Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 26 May 2012 10:50

ከዚህ ጥበብ ጀርባ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት (UNICEF) መረጃ እንደሚያመለክተው ህገወጥ የህፃናት ዝውውር በአመት ከሰባት እስከ አስር ቢሊየን ዶላር ለህገወጥ አዘዋዋሪዎቹ ያስገኛል፡፡ ህገወጥ ዝውውሩ ህፃናት አፈላላጊዎች፣ ደላሎች፣ አጓጓዦች እና ቀጣሪዎችን ያካተተ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ውስጥ የቤተዘመድ ተሳትፎ ቀላል አይደለም፡፡ እናም የመጀመሪያው ተግባር ህፃናቱን በገጠራማ አካባቢዎች እና በአነስተኛ ከተሞች ማፈላለግና መለየት ነው፡፡ቢኒያምና ጓደኞቹ(ለዚህ ፅሁፍ ሲባል ስማቸው የተጠቀሰ ሰዎች ሁሉ ስማቸው ተቀይሯል)ደቡብ ክልል ጋሞ ጎፋ ዞን ጨንቻ ወረዳ ከሚባል አካባቢ ነው ቢኒያም ወደ አዲስ አበባ የመጣው፡፡ ቢኒያም ከልጅነቱ አንስቶ አባቱና አጎቱን የመርዳት ግዴታ ስለነበረበት በሽመና ስራ ተክኗል፡፡ ይህን ችሎታውን የተገነዘበ ዝምድናው የአጎትነት ባይሆንም ቢኒያም አጎቴ የሚለው የቅርብ ዘመድ አዲስ አበባ ጥሩ ስራ እንዳለ ቢኒያም እየተማረ ቤተሰቡን ሊረዳበት የሚያስችለው ስራ እንደሚያስገኝለት በመናገር የ11 አመት ጨቅላው ቢኒያምን ወደ አዲስ አበባ ይዞት መጣ፡፡

ቢኒያም እንደነገረኝ ከጨንቻ ሲነሳ አንድ ሱሪና ኮት ያሰፉለት “አጎቱ” አዲስ አበባ ቤታቸው ሁለት ቀን አሳርፈው በሶስተኛው ቀን ቀጨኔ ወደሚባለው ሰፈር ይዘውት ተጓዙ፡፡ ቢኒያም የሄደበትን አካባቢ እንዲህ ተረከልኝ “ቤቱ አባቴ ጨንቻ የሚሰራበትን ቤት ነው የሚመስለው፡፡ ግን እዚህ ቤቱ ጠባብ ቢሆንም አስር የሽመና ቦታ አለ፡፡ እኔን የሚያክሉ እኩዮቼ የሚሆኑ ስምንት ልጆች ሲኖሩ ሁለቱ የሚሰራባቸው ሰው የለም፡፡ እኔን ከልጆቹ ጋር ተጫወት ብሎኝ አጎቴ ከቤቱ ባለቤት ጋር ሊያወራ ወደ ውጭ ወጣ”፡፡የቢኒያም “አጎት” ለቤቱ ባለቤት (ለቀጣሪው) አስረክበውት ሄዱ፡፡ የቢኒያም አስከፊ ህይወትም ይህኔ ይጀምራል፡፡ እንኳን የተመኘውን ትምህርት ሊጀምር በቂ እረፍት ማግኘት አይችልም፡፡ “ገና ፀሃይ ከመውጣቷ ጀምሮ እስከ ለሊት እንሰራለን፡፡ ዳቦና ሻይ ለቁርስና ለእራት ይሰጠናል”፡፡ ቢኒያምና ጓደኞቹ ያለ በቂ ምግብና እረፍት በተዘጋ ቤት የልጅነት እድሜያቸውን ሸማን “ሲጠበቡባት” ድካሙ ሲበረታም እዛው ሸማው ላይ እንደሚያቀላፉ ነገረኝ፡፡ “ግን ገና እንቅልፌ ከመጀመሩ ጋሽ አማረ(አሰሪያቸው) በቁጣ ያንባርቅብኛል” አለኝ ቢኒያም፡፡የህፃናቱ ስቃይበኢትዮጵያ እድሜያቸው ከ5 እስከ17 የሆኑ 28 ሚሊየን ህፃናት እንዳሉ የማእከላዊ እስታትስቲክስ መረጃ ያመለክታል፡፡ MEDA (Mennonite Economic Development Associates) የተሰኘ አለም አቀፍ የረድኤት ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው ከነዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ ህፃናት በሳምንት 33ሰአታትን ስራ ላይ ያሳልፋሉ(በኢትዮጵያ በመንግስት እውቅና የተሰጠው የአዋቂዎች መደበኛ የስራ ሰአት በሳምንት 48 ሰአት ነው)፡፡ ምንም እንኳን በኢትዮጵያ ለህፃናት ከለላ የሚሰጡ ጠንካራ ህጎች ቢኖሩና ሃገሪቱ በርካታ አለም አቀፍ ስምምነቶችን የፈረመች ቢሆንም ህፃናቱ ከመንግስት እውቅና ውጭ መደበኛ ባልሆነ ስራ ላይ እንዲሰማሩ መደረጋቸው ቁጥጥሩን አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡በገጠር ያለው ኢትዮጵያዊ በቁጥርም አብላጫውን ድርሻ ስለሚይዝ የህፃናት ጉልበት ብዝበዛውም በዛው ይከፋል፡፡ በከተማ ደግሞ በተለይ ሴት ህፃናት በቤት ውስጥ ስራና ሲብስም በወሲብ ባርነት የልጅነት ወዛቸው ሲመጠጥ፤ ወንዶቹ ደግሞ እንደ መላላክ፣ ሽመና፣ የሚኒባስ ታክሲ ረዳትነት ባሉ ስራዎች ጉልበታቸው ይበዘበዛል፡፡ የገጠሩም ሆነ የከተማው የጉልበት ብዝበዛ በአብላጫው በቤተዘመድ የሚፈጸም ቢሆንም የገጠሩ ካለማወቅ ጋር የተዳመረ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ የከተማው ግን ሆን ተብሎ የሚደረግና በወንጀል የማስጠየቅ አግባብነቱ የላቀ ነው፡፡MEDA ከWORLD VISION ጋር በመተባበር በተለይ በአዲስ አበባ ቀጨኔና ሽሮሜዳ አካባቢ ባደረገው ጥናት ሸማኔ ህፃናቱ በቀን ቢያንስ 14 ሰአት ይሰራሉ፡፡ ይህን ያህል ከሰሩ በኋላም የሚከፈላቸው ገንዘብ በሳምንት ከ15ብር በታች ነው፡፡ አለም አቀፉ የስራ ድርጅት ILO በ2004 ያከናወነው ጥናት እንደሚያመለክተው በሽመና ስራው አብላጫውን ቁጥር የሚይዙት እድሜያቸው ከ6 እስከ 17 የሚሆኑት ናቸው፡፡ እናም እነዚህ ህፃናት ያለ በቂ ምግብ፣ ያለ በቂ እረፍት፣ ያለ በቂ ክፍያ የልጅነት ህልማቸውን በሚያደበዝዝ “የጥበብ” ስራ ላይ ተሰማርተዋል፡፡ አለማየሁና ወንድሙWORLD VISION AUSTRALIA የትምህርት እድል የከፈተለት አለማየሁ ስለ ሽመና ህይወቱ ይናገራል፡፡ “ከተወለድንበት ወላይታ ከቤተሰብ ጠፍተን ህይወታችን ተቀይሮ ወላጆቻችንን እናስደስታለን ብለን ወደ አዲስ አበባ ስመጣ እኔ 10አመቴ ወንድሜ ደግሞ12 አመቱ ነበር”፡፡ አዲስ አበባ እንደመጡ ግን የአለማየሁና የወንድሙ እጣ በጉልበት በዝባዥ መጠመድ ነበር፡፡ እናም አለማሁም ሆነ ወንድሙ ያለ አንዳች እረፍት፣ ያለ ስባሪ ሳንቲም ክፍያ፣ ያለ ፍንጣቂ ተስፋ ሽመና ስራቸው ላይ ተደፉ፡፡ከጠዋት 12ሰአት እስከ ምሽት 12 ሰአት ያለማቋረጥ እንሰራለን የሚለው አለማየሁ ከአንድ ሰአት እረፍት በኋላ ደግሞ እስከ እኩለ ለሊት እንደሚሰሩ ይናገራል፡፡ ይህ ሁኔታ በቀን 16አሰት፣ ከሳምንት እስከ ሳምንት፣ ከወር ወር እያለ ለሰባት አመታት ዘለቀ፡፡አለማየሁ የኑሮ ሁኔታው ከባድ እንደነበረ ያስታውሳል፡፡ በጣም በተጨናነቀና በሚቀዘቅዝ ክፍል ውስጥ፣ ያውም ድካም እንኳን በርትቶበት አንዳች ጥፋት ቢፈጽም እየተደበደበ የሚሰራው ስራ መጨረሻው ደርሶ አረፍ ሲል መሬት ላይ ብርዱን ችሎ መተኛት ይፈረድበታል፡፡ አለማየሁና ታላቅ ወንድሙ ከሰባት አመታት በኋላ ጠፍተው ወደ ወላይታ ተመልሰዋል፡፡ አለማየሁምበWORLD VISION AUSTRALIA እገዛ ትምህርቱን በመጀመር እነሆ በ20 አመቱ ሶስተኛ ክፍል ደርሷል፡፡አስቸጋሪው ሁኔታበእርግጥ ቢኒያምና ጓደኞቹ ራሳቸው በዘየዱት መላ ከአሰሪያቸው ቤት ጠፍተው ወጥተዋል፡፡ ከአምስት ጓደኞቹ ጋር በመሆን አሁን ቢኒያም ሃያ ሁለት የሚባለው አካባቢ ሊስትሮነት ይሰራሉ፡፡ ምሽት ደግሞ የናፈቃቸውን ትምህርት እዛው አካባቢ በሚገኘው ብርሃንህ ዛር ትምህርት ብት ይከታተላሉ፡፡ከኛ መሃል በእድሜ የሚበልጥ ልጅ “ብንጠፋ ባለን ሳንቲም ሊስትሮ እንሆናለን፡፡ በፊትም እነ ታደለ(በፊት ሽመና ይሰሩ የነበሩ) ጠፍተው ሄደዋል” ካለን በኋላ ነው ያመለጥነው፡፡ ቢኒያም ከአራት አመት በኋላ ከአሰሪው ጠፍቶ በጀመረው የሊስትሮ ስራ ደስተኛ ነው፡፡ ቤተሰቦቹንም አንዴ ለማየት ታድሏል፡፡ ቢኒያምን ጠይቄው ነበር “አሁንም ከናንተ መንደር ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ ልጆች አሉ?”“አዎ፡፡ ልጆቻቸውን ለዘመድ የሚሰጡ አሉ”እነ ቢኒያም ችግሩን ዘግይቶም ቢሆን በራሳቸው መንገድ በከፊል የፈቱት ቢሆንም በርካታ ህፃናት ግን ተመሳሳይ የጉልበት ብዝበዛ ላይ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ በርካቶች የሸማኔ ጉድጓድ ውስጥ የልጅ እግሮቻቸውን ቀብረው፣ ሸማው ላይ አንገታቸውን ደፍተው ይህን ፅሁፍ በምናነብበት ቅፅበት እንኳ ከድካምና እንቅልፍ ጋር እየታገሉ ናቸው፡፡ ህፃናቱ በልጅነት አቅማቸው ከመጠን በላይ እየሰሩ፣ ወደ ምግብም ሆነ ወደ እውቀት ማእድ ሳይቀርቡ፣ እንኳን ለነገ ህይወታቸው መሰረት ሊጥሉ ቀርቶ የዛሬው የጨቅላ ህይወታቸው እየደበዘዘ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ይህ ግን እንዴት ይፈታ የሚለው መልስ በእያንዳንዳችን ውስጥ ሊንቀለቀል ይገባል፡፡ ራሳችን ጀምረን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የህፃናቱ ሰቆቃ ፈፃሚና ተባባሪ የሆኑትን ልንታገላቸው ይገባል፡፡

 

 

 

 

Read 2929 times Last modified on Saturday, 26 May 2012 11:06