Saturday, 12 January 2019 14:11

ፓርቲዎች በምን ጉዳዮች ላይ ሊደራደሩ አቅደቀዋል?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

ህገ መንግስት፣ ሰንደቅ ዓላማ፣ የአዲስ አበባ ጉዳይ …

     በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በቀጣይ የሚደረገው ውይይት የሚመራበት ስርአትና ደንብ ሰሞኑን የፀደቀ ሲሆን የህገ መንግስት ሰንደቅ አላማ፣ የክልሎች አወቃቀርና የአዲስ አበባ ጉዳይ በድርድር አጀንዳነት ቀርቧል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች ከረቡዕ ጀምሮ ለሁለት ቀናት ውይይቱ በሚመራበት ህገ ደንብ ላይ ውይይት ሲያደርጉ የሰነበቱ ሲሆን ትናንት ሁሉም በደንቡ ላይ የጋራ መግባባት ላይ ደርሰው አፅድቀዋል፡፡
ደንቡ በህግ ባለሙያዎች የተዘጋጀና በፓርቲዎች ውይይት የዳበረ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ፓርቲዎች በውይይቱ ወቅት የሚመሩበትን መርሆዎች፣ ውይይቱ የሚካሄድበትን ስርአት፣ ከውይይቱ ተሳታፊዎች የሚጠበቅ ኃላፊነት፣ የአወያዮቹ ኃላፊነትና ግዴታ፣ የመገናኛ ብዙኃን ሚናና ግዴታን ያካተተ ነው፡፡
16 አንቀፆች ያለው ደንቡ ውይይቱ በገለልተኛ ወገኖች እንዲመራና ገለልተኛ አካላቱ በፓርቲዎቹ የጋራ ስምምነት እንደሚመረጡ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ታዛቢዎችም ከሙያ ማህበራት እንዲሁም ከንግድና ስራ ማህበራት ይመረጣሉ ተብሏል፡፡
ፓርቲዎቹ በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ውይይት ካደረጉ በኋላ የጋራ ስምምነት ላይ መድረስ ካልቻሉ በአጀንዳው ላይ የሚተላለፈው ውሳኔ በአብላጫ ድምፅ እንዲሆንም ተስማምተዋል፡፡
ለሁለት ቀናት በተካሄደው በዚህ ውይይት ላይ በፓርቲዎች መካከል ለሚደረገው ድርድርና ውይይትም 32 አጀንዳዎች መቅረባቸው ታውቋል፡፡
በእነዚህ አጀንዳዎች በዋናነት ከተካተቱት መካከልም ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚደረግ ድጋፍ፣ ስለ ፓርቲዎች ውህደትና ትብብር፣ የምርጫ ቦርድ አደረጃጀት፣ የ2012 የምርጫ መራዘም ጉዳይ፣ የሃገሪቱ ሰላምና መረጋጋት፣ የፀጥታና ደህንነት ተቋማትን ግንባታ ጉዳይ፣ የህገ መንግስት ማሻሻያ፣ የፌደራል የስራ ቋንቋን በተመለከተ፣ የአዲስ አበባ ጉዳይ፣ ሰንደቅ አላማ፣ የመንግስት አደረጃጀትና የክልሎች አወቃቀርን የተመለከቱ ናቸው፡፡ ፓርቲዎቹ በቀጣይ መደበኛ ውይይትና ድርድር የሚጀምሩበት ቀን ይፋ ይደረጋል ተብሏል፡፡

Read 1558 times