Saturday, 12 January 2019 13:58

በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ100 ያላነሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ይዘጋሉ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

   - የቀድሞ አዋጅ ከተጀመረው የለውጥ ሂደት ጋር የማይሄድ ነው
           - የድርጅቶቹ የአስተዳደር ወጪ ከገቢያቸው 20 በመቶ ብቻ መሆን ይገባዋል ተብሏል
              
    በኢትዮጵያ መንቀሳቀሻ ገንዘብ በማጣትና በሌሎች ምክንያቶች በአማካይ በየዓመቱ ከአንድ መቶ የማያንሱ አገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንደሚዘጉ ተገለፀ፡፡ ለዚህም የቀድሞ አዋጅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል ተብሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት በስራ ላይ የሚገኘው የበጐ አድራጐት ድርጅቶችና ማህበራት ህግ ድርጅቶቹ ሥራቸውን በአግባቡ ለመስራት እንዳይችሉ ያደረገና ከፍተኛ ችግሮችን የጋረጠ በመሆኑ ህጉን ማሻሻል እንደሚገባ ታምኖ ረቂቅ አዋጁ መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡
ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለውይይት የቀረበው ይኸው ረቂቅ አዋጅ እንደሚያመለክተው፤ የበጐ አድራጐት ድርጅቶችና ማህበራት ህግ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ቁጥር እጅግ አናሳ እንዲሆን አድርጓል፡፡
በተጨማሪም ህጉ፤ የገንዘብ ምንጭን መሰረት በማድረግ፣ ሀገር በቀል ድርጅቶችን፣ “የኢትዮጵያ በጐ አድራጐት ድርጅት/ማህበር” እና “የኢትዮጵያ ነዋሪ በጐ አድራጐት ድርጅት በሚል የሚከፋፍል ሲሆን፤ በሰብአዊ መብት፣ ዲሞክራሲ፣ የሴቶች የህፃናትና አካል ጉዳተኞች” መብቶች እንዲሁም በሃይማኖትና በብሔር ዙሪያ መቻቻልን የማበረታታት ስራ እንዲሰሩ የተፈቀደላቸው 90 በመቶ እና ከዚያ በላይ ገቢያቸውን ከአገር ውስጥ የሚያገኙት የበጐ አድራጐት ማህበራትና ድርጅቶች ብቻ ናቸው፡፡ በሌላ አነጋጋር፣ በእነዚህ ዘርፎች ለመስራት ከውጪ ከ10 በመቶ በላይ ገንዘብ ማግኘት እንደማይቻል በመደንገጉ ድርጅቶቹ ህብረተሰቡን ከማስተማርና ከማወያየት ስራ ተቆጥበው በአገልግሎት አቅርቦት ላይ ብቻ እንዲሰማሩ አድርጓል፡፡
ይህም ሙስና እንዲስፋፋ፣ የህዝብ ቅሬታ እንዲጨምርና አማራጭ የመወያያ መድረኮች እንዳይኖሩ በማድረጉ ባለፉት አመታት በስፋት ለታየው የመልካም አስተዳደር እጦትና ህዝባዊ ተቃውሞ አስተዋጽኦ ማድረጉ በረቂቅ አዋጁ ላይ ተገልጿል፡፡
በመብትና ዲሞክራሲያዊ ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ ተቋማትን በገንዘብና በተለያዩ መንገዶች መደገፍና መርዳት በተቃዋሚነት ያስፈርጀናል የሚል ስጋት በግል ባለሃብቶች ዘንድ በመኖሩ ሳቢያ በሰብአዊ መብትና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች በከፍተኛ ሁኔታ ከስራ ውጪ እንዲሆኑ ተደርገዋል። የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለማጋለጥና ለመከላከል ትርጉም ያለው ስራ መስራትም አዳጋች ሆኖ መቆየቱን አዋጁ ጠቁሟል፡፡
በስራ ላይ በነበረው አዋጅ ላይ በገንዘብ ተረገድ የተቀመጠው ክልከላ የጐዳው ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን፣ በአጠቃላይ ህብረተሰቡን ሆኗል የሚለው ማሻሻያ አዋጁ፤ ለሀገር ደህንነት ስጋት የሆነ ህገወጥ ተግባር የሚፈጽሙ ድርጅቶች ላይ ክትትል በማድረግ በተጨባጭ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ ሲገባ፣ በአጠቃላይ ከውጪ አገር የሚመጣ ድጋፍ ላይ ክልከላ መጣሉ በህገ መንግስቱ ላይ የተደነገገውን የመደራጀት መብት የሚገድብና አገርን ያልጠቀመ እንደሆነ አመልክቷል፡፡
ከትናንት በስቲያ ለምክር ቤቱ የቀረበውና አባላቱ ውይይት ያደረጉበት ረቂቅ አዋጁ፤ ቀድሞ በአዋጁ ውስጥ የተካተቱት ህጐችና የመተዳደሪያ ስርዓቶች የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንዳይስፋፉ፣ ያሉትም ከስራ ውጪ እንዲሆኑ ያደረገና ከተጀመረው የለውጥ ሂደት ጋር ፈጽሞ አብሮ የማይሄድ መሆኑን ይገልፃል፡፡
በቀደመው የበጐ አድራጐት ማህበራት አዋጅ ላይ የተገለፀውና ድርጅቶቹ ከውጪ የሚያገኙት ገቢ ከ10 በመቶ መብለጥ የለበትም በሚለውና ከገቢያቸው 30 በመቶ ያህሉን ለአስተዳደር ወጪ ማድረግ እንደሚችሉ በሚደነግጉት የአዋጁ አንቀፆች ላይ በስፋት ተወያይተዋል፡፡ ረቂቅ አዋጁ በድርጅቶቹ የገንዘብ ማግኛ መንገድ ላይ የተጣለው ገደብ እንዲነሳ ማድረጉንና ድርጅቶቹ ከገቢያቸው ላይ ለአስተዳደር ወጪዎች ማውጣት የሚችሉት 20 በመቶውን ብቻ እንዲሆን ማድረጉ ከፍተኛ ተቀባይነትን አግኝቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ማንኛውም ድርጅት የተቋቋመበትን ህጋዊ ዓላማ ለማሳካት በየትኛውም ህጋዊ ስራ ላይ የመሰማራት ሙሉ መብት እንዳለው በረቂቁ ላይ ተመልክቷል፡፡
ድርጅቱ ለዓላማው መሳካት ገቢ ለማግኘት በማንኛውም ህጋዊ የንግድና ኢንቨስትመንት ስራ ውስጥ አግባብነት ባላቸው የንግድና ኢንቨስትመንት ህጎች መሰረት የመሳተፍ መብት አለው፡፡ ሆኖም ከስራው የሚገኘውን ትርፍ ለአባላት ጥቅም ማስተላለፍ አይችልም፡፡ ለዓላማው መሳካት ከየትኛውም ህጋዊ ምንጭ ገንዘብ የመጠየቅ፣ የመቀበልና የመጠቀም መብት አለው፡፡
ድርጅቶቹ በየትኛውም መንገድ ከሚያገኙት ገቢ፣ ለአስተዳደር ስራዎች ማውጣት የሚችሉት 20 በመቶውን ብቻ እንደሆነም ይኸው ረቂቅ አዋጅ አመልክቷል፡፡ ድርጅቶቹ አግባብ ባለው ህግ መሰረት፣ የስራ ፈቃድ ያልተሰጠውን የውጪ ዜጋ መቅጠር እንደማይችሉና ከድርጅቱ የአገር ውስጥ ተወካይ በስተቀር ሌሎች የውጪ አገር ዜጎችን በድርጅቱ ለመቅጠር የሚችት ሥራው በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች መከናወን የማይችል በመሆኑ ሲረጋገጥ ነው መባሉን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላቱ ደግፈውታል፡፡ በረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት የተወያዩት የምክር ቤቱ አባላት፤ ረቂቅ አዋጁን በዝርዝር በመመልከት፣ ከውሳኔ ሃሳብ ጋር ለምክር ቤቱ እንዲያቀርብ ጉዳዩ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡   

Read 731 times