Saturday, 12 January 2019 14:20

32ኛው የአፍሪካ ዋንጫን

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

  • ግብፅ በመንፈቅ ውስጥ ልታዘጋጅ ነው
   • በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ 24 ብሄራዊ ቡድኖች ይሳተፉበታል
   • የ2018 የአፍሪካ ኮከብ ሞሃመድ ሳላህ ማሸነፍ ይፈልጋል


   የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን በሳምንቱ መግቢያ ላይ በዳካር፤ ሴኔጋል  ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ 32ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ካሜሮንን በመተካት ግብፅ እንድታስተናግድ ውሳኔ አሳልፏል። የካፍ ስራ አስፈፃሚ የካሜሮንን አዘጋጅነት ከነጠቀ በኋላ ያለፉትን ሁለት ወራት  ተተኪ አዘጋጆን  እንዲያመለክቱ አድርጎ ነበር፡፡ አልጄርያ፤ ጋናና ሞሮኮ አዘጋጅነቱን ለመረከብ ከጅምሩ ፍላጎት ቢያሳዩም ከግብፅ ጋር እስከመጨረሻው የተፎካከረችው ደቡብ አፍሪካ ብቻ ነበረች፡፡ የአፍሪካ ዋንጫውን በ6 ወራት ውስጥ ለማስተናገድ የተሟላ የስፖርት መሰረተልማት፤ የበጀት አቅምና እና የመንግስት ዝግጁነት አስፈላጊ መሆኑ አገራቱን ተፈታትኗቸዋል። በመጨረሻም የካፍ ስራ አስፈፃሚ በስታድዬም መሰረተ ልማት፤ በተቀናጀ የውድድር አመራር እና በመንግስት ዝግጁነት በተሻለ ደረጃ ላይ ለነበረችው ግብፅ አዘጋጁን ሲሰጣት፤ እስከመጨረሻው ምዕራፍ ለመስተንግዶው የተፎካከረችውና የበጀት አቅም ያልነበራትን ደቡብ አፍሪካ ደግሞ በከፍተኛው በማመስገን አሰናብቷታል፡፡
ካሜሮን በ2017 እኤአ ላይ 31ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ በጋቦን ካሸነፈች በኋላ በሻምፒዮናነት በ2019 እኤአ ውድድሩን እንድታዘጋጅ መመረጧ ትልቅ እድል ነበር፡፡ ይሁንና አጠቃላይ ዝግጅቶቿ በመጓተታቸው፤ ከቦኮ ሀራም ጋር በተያያዘ በመላው አገሪቱ ሁከት እና ብጥብጥ  መስፋፋቱ  እንዲሁም በመንግስት በኩል አስፈላጊውን በጀት አለመሰጠቱን በማገናዘብ የካፍ ስራ አስፈፃሚ አዘጋጅነቱን ሊነጥቅ ግድ ሆኖበታል፡፡ ካፍ በሚከተለው  ህገ ደንብና መመሪያ አንጻር ውድድሩን የማራዘሙ ጉዳይ አዳጋችና ከፍተኛ ኪሳራ የሚፈጥር በመሆኑ ተተኪ አዘጋጅ የግድ ያስፈልገው ነበር፡፡    ከ1972 እኤአ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫውን የማስተናግድ እድል አግኝታ የነበረችው ካሜሮን በ31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለ5ኛ ጊዜ ያገኘችውን የሻምፒዮናነት ክብር በአዘጋጀነቷ ለማስጠበቅ ልዩ የታሪክ አጋጣሚ ተፈጥሮላት ነበር፡፡ ካሜሮን ከ2 ዓመት በፊት ለአዘጋጅነቱ ስትመረጥ የተፎካከሯት አልጄርያ እና አይቬሪኮስት የነበሩ ሲሆን፤  ሁለቱ አገራት ምትክ አዘጋጅነቱን ለማግኘት የመጀመርያዎቹ ጠያቂዎች ነበሩ አልተሳካላቸውም እንጅ፡፡ በካሜሮን እግር ኳስ በርካታ ተከታታይ ያለው ንጉሱ ስፖርት ሲሆን በአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት የሚፈጠረውን መነቃቃት ለመጠቀም ባለመቻሉ የአገሬው ሚዲያዎች ተቆጭተዋል፡፡ አፍሪካ ዋንጫን በተሳካ ሁኔታ ማስተናገድ ለሌሎች  ዓለም አቀፍ የስፖርት መድረኮች በቂ ተመክሮ የሚቀሰምበትና ዓለም አቀፍ ትኩረት የሚገኝበት ነበር፡፡
ግብፅ የምታዘጋጀውን 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ብዙ ሁኔታዎች ልዩ ያደርጉታል፡፡ የተሳታፊ አገራት ብዛት በውድድሩ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ከ16 ወደ 24 ማደጉ የመጀመርያው ሲሆን ግጥሚያዎች የሚካሄዱበት ወቅት ከፈረንጆች አዲስ አመት መግቢያ ወደ ፈረንጆች ሰኔ እና ሐምሌ ወራት መዛወሩ ሌላኛው ነው፡፡ ወደ 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማለፋቸውን ያረጋገጡት 14 አገራት ሲሆኑ በአዘጋጅነት ካሜሮንን የተካችው ግብፅ፤ ማዳጋስካር፤ ቱኒዚያ፤ ሴኔጋል፤ ሞሮኮ፤ ናይጄርያ፤ ኡጋንዳ፤ ማሊ፤ ጊኒ፤ አልጄርያ፤ ሞውሪታኒያ፤ አይቬሪኮስት፤ ኬንያ እና ጋና ናቸው፡፡ ማዳጋስካር እና ሞሪታኒያ በአፍሪካ ዋንጫው ለመጀመርያ ጊዜ የሚሳተፉ ናቸው፡፡  በቀሪዎቹ የ10 ብሄራዊ ቡድኖች ኮታ ላይ ለመግባት ኮሞሮስ፤ ብሩንዲ፤ ጋቦን፤ ቤኒን፤ ቶጎ፤ ደቡብ አፍሪካ፤ ሊቢያ፤ ዚምባቡዌ፤ ላይቤርያ፤ ዲ.ሪ ኮንጎ፤ አንጎላ፤ ቡርኪናፋሶ፤ ጊኒ ቢሳዎ፤ ሞዛምቢክ፤ ሌሶቶ እና ዛምቢያ በሚቀጥሉት ወራት የሚደረጉት የመጨረሻ ዙር የማጣርያ ግጥሚያዎች እድላቸውን ይወስናሉ፡፡
ግብፅ በ5 ከተሞቿ  በሚገኙ 8 ስታድዬሞችን በመጠቀም 32ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ለማስተናገድ የወሰነች ሲሆን በሚቀጥሉት 6 ወራት የመጨረሻ ዝግጅቶቿን ለማድረግ ሩጫ ገብታለች፡፡ የግብፅ ብሄራዊ የቲቪ ጣቢያ ሁሉንም የአፍሪካ ዋንጫዎች እንደሚያስተላልፍ ማሳወቁንና የአገሪቱ መንግስት የበጀት አቅሙን ለመደገፍ መስማማቱና ስለሰላምና ፀጥታው ማስተማመኛ መስጠቱን ሰሞኑን ትልልቅ የአፍሪካ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡ በተለይ በካይሮ ከተማ የሚገኙት ሁለት ስታድዬሞች የመክፈቻ እና የዋንጫ ጨዋታ የሚያስተናግዱበት የተሟላ መሰረተልማትና እና ዘመናዊነት ስላላቸው ለውድድሩ ድምቀት እንደሚፈጥሩ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን እምነት አሳድሯል፡፡ ውድድሩ በፈረንጆች ሰኔ እና ሐምሌ ወራት መካሄዱ ግን ብዙዎችን እንዳሰጋ ነው፡፡ የግብፅ ከተሞች አፍሪካ ዋንጫው ሊካሄድ በታቀደበት ወቅት የአየር ንብረታቸው ሞቃታማ እንደሚሆን መገለፁን ተከትሎ የአፍሪካ ዋንጫ አንዳንድ ግጥሚያዎችን በምሽት ማድረግ እንደመፍትሄ እየታሰበ ነው፡፡ 24 ብሄራዊ ቡድኖች በሚሳተፉበት የአፍሪካ ዋንጫ ከመጀመርያው የምድብ ጨዋታ እስከ ፍፃሜው ድረስ 51 ግጥሚያዎች ይደረጋሉ፡፡ ካይሮ፤ አሌክሳንድርያ፤ ኢስማሊያ፤ ስዌዝ እና ፖርትሰይድ እነዚህን የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች እንዲያስተናግዱ የታሰቡት ከተሞች ናቸው፡፡
የአፍሪካ ዋንጫን ለሰባት ጊዜያት በማሸነፍ በከፍተኛ ውጤት ክብረወሰን የያዘችው ግብፅ ውድድሩን ከ6 ወራት በኋላ የምታዘጋጀው በታሪኳ ለአምስተኛ ጊዜ ይሆናል፡፡ ከ32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በፊት  4 የአፍሪካ ዋንጫዎችን  በ1959, 1974, 1986, 2006 እኤአ ላይ አስተናግዳ ነበር፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ አዘጋጅነቷን አግኝታ የነበረው በ2ኛው አፍሪካ ዋንጫ ላይ ሲሆን በሻምፒዮናነት አጠናቅቃለች። ሁለተኛ መስተንግዶዋን ከ15 ዓመታት በኋላ በ1974 ላይ አግኝታ በግማሽ ፍጻሜ ተሰናብታ በደረጃ ጨዋታ 3ኛ ነበረች፡፡ 3ኛውን አዘጋጅነት በ1986 እኤአ ስታገኘው በድጋሚ ዋንጫውን ምድሯ ላይ አስቀርታዋለች፡፡ ለ4ኛ ጊዜ ያዘጋጀችው በ2006 እኤአ ሲሆን ለፍፃሜ ደርሳ ዋንጫውን በአይቬሪኮስት የተነጠቀችበት ነበር፡፡ ባለፉት 62 ዓመታት የተካሄዱትን 32 የአፍሪካ ዋንጫዎች አንዴና ከዚያም በላይ ለማዘጋጀት የቻሉት 19 አገራት ናቸው፡፡ ግብፅ 32ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ከተረከበች በኋላ ለአምስተኛ ጊዜ ውድድሩን በማዘጋጀት ቀዳሚ ሆናለች፡፡ አራት ግዜ በማዘጋጀት ተከታዩን ስፍራ የምትይዘው ጋና ናት፡፡ እያንዳንዳቸው ሶስት ጊዜ ማስተናገድ የቻሉት ሁለት አገራት ደግሞ ኢትዮጵያ እና ቱኒዚያ ናቸው፡፡ እያንዳንዳቸው ሁለት ጊዜ  አዘጋጅ በመሆን ደግሞ 5 አገራት ናይጄርያ፤ ሞሮኮ፤ ደቡብ አፍሪካ፤ ሱዳን እና ጋቦን ተሳክቶላቸዋል፡፡ 9 አገራት ደግሞ የአፍሪካ ዋንጫን አንድ ጊዜ ያዘጋጁ ሲሆን እነሱም አልጄርያ፤ አንጎላ፤ ቡርኪናፋሶ፤ ካሜሮን፤ አይቬሪኮስት፤ ኢኳቶርያል ጊኒ፤ ማሊ፤ ሴኔጋል እና ሊቢያ ናቸው፡፡
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን የአፍሪካ ዋንጫውን ተሳታፊ አገራት ብዛት ከ16 ወደ 24 ካሳደገ በኋላ ለአዘጋጅነት ብቁ አድረጎ የሚመርጣቸው አገራት  በሆቴል እና መስተንግዶ፤ ቢያንስ 6 አለም አቀፍ ደረጃ የጠበቁ ስታድዬሞች ከእነ ልምምድ ስፍራቸው፤ በቂ የአየር እና የየብስ ትራንስፖርት አገልግሎት፤ አስተማማኝ ደህንነት እና ፀጥታን በዋና መስፈርቶቹ ይመለከታል፡፡ የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ደግሞ ከ50 እስከ  80 ሚሊዮን ዶላር  በጀት ያስፈልጋል፡፡ የአፍሪካ ዋንጫ መስተንግዶ ከመንግስት የበጀት ድጋፍ፤ ከካፍ የገንዘብ አስተዋፅኦ፤ ከስፖንሰርሺፕ እና ከተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች በሚገኝ ገቢ ሊንቀሳቀስ የሚችል ነው፡፡ የውድድር ማካሄጃ፤ የአስተዳደር ስራዎች፤ የጉዞ እና የሆቴል አገልግሎት እና ሌሎች ተግባራትን ለማከናወን ደግሞ ወጭዎች ይኖሩታል። የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ለአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ አገር 6.2 ሚሊዮን ዶላር የሚያበረክት ሲሆን በሁሉም አዘጋጅ ከተሞች የውድድሩ ብሄራዊ ኮሚቴ አብሮ የሚሰራበት ምክር ቤትና ከአምስት በላይ ከብሄራዊ ኮሚቴው ጋር ተፈራርመው የሚሰሩ የመንግስት ተቋማት በስሩ መንቀሳቀስ አለባቸው። ለ24 ብሄራዊ ቡድኖች በአዘጋጅ ከተሞች ሙሉ የስልጠና ሜዳ እና ከስታድዬም ከ5 እስከ ሰላሳ ደቂቃ ጉዞ ያላቸው የማረፊያ ሆቴሎች፤ዓለም አቀፍ ደረጃ ያሟሉ ቢያንስ ስድስት ስታድዬሞች ያስፈልጋሉ፡፡ ከ200 በላይ ከብሄራዊ ኮሚቴው ጋር የሚሰሩ ሰራተኞች፤ ከ2500 በላይ ውድድሩን የሚያስተናግዱ በጎፍቃደኞች፤ የውድድሩ ኦፊሴላዊ ድረገፅ፤ ውድድሩን የሚገልፅ መርህ፤ የውድድሩ መለያ የሆነ ምልክት እና ሎጎ፤ በከፍተኛ ደረጃ ውድድሩን የሚያስተዋውቁ ባነሮች፤ ቢልቦርዶች እና ፖስተሮችም አንድ የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ አገር ለስኬታማ መስተንግዶ የሚያከናውናቸው ስራዎች ናቸው፡፡
በተያያዘ የዓለማችን ግዙፉ የግብይት ካርድ ቪዛ በ2019 እና በ2021 የሚካሄዱትን የአፍሪካ ዋንጫዎች ስፖንሰር ለማድረግ ከካፍ ጋር ስምምነት አድርጓል። የውል ስምምነቱ ዓለም አቀፉን ብራንድ እና ቴክኖሎጂውን ወደ አፍሪካ እግር ኳስ እንደሚያስገባ ተጠብቋል፡፡ ቪዛ ከ2007 ጀምሮ ከፊፋ ዓለም ዋንጫ በስፖንሰርሺፕ አጋርነት እየሰራ ቆይቷል። ቶታል በ2016 እኤአ የካፍን 10 ውድድድሮች እስከ 2024 እኤአ በስፖንሰርሺፕ ለመደገፍ ከካፍ ጋር ስምምነት ማድረጉ ይታወቃል፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ ለሽልማት የሚቀርበው ገንዘብ እስከ 16.4 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን አሸናፊው 4 ሚሊዮን ዶላር፤ 2 ሚሊዮን ዶላር ለሁለተኛ፤ ለግማሽ ፍጻሜ 1.5 ሚሊዮን ለእያንዳንዳቸው፤ ለሩብ ፍጻሜ 800ሺ፤ ለምድብ 3ኛ ደረጃ 57ሺ ዶላር እንዲሁም በ4ኛ ደረጃ ምድባቸው ላይ ለሚጨርሱ 475ሺ ዶላር ይበረከታል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግብፃዊው ሞሀመድ ሳላህ የ2018 የአፍሪካ ኮከብ ተጨዋች ሆኖ የተመረጠ ሲሆን ከቀድሞው ኳስ ተጨዋች እና ከአሁኑ የላይቤርያ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ዊሃ እጅ ሽልማቱን የተቀበለው ሰሞኑን በዳካር ሴኔጋል በተከናወነ ስነስርዓት ነው፡፡ ሞሃመድ ሳላህ ለሁለተኛ ተከታታይ ዓመት የአፍሪካ ኮከብ ተጨዋች ለመሆን ሲበቃ እስከ መጨረሻው የተፎካከሩት ሴኔጋላዊው ሳዲዮ ኦማኔ እና ጋቦናዊው ፒየር ኤምሪክ ኦቤምያንግ ነበሩ፡፡ በኮከቦች ምርጫው ከካፍ 56 አባል አገራት በመጀመርያው ምዕራፍ የካፍ ቴኒክና ዴቨሎፕመንት ኮሚቴ፤ በምእራፍ 2 አሰልጣኞች፤ አምበሎች እና ቴክኒካል ዲያሬክተሮች ከአባል ፌደሬሽኖች እንዲሁም በመጨረሻው ምዕራፍ የሚዲያ ኤክስፐርቶች፤ የቀድሞ እውቅ ተጨዋቾች እና አሰልጣኞች ድምፅ በመስጠት ተሳትፈዋል፡፡
በሌሎች የካፍ ሽልማቶች የዓመቱ ምርጥ ሴት ተጨዋች የደቡብ አፍሪካዋ ክሪስቲናህ ቴምቢ ካግታላና፤ የዓመቱ ወጣት ተጨዋች ለጀርመኑ ቦርስያ ዶርትመንድ የሚጫወተው ሞሮካዊው አችራፍ ሃኪሚ፤ የዓመቱ ምርጥ አሰልጣኞች በወንዶች ፈረንሳዊው ሄርቬ ሬናርድ በሞሮኮ ብሄራዊ ቡድን እንዲሁም በሴቶች ዴሳይሪይ ኤሊስ በደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድን፤ የዓመቱ ምርጥ ብሄራዊ ቡድን በወንዶች ሞውሪታኒያ በሴቶች ናይጄርያ፤ የካፍ ፕላቲኒዬም አዋርድ ለሴኔጋሉ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል እና የዓመቱ ምርጥ የፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ይድነቃቸው ተሰማ ሽልማት ፋውዚ ሌካጃን ተሸልመዋል፡፡
በተጨማሪም የዓመቱን ምርጥ ጎል የደቡብ አፍሪካዋ ክሬስታናህ ቴምቢ ስታሸንፍ በ2018 የአፍሪካ ምርጥ ቡድን CAF –FifPro Best XI ደግሞ ግብ ጠባቂ: ዴኒስ ኦናያንጎ (Uganda & Mamelodi Sundowns)፤ ተከላካዮች: ሴርጄ ኦርዬር (Cote d’Ivoire & Tottenham Hotspur) ካሊዱ ኩሊባሊ (Senegal & Napoli) ኤሪክ ባዬሊ (Cote d’Ivoire & Manchester United), መሀዲ ባኔትያ (Morocco & Juventus)፤ አማካዮች: ናቢ ኪዬታ (Guinea & Liverpool) ቶማስ ፓርቲዬ (Ghana & Atletico Madrid) ሪያድ ማህሬዝ (Algeria & Manchester City) እና አጥቂዎች: ሞሃመድ ሳላህ (Egypt & Liverpool) ሳዲዮ ማኔ (Senegal & Liverpool) ፒዬር ኦምሪክ ኦቤምያንግ (Gabon & Arsenal) ናቸው፡፡
ሞሃመድ ሳላህ የአፍሪካ ኮከብ ተጨዋች ሆኖ ሽልማቱን በተቀበለበት ወቅት ‹‹ይህ ሽልማት ለእኔ ትልቅ ነው፡፡ የምወድበት ልዩ ምክንያት ገና በታዳጊነት እያለሁ አንድ ቀን እንደማሸንፈው ሳልም ነበር፡፡ ሁለት ጊዜ አከታትዬ በመሸለሜም ኩራት ተሰምቶኛል፡፡ ቤተሰቤን የቡድን አጋሮቼን ማመስገን አለብኝ፡፡ ይህ ሽልማት መታሰቢያነቱ ከአገሬ ግብፅ ነው፡፡›› በማለት ተናግሯል፡፡ አገሩ በምታዘጋጀው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ሻምፒዮን ለመሆን ፍላጎት እንዳለው ገልጿል፡፡ የ26 ዓመቱ ሞ ሳላህ በ2018 ሩስያ ባዘጋጀችው 21ኛው ዓለም ዋንጫ ለግብፅ ተሰልፎ ሲጫወት ሁለት ጎሎች ያስመዘገበ ሲሆን ሊቨርፑል ለሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ እንዲበቃ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበረው፡፡ በ2017-18 በሊቨርፑል 44 ጎሎች ያስመዘገበ ሲሆነ ለግብፅ ብሄራዊ ቡድን በ62 ጨዋታዎች ተሰልፎ 39 ጎሎች አስመዝገቧል፡፡ በ2018/ 19 ለሊቨርፑል 13 ጎሎችን እስካሁን  ማስመዝገብ በሊጉ የመሪነት ስፍራ ላይ እንዲቀመጥ ያስቻለው ሲሆን እስከ 2023 እኤአ በክለቡ በሚያቆየው ኮንትራት በዝውውር በገያው የዋጋ ተመኑ 150 ሚሊዮን ዩሮ ነው፡፡

Read 8566 times