Sunday, 06 January 2019 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)

“ፍቅር፣ ንፅህና፣ እውነትና ዕውቀት የልቦና ብርሃን ናቸው”
               
    ተነገ ወዲያ የገና በዓል ይከበራል፡፡ አንዳንዶች “የበጋ ወቅት በዓል” እያሉ ይጠሩታል፡፡ ገና የልደት ብርሃን መገለጫ ነው፡፡ ፋሲካን የትንሳኤ ብርሃን እንደምንለው፡፡ እንኳን አደረሳችሁ!!
ብርሃን ቅድስና ነው፡፡ ፍቅር፣ ንፅህና፣ እውነትና ዕውቀት የልቦና ብርሃን ናቸው፡፡ ብርሃን የህይወት መገለጫ ነው፡፡ ክርስቶስ “እኔ የህይወት ብርሃን ነኝ” ሲል … “እኔ ከሌለው ህይወት የለም” ማለቱ ነው፡፡ ብርሃን ከሌለ ሞት፣ ብርሃን ከሌለ ጨለማ ነው፡፡ … ኦና!!
“እፍ!” ተብሎ ትንፋሽ የተሰጠው ሰው፤ “እፍ!” ተብሎ የነፍሱ ብርሃን ሲጨልም “ሞተ” ይባላል። … ኦቴሎ፤ “ጥፊ! አንቺ መብራት” ነበር ያለው… ዴዜዴሞናን “እፍ!” ብሎ ራሱንም፣ ሃሳቡንም አጨልሞ፡፡ … እውነት ከፀሐፊው ጋር ቀረ፡፡ የሃሳብ ብርሃን ስለሆነ፡፡
ወዳጄ፡- የብርሃን ነገር ሲነሳ ቡድሃም ይነሳል፡፡ ቡድሃ ማለት ብርሃን ማለት ነውና፡፡ … ቡድሂዝምን ጨምሮ አንዳንድ እምነቶች፣ ሰው ሆነ እንስሳ ከሞተና ከተረሳ በኋላ ተመልሶ ይመጣል፣ እንደገና ይወለዳል ብለው ያምናሉ፡፡ የህልም ጉዳይ እንዳለ ሆኖ፣ አንዳንድ ጊዜ ፍፁም የረሳናቸውን ሰዎች የሚመስሉ ሌሎች ሰዎች ያጋጥሙናል፡፡ … እንደነግጣለን፡፡ እኛንም አይተው ‹ክው› የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡
በሳይኪክ ሳይንስ ኢንሳይክሎፒዲያ (Encyclopedia of psychic science) ናንደር ፌዶር የተባለ ሰው እንዲህ ፅፏል፡-
ሮበርት ስዌን ጓፎርድ የተባለ አሜሪካዊ ሰዓሊ ከሞተ ከብዙ ጊዜ በኋላ በብሮንክሌን የሚኖር ቶምሰን የተባለ አንጥረኛ ወደ ፕሮፌሰር ሂስሎን መጣና እንዲህ አለው፡- በልጅነቴ እንደ ማንኛውም ህፃን ወረቀት ላይ ከምሞነጫጭረው ዝባዝንኬ በስተቀር የሰዓሊነት ዝንባሌ አልነበረኝም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ልቋቋመው ያልቻልኩት የስዕል ፍቅር አድሮብኛል፡፡ ውብ የሆኑ ስዕሎችን በቀላሉ የምሰራ ጥሩ ሰዓሊ ወጥቶኛል፡፡ የገረመኝ ነገር የአሳሳል ዘይቤዬ ከታላቁ ሰዓሊ ጊፎርድ ጋር ተመሳሳይ መሆኑ ነው፡፡ የጊፎርድን አንዳንድ ስራዎች በአጋጣሚ ከማየቴ በስተቀር ስለ ሰውየው አላውቅም፡፡ አሁን ስለሱ ሳላስብ መቆየት አልችልም፡፡ ባለፈው ሰሞን የጊፎርድ ስዕሎች የሚታዩበት ኤግዚቢሽን ወደሚገኝበት ከተማ ሄድኩ፡፡ ስዕሎቹን ሳያቸው “ራሴ የሰራኋቸው ነበር የመሰለኝ፡፡ ይኼኔ የታመምኩ መሆኑ ገባኝ፡፡ ለዚህ ነው ወደ እናንተ የመጣሁት፡፡ አስደንጋጩ ነገር ደግሞ ተጀምረው ያላለቁ ስራዎቹን እየተመለከትኩ ሳለሁ፣ “አየሃቸው?” የሚል ድምፅ ሰማሁ፡፡ በአካባቢው ማንም አልነበረም፡፡ “… ውሰድና ጨርሳቸው” አለኝ፡፡ ግራ የሚያጋባ ነገር ነው፡፡ እንደዛ ያወራኝ ጊፎርድ ነው? ወይስ እራሴ ለራሴ ነበር የምነግው? … ምናልባት ደግሞ ሟቹ ጊፎርድ እኔ እራሴ እሆን ፕሮፌሰር?” በማለት ጠየቀው ይላል፤ፌዶር፡፡ ይሄ የመመሳሰልና የመሆን ጉዳይ በተለያየ መንገድ ተጣርቶና ተጠንቶ፣ቅዠት እንዳልሆነ ተረጋግጧል፡፡ ሌሎችም ተመሳሳይ ታሪኮች መኖራቸው ተፅፏል፡፡
ወዳጄ፡- የክርስትና እምነት ከሚከተሉ ህዝቦች በተለየ በእስያና በሌሎች ቦታዎች የሚኖሩ ሰዎች፤ ክርስቶስን ዳግም የወለደ ቡድሃ ነው ብለው ያስባሉ፡፡ ቡድሃ ግን በተወለደበት ቀን “እኔ የመጨረሻው ነኝ፣ ካሁን በኋላ አልወለድም” ማለቱ ተፅፏል፡፡ አጋጣሚ ሆኖ ሁለቱ ቅዱሳን፤ ወርቃማውን ህግ ጨምሮ የሚመሳሰሉባቸው መልካም ነገሮች ብዙ ናቸው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ከድንግል ማርያም በመንፈስ የተፀነሰ ሲሆን፣ ጌታ ቡድሃ ደግሞ እናቱ ማሃ- ማያ የፀነሰችው በህልሟ ነበር፡፡ ከክርስቶስ ልደት 200 ዓመታት ቀደም ብሎ፣ ፖሊ በሚባለው የቀድሞ ህንድ ቋንቋ የተፃፈው ቡድሃ ሳንስክሪት እንደሚገልፀው፡-
“አራቱ ጠባቂ መላዕክት ንግስት ማሃ-ማያን ከእነ መኝታዋ ተሸክመው፣ ሂማላያ ተራሮች ላይ ወደሚገኝ የብር ኮረብታ (Silver hill) ወሰዷት። እዛም ሲጠባበቁ የነበሩት የመላዕክቱ ሚስቶች ተቀብለው በአናቲታ ባህር ውስጥ ሰው፣ ሰው” የሚለውን ጠረኗን ሙልጭ አድርገው ካጠቧት በኋላ ኮረብታው ጫፍ ላይ ባለ የወርቅ ቤተ መንግስት አስገቧት፡፡ ፊቷን ወደ ምስራቅ አቅጣጫ አዙረው አስተኟት፡፡ በሌላ በኩል ነጭ ዝሆን ተራራውን ወጥቶ ወደ ቤተ-መንግስቱ እየተቃረበ ነበር፡፡ እንደደረሰ ንግስቲቱ ወዳለችበት ዘልቆ ሶስት ጊዜ መኝታዋን ከዞረ በኋላ በቀኝ ጎኗ በኩል ወደ ማህፀኗ ገባ” ይላል፡፡ ይህ ተረክ በቅደም ተከተል በድንጋይ ላይ ተቀርፆ ፓኪስታን ጋዳራ ይገኛል፡፡
ንግስቲቱ ህልሟን ለባሏ ለንጉሥ ሱድሆዳና ነገረችው፡፡ እሱም ታላቅ ድግስ አዘጋጅቶ ዋና፣ ዋና የሚባሉትን 64 የህንድ ቀሳውስት ወደ ቤተ መንግስቱ አስጠርቶ፣ በአዳዲስ ቀሚስ አስውቦ፣ ባለቤቱ ያየችውን ህልም ነገራቸው፡፡ እነሱም፡-
“ታላቁ ንጉሳችን ደስ ይበልህ፡፡ ባለቤትህ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፡፡ በቤተ መንግስትህ ከኖረ፣ ዓለማትን የሚገዛ ታላቅ መሪ ይሆናል፡፡ ምቾትና እንክብካቤን ጠልቶ ከመነኮሰ ግን የሰውን ልጅ ሃጢአት የሚሽር፣ ከበደል የሚያነፃ ኃይል ያለው፣ ዓለማትን የሚሞላ ብርሃን (Buddha) ይሆናል” በማለት ህልሙን ፈቱ። በዛው ቅድስት አስር ሺ አለማት ተነቃነቁ፣ ሰላሳ ሁለት ታላላቅ ተዓምራቶች ተከሰቱ፣ ህመም፣ ስቃይና መከራ ተወገዱ፣ የገሃነም እሳት ጠፋ፣ የውቅያኖስ ውሃ ጣፋጭ ሆነ፣ በየቦታው የነበሩ የሙዚቃ መሳሪያዎች ማንም ሳይነካቸው ለዛ ያላቸውን ጣዕመ ዜማዎች መጫወት ጀመሩ፡፡
ንግስቲቱ መውለጃዋ በደረሰበት ጊዜ፣ ከዕለታት ባንዱ ቀን፣ በመናፈሻዋ ስትንሸራሸር፣ ከዛፎቹ ቅርንጫፍ ዝንጣፊ ለመውሰድ ስታስብ ትልቁ ዛፍ አጎነበሰላት፡፡ ቀንበጡን ስትነካ፣ ቡድሃ ዱብ አለ፤ በቆመችበት፡፡ ከደረጃ እንደሚወርድ ሰው ቀጥ ያሉ እግሮችና የተዘረጉ እጆች ነበሩት፡፡ ንፁህ ስለነበር ከማህፀን የወጣ አይመስልም፡፡ ወዲያውም ከአናቱ በላይ የብርሃን ጃንጥላ ተዘረጋ፡፡ ሰባት እርምጃ ተራምዶ በሁሉም አቅጣጫ ተመለከተና፤ “ከእኔ በኋላ ማንም የለም” ማለቱ ይነገራል፡፡
ወዳጄ፡- በእንደዚህ ዓይነት በዓላት ወቅት ከተለያዩ ቦታዎች የተሰበሰቡ ምዕመን በአንድ አዳራሽ፣ መስጂድ ወይም ቤተ ክርስቲያን ተሰብስበው፣ሥርዓተ አምልኮታቸውን ያከናውናሉ። ለመተጋገዝና ለመረዳዳት ካልሆነ በስተቀር ማንም ማንንም አይጋፋም፡፡ ነጭ፣ ጥቁር፣ አጭር፣ ረዥም፣ የዚህ ብሔር፣ የዛ ነገድ የሚባል ነገር አይታሰብም። አመት በዓልም የሚደምቀው ሁሉም በጋራ ሲያከብረው ነው፡፡ የሙስሊሙም፣ የክርስቲያኑም የቡድሂስቱም በዓል መንፈስና መዳራሻ  አንድ ነው፡፡
ታላቁ ራማ ክሪሽና፡- “ሂንዱ ነኝ፣ ክርስቲያንም፣ ሙስሊምም ሆኜ አይቸዋለሁ፤መንገዱ ይለያያል እንጂ የሁሉም ግብ አንድ ነው” ይለናል፡፡
እና ወዳጄ፡- ኢድ ሙባረክ! ወይም መልካም በዓል! ወይም ሃፒ ሆሊዴይ ብትሉኝ ለኔ አንድ ነው። ልዩነቱ ቋንቋው ነው፡፡ ለቋንቋ፣ ለቋንቋ ደግሞ “መወለድም ቋንቋ ነው” ይባል የለ?!
ሠላም!!

Read 964 times