Print this page
Saturday, 12 January 2019 14:23

የህወሓት መኳንንት ነገር ....

Written by  በመስከረም አበራ
Rate this item
(2 votes)

 በሃያ ሰባት አመታት የህወሓት/ኢህአዴግ አምባገነናዊ ስርዓት የኖረው የሃገራችን ህዝብ፤ በትግሉ የህወሓትን የበላይነት ከኢትዮጵያም ከኢህአዴግም ትከሻ ማሽቀንጠርን ችሏል፡፡ ስልጣን እየጣመው የቀረበት ህወሓት፤እሱ የማይዘውራት ኢትዮጵያ በሰላም ውላ ማደሯን የሚወድ አይመስልም፡፡ በስልጣን ዘመኑ “እኔ ከሌለሁ ሃገር ይፈርሳል” እያለ ሲያስፈራራ ስለኖረ፣ እሱ በሌለበት ሃገር ሰላም ውላ ማደር እንደማትችል ማስመስከር ይፈልጋል፡፡ ህዝብ ለውጡን ለመደገፍ ነቅሎ በወጣበት የድጋፍ ሰልፍ ላይ ቦምብ በመወርወር፣ በሃገሪቱ አራቱም አቅጣጫ የሚከሰቱ ብጥብጦችን በመቆስቆስ፣ እንደ ኦነግ ያለውን ወዳጅ ጠላት የማይለይን የፖለቲካ ቡድን አይዞህ እያለ በማበጣበጥ ይጠረጠራል - ስልጣን ወዳዱ ህወሓት፡፡
ሳይፈልግ ብቻ ሳይሆን ሳያስብ የለውጥ ማዕበል ያጣለመው ህወሓት፤ ለውጡ ይዞት የመጣውን አመራር ለመቀበል እንደተቸገረ ያስታውቅበታል፡፡ አሁን የለውጥ ሃይል ሆነው ስልጣን የተቆናጠጡት  አካላት (በዋናነት ኦዴፓ እና አዴፓ) ቀድሞ የህወሓት ታማኝ ታዛዥ አገልጋዮቹ የነበሩ መሆናቸው፣ ህወሓት ለራሱ ከሚሰጠው የተጋነነና የተሳሳተ ግምት ጋር ሲደመር፣ ያፈጠጠውን እውነት ለመቀበል እንዲቸገር ሳያደርገው አልቀረም፡፡
ህወሓት ሊወድቅ ዘመም ዘመም ሲል ወደ ጀርመን ተጉዘው፣የድርጅቱን ደጋፊዎች ያነጋገሩት አቶ ጌታቸው ረዳ፤ “ህወሓት በሌላ ይታዘዝ ማለት ነውር ነው” ሲሉ የተናገሩት ንግግር ህወሓቶች ንዑስነታቸውን በማይመጠን ሁኔታ ለራሳቸው የሰጡትን ትልቅ ግምት አመላካች ነው፡፡ እንዲህ ባለ ያለቅጥ በተጋነነ የትልቅነት ሥነ-ልቦና ውስጥ የቆየው ፓርቲው፤በራሱ አገልጋዮች ተባርሮ መቀሌ መግባቱ ሊቀበለው የማይፈልገው ሃቅ ነው፡፡ ሃቅን መቀበል ባለመቻሉ ሳቢያ በሥነ-ልቦና ቀውስ ውስጥ ያለው ድርጅቱ፤የራሱን ቀውስ ሃገራዊ ቀውስ ለማስመሰል ታጥቆ እየሰራ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት በሃገራችን የታየውን የለውጥ ጭላንጭል በማጨለም ረገድ ህወሓት ቀዳሚው ስጋት ሳይሆን አይቀርም፡፡
ህወሓት የለውጡ ስጋት መሆኑን የሚያስመሰክርበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ የመጀመሪያውና ዋነኛው በወንበሩ ላይ የተቀመጠውን የለውጥ አመራር እንደ መንግስት ለመቀበል መቸገር ነው፡፡ ይህ ዝንባሌ ከሚገለፅባቸው ሃቆች አንዱ የዶ/ር ዐቢይ አስተዳደር፣ በወንጀል የሚፈልጋቸውን ግለሰቦች ትግራይ ሰብስቦ ማስቀመጡ ነው። ጌታቸው አሰፋን የመሰለ ተጠርጣሪ ወንጀለኛ በጉያው የያዘው ድርጅቱ፤ “ጀነራል ክንፈ ዳኘውን ይዤ ለማእከላዊው መንግስት የሰጠሁት እኔ ነኝ” ሲልም ይደመጣል። ጀነራል ክንፈ ዳኘው በተያዙ ሰሞን ወንጀለኞችን ለመያዝ የትግራይ ክልላዊ መንግስት ከማዕከላዊው መንግስት ጋር ተባብሮ እንደሚሰራ የክልሉ መሪ ዶ/ር ደብረፅዮን ተናግረው ነበር፡፡ ይህን ብለው አፍታም ሳይቆዩ ደግሞ “ወንጀለኞችን ተጠያቂ የሚያደርገው የመንግስት አካሄድ የትግራይን ህዝብ ለማንበርከክ ያለመ ነው” ሲሉ ነገሩን፡፡ ሁሉ እግር በራስ አድርገውት ቁጭ አሉ፡፡ ይህ አደገኛ አስተሳሰብ የሚመሩት ክልል ህዝብም የሚጋራው እንደሆነ በተግባር ለማሳየት፣ ሰላማዊ ሰልፍ በማታውቀው ትግራይ ክልል፣ ሰው በቤቱ የቀረ የማይመስልበት ሰልፍ አሰለፉ፡፡
ህግ የሚፈልጋቸውን ተጠርጣሪ ወንጀለኞች የደበቀ ክልል፣ “ህገ-መንግስት ይከበር” ሲል የዋለበት ሰልፍ፤ የትግራይ ክልል መንግስት ለዶ/ር ዐቢይ አስተዳደር ለመታዘዝ ዝግጁ አለመሆኑን ያስመሰከረበት ነው፡፡ በሰልፉ ላይ  ከተደረገው የዶ/ር ደብረፅዮን ንግግር በተጨማሪ እንደ አቶ አስመላሽ ገ/ስላሴ፣ አቶ ስብሃት ነጋን የመሰሉ የህወሓት አባላትም በትግራይ ቲቪ ብቅ  እያሉ የሚወረውሩት ንግግር፣ ኢትዮጵያ ከህወሓት ውጭ በሌላ መተዳደሯ እንደማይዋጥላቸው የሚያሳብቅ ነው። አልዋጥ ያላቸው ሃቅ ደግሞ ህዝብን አግተልትሎ ሰልፍ ከማስወጣት አልፎ በመላ ሃገሪቱ የሚደረጉ ብጥብጦችን እስከ ማጋፈር የደረሰ ሚና እየተጫወተ እንደሆነ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እየተገለፀ ነው፡፡
የትግራይ ክልላዊ መንግስት፣ ለፌደራሉ መንግስት አልታዘዝም ከማለት አልፎ ራሱን እንደ ሉዓላዊ ግዛት በማሰብ በህገ መንግስቱ ያልተፈቀደለትን አካሄድ እንደ መብት በመቁጠር ለኤርትራ መንግስት ደብዳቤዎችን በመፃፍ ግንኙነት ለማድረግ ሲሞክር ታይቷል፡፡ የሃገር መከላከያ ሰራዊት በፌደራል መንግስቱ ታዝዞ ከዛላምበሳ በሚነሳበት ወቅት የአካባቢው ነዋሪ ያለ መብቱ ገብቶ ለማዘዝ ሞክሯል፡፡ የክልሉ መንግስት፣በማዕከላዊ መንግስት ትዕዛዝ ለስራ ጉዳይ ወደ ትግራይ የሚገቡ ወታደራዊ መኮንኖችንና ተሽከርካሪዎቻቸውን አግቶ ለወራት በትግራይ አስቀምጧል፡፡ ዶ/ር ደብረፅዮን፣ አቶ አስመላሽ ወ/ስላሴ፣ አቶ ጌታቸው ረዳና አቶ አባይ ፀሃዬን ጨምሮ አብዛኞቹ የህወሓት አባል የፓርላማ ተመራጮች፣ ሌላው ቀርቶ ዶ/ር ዐቢይ ፓርላማ በሚገኙባቸው ቀናት እንኳን የፓርላማ ወንበራቸው ላይ አይታዩም፡፡
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ፓርላማው ከፍተኛው የሥልጣን ባለቤት ነው፡፡ የፓርላማ አባላት የተባሉ ሰዎች በመርህ ደረጃ ይህን ከፍተኛ ስልጣን የተሸከሙ ግለሰቦች ናቸው፡፡ ስልጣን ደግሞ ሃላፊነትና ተጠያቂነት ያለው ነገር ነው፡፡ የፓርላማ አባልነትን የመሰለ ክብር ያለው ሃላፊነት የተሸከሙ ሰዎች ከኔ ቢጤው ተራ ህዝብ ላቅ ያለ ህግ የማክበር ሰብዕና ሊኖራቸው ግድ ነው፡፡ በእኛ ሃገር በተለይ በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ የፓርላማ አባላት ላይ እየታየ ያለው ፈለግ ግን ህግ አክባሪነትን የሚያንፀባርቅ አይደለም፡፡ የህዝብ ድምፅ ይሆናሉ ተብለው በክቡሩ የፓርላማ ወንበር የተሰየሙ አባላት አዘውትረው በፓርላማ ስፍራቸው ላይ እየተገኙ አይደሉም፡፡  
ይህ ነገር በህወሓት ባለሥልጣናት በተለይ ባስ ይላል፡፡ ከላይ በስም የተጠቀሱት የህወሓት ባለሥልጣናት የዶ/ር ዐቢይን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ፣ በፓርላማ አዘውተረው ሲገኙ አይታይም። በተመሳሳይ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ባለቤታቸው ካረፉ ወዲህ ወደ ፓርላማ ትውር ብለው አያውቁም፡፡ ይብስ የሚገርመው ደግሞ ህግ - ይከበር ብለው ሰልፍ የሚወጡት/የሚያስወጡት እነሱው መሆናቸው ነው፡፡ ከዚህ የምንረዳው ለነዚህ የህወሓት ባለሥልጣናት ፓርላማ የሚያስቀምጣቸው፣ ሃላፊነቱ የሚጥማቸው፣ ህግ አክባሪ ከእኔ በላይ ላሳር የሚያስብላቸው ሁሉ የተቆራኛቸው የስልጣን ጥም እንጂ ሌላ እንዳልሆነ ነው፡፡ ባይሆን ኖሮ የአዲስ አበባውን ሥልጣን ተነጥቀው ወደ መቀሌ በኮበለሉ ማግስት፣ ስለ ህግ አክባሪነታቸው ሃያ ሰባት አመት ሙሉ ሲመፃደቁ መኖራቸውን ረስተው፣ የፓርላማ ወንበራቸው ላይ እንኳን ያለመገኘት “ተራ አመፀኛነት” ውስጥ አይገቡም ነበር፡፡
እነዚህ ባለሥልጣናት ፓርላማ አለመገኘታቸውን አስመልክቶ ሃይ የሚላቸው አካል የሌለ መሆኑ ደግሞ ኢህአዴግ መሪ በሆነበት መንግስት፣ ህግ ምን ያህል መቀለጃ እንደሆነ ያሳያል፡፡ መቼም የፓርላማ አባላት ሥነ-ምግባር፣ ከፓርላማ ስንት ቀን መቅረት እንደሚያስቀጣ ሳያስቀምጥ አይቀርም። ፓርላማ ቀርቶ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ አንድ ተማሪ ምን ያህሉን የትምህርት ቀን በክፍል ውስጥ መገኘት እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ ራሳቸውን እንደ ህግ አክባሪ በመቁጠር አትዝረፉ ያላቸውን ሁሉ በህገ-ወጥነት እየከሰሱ፣ የሞት ፍርድ ሲፈርዱ የነበሩ ግብዝ የህወሓት ባለስልጣናትም፣ ከፓርላማ መቅረት ህጋዊ እንዳልሆነ አያጡትም፡፡ ከፓርላማው የሚያስቀራቸው ጉዳይ ሌላ ነው - የአዲስ አበባውን ወንበራቸውን የማጣት እብድ የሚያደርግ ቁጭት፡፡
ሕወሓት ተበድሏል?
ሳያስቡት ከአዲስ አበባ ተባረው መቀሌ የከተሙት አዛውንት የህወሓት ባለስልጣናት፣ ቁጭታቸውን ተንፈስ የሚያደርግላቸው እጃቸው ላይ የቀረ ነገር ቢኖር፣ ስልጣናቸውን ለቀማቸው አካል ባለመታዘዝ ንቀታቸውን ማሳየት፣ የወንበር ነጣቂያቸውን ሰላም ከሚያደፈርስ ጋር ሁሉ ማህበር መጠጣት ነው። ህወሓት ተከፋሁበት የሚለው ነገር፣ ሃገር ቆማ እንዳትሄድ አድርጎ ሲዘርፍ የኖረውን ሜቴክን ሲያጋፍሩ የኖሩት ጀነራል ክንፈ ዳኘው ሲያዙ፣ በሃገሪቱ ቴሌቪዥን ቀጥታ መተላለፉ፣ እጃቸው ላይ ካቴና ገብቶ መታየቱ፣ ሰውየው ይመሩት የነበረውን ሜቴክን ሁለንተናዊ ሌብነት የሚያሳይ ዶክመንተሪ ፊልም መሰራቱ ነው፡፡ ክንፈ ዳኘው ሊያመልጡ ሲሉ የተያዙበት ሁኔታ ከቦታው በቀጥታ መተላለፉም ሆነ ሰውየው ሲያዙ እጃቸው ውስጥ ሰንሰለት መግባቱ ምንም ነውር ያለበት ነገር አይደለም፡፡ ይልቅስ ማንም ሰው ከህግ ስለማያመልጥ የፍርድ ቤት ጥሪ ሲደርሰው አክብሮ ህግን መጋፈጥ እንዳለበት፣ መሸሽ እንደማያዋጣ ትምህርት ይሰጣል፡፡ የጀነራል ክንፈ ጉዳይ በፍርድ ቤት ተይዞ ሳለ ጉዳዩን አስመልክቶ ዶክመንተሪ ፊልም መስራቱ ይልቅ ጥፋት ነው፡፡ ኢህአዴግ ይህን አባዜውን ሊያቆም ይገባዋል፡፡   
በተረፈ ተጠርጣሪ ወንጀለኛው እጅ ላይ ለምን ካቴና ገባ የሚለው ነገር ከህወሓት ሲመጣ የሚያስመሰክረው የህወሓትን ድልብ ዘረኝነት ነው፡፡ ምክንያቱም ይህን ወንጀል አድርጎ የሚያወራው ድርጅቱ፤ራሱ ክስ ፈብርኮ በከሰሳቸው መናኝ መነኮሳት ሰላላ እጅ ውስጥ ካቴና አስገብቶ፣ እንደ በግ አቆራኝቶ አስሮ ሲያንገላታ የኖረ፣ እነ ኡስታዝ አቡበክርን፣ እነ አንዱአለም አራጌን፣ እነ ዶ/ር መረራ ጉዲናን በካቴና ጠፍንጎ አስሮ፣ በቴሌቪዥን ሲያሳይ የነበረ ግፈኛ መሆኑ ነው፡፡ አሁን የጀነራል ክንፈ ዳኘው ልዩ ሆኖ የታየው፣ የወንዙ ሰው ስለሆኑ ብቻ ነው፡፡ የሚያሳዝነው ህወሓት፣ ይሄ እበልጣለሁ ባይነቱ ከዙፋኑ ባፍጢሙ እንደደፋው እስከ ዛሬ እንኳን አለመገንዘቡ ነው፡፡           
ሌላው ህወሓት ትልቅ በደል እንደደረሰበት አድርጎ የሚያቀርበው ነገር፣ ፓርቲው  ሲያጋፍረው በኖረው የደህንነት መስሪያ ቤት አዛዥነት፣ በሰው ልጆች ላይ ሲደረግ የኖረው አረመኔያዊ የሰብአዊ መብት ጥሰት በሃገሪቱ ቴሌቪዥን መጋለጡ፣ ሲጋለጥ ደግሞ ተጎጂዎቹ “የገረፉን ትግርኛ የሚናገሩ ሰዎች ናቸው” ማለታቸውን ነው፡፡ ይህን የሚለው ህወሓት ሃገሪቱን በሚዘውርበት ዘመን፣ በፓርላማ የካቢኔ ሹመት ሲፀድቅ፣ከእጩዎቹ ስም ቀጥሎ የሚጠራው  ዘራቸው እንደነበር ማንም አያጣውም፡፡ ህወሓት ባዋቀራት ኢትዮጵያ ለመሾም ለመሻር፣ለመግረፍ ለመገረፍ፣ነግዶ ለማትረፍ ለመክሰር፣ለመውጣት ለመግባት ሁሉ ዘር ሳይጠራ አይሆንም ነበር፡፡ ስለዚህ የገራፊ ዘር ሲጠራ፣ ሰማይና ምድር ቦታ የተቀያየሩ ማስመሰሉ ቅን ነገር አይደለም፡፡ በአጠቃላይ ዘር ሳይጠራ ምንም በማይደረግበት ሃገር፣ በራስ እጅ ካበጃጁ በኋላ “ለምን የገራፊ ዘር ተጠራ” ብሎ ተበደልኩ ማለት ትርጉም የለውም፡፡
የአማራ ክልልና የራያ ወጣቶች ወደ ትግራይ የሚሄደውን መንገድ ሲዘጉብን፣ የዶ/ር ዐቢይ መንግስት ዝም ማለቱም አስከፍቶናል ባዮች ናቸው ህወሓታዊያኑ፡፡ በፌሮ ሲገረፍ የኖረ፣በማንነት ጥያቄው ላይ ሲሾፍበት የኖረ ህዝብ ለተወሰነ ቀን መንገድ መዝጋቱ እሪ ሊያስብል አይገባም፡፡ የሚያዋጣው ስህተትን አምኖ ለበደል ይቅርታ መጠየቅ እንጂ ስገርፍ የኖርኩት ህዝብ ዘንባባ ያንጥፍልኝ የሚል ትዕቢት አይደለም፡፡ በዚህ ላይ የቆየውን ያህል ቆይቶም መንገዱን ያስከፈተው የዶ/ር ዐቢይ መንግስት መሆኑ መረሳት የለበትም፡፡ የዶ/ር ዐቢይ መንግስትም ቢሆን ህዝብ ቅሬታውን ማቅረብ ያለበት መንገድ በመዝጋት እንዳልሆነ ህዝብን ቀርቦ እስኪያስረዳ ቀናት እንደሚያልፉ መገንዘብ ከባድ ነገር አይደለም፡፡ “ጠ/ሚኒስትሩ መንገዱ የተዘጋ የዕለቱ ዕለት ከዙፋኑ ወርዶ ሲገሰግስ አድሮ ለምን በማግስቱ አላስከፈተልንም” የሚለውም እበልጣለሁ ባይነትን የተሸከመ፣ ትዕቢት ያለበት ክርክር ስለሆነ የሚያስኬድ ነገር አይደለም፡፡  
ከሁሉም በላይ ህወሓት መንገድ ተዘጋብኝ ብሎ በሚጮህበት ወቅት ደቡብ ኢትዮጵያ ላይ እሪ የማይሉ ግን ለወራት መንገድ ተዘግቶባቸው ያሉ ወገኖች ነበሩ፤ወለጋ ላይ በጥይት የሚቆሉ ሰዎች ነበሩ፡፡ ወቅቱ የሽግግር እንደመሆኑ፣ህወሓት ደግሞ ደህና በመስራት የማይታወቅ ፓርቲ እንደመሆኑ ጥፋቱን አምኖ ይቅርታ ባልጠየቀበት ሁኔታም ሁልቀን ፋሲካ መጠበቅ የለበትም፡፡ ህወሓት ራሱ በሰጣት የቤት ስራ ምክንያት እየታመሰች ባለች ሃገር፣ “ለምን የኔ ሰፈር ብቻውን በቸር ውሎ አላደረም” ማለት፣ይህንንም አምርሮ ማራገብ ክፉ ራስ ወዳድነት ነው፡፡
በሙስና እና በሰብዐዊ መብት ጥሰት የተጠየቁ አመራሮች ሁሉ ህወሓቶች ብቻ ናቸው፤ይህ የሆነው ደግሞ የትግራይን ህዝብ ለማንበርከክ ነው የሚለው ሌላው ህወሓቶች ተለይተን ተጠቃን የሚሉበት ነገር ነው፡፡ ለዚህ ነገር የመጀመሪያው ክርክር በወንጀል መጥሪያ የተቆረጠባቸው ተጠርጣሪ ወንጀለኞች ህወሓቶች ብቻ አይደሉም፡፡ ህወሓቶች ብቻ የሆኑት የፍርድ ቤት መጥሪያ ተቆርጦባቸው ሳለ፣ ለህግ አንታዘዝም ብለው በትውልድ ቦታቸው የከተሙት ተጠርጣሪ ወንጀለኞች ናቸው፡፡ ለተጠርጣሪ ወንጀለኛ የወንዙ ልጆች መጠለያ እየሰጠ ያለውም የትግራይ ክልላዊ መንግስት ብቻ ነው፡፡ እነ ያሬድ ዘሪሁን፣ ተስፋዬ ኡርጊ፣ ጠና ቁርንዲ ወዘተ ትግሬዎች ያልሆኑ፣ የክልላቸው መንግስትም ያልደበቃቸው ተጠርጣሪ ወንጀለኞች ናቸው፡፡ በተረፈ ወደፊትም በተጠያቂነቱ ዝርዝር የህወሓት ሰዎች በርከት ብለው ሊታዩ ይችላሉ፡፡ ይህ ህወሓት ከመባረሩ በፊት መስርቶት የነበረው ስርዓት፤ የወንዝ ልጆች ተጠራርተው፣ፍትሃዊ ባልሆነ ሁኔታ የሃገሪቱን ሁለመና የመዘወራቸው ነፀብራቅ እንጂ እንደሚያወሩት፣ ትግራይን የማጥቃት ሃራራ ያለበት መንግስት ስለመጣ አይደለም፡፡ ማገናዘብ ደግ ነው!                 
ህወሓት እንዴት አደብ ይግዛ?
ወንጀለኛ ሰብስቦ የያዘው፣ የፌደራሉን መንግስት በግልፅ “ሃገር ማስተዳደር የማይችል ነው” የሚለው የትግራይ ክልልን የሚመራው የህወሓት አዛውንቶች ስብስብ፤ በሃገር ላይ ሌላ ሃገር መስርቶ የመኖሩ ነገር ሊያበቃ ይገባል፤በክልሉ የከተሙ ተጠርጣሪ ወንጀለኞችም ከህግ በላይ አለመሆናቸው ግልፅ ሊሆን ይገባል፡፡ አለበለዚያ ኢትዮጵያ የህግ የበላይነትን የሚያረጋግጥ ለውጥ ውስጥ ነኝ ብላ መናገር አትችልም፡፡ ትዕግስት የህግ የበላይነትን ተፈታትኖ፣አለቃና ምንዝር የማይታወቅበት ስድ ፖለቲካ እስኪያመጣ ድረስ ልቅ መሆን የለበትም፡፡
የትግራይ ክልል በኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግስት ስር እንደመሆኑ መጠን በክልሉ ያሉ ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን እንዲሰጥ መለመን ሳይሆን መታዘዝ ነው ያለበት፡፡ ለወራት ወንጀለኛን ደብቆ ያስቀመጠው የትግራይ ክልል መንግስት፣ወንጀል ሰርቷልና ከደበቃቸው ወንጀለኞች እኩል መጠየቅ አለበት፡፡ ዛሬ የተናገሩትን ነገ የማይደግሙት የክልሉ ፕሬዚደንት ዶ/ር ደብረፅዮን፣ በተለይ በግንባር ቀደምነት መጠየቅ አለባቸው፡፡ ይህን ለማድረግ እንደ መንግስትም እንደ ፓርቲም እርምጃዎችን መውሰድ ይቻላል፡፡
እንደ መንግስት፣የትግራይ ክልል መንግስት፣ ተጠርጣሪ ወንጀለኞቹን ለፌደራሉ መንግስት የሚያስረክብበት የጊዜ ገደብ ማስቀመጥ የመጀመሪያው እርምጃ ሊሆን ይችላል፡፡ በጊዜ ገደቡ የማያቀርቡ ከሆነ በሚኒስትሮች ምክር ቤት አስወስኖ የዶ/ር ደብረጽዮንን ያለመከሰስ መብት ለማንሳት በፓርላማ ማስወሰን፡፡ ወንጀለኛ የደበቀ ወንጀለኛ ነውና፣ ዶ/ር ደብረፅዮንም ከተፈላጊ ወንጀለኞች ዝርዝር  ውስጥ መግባት አለባቸው፡፡ ክልሉ ደግሞ በታዳኝ ወንጀለኛ መመራት ስለሌለበት የፌደራል መንግስቱ በደብረፅዮን ለሚመራው የክልሉ መንግስት እውቅና መንፈግ አለበት፡፡ እንደ መንግስት ይህን ካደረጉ በኋላ ኢህአዴግ እንደ ፓርቲ ተሰብስቦ ህገ-ደንቡን በተከተለ ሁኔታ በህወሓት ላይ ቅጣት መጣል አለበት፡፡ ይህ ሁሉ ተደርጎ ለውጥ ከሌለ ደግሞ መንግስት ለክልሉ የሚሰጠውን የበጀት ድጎማ እስከ ማቆም የሚደርስ  እርምጃ ሊወስድ ይችላል፡፡  
***
ከአዘጋጁ፡- ጽሁፉ የጸሃፊዋን አመለካከት  ብቻ የሚያንጸባርቅ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

Read 101503 times