Sunday, 06 January 2019 00:00

አዳም ረታና የኤግዚስቴንሻሊዝም ፍልስፍና

Written by  መኮንን ማንደፍሮ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(6 votes)

 ማጠቃለያ  
በሁለተኛው ክፍል በደራሲ አዳም ረታ የሥነ-ጽሑፍ ሥራዎች ውስጥ የሚገኙ መሠረታዊ የኤግዚስቴንሻሊዝም ፍልስፍና ርእሰ ጉዳዮችን መዳሰሴ ይታወቃል፡፡ ይህ ሦስተኛው ክፍል ማጠቃለያ ነው፡፡
ባይተዋርነት (estrangement) የኤግዚስቴንሻሊዝም ፍልስፍና አትኩሮቱን ካዳረገባቸው መሰረታዊ ርእሰ ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ ይህ ርእሰ ጉዳይ በአዳም “ግራጫ ቃጭሎች” የፈጠራ ሥራ፣ በዋናው ገፀ-ባሕሪ መዝገቡ ዱባለ ታሪክ ውስጥ ተገልፆ ይገኛል፡፡ ታሪኩ ውስጥ ገፀ-ባሕሪው በንፋስ መውጫ ሳለ የልጅነት ጊዜውን ከሰው ርቆ ከሚኖርበት ከተማ መሐል ከሚገኘው ጉብታ ላይ ዘወትር ብቻውን ተቀምጦ በመዋል ጊዜውን ያሳልፍ ነበር፡፡ እንደ ኤግዚስቴንሻሊዝም አስተምህሮ አንዱ የባይተዋርነት (estrangement) ስሜት መነሻ፣ ግለሰቡ ከሚኖርበት ማህበረሰብ ጋር ያለው የሞራልና የአመለካከት ርዕዮተ-ዓለም ተቃርኖ ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩም የመዝገቡ የብቸኝነት (ገለልተኝነት) ስሜት መነሻ አብሮት ከሚኖረው ማህበረሰብ ጋር ያለው የህልውና ርዕዮተ-ዓለም ተቃርኖ ነው፡፡
… ይህ ሁሉ ሕዝብ የዚችን ፀሐይ አወራረድ ሳያይ በየቤቱ ሲገባ ቅር አይለውም እላለሁ፡፡  በየቤታቸው ምን ይሠራሉ እላለሁ፡፡ የሚሠሩትን አስቤ አስቤ ከጥቂት  ነገሮች የበለጠ መዘርዘር አልቻልኩም፡፡ ይኼ ሁሉ ሕዝብ እነዚህን ትንሽ ትንሽ የመሠሉ ነገሮች ይሠራል፡፡
ራት ይበላሉ (ካልበሉ ስለሚራቡ)
ይጠጣሉ (ካልጠጡ ስለሚደርቁ)
ይጫወታሉ (ካልተጫወቱ ስለሚያብዱ)
ይተኛሉ (ካልተኙ ስለሚደክማቸው)
ያወራሉ (? )
እኔ በማትደክም ቂጤ ተቀምጫለሁ፣ በማይደክሙ ዐይኖቼ ዙሪያ ገባየን አያለሁ፣ እዚያው እንደተቀመጥኩ ይመሻል፡፡ ጥቁሩን ሰማይ ማጥናቴን እቀጥላለሁ፡፡ ከዋክብት እቆጥራለሁ፡፡ ሁልጊዜ ከዋክብት ለመቁጠር እሞክራለሁ (አዳም፣ ግራጫ ቃጭሎች፣ ገፅ4፣ 1997)።
… በየቤታቸው ያሉትን ሰዎች ከእኔ የሚለያቸው አንድ ትልቅ ጉዳይ ከሌሎች ሰዎች ጋር መሆናቸው ነበር፡፡ እኔ እዚያች መልዕልት ላይ ብቻየን  ነበርኩ፡፡ ከቤቴ ደሞ ተጨንቆ ራት እንድበላ የሚጠራኝ ማንም የለም፡፡ ሁለመናየ እንደሌሎች ቢሆንም የምቀርበው፣ የማፈቅረው፣ የማምነው ህፃን ጓደኛ አልነበረኝም (ዝኒ ከማሁ)፡፡
በአንድ ግለሰብ ሕይወት ውስጥ ያሉ አንዳንድ ነባራዊ ነገሮች (የግለሰቡ ቁመት፣ የተወለደበት ቦታ፣ የሚናገረው ቋንቋ፣ የሚኖርበት ጊዜ፣ ብሔር፣ የተወለደበት ቤተሰብ፣ የቆዳ ቀለም፣ ሞት… ወዘተ) ግለሰቡ በራሱ ውሳኔ ሊለውጣቸው የማይቻሉ፣ ወደ ህልውና ሲመጣ አብረውት የነበሩ ሐቆች ናቸው። ይህን አይነቱን ግለሰባዊ ሁኔታ ሳርተር ነባራዊ ሐቅ (facticity) ብሎ ይጠረዋል፡፡ ይህ ርእሰ ጉዳይ በአዳም የልብወለድ ሥራ ግራጫ ቃጭሎች ውስጥ ተዳስሶ ይገኛል፡፡  
… መሆን የምመኛቸውን ግን መሆን የማልችላቸው ብዙ ነገሮች ነበሩ፡፡ እድሜዬ ልጅ ነው ታድያ ሚስት ማግባት እችላለሁ አልችልም፡፡ ስለዚህ ሚስቶችን አያለሁ፡፡ ፀሐይን መሆን እችላለሁ እልችልም፡፡ ስለዚህ ፀሐይን አያለሁ (አዳም፣ ግራጫ ቃጭሎች፣ ገፅ 7-8፣ 1997)፡፡
እኩይ አመለካከት (self deception) ሌላኛው “ግራጫ ቃጭሎች” ውስጥ የሚገኝ ዐቢይ የኤግዚስቴንሻሊዝም ፍልፍስና ፅንስ-ሐሳብ ሲሆን መጽሐፉ ውስጥ በስፋት ተዳስሶ ይገኛል፡፡ አንድ ግለሰብ በእኩይ ሥነ-ልቦናዊ አመለካከት (bad faith) ውስጥ ሲሆን በህልውና ውስጥ ለሚፈጠሩ ነገሮች፣ ግላዊ ውሳኔው የራሱ እንደሆነ ያለውን ግንዛቤ ይሸሻል፣ ስለሆነም በኑሮው ለሚከናወኑ ነገሮች ሁሉ ኃላፊነቱን የሚወስድ ሌላ አካል አለ ብሎ ያምናል፡፡ የዚህ ፅንሰ ሐሳብ ተቃራኒው ትክክለኛ አመለካከት (good faith) ወይም እውነተኛነት (authenticity) ነው፡፡ አንድ ግለሰብ እውነተኛ ነው የሚባለው ያለምንም ይሉኝታ በነፃነት ራሱን ሆኖ ሲኖር፣ የራሱን ህልውናዊ ነባራዊ ሁኔታ ለመለወጥ ሙሉ ኃላፊነትን ሲወስድና ትክክለኛ ማንነቱን ሲቀበል ነው፡፡ ይህ ፅንሰ-ሐሳብ በመጽሐፉ ዋና ገፀ-ባሕሪ መዝገቡ እንጀራ እናት ግላዊ ሰብዕና  ውስጥ ይገለፃል፡፡ የመዝገቡ እንጀራ እናት (እእ) በግል ለምታደርጋቸው ማናቸውም አይነት ድርጊቶቿ ተጠያቂ መሆኗን ከመቀበል ይልቅ በእኩይ አመለካከት ውስጥ ሆና ግላዊ ተጠያቂነቷንና ኃላፊነቷን በሌላ ሁለተኛ ወገን ላይ ስታደርግ ይስተዋላል፡፡
…እንጀራ እናቴ (እእ) ሲኦል ስትወርድ እግዜር በእኔ ነገር ክስ ያቀርብባታል፤ታዲያ እሳት ውስጥ ቆማ “ያ መዘዘኛ ልጅ ነው እዚህ የነዳኝ ማለቷ አይቀርም” (ማላከክ ትወዳለች)፡፡ “መዘዘኛው መዝገቡ ነው” ማለቷ አይቀርም (አዳም፣ ግራጫ ቃጭሎች፣ ገፅ 9፣ 1997)፡፡
የዚህ ጽሑፍ ዋና አላማ፣ ደራሲ አዳም ረታ፣ ዋና የኤግዚስቴንሻሊዝም ፍልስፍና ደጋፊ ነው ብሎ ከዚህ የፍልስፍና ጎራ ለመፈረጅ አይደለም (ምክንያቱም የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ፣ ደራሲው ለየትኛው ፍልስፍናዊ አስተምህሮ የተለየ አትኩሮት እንዳለው በተጨባጭ ያገኘው መረጃ ስለሌለውና ደራሲውንም በቅርበት ስለማያውቀው) ዐቢይ አላማው፣ ደራሲው በፈጠራ የሥነ-ጽሑፍ ሥራዎቹ ያነሳቸውን ርእሰ ጉዳዮች ከኤግዚስቴንሻሊዘም ፍልስፍና እሳቤ አንጻር መቃኘት ነው፡፡

Read 657 times