Print this page
Sunday, 06 January 2019 00:00

በተቃውሞ የተወጠረው የአልበሽር መንግስት

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 የሱዳን መንግስት በአንድ ዳቦ ዋጋ ላይ ያደረገውን የአንድ የሱዳን ፓውንድ ጭማሪ ሰበብ በማድረግ ከሳምንታት በፊት በአገሪቱ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ተባብሶ በመቀጠል፣ አገሪቱን ለሃያ ዘጠኝ አመታት የገዙት ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር  ስልጣናቸውን እንዲለቁ ወደሚጠይቅ ፖለቲካዊ ተቃውሞ መሸጋገሩ ተዘግቧል፡፡
መዲናዋን ካርቱም ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ተባብሶ የቀጠለው ተቃውሞ፣ የአልበሽርን መንግስት ጭንቅ ውስጥ እንደከተተው የዘገበው አሶሼትድ ፕሬስ፤22 የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፕሬዚዳንቱ ስልጣናቸውን እንዲለቁና ለዲሞክራሲያዊ ምርጫ ሁኔታዎችን የሚያመቻች የሽግግር መንግስት ተቋቁሞ አመራሩን እንዲረከብ ባለፈው ረቡዕ በይፋ መጠየቃቸውን ጠቁሟል፡፡
የአልበሽር መንግስት አገሪቱን ከገባችበት የኢኮኖሚና የፖለቲካ ቀውስ የማውጣት ብቃትም ሆነ ዝግጁነት የለውም ያሉት ፓርቲዎቹ፤ ስልጣናቸውን እንዲለቅቁ የሚጠይቅ ደብዳቤ ባለፈው ረቡዕ ለፕሬዚዳንቱ መላካቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
 ናሽናል ፍሮንት ፎር ቼንጅ በሚል ጥላ ስር የተሰባሰቡት ፓርቲዎቹ፤ አልበሽር ጥያቄውን ተቀብለው ስልጣናቸውን የማይለቁ ከሆነ፣ አገሪቱ ወደ ከፋ ቀውስና እልቂት ልትገባ እንደምትችል ያላቸውን ስጋት መግለጻቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ተቃዋሚዎቹ የገዢው ፓርቲ ንብረት የሆኑ ህንጻዎችን በእሳት ማጋየታቸውንና ፖሊስም በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮችንና ተቃዋሚዎችን ማሰሩን አመልክቷል፡፡
የሱዳን ገዢ ፓርቲ ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ በበኩሉ፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ አልበሽር ስልጣናቸውን እንዲለቅቁ ያቀረቡትን ጥያቄ እንደማይቀበለው አስታውቆ፣ ከሁለት አመታት በፊት የተፈጸመውን ብሄራዊ መግባባት የሚጥስ ነው በማለት ያወገዘው ሲሆን  የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽርም፣ በፍትህ ሚኒስትሩ የሚመራ ቡድን ተቋቁሞ፣ በተቃውሞው ዙርያ አፋጣኝ የማጣራት ስራ እንዲጀምር ትዕዛዝ መስጠታቸውን ዘገባው አስረድቷል፡፡
ፕሬዚዳንቱ፤ የፖሊስ ሃይሎች ተቃውሞውን ለማርገብ በሚያደርጉት ጥረት ተመጣጣኝ ያልሆነ ሃይል እንዳይጠቀሙ ቢያስጠነቅቁም፣ መዲናዋን ካርቱም ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች በተቀሰቀሰው ተቃውሞ እስካሁን ድረስ ከ19 በላይ ሰዎች መገደላቸውንና በመቶዎች የሚቆጠሩትም መቁሰላቸውን የዘገበው ሮይተርስ፣አለማቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋም አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ፤ የሟቾች ቁጥር 37 ይደርሳል ማለቱን ጠቁሟል፡፡
ሱዳን በከፋ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ውስጥ እንደምትገኝ የጠቆመው ዘገባው፤ፕሬዚዳንት አልበሽር ሰኞ ዕለት ባወጡት መግለጫ፣ ዜጎች ከብጥብጥና ጥፋት እንዲቆጠቡ በማሳሰብ፣ መንግስታቸው በአዲሱ የፈረንጆች አመት በበርካታ ሸቀጦች ላይ ድጎማ እንዲሁም የደመወዝ ጭማሪ እንደሚያደርግና ተጨማሪ ታክሶችን እንደማይጥል ለዜጎቻቸው ቃል መግባታቸውን አስታውቋል፡፡
እ.ኤ.አ በ1989 በተካሄደ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ወደ ስልጣን የመጡት አልበሽር በአምባገነን አገዛዝ አገሪቱንና ህዝቦቿን ማቆርቆዛቸውን ማቆም ይገባቸዋል የሚል አቋም የያዘው ተቃውሞው መባባሱን ቀጥሎ መንግስት ፌስቡክ፣ ትዊተርና ዋትሳፕን ጨምሮ ተቃውሞውን በማስተባበርና መረጃዎችን በማሰራጨት ቀውሱን እያባባሱ ነው ያላቸውን ታዋቂ የማህበራዊ ድረገጾችን ባለፈው ረቡዕ መዝጋቱን ዘገባው አመልክቷል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ባለፈው ረቡዕ የተሰበሰበው የሱዳን ፓርላማ በከሰላና ሰሜን ኮርዶፋን ግዛቶች ውስጥ የጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በስድስት ወራት እንዲራዘም መወሰኑን ሽንዋ ዘግቧል፡፡
ፓርላማው በግዛቶቹ የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከ መጪው ሰኔ ወር አጋማሽ እንዲራዘም የወሰነው በአካባቢዎቹ ያለው ህገወጥ የሰዎች፣ የጦር መሳሪያዎችና አደንዛዥ ዕጽ ዝውውር ተባብሶ በመቀጠሉ መሆኑን ዘገባው አመልክቷል፡፡

Read 1140 times
Administrator

Latest from Administrator