Print this page
Sunday, 06 January 2019 00:00

ያሬዳዊው ሥልጣኔ ክፍል- ፬ የብህትውና አሻራዎች በኪነ ጥበባችን ውስጥ

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(0 votes)

ብህትውና በያሬዳዊው ሥልጣኔ ውስጥ ላለፉት 1500 ዓመታት የባህል ምንጭ ሆኖ ስላገለገለ አሻራው እስከ አሁን ድረስ በፖለቲካችን፣ በታሪክ አተራረካችን፣ በስነ ልቦናችን፣ በሃይማኖታችንና በኪነ ጥበባችን ውስጥ በብዛት ይታያል፡፡ በዚህ ፅሁፍ ውስጥ የምንመለከተው በኪነ ጥበባችን ላይ የታተመውን የብህትውና አሻራ ነው፡፡
ኪነ ጥበብ የሰውን ልጅ ጥልቅ ስሜቶች በሙዚቃ፣ በስዕል፣ በሥነ ፅሁፍ ወይም በኪነ ህንፃ የምንገልፅበት መንገድ ነው፡፡ ይሄም ማለት፣ ኪነ ጥበባዊ ሥራዎች የሰው ልጅ ውስጣዊ ስሜቱን በድምፅ፣ በቀለም፣ በምልክትና በቅርፃ ቅርፅ የሚወክልበት መንገድ ነው ማለት ነው፡፡ በመሆኑም፣ ውስጣዊ ስሜቶችና ውጫዊ መገለጫዎች ሁልጊዜ ተመሳሳይና አንድ ዓይነት ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ በመሆኑም፣ በሀገራችን በጥንትና በመካከለኛው ዘመን የተሰሩ ኪነ ጥበባዊ ሥራዎችን ተመልክተን የዘመኑን ገዥ አስተሳሰብና ባህል ማወቅ እንችላለን፡፡
በዚህም ምክንያት፣ ኪነ ጥበባዊ ሥራዎች በዘመናቸው መዝናኛ፣ በአሻራቸው ደግሞ የታሪክ ማስረጃ ሆነው ይቀርባሉ፡፡ በዚህ ርዕስ ሥር የማነሳውም የጥንትና የመካከለኛው ዘመን የኪነ ጥበብ አሻራዎችን እያነሳን፣ አሻራዎቹ በዘመኑ ገዥ የነበረውን የብህትውና አስተሳሰብና ባህል በታሪክ አስረጅነት እንደሚገልፁ እንመለከታለን፡፡
በኪነ ጥበብ ውስጥ ልዩ ትኩረት የሚያስፈልጋቸው ሁለት ነገሮች የአርቲስቱ ስሜትና ምናብ ናቸው፡፡ ምናብ (Imagination) የአርቲስቱ ሉዓላዊ የፈጠራ ቦታ ሲሆን፣ የምናቡ ጥልቀትና ስፋት የሚወሰነው ደግሞ በአርቲስቱ ዕውቀትና በስሜት የመነካት መጠኑ ነው፡፡ በመሆኑም፣ ኪነ ጥበባዊ ሥራዎች የአርቲስቱን የምናብ፣ የዕውቀትና የስሜት ጥልቀት የሚገልፁ ናቸው፡፡ የአርቲስቱ የምናብ፣ የዕውቀትና የስሜት ዓይነት ደግሞ ‹‹በዘመኑ መንፈስ›› የሚወሰን ነው። በመሆኑም፣ በአንድ ዘመን ላይ በተሰራ ኪነ ጥበባዊ ሥራ ላይ የምናገኘው አሻራ የአርቲስቱን የምናብ፣ የዕውቀትና የስሜት ጥልቀት ብቻ ሳይሆን፣ የአርቲስቱ ምናብ ሲሰራበት የነበረውን ክበብ ወይም ‹‹የዘመኑን መንፈስ›› ጭምር ነው፡፡
በጥንቱና በመካከለኛው ዘመን የተሰሩ ኪነ ጥበባዊ ሥራዎችን ተመልክተን፣ የዚያ ዘመን አርቲስቶች በተካረረ የዓለማዊና የመንፈሳዊ ህይወት ተቃርኖ በተወጠረ ‹‹የዘመን መንፈስ›› ውስጥ ሆነው ሲሰሩ እንደነበረ በቀላሉ መረዳት እንችላለን፡፡ በዚህም የተነሳ ኪነ ጥበባዊ ሥራዎቻቸው ብቸኝነትን፣ ምናኔን፣ በምድራዊ ህይወት መከፋትን፣ ሰማያዊ ተስፋን … የተሸከሙ ናቸው፡፡ እስቲ ለዚህ ድምዳሜያችን አንድ ሁለት አብነቶችን እንጥቀስ፡፡
ሥነ ፅሑፍ
በኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክ ውስጥ ‹‹የመጀመሪያው የሥነ ፅሑፍና የኪነ ጥበብ ዘመን›› ተብሎ የሚጠራው ያሬዳዊው ሥልጣኔ የተወለደበት 6ኛው ክ/ዘ ነው፡፡ የ9ኙ ቅዱሳን ወደ አክሱም መምጣታቸውን ተከትሎ በድንገት ባበበው በዚህ የሥነ ፅሑፍ ዘመን ውስጥ ከተሰሩ ሥራዎች ውስጥ (ለምሳሌ - ስንክሳር፣ መፅሐፈ መነኮሳት፣ ገድላት (ቄርሎስ፣ አትናቲዎስ፣ ባሲል…) አብዛኛዎቹ ብህትውናን የሚያስተምሩና ባህታውያንንም በመንፈሳዊ ህይወት ‹‹የበቁ›› አድርገው የተፃፉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ፣ ፍትሐ ነገስት ባህታውያንን ‹‹የምድር መላዕክት፣ የሰማይ ሰዎች›› ይላቸዋል፡፡
በእነዚህ ሥነ ፅሁፎች ውስጥ የሰው ልጅ ነፃ ፈቃድ፣ አካል፣ ስሜት፣ የአመክንዮ ኃይልና ምድራዊ ብልፅግና የተናቁ ናቸው፡፡ በሥነ ፅሁፎቹ ውስጥ ሰው የቱንም ያህል በራሱ ጥረት ቢፍጨረጨር መለኮታዊ ፀጋ እስካላገኘ ድረስ የማይሳካለትና ተሰባሪ ሸክላ ሆኖ ተስሏል፡፡ ሐብታም በሐብቱ ተመክቶ ሲወድቅ፣ ድሃ ግን በእምነቱ የተነሳ ሲድን ይታያል፡፡
በሥነ ፅሁፎቹ ውስጥ ‹‹እውነት›› ሚስጥራዊ ተደርጎ የሚሳል ሲሆን፣ ይሄም ‹‹ሚስጥራዊ እውነት›› በሰው ልጅ ህሊና የሚደረስበት ሳይሆን፣ በመለኮታዊ ፀጋ የሚገለጥ ክስተት ይደረጋል፡፡ ሰው በስተመጨረሻ ‹‹ሚስጥራዊውን እውነት›› እንዲደርስበት በመጀመሪያ ወደ ተራራ እንዲወጣ፣ በረሃ ለበረሃ እንዲንከራተት፣ በየገዳማቱ እንዲኳትን፣ በፆምና በፍትወት አካሉ እንዲደክምና መንፈሱ እንዲጠነክር ይደረጋል፡፡
እንደዚህ ዓይነቱ የተአምራትና የብህትውና አሻራዎችን በደማቁ የተሸከሙ የመካከለኛው ዘመን ሥነ ፅሁፎች፣ በሀገራችን ዘመናዊ የሥነ ፅሁፍ ውስጥም ‹‹ዓለማዊ ቅርፅን›› ይዘው ተጠናክረው የቀጠሉ ሲሆን ከህብረተሰቡም አሁንም ድረስ በርካታ አንባቢ አላቸው፡፡ ዴርቶጋዳ፣ እመጓ፣ ዝጎራ፣ መርበብት፣ ረጢን፣ እንዲሁም አብዛኛዎቹ የዲ/ን ዳንኤል ክብረት ሥራዎች ይህ የሥነ ፅሁፍ ዘውግ የሚጫናቸው ናቸው።
ስዕልና ኪነ ህንፃ
በሥነ ፅሁፋችን ላይ የሚገለፁት የብህትውና አሻራዎች፣ በስዕሎቻችንና በኪነ ህንፃዎቻችንም ላይ ሲገለፅ ይታያል፡፡ ሰዓሊያኑ ሰውን ሲስሉ ደካማና የተከፋ የፊት ገፅታ እንዲኖረው የሚያደርጉ ሲሆን፣ በነፃ ፈቃድና በውስጣዊ ኃይሉ ከመኖር ይልቅ በመለኮታዊ ፀጋ የሚኖር መሆኑን ለማሳየትም ዓይኑን ወደ ሰማይ እንዲሰቅልና እጆቹንም ወደፊት እንዲዘረጋ ይደረጋል። በዚህም አካልና ስነ ልቦና ወደ ውስጥ ይኮማተራሉ፡፡
የጥንቱና የመካከለኛው ዘመን አብያተ ክርስትያናት የተሰሩበት ኪነ ህንፃዎች ላይ የብህትወናን አሻራ የምናገኘው ደግሞ በሁለት ነገራቸው ላይ ነው፤ የመጀመሪያው ከዓለም ርቀው መሰራታቸው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከዓለም መራቅ ብቻ ሳይሆን በቀላሉ የማይደርስባቸው አካባቢዎች ላይ (ለምሳሌ - ዋሻ ውስጥ፣ የገደል አፋፍና የተራራ አናት ላይ) መሰራታቸውም ነው፡፡ የኪነ ህንፃዎቹ አሰራር ሰው በቀላሉ የማይደርስባቸው፣ ከዚህ ዓለም መለየት ለሚፈልግ ሰው ደግሞ ዳግም ወደ ዓለም የማይመለስባቸው ተደርገው ነው የተሰሩት፡፡
ሙዚቃና ዳንስ
ሙዚቃን በተመለከተ ከዚህ ቀደም ቅዱስ ያሬድን በተደጋጋሚ አንስቻለሁ፡፡ ቅዱስ ያሬድ የተነሳበት ዘመንና አክሱም ወደ ብህትውና የገባችበት ዘመን ተመሳሳይ መሆን፣ እንዲሁ ተራ ግጥምጥሞሽ አይደለም፡፡ ያሬድን የፈጠረችው ባህታዊዋ አክሱም ነች፡፡ አክሱም በብህትውና ከዓለም ተነጥላ፣ እየሱስና እናቱ በሰሞነ ሕማማት የገጠማቸውን ሐዘንና መከራ እያሰበች በምትቆዝምበትና እያስለቀሰ የሚያፅናናትን ዜማ በናፈቀችበት ወቅት ላይ ነው ቅዱስ ያሬድ የደረሰላት፡፡ በዚህም፣ ሲሰሙት ወደ ሌላ ዓለም የሚያስተላልፍ፣ ነፍስንም ከባድ ትካዜ ላይ የሚጥል ‹‹በእየሱስ መከራ የተቃኘ ዜማን ፈጠረላት››፡፡
በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ውስጥ የብህትውና አሻራዎች የሚገለፁት ደግሞ በዘፈኖቻቸው ለሰው ልጅ ነፃ ፈቃድ፣ ኃይልና ድካም ዕውቅና በመንፈግ ሲሆን፤ በህይወታቸው ደግሞ ሙዚቃን ኃጢያት በማድረግ ምናኔን መምረጥ አሊያም ዘማሪ ብቻ መሆን ነው። ‹‹ከሌላው ዓለም በተለየ፣ በኢትዮጵያ ቤተ እምነት ውስጥ ሙዚቀኛው ለዘላለም ጥፋት (ለገሃነም) የተዘጋጀ ሙያተኛ ተደርጎ ተፈርጇል›› (ዮናስ ጎርፌ 2008፡ 16)፡፡
ዳንሶቻችንም የብህትውና አሻራ ተሸካሚ ናቸው። ይሄም በዋነኛነት በሰውነት እንቅስቃሴዎቻችንና የውዝዋዜ አለባበሳችን ላይ የሚንፀባረቅ ነው፡፡ የሰሜኑ ባህል፣ ጭፈራን ከወገብ በላይ አንገትና ትከሻ ላይ ያደረገው የወሲብ የአካል ክፍሎች በጭፈራው ውስጥ እንዳይሳተፉ ለመከልከል ነው፤ ምክንያቱ ደግሞ በብህትውና ባህል ውስጥ ጥብቅ ቁጥጥር ከሚደረግባቸው አካላዊ ስሜቶች ውስጥ ዋነኛው የወሲብ ስሜት ነው፡፡ አለባበሳቸውም ይሄንን ባህል ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ ፕ/ር አሸናፊ ከበደም (1971፡ 181) ይሄንን ነገር አስተውለዋል፡፡
በአንፃሩ፣ የደቡብ ኢትዮጵያን ጭፈራዎች ተመልከቱ፡፡ አብዛኛዎቹ ጭፈራዎች የሰሜኑ የብህትውናው ባህል የከለከለው የአካል ክፍል ላይ (ከወገብ በታች) የሚደረጉ ናቸው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ብሩህ ዓለምነህ፤ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር ሲሆን “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” ደራሲ ነው፡፡ በኢ-ሜይል አድራሻው፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 536 times