውና መሠረታዊው የትምህርት አላማ እንደሆነ ተዘንግቶና ተጠልቶ)፣... እውነትና እውቀት ላይ ያልተመሰረተ፣... “ምናባዊ ፈጠራ፣ የሃሳብ ፍጭት፣ ብዝሃነት፣...” ምናምን... የተሰኙትና ነባሮቹን ቀሽም ሃሳቦች እንደ አዲስ ሃሳብ አግዝፎ የሚያባብስ ነው - የትምህርት ፍኖተ ካርታው።
ለ25 ዓመታት በአገሪቱ የትምህርት ፖሊሲ ውስጥ የነበሩ፣ የተሳሳቱና ውድቀትን ያስከተሉ ሃሳቦች፣... እንደገና በአዲስ መልክና ሃይል መድገም፣... ተጨማሪ ውድቀትን እንጂ፣ የተለየ ውጤት አያስገኝም።
ትምህርት ቤትን እንደ ፌስቡክ የማድረግ ያህል ቁጠሩት። “ሳይንሳዊ ዘዴ”... ድሮ ድሮ ተረስቷል ወይም ተወግዟል። “ሳይንሳዊ ዘዴ፣... ትክክለኛው ዘዴ ነው” ብሎ መናገር እንደ ወንጀል እንደ አምባገነንነት የሚቆጠር እየሆነ ነው፡፡ እውነትና እውቀት ላይ ያተኮረው ሳይንሳዊ ዘዴ፣... “ምናባዊ ፈጠራን፣ ብዝሃነትን፣ የሃሳብ ፍጭትንና ነፃነትን የሚገድብ አፋኝ አምባገነንነት” እንደሆነ ተቆጥሮ ወዲያ ተሽቀንጥሮ ተወርውሯል። እናስ?
እውነትንና እውቀትን ጥለህ፣ በስሜት የመጣለትን የተሳከረ ሃሳብ እየጎተተ፣ ወይም የሰማችውን ቁርጭራጭ ንግግር በጭፍን የማራገብ ነፃ ውይይት? እሺ ይሁን። ስለ ፕሪሚዬር ሊግም ሆነ ስለ ፖለቲካ ምርጫ በጭፍን ስሜት የመወያየት ነፃነት አለኝ የሚል ሰው፣ ስፖርቱም በግርግር ተቋርጦ፣ ምርጫውም በግጭት አገርን አተራምሶ መጨረሻው አያምርም እንጂ... ለጊዜው እድል አግኝቶ በነፃነት ሊወያይ ይችላል። ነገር ግን፣ እንዲህ አይነት ውይይት፣ የመሳከር ቅዠት እንጂ የእውቀት፣የትምህርትና የመግባባት ዓለም ሊሆን አይችልም።
“እውነትና እውቀት ላይ ያልተመሰረተ”፣... “ምናባዊ ፈጠራ፣ የሃሳብ ፍጭት፣ ብዝሃነት”... በጎ ከመሰለንና ከናፈቀን፣... ፌስቡክ ላይኮ ሞልቶ ተትረፍርፎልናል። በጭፍን የመሳከር፣ የመበሻሸቅ፣ በስድብ የመናቆርና የመወነጃጀል ድግስ ሲጧጧፍ ደግሞ ውጤቱ ምን እንደሚመስል በአሳዛኝና ዘግናኝ መዘዞቹ እለት በእለት እያየን ነው።
ነፃነት፣... ያለ እውነትና ያለ እውቀት ብዙም አይዘልቅም ለማለት ፈልጌ ነው።
ለእውነትና ለእውቀት ቀዳሚ ትኩረት የሚሰጥ ብዙ ሰውና ጠንካራ አስተሳሰብ ከሌለ፣... ነፃነትን የሚፈልግ ብዙ ሰው አይኖርም። ነፃነት በአጋጣሚ ብቅ ቢል እንኳ እድሜ አይኖረውም።
በሌላ አነጋገር፣... እንደመታደል ሆኖ፣ የታሰረው ምላስ ድንገት ስለተለቀቀ ብቻ፣ የታፈነውም አፍ ከልጓሙ ስለተገላገለ ብቻ፣... “በአውቶማቲክ” እውነትን የሚመሰክር እውቀትን የሚያስተምር አንደበት ይሆናል ማለት አይደለም።ያ፣... የእያንዳንዱ ሰው የግል ሃላፊነት ነው - ሰው የመሆን ክብርን የሚያቀናጅ ቅዱስ ሃላፊነት።
2.”መብት” - ያለ ግል ንብረት፣... ያለ ትጋትና ምርታማነት ትርጉም ያጣል!
ታስረው የነበሩ እጆች ከዛሬ ጀምሮ ነፃነትን ቢያገኙ እንኳ፣... እነዚያ እጆች “በአውቶማቲክ”ና በአንዳች ተዓምር፣ “የስራ ወዳድና የስኬታማ ባለሙያ ጥበበኛ እጆች” ይሆናሉ? ይሄንንም ጥያቄ ዘንግተነዋል።
በአላስፈላጊ የመንግስት ቁጥጥርና ክልከላ፣ በታክስ ጫና፣ በየጊዜው በሚፈለፈሉ የዘፈቀደ ህጎችና ደንቦች፣... ማንኛውም አምራች ሰው፣ በማንኛውም ወቅት ወደ ኪሳራና ወደ እዳ አዘቅት ተገፍቶ ሊወርድ ይችላል። ግን፣ የመንግስት ብቻ አይደለም ሃጥያቱ። በመንግስት ሳቢያ ተተብትበውና የተሳስረው መፈናፈኛ ያጡ እጆች ነፃ ቢለቀቁ እንኳ፣ የተሟላ መፍትሄ አይሆንም።
“እጁ ተፈታ” ማለት፣ እዚያው በዚያው “ምርጥ የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋች ሆነ” ማለት አይደለም... የሚለውን አባባል ማስታወስ ይቻላል። “ሰርቶ ንብረት የማፍራት ነፃነትን” ከምር መሻት የምንችለው...  ምንነቱን፣ ፋይዳውንና ቅዱስነቱን ከምር መገንዘብና ከምር ክብር መስጠት የምንችለው፣... መስራትንና ንብረት ማፍራትን ወድደን የምናከብር ከሆነ ነው። ለፋብሪካና ለስራ ትጋት፣ ለምርታማነትና ለብልፅግና ከፍ ያለ ክብር የሚሰጥ አስተሳሰብ፣ የተግባር መርህ፣ ስብዕናና ባህል ያስፈልጋል። በሃሳብ፣ በተግባርና በመንፈስ... መሆኑ ነው።
ነገር ግን፣ በትጋት ሰርቶ ንብረት ማፍራትን የሚያከብር የብልፅግና ባህል ገና ለምልክት ያህል እንኳ አላቆጠቆጠም። ሊያቆጠቁጥ ይቅርና፣ አስፈላጊነቱንም ገና በወጉ የተገነዘቡ ዜጎች በጣም ጥቂት ናቸው። እናም፣... መንግስት እጆቹን ከጥፋት ቢሰበስብና ነፃነትን ከመጣስ ቢቆጠብ እንኳ፣...” የፋብሪካ ስራ ከዛሬ ጀምሮ እየለመለመ ይሰምራል፤ አብቦ እያፈራ ነጋችንን ያሳምራል”... ማለት አይደለም።
“የሁሉም ችግር መንስኤ፣ የሁሉም ነገር መፍትሄ” መንግስት ቢሆንልንና... መንግስት ከጥፋት ሲቆጠብልን፣ “በአውቶማቲክ”... “ችግር ሁሉ አበቃ፣ ምኞት ሁሉ ተሳካ” ወደሚያስብል ዓለም የምንገባ ከመሰለን ተሳስተናል። ወይም እየተሞኘኝ ነው፣ አልያም ራሳችንን እያታለልን።
እንዲያው እንደመታደል ሆኖ፣ መንግስት ጤናው ቢሻሻልና ነፃነትን ለማስከበር በህጋዊ ስርዓት ወንጀለኞችን ከማሰር በቀር፣ ከዚያ ውጭ በዘፈቀደና አላግባብ የስራ እጆችን ማሰር ቢያቆም አስቡት።... ደስ ይላል። ነገር ግን፣ በአላስፈላጊ የዘፈቀደ ቁጥጥርና ክልከላ በከንቱ ታስረው የነበሩ እጆች ዛሬውኑ  ነፃነትን ቢያገኙ እንኳ፣... እነዚያ እጆች “በአውቶማቲክ”ና በአንዳች ተዓምር፣ “የስራ ወዳድና የስኬታማ ባለሙያ ጥበበኛ እጆች” ይሆናሉ ማለት አይደለም። ለምን? በሁለት ምክንያቶች!
አንደኛ ነገር፣ ምቀኝነትንና ውድመትን በሚፈቅድ ኋላቀር ፀረ ብልፅግና ባህል ሳቢያ፣ ያኛው ፋብሪካ መቼ በአመፅ እንደሚዘረፍና ይሄኛው ፋብሪካ መቼ በነውጠኞች እንደሚቃጠል አይታወቅም። ሁለተኛ ነገር፣ የስራ ፍሬህን የሚነጥቅ መንግስትና ወሮበላ፣ ወይም የሚያቃጥል ነውጠኛና ምቀኛ ባህል ባይኖር፣ የነፃነት እድል ድንገት ቢስፋፋ እንኳ፣ “ንብረት” በዚያው ቅፅበት ከስር በነፃነት የሚበቅል፣ ወይም ከላይ በነፃነት የሚዘንብ ተዓምር አይደለም። ንብረትን ለማፍራት በነፃነት የሚጥር የስራ ሰው (የአላማ፣ የትጋትና የብቃት ሰው) ያስፈልጋል።
ብዙ ጊዜ የምንታዘበው ግን፣... “መንግስት ነፃነትን ያክብር፣ ያስከብር” ምናምን ተብሎ ሲነገር፣... በቃ ሁሉም ነገር እንደሚሟላ በሚያስመስል ስሜት ነው።    
“ሰርቶ ንብረት የማፍራት ነፃነት”፣ ከፀረ ብልፅግና አስተሳሰብና ባህርይ ጋር፣  ከፀረ ስልጣኔ ባህል ጋር አይሄድም፡፡ ትርጉምም፣ ውጤትም፣ እድሜም አይኖረውም። “ሰርቶ ንብረት ማፍራትን” የሚያከብር የብልፅግና ባህል እና ባህርይም፣ ከነፃነት ጋር እንጂ ከዘፈቀደ ክልከላና ከዘረፋ ጋር አብሮ አይሄድም፤ ቀስ በቀስም እየመነመነ ይመክናል እንጂ አይዘልቅም።
በአጭሩ፣ ስራ ወዳድ ታታሪ ጥበበኛ እጅ፣... ስራውን በትጋት ለውጤት ለማብቃትና ለማፍራት ይፈልጋልና፣ በእጅጉ ነፃነትን ይሻል፣ ይወዳል፣ ያከብራል፣ እንዲስፋፋ ማድረግም ይችላል። ነፃነት፣... ከምር ትርጉም የሚኖረውና ወደሚያምር ለውጥ የሚደርሰው፣... በሃሳብ፣ በተግባርና በመንፈስ፣... አእምሮውን ተጠቅሞ እያወቀ፣ ለራሱ ሕይወት ዋጋ በሚሰጥ ጎዳና ስኬትን አልሞ እየተጋ፣ ለዚህም ብቁና ንፁህ ሰብዕናን እየገነባ ለመኖር በሁለመናው የሚጣጣር ሰው ሲበራከት፣... ለዚህም መሰረት የሚሆን ትክክለኛ የስነምግባር መርህ ሲጎላ፣ ቀስ በቀስም ብቃትንና ስኬትን ከሚያደንቅ ቅንነት ጋር፣ እያንዳንዱን ሰው በብቃቱ፣ በተግባሩና በባህርይው የሚመዝን፣... ብሩህና ስልጡን ባህል እያቆጠቆጠ፣ መሬት እየያዘ ሲሄድ ነው።
“ሰርቶ ንብረት ማፍራትን” የሚያከብር ባህል ሲያቆጠቁጥ፣... “ሰርቶ ንብረት የማፍራት ነፃነት” በመንግስት የሚከበርበት እድል እንዲስፋፋ ያግዛል። በዚያው መጠን፣ በመንግስት በኩል ነፃነትን የማክበር ጅምር ሲታይና ሲሻሻልም፣... “ሰርቶ ንብረት ማፍራትን” የሚያከብር ባህል እንዲለመልም ያግዘናል - እንዲጠወልግ ሳይሆን እንዲለመልም የሚፈልግ ሰው ካለ፣... ሰርቶ ንብረት ማፍራትን በሙሉ ሃሳብ፣ በሙሉ ልብና በሙሉ መንፈስ የሚያከብር ሰው ካለ። ከሌለስ?
ከሌለ፣... ያው፣... ስራን የጠላ ከንቱ እጅ፣... ነፃ ቢሆንም እንኳ፣ ታታሪና አምራች፣ ጥበበኛና ስኬታማ እጅ እንዲሆን ይገደዳል ማለት አይደለም። ነፃነት ማለት፣... ትጉህ ወይም ሰነፍ፣ አምራች ወይም ተመፅዋች፣ ሃብት ፈጣሪ ጥበበኛ ወይም ሃብት ዘራፊ ነውጠኛ፣ ስኬታማ ወይም ምቀኛ የመሆን ግዴታ ማለት አይደለም። ሰርቶ ንብረት ማፍራትን አይከለክልም፤ የስራ እጆችን ከትጋት ለማሰናከል አያስርም። በዚያው ልክ፣ ሰርቶ ንብረት የማፍራት ግዴታን አይጭንም። በግዴታ የማሰራት ባርነትንም አያውጅም።
ነፃነት፣ የስራ ፍሬህን አይነጥቅም፣ ስኬትሽን አይዘርፍም። ግን በዚያው ልክ፣ ፍሬ ልሁንልህ፣ የስኬት ዋስትና ልስጥሽ የሚልም አይሆንም።
3. “ፍትህ” - ያለግል ማንነት (ያለእኔነት)፣...ያለብቃትና የራስ ሃላፊነት አይዘልቅም!
ምርጫ ቦርድን፣ ፍርድ ቤትን በትክክል የሚመሩ ባለሙያዎች ስለተገኙ ብቻ፣ ምርጫው ከውዝግብ ይድናል? የፍርድ ቤት ዳኝነት ይከበራል? ይሄንንም ጥያቄ ሸሽተነዋል።
የዘመናችን መፈክር፣... “የሕግ የበላይነት” ሳይሆን፣ “አሳታፊ፣ ውይይት፣ የሕዝብ ጥያቄ”... ምናምን የሚል ነው። ትክክለኛ ሕግ እና ሥርዓት የሚል መመዘኛ ሳይሆን፣... “ገለልተኛ” የሚል ሆኗል - ወሬያችን ሁሉ። ለምን? ከዚያስ?... የማይጥመንን ዳኝነት በጭፍን ለማጣጣልና ለማውገዝ ይመቻል - “አላወያየንም፣ የሕዝብን ጥያቄ አይመልስም፣ ገለልተኛ አይደለም” በማለት።
በሌላ አነጋገር፣... ለውዝግብ፣ ለፀብና ለግርግር ነው የምናመቻቸው። ያኔ ሰላም ሲጠፋ፣... እንደገና እናማርራለን።

Read 2264 times