Sunday, 06 January 2019 00:00

የገናዋ በግ

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)


    የሙሽራ ሞገስ ያላት፣ ጀንበር በሳቅ የተንከተከተች ያህል አስቦረቃት፡፡ ለምለም መስክ ላይ ከላይ ወደ ታች እያለች ፈነጨችበት፡፡ እረኛው አንድ ጥግ ቆሞ ይስቃል። ባልንጀሮችዋ ይገረማሉ፡፡ ምን እንደተፈጠረ ምን አበባ እንደፈነዳ፣ ምን መዝሙር እንደሰማች አይታወቅም፡፡ ብቻ ሜዳው አልበቃ አላት፡፡
ከባልንጀሮችዋ አንዷ በመገረምና በመደነቅ እየተከተለች፣ ደስታዋን ልትጋራት ብትፈልግም ፋታ አልሰጠቻትም፡፡ በርግጥ የተለያዩ ቤት ነው ያደሩት። ይሁን እንጂ ሁለቱም የሚውሉት አንድ መስክ፣ የሚግጡትም ተመሳሳይ ሳር ነው፡፡ ግን ዛሬ ነገሯ የተለየ ሆኗል፤ ይህቺ ጓደኛዋ እንደምንም አግባብታ፡፡
“ውዴ ምን ሆነሽ ነው?”
“በቀደም የነገርኩሽን ረሳሽው?”
“ምን ነበር?”
“ለፋሲካ በኔ ላይ የተወራውን?”
“እ…ና ምን ሆነ?”
“ተሻረልኛ! … ተሻረልኝ!”
“ታድለሽ! … ማነው የሻረው?”
“ጌቶች ናቸው! … ጌቶች ዛሬ በጧት ሁላችንም እንደማንታረድ ነገሩን! አህዮቹም ጭነት የሚባል ነገር አይጫንባቸውም!”
አልገባትም፡፡
“ምን ማለት ነው?” ደግማ ጠየቀቻት፤ “ታዲያ ምን ታደርጉላቸዋላችሁ?”
“እኛ ታሪኮች ነን! … እኛ የተዐምራት ቤተሰብ ነን!”
“ወድዬ ምን ሆንሽ? … የእኛ ቤት የዘላለም ትውስታ፣ የዝንታለም ታሪክ ነው፡፡ የዓለምን ታሪክ አቅጣጫ ቀያሪ፣ የዘመን ሽግግር መነሻ ነው፡፡”
“ጌታሽ ያሉትን እያወራሽልኝ ነው?”
“በዐይኔ ያየሁትን፣ በጆሮዬ የሰማሁትን ነው!”
“እኛ ያላየነውን ምን አይተሻል? … እውነት ለመናገር ታሪካችን የነበረው ሙሴ እስራኤልን ከግብፅ ያወጣ ቀን፣ የግብፅ በኩር የተመታ ቀን ነበር!”
“ያ - ታሪክ ያንድ ቀን ማምለጫ ነበር! … ያሁኑ ግን ይበልጣል፡፡ አንቺ የምታወሪው ቅድመ አያቶቻችን ታርደው፣ ደማቸው ጉበን ላይ ተቀብቶ የነበረበትን ቀን ነው፡፡ የእኛ ቤት ታሪክ ከዚያ ያልፋል!”
“ይቅርታ ዛሬ ሌላ በግ ሆንሺብኝ! … ባልንጀራዬ አልመስል አልሺኝ! … እኔና አንቺ ምን ልዩነት አለን? … አንቺም በግ! እኔም በግ!”
“እስከ ትናንት ድረስ ልዩነት አልነበረንም፤ ዛሬ ምሽት ግን በታሪክ ማህደር ልዩነት ተፈጥሯል”
“አዝናለሁ!”
“አትዘኚ … ይልቅ ነገሩን አድምጪኝና በዚህ አጋጣሚ ተደነቂ!”
“ትንሽ ሳር ነጨት - ነጨት እናድርግና እናውራ!”
ሁሉም በየቦታው ተጋድመውና ቆመው በአድናቆት እያወሩ ነው፡፡ አህያዋም አቧራ ላየ መንከባለል ትታ ለምለሙ መስክ ላይ ትንደባለላለች፡፡ እረኛው አንድ ቦታ ላይ ፈገግታ ውስጥ ሆኖ እየዘመረ አምላኩን ያመሰግናል፡፡ አንዳንዴም እንደ በጎቹና እንደ ጥጃዎቹ ፍንጥዝ ፍንጥዝ ይለል፡፡
ሁሉም ነገር ህልም፣ ሁሉም ነገር የማይታመን ሆኖበታል፡፡
ትናንት አመሻሽ ላይ ህዝብ ቆጠራ ፕሮግራም በመንግስት ተጠርተው፣ ወደቤታቸው የመጡት እንግዶች፣ የዚህ ዓይነት አስገራሚ ገጠመኝና የህይወት ገመና ይዘው ይመጣሉ ብሎ አላሰበም ነበር፡፡
ይልቁኑ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ አገልግል ተከፍቶ፣ የወይን መጠጥ ተቀድቶ፣ የሚበላ ነገር ተዘጋጅቶ፣ ደስ የሚል ጨዋታ በመኖሩ አዲስ ስሜት ተፈጥሮ ነበር፡፡ የሥጋ ዘመዶቻቸውና ትውውቅ ያላቸው የሩቅ ሰዎች ግንባራቸውን እየሳሙ፣ ወደ ቤት ሲገቡ ሲሳይ የገባ ያል ቆጥሮት ነበር፡፡
አምሽተው የመጡት ሁለት ምስኪኖች ግን ከማሳዘን በቀር፣ መምጣታቸውን ከቁብ አልቆጠረውም፡፡ ግን ለፈጣሪ ብለው፣ ማደሪያ ስላጡ፣ የበጎች የከብቶች ጋጣ አስገቧቸው፡፡
በተለይ ልጅትዋ ታሳዝናለች፡፡ ሆድዋ የገፋ፣ አንገት የደፋች ትሁት ነገር ናት፡፡ አባቱ ፈቅዶላቸወ ሲገቡ፣ ትንሽ ውሃ ካቀበላቸው በኋላ፣ አንድ ኬሻ ቢጤ ወረወረላቸውና ከእንግዶቹ ጋር የቆጥ ባጡ ሲያወራ ለመስማት ገባ፡፡ ትርክክ ያለ ፍም መሀል ላይ ተቀምጦ እየተሳሳቁ ሲጫወቱ አመሹ፡፡ … በረት ውስጥ የገቡት ሰዎች ብርዱ ሲነጫቸው አንዳንዴ እየታሰበው፣ እንቅልፉ መጣና በዚያው ተኛ፡፡
በኋላ ግን የሆነ ድምፅ ሲሰማ፣ እንግዶቹን ጨምሮ ሁላቸውም ተወርውረው ወጡ፡፡ እንግዳዋ ምጥ ላይ ነበረች፡፡ ቢሆንም ብዙም ትኩረት ስላልሰጧት የተወሰኑት ተመልስ ገቡ፡፡ ሊረዷት አጠገቧ የሆኑም ነበሩ፡፡ ከዚያም በሰላም ተገላገለች፡፡ ቤት እንዳያስገቧት እንግዶች ሞልተውታል፤ ቦታ የለም፡፡
ሁሉም ተመልሰው ተኙ፡፡ ይህ እረኛም እንቅልፍ አሸነፈው፡፡ “በረት ውስጥ የሚወለድ ምን ዕድለቢሱ ነው!” ብሎ እየተገረመ ወደ መኝታው ገባ፡፡
በረትዋ አሁንም ፈንጠዝያ ውስጥ ሆና ለጓደኛዋ ወሬዋን ጀመረች፡፡
“ማታ ምን ሆነ መሰለሽ … ሁለት ባልና ሚስት እንግዶች ብረታችን ገቡ፡፡ ሁላችንም ደነገጥን፡፡ በዚያ ብርድ እንዴት ያድራሉ? ብለን ሁላችንም ተያየን፡፡ አንዳንዶቹም አጉረመረሙ፡፡ ቦታ ያጣብቡናል ያሉም ነበሩ፡፡ እኔ ግን ሳላውቀው ደስ ደስ አለኝ፡፡ ሳቅ ሳቅ አለኝ! … ዝለዩ ዝለዩ አለኝ፡፡
“ከዚያስ?”
“ከዚያማ ሌሎች ላይ ጉድ መጣ! … ልጅቷ ምጥ ያዛት! …” “ሁላችንም ተደናገጥን!”
“ከ-ዚ-ያ-ስ?”
“ልጁ ተወለደ!”
“ሲያሳዝን! በረት ውስጥ እንዴት ተወለደ? ከሚታረዱ በጎች ጋር ይታረዳል? የገረመኝ እሱ ነው! ሲያለቅስ ደግሞ ድምፁ ሆድ ይገባል፡፡ ባልጠፋ ቦታ፣ በዚያ ሽታ ውስጥ መወለዱ ገረመኝ፡፡ ሰዎች ግን የገዛ ወገናቸውን ሲገፉ አያሳዝንሽም ምናለ እቤት ቢያሳድሩት፡፡
በፊት ያሰብኩትን ነው ያወራሁልሽ!
“ይገርማል! ግን ታዲያ ምን አዲስ ነገር አለው፡ … ትንሽ ያጋነንሽ አይመስልሽም! … በቃ አንድ የሰው ልጅ ከተናቁት በጎች መሀል ተወለደ! ይህ ሊያጋጥም ይችላል! … ለዚህ ከሆነ ሳሬን ልጋጥ አንቺም በማያዘልል ነገር አዝለዩ!”
“ገና መች ጀመርኩና!”
አንዴ ነጨት አድርጋ፤ “ታዲያ ቶሎ ቶሎ ንገሪኛ… ለነገሩ ዛሬ እረኛችም ተረጋግቷል!”
“እረኛችን የራሱን እረኛ አግኝቶ ተደንቋል ለዚያ ነው!”
“ከዚያ በኋላ ምን ቢሆን ጥሩ ነው?”
“ምን ሆነ!”
“ሁለት ወንበዴዎች በረታችንን በኃይል ሲከፍቱ፣ ጌቶች መጡና አንገታቸውን አንቀው አሰሯቸው! ደበደቧቸው!”
“ምን ሊያደርጉ ነው የመጡት?”
“ንጉሱ ልኮናል እያሉ ያጭበረብራሉ!”
“ቀጥሎስ ምን ሆነ?”
“ሁሉም ወደ ቤት ተመለሱ፡፡ መቸም ምሽቱ ህልም ይመስላል፡፡ ሁላችንም ትንሽ ስናኮርፍ፣ ሌሎች ሰዎች ደግሞ መጥተው በረት አያንኳኩ መሰለሽ?”
“እነርሱ ደግሞ ማን ላከን አሉ?”
“የእነርሱ ያስፈራል!”
“ከነዚያ ባሰ ነው በይኛ!”
“ታዲያስ እግዚአብሔር ላከን!” አሉ፡፡
ሳቀች፡፡ ከትከት ብላ ሳቀች፡፡”
“አትሳቂ! ምን ያስቅሻል!
“እንዴት አልስቅ! እግዚብሄር ወደ ከብቶች በረት ሰዎችን ሲልክ!”
“ብታስጨርሺኝ ምናለ?”
“እሺ ጨርሺያ!...ቁጣ ቁጣ አይበልሽ! … በዚህ ደስታሽ መሃል ቁጣ ደስ አይልም!”
“አልተቆጣሁም! ልነገርሽ ቸኩዬ እኮ ነው!”
“እሺ ንገሪኝ”
“ከዚያ ጌቶችና ሰዎቹ ምን የሚያካክል ቆመጥ ይዘው በታላቅ ቁጣ” ቁም! ቁም! … ሌባ ሌባ!” ሲሏቸው፣ ተረጋግተው ‹ሌቦች አይደለንም!› አሉ፡፡
“እናስ” አሉ ጌቶች? “እኛ ሰብዓሰገል ነን፣ በክዋክብት እየተመራን ወደዚህ መጥተናል፡፡” አሉ፡፡
ጌቶች ተቆጡ “ቅድም እነዚያ ሌቦች ንጉስ ላከን አሉ፤ እናንተ ደግሞ ጭራሽ ፈጣሪ ላከን ትላላችሁ!”
“ሰዎቹ ተረጋግተው የያዙትን የስጦታ ዕቃ ሲያሳዩዋቸውና ለእኔና ላንቺ የማይገባንን ነገር ሲነግሯቸው፣ ጌቶች እንደ ህፃን ልጅ ድፍት ብለው አለቀሱ፡፡ ‹ወይኔ - ወይኔ ጌታዬ!›...ብለው፤ እዬዬያቸውን አቀለጡት፡፡
“አህዮቹስ ምን ዕድል አገኙ?”
“በነቢዩ ዘካሪያስ ትንቢት የተነገራት ውርንጫ፣ ከኔ አህያ ዘር ልትወለድ ትችላለች” አሉ፡፡
“ወንበዴዎቹስ ተለቀቁ?”
“አዎ፤ ሄሮድስ የሚባል ቀናተኛ ከላካቸው ውስጥ ነበሩ!”
“አልገባኝም!”
“ንጉሥ ተወልዷል ሲባል ህፃናትን ሁሉ ፍጁ ብሎ ልኳው ነበር!”
“ታዲያ ለምን ተለቀቁ!”
‹ለምህረት በተወለደው ጌታ አጠገብ - በሀጥእ አይቀጣም አሉ› ጌቶች!
“ደስ ሲሉ” ምነው እኛም ጋ በተወለደ!”
“ሁለት ጌታ የለማ እመቤቴ! - ዕጣው በእኛ በረት ሆነ … ቂቂቂቂቀ”
መስኩ አልበቃ አላት!

Read 868 times