Monday, 07 January 2019 00:00

ጃኮብ ዙማ የሙዚቃ አልበም ሊያወጡ ነው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ በጸረ አፓርታይድ ትግልና በነጻነት ተጋድሎ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ የሙዚቃ ስራዎችን ያካተተና ስትራግል ሶንግስ የሚል ስያሜ ያለው የሙዚቃ አልበም በማሳተም ለአድማጮች ለማቅረብ ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙ ተነግሯል፡፡
ባለፈው የካቲት ወር ላይ በሙስና ቅሌት ስልጣናቸውን የለቀቁትና ህዝበ በተሰበሰበባቸው ስፍራዎች በመደነስና በመዝፈን የሚታወቁት ጃኮብ ዙማ፣በመጪው ሚያዝያ ወር የመጀመሪያውን አልበም እንደሚያሳትሙ መነገሩን የዘገበው አሶሼትድ ፕሬስ፤ አልበሙን ፕሮዲዩስ ለማድረግ የሚያስፈልገውን ወጪ የሸፈነላቸው የትውልድ አውራጃቸው ኩዋዙሉ ናታል አስተዳደር መሆኑንም አመልክቷል፡፡
በጸረ አፓርታይድ ትግል ዙሪያ የሚያጠንጥኑ ሙዚቃዎችን የማሳተም ሃሳቡ የተጠነሰሰው ከሶስት አመታት በፊት እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ አሳታሚው ቲምቢንኮሲ ንኮቦ የተባለ የመዝናኛው ዘርፍ ድርጅት እንደሆነም ገልጧል፡፡ ዙማ የላቀ የሙዚቃ ተሰጥኦ እንዳላቸውና የሙዚቃ መረዳታቸው ከፍ ያለ እንደሆነ ምስክርነቱን የሰጠው አሳታሚ ድርጅቱ በቀጣይም ከጃኮብ ዙማ በተጨማሪ በጸረ አፓርታይድ ትግል ዙሪያ የሚያጠንጥኑ ሙዚቃዎችን የሚሰሩ ሌሎች ታዋቂ የአገሪቱ ድምጻውያንን ስራዎች ለማሳተም ማቀዱንም ዘገባው አመልክቷል፡፡

Read 2587 times