Saturday, 12 January 2019 14:17

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትሪያሪክ አቡነ መርቆሪዮስ ዛሬ ጐንደር ይገባሉ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ - (ጐንደር)
Rate this item
(2 votes)

ህዝቡ በጉጉት ይጠብቃቸዋል ተብሏል
                
    ብፁዕ ወቅዱስ ፓትሪያሪክ አቡነ መርቆሪዮስ ዛሬ ጐንደር የሚገቡ ሲሆን ከ27 ዓመታት በኋላ የጐንደርን መሬት ይረግጣሉ ተብሏል፡፡ የአቀባበሉ ኮሚቴ አባል ዲያቆን አደራጀው አዳነ ለአዲስ አድማስ እንደገለፀው የጐንደር ህዝብ በጉጉት ነው የሚጠብቃቸው፡፡
ለፓትሪያሪኩ ከጐንደር አፄ ቴዎድሮስ አየር ማረፊያ ፋሲል ግንብ አጠገብ እስከሚገኘው አደባባይ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ድረስ በበርካታ ህዝብና ተሽከርካሪዎች ታጅበው እንደሚጓዙ የተገለፀ ሲሆን፤ ዘጠኝ ሊቀጳጳሳትም ከአዲስ አበባ አጅበዋቸው እንደሚመጡ ተሽከርካሪዎች ኮሚቴው አስታውቋል፡፡ በአቀባበሉ ላይ የጐንደር ሁሉም አድባራት፣ የአድባራቱ አስተዳዳሪዎች፣ ካህናት፣ የሰንበት ት/ቤት መዘምራን፣ የማህበረ ቅዱሳን አባላት፣ ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎችና ሌሎችም የማህበረሰብ አባላት በድምቀት ይቀበሏቸዋል ተብሏል፡፡ አቡነ መርቆሪዮስ በአደባባይ ኢየሱስ እረፍት ካደረጉ በኋላ በመስቀል አደባባይ በተዘጋጀላቸው የአቀባበል መርሃ ግብር ላይ እንደሚታደሙ ታውቋል፡፡
አቡነ መርቆሪዎስ ከዛሬ ጀምሮ የጐንደርን ህዝብ ለመባረክና ለመጐብኘት እቅድ እንደያዙና ዘንድሮም በድምቀት በሚከበረው የጥምቀት በዓል ላይ እንደሚታደሙ የገለፁት ዲያቆን አደራጀው ህዝቡ ላለፉት 27 ዓመታት የተለያቸውንና የናፈቃቸውን እኒህን ትልቅ አባት በአካል ለማየት በጉጉት እየጠበቀ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትሪያሪክ አቡነ መርቆሪዮስ፤ ፓትሪያሪክ ከመሆናቸው በፊት የጐንደር ሊቀጳጳስ በነበሩበት ጊዜ በመንፈሳዊ አገልግሎታቸውና በሰሯቸው በርካታ የልማት ሥራዎች በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት እንደነበራቸውም ታውቋል፡፡ ፓትሪያሪኩ በመንግስት ጫና ከአገር ሲሰደዱና አቡነ ጳውሎስ ፓትሪያሪክ ሆነው ወደ አገር ውስጥ ሲመጡ የጐንደር ህዝብና አድባራቱ ከቤተክርስቲያኗ ሥነ ሥርዓትና ህግ አንፃር ፓትሪያሪክ ሳይሞት ሌላ ፓትሪያሪክ መሾም አይቻልም በሚል፣ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲያሰማ መቆየቱን ያስታውሱት ዲያቆን አደራጀው፤ አሁን በድጋሚ የጐንደር ህዝብን ለመባረክ በመምጣታቸው የህዝቡ ደስታ ወደር የለውም ብለዋል፡፡
ከፓትሪያሪክ አቡነ መርቆሪዮስ ጋር ከአዲስ አበባ አብረዋቸው ከሚሄዱት ዘጠኝ ሊቀ ጳጳሳት በተጨማሪ የባህርዳሩ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ አብረሃምና የደቡብ ጐንደሩ ሊቀጳጳስ አቡነ ሚካኤልም እንደሚያጅቧቸው ታውቋል፡፡

Read 10211 times