Saturday, 12 January 2019 14:24

ቃለ ምልልስ “አሁን በትግራይ ያለው ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ነው”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

• ያልተገባ ቅስቀሳ በማድረግ ህዝብን ወደ ጦርነት መግፋት ፈጽሞ ሊፈቀድ አይገባውም
   • ሀገርን በእልህ ለማፍረስ ከመጣደፍ፣ መንግስት በሆደ ሰፊነት መደራደር አለበት
   • የትግራይ ፖለቲከኞች፤ ህዝቡን 360 ድግሪ ተከበሃል እያሉ እያስጨነቁት ነው

    የህወሓት መሥራችና የ”አረና” አመራር የነበሩት አቶ ገብሩ አስራት፤ በወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡ እነሆ፡-


    የትግራይ ክልል በሠብአዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩት የቀድሞ የብሔራዊ መረጃ ደህንነት ኃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋን ለህግ አሳልፎ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆኑ ተነግሯል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
በኢትዮጵያ ህግ መከበር እንዳለበት ጥፋተኛም ሊጠየቅ እንደሚገባው አምናለሁ፡፡ ያም ሆኖ ግን ህግ ሲከበር በተለይ አሁን ያለው የሙስና፣ የሌብነት ወይም የሰብአዊ መብት ጥሰት በግለሰቦች ደረጃ ብቻ የሚታይ አይደለም፡፡ ጉዳዩ የስርአት ነው፡፡ ሀገራዊ ነው፡፡ ሠፊ ፖለቲካዊ አንደምታ ያለው ጉዳይ ሆኗል፡፡ እንግዲህ እንደምናውቀው፣ ከአሁን በፊት በግለሰቦች ደረጃ ይታይ የነበረ ነው፡፡ አሁን ግን በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚታይ ነው፡፡ ይሄ ሲሆን የትግራይ ክልል የሚያቀርባቸው ክርክሮች አሉ፡፡ ክርክሮቹ ትክክል ናቸው አይደሉም የሚለውን ወደ ጐን ትተን፣ አሁን የሚደረገውን በሌብነት የተጠረጠሩትን የማሠርና የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈፀሙ ሰዎችን የመቆጣጠር ጉዳይ፣ ከወንጀል አልፎ ፖለቲካዊ ይዘት አለው፡፡ ይሄ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ትልቁ ሚስጥር ይሄ ነው፡፡
ይህን ለማለት ያበቃዎት ምክንያት ምንድን ነው?
እንግዲህ ሁላችንም እንደምናውቀው፣ ባለፉት 27 አመታት፣ የኢህአዴግ ባለስልጣን ሆኖ ሙስና ያልፈፀመ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት ያልፈፀመ የለም። በእኛም በኩል ቢሆን የተፈፀመ ይኖራል፡፡ እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ፣ አንዱ አሳሪ ሌላው ታሣሪ የሚሆንበት ሁኔታ እንዴት ይፈጠራል የሚለው ትክክለኛ ጥያቄ ይመስለኛል፡፡ አሸናፊው አሳዳጅ፣ ተሸናፊው ተሳዳጅ መሆን  የለበትም፡፡
ታዲያ የሙስና ወንጀልና የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈፀሙ አካላት እንዴት ተጠያቂ ሊደረጉ  ይችላሉ?
ነገሩ ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም ገለልተኛ ኮሚሽን ተቋቁሞ፣ የማጣራት ስራ መሰራት አለበት። ማን ምን ድርሻ ነበረው የሚለውን በመተማመን ለመፍታት፣ ገለልተኛ ኮሚሽን መቋቋም አለበት። ኢህአዴግ እርስ በእርሱ ካለበት የፖለቲካ ንትርክ ጋር ተያይዞ፣ ጉዳዩ እየታየ ያለበት ሁኔታ ካልተለወጠ፣ መፍትሔው ገለልተኛ ኮሚሽን አቋቁሞ፣ መመርመርና የሚታሠረውን ማሠሩ ነው የሚበጀው፡፡ አሁን የኢህአዴግ የእርስ በእርስ ንትርክ ይኸውና “በትግራይ ላይ ያነጣጠረ ዘመቻ ተከፍቶብናል” ለሚለው ክስ አመቺ ሆኗል። አጠቃላይ ፖለቲካው ከእነ አካቴው ከመበላሸቱ በፊት ይሄ ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ከሁሉም አስቀድሞ ፖለቲካው ነው መጥራት ያለበት፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ይሄ የሰብአዊ መብት ጥሰት ምርመራ፣ ከመቼ ጊዜ ጀምሮ ያለው ነው የሚለው በግልጽ መታወቅ  አለበት፡፡ ያለፉት 27 አመታት ነው ወይስ የቅርብ ጊዜ ብቻ ነው? በየትኛው እርከን ላይ ያሉ ኃላፊዎች ናቸው መጠየቅ ያለባቸው? የሚሉት መሠረታዊ ጉዳዮች መነሣታቸው አይቀርም፡፡ አሁን ያለነው በሽግግር ወቅት ላይ ነው፡፡ በሽግግር ወቅት ደግሞ የሽግግር ፍትህ ተግባራዊ የሚሆንበት የአፈፃፀም አቅጣጫ ተቀምጦለት፣ ሁላችንም ግልጽ ሆኖልን፣ ሃገርም ግልጽ ሆኖለት ቢፈፀም የበለጠ ውጤታማ ይሆናል፡፡ ከዚህ ውጭ የሚደረግ እንቅስቃሴ ለሴራ ፖለቲከኞች አመቺ ስለሚሆን፣ ብዙ የፖለቲካ ሂደቶችን ሊያከሽፍ ይችላል፡፡ ጉዳዩ በሰፊ ማዕቀፍ ነው መታየት ያለበት፡፡
የሠብአዊ መብት ጥሰት የተፈፀመባቸው ሰዎች ዛሬም ከእነ ጉዳታቸው ነው ያሉት፡፡ እነዚህ ተጎጂዎች እንዴት ነው ሊካሱ የሚችሉት? በሌላ በኩል ባለፉት 27 ዓመታት፣ አብላጫውን ስልጣን ይዞ የቆየው ህወሓት እስካሁን ለተፈፀሙ ጥፋቶች  እንኳ ይቅርታ አልጠየቀም የሚል ቅሬታ የሚያነሱ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ  ምን ይላሉ?
ለኔ ህወሓትም ሆነ ኢህአዴግ በዚህ ጉዳይ ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ ህወሓት ብቻውን በተናጠል አይደለም መጠየቅ ያለበት፡፡ ምናልባት የሚጠየቁት ሰዎች ቁጥር የህወሓት ሊበዛ ይችላል፡፡ ምክንያቱም በርካታ የስልጣን እርከኖች በእነሱ ተይዘው ስለነበር። ነገር ግን ብአዴንም ኦህዴድም ደህዴንም በዚህ ጉዳይ ተጠያቂ ናቸው፡፡ በትግራይ ለተፈፀሙ ወንጀሎች በሙሉ ህወሓት ኃላፊነቱን  ይወስዳል፤ ብአዴን ለአማራ ክልል ኃላፊነቱን  መውሰድ አለበት። እኛኮ ትግራይ ላይ እስካሁን የፖለቲካ እስረኞች አሉን፡፡ ያለ አግባብ በግፍ የታሰሩ፣ አካላቸው የጐደሉ ሰዎች አሉን፡፡ ጥያቄው ሀገር አቀፍ ነው፤ ስለዚህ መፍትሔውም በግንባር አቀፍ ደረጃ ነው መሆን ያለበት፡፡ የካሣ ጥያቄ ከመፍትሄዎቹ አንዱ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንዱ መፍትሔ በይቅርታ፣ በምህረት ሊመጣ ይችላል፡፡ ስለዚህ ግለሰቦችን ማሳደድ ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ ሀገር አቀፍ ሆኖ፣ ጉዳዩ በገለልተኛ ኮሚሽን መታየት አለበት። ይሄ ባልሆነበት ሁኔታ የሚደረግ እንቅስቃሴ ግን  ለፖለቲካዊ ትርጉም የተጋለጠ፣ ያለፈ ታሪክን የሚደግም ይሆናል፡፡ በርካታ መጠየቅ ያለባቸው ወገኖች ተዘርዝረው ታውቀው በይቅርታ፣ በምህረት የሚታለፉት (ከጠየቁ ማለት ነው)፣ እንዲሁም በወንጀል የሚቀጡት የትኞቹ ናቸው የሚለው በግልጽ ተለይቶ መቅረብ አለበት፡፡ ለነገሩ እስካሁን ፖለቲካችንም ግልፅ ፍኖተ ካርታ የለውም፡፡ የህግ ማስከበሩም ጉዳይ ግልጽ ፍኖት ካርታ የለውም፡፡ ይሄ ሊቀመጥ ይገባል፡፡ የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች እርስ በእርስ እየተሻኮቱ ባሉበት ሁኔታ፤ማን ጠያቂ ማን ተጠያቂ ሊሆን ነው? ሁሉም እንደሆኑ ኢህአዴጐች ናቸው፡፡ ይሄን ስል ጉዳዩ ተዳፍኖ መቅረት አለበት ማለቴ አይደለም፤ ጉዳዩ እንዲያውም በሰፊ አድማስ መታየትና ትልቅ ትኩረት ሊደረግበት የሚገባ ነው። የካሣ ጉዳይ ከዚያ በኋላ የሚመጣ ነው፡፡ እኔ ራሴ የምጠይቀው ካሣ ሊኖርም ይችላል፡፡ መፍትሔው እስር ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ አድማሱም ታይቶ ነው ጉዳዩ መካሄድ ያለበት፡፡  
በወንጀል የተጠረጠረን ግለሰብ  በፖለቲካ ሽፋን ከለላ መስጠት ተገቢ ነው ይላሉ?
አሁንም ልናገር የምችለው አስቀድሜ ያልኩትን ነው፡፡ ነገር ግን አሁን የህወሓት ፖለቲከኞች በጠቅላላ ሸሽተው ትግራይ ላይ ተደብቀዋል፡፡ ይሄ መታወቅ አለበት፡፡ እነዚህ ሰዎች የኢህአዴግ አባላት ናቸው፡፡ በጉባኤ ተሳትፈዋል፡፡ ግን ሸሽተው ነው ትግራይ የተሰባሰቡት፡፡ ለምን ሸሹ የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ፣ እነዚህ ባለስልጣናት ሸሽተውም ዝም ብለው አልተቀመጡም፡፡ ህዝቡን እየቀሰቀሱት ነው፤ ለዚህ መሠረት የሚሆናቸው የፖለቲካ ድባብ ደግሞ ተፈጥሮላቸዋል፡፡ ለምሣሌ በብአዴን እና በተወሰኑ የአማራ ልሂቃን እየተነሳ ያለው የመሬት ማስመለስ የጦርነት ንግግሮች፣ ህዝቡን ለማወናበድ  ተጨማሪ ስንቅ ሆኗቸዋል፡፡ በሌላ በኩል የኤርትራ ፕሬዚዳንት ፉከራም አለ፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች በሙሉ ተደማምረው ፖለቲካዊ ሁኔታውን ቀይሮታል፡፡ ፖለቲካዊ ሁኔታው ስለተቀያየረና ህግ ለማስከበር አመቺ ባለመሆኑ ነው፣ እነዚህ ተጠርጣሪ ግለሰቦች ያልተያዙት፡፡ በትግራይ የተደበቁ ፖለቲከኞች፤ በየቦታው ትግራይን አስመልክቶ የሚነገሩትን ነገሮች ፍርሃት መፍጠሪያ እያደረጓቸው ነው፡፡ ህዝቡን 360 ድግሪ ተከበሃል እያሉ እያስጨነቁት ነው። አንዳንዶች ደግሞ የትግራይ ህዝብን ከህወሓት መለየት ተስኗቸው፣ አብረው ደምረው ጦርነት እያወጁበት ነው፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ነገሮችን የሚያባብሱ ናቸው፡፡ ራሱ ህወሓት እኮ በሙስና ተዘፍቄያለሁ ብሎ ገምግሟል፤ ግን ተጠያቂ ያደረገው አካል እስካሁን የለም፡፡ ይሄ ሁኔታ በሁሉም ክልሎች አለ፡፡ ግን እስካሁን የተጠናከረ የህግ ተጠያቂነት አልተፈጠረም፡፡ አሁን በአጠቃላይ በሀገር ደረጃ የተምታታ ነገር ነው ያለው፡፡ ይሄ በመጀመሪያ መጥራት አለበት፡፡ የተምታታው ነገር በራሱ ለአጥፊዎች መደበቂያ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡
አሁን በትግራይ ያለው ፖለቲካ በእርስዎ እይታ እንዴት ይገመገማል?
አሁን በትግራይ ያለው ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ የህወሓት ባለስልጣኖች ይሄን ሁሉ ጥፋት አጥፍተው ከአዲስ አበባ ወደ ትግራይ በሸሹበት ወቅት በመጀመሪያ ወጣቱና ህዝቡ ቁጣ ነበረው፡፡ ለምን መጣችሁ? ይሄን ሁሉ ጥፋት አጥፍታችሁ፣ የኛ መሬት መደበቂያ አይሆንም ብሏቸው ነበር። ኋላ ላይ ግን በግዛት ይገባኛል ሰበብ በትግራይ ላይ የሚፈጽሙት ነገሮች፣ የትግራይ ተወላጆች ንብረት መዘረፍና መፈናቀል ጉዳይን እነዚህ ሃይሎች ለራሳቸው የፖለቲካ አላማ ተጠቅመውበታል፡፡ ኢሳያስ አፈወርቂም ህወሓት ላይ በጐ አመለካከት እንደሌለው በቂ ፍንጭ አሳይቷል፡፡ እነዚህን ሁኔታዎች ደግሞ በአማራ ክልልና በዚያው በትግራይ ክልል ያሉ ሚዲያዎች ወዳልተፈለገ ፕሮፓጋንዳና የጦርነት ቅስቀሳ በመምራት ጉዳዩን አወሳስበውታል፡፡ በመጀመሪያ ይሄ የሚዲያዎች ፕሮፓጋንዳ መቆም አለበት፡፡ ልዩነቶችን  እያሰፉ ያልተገባ ቅስቀሳ በማድረግ ህዝብን ወደ ጦርነት መግፋት ፈጽሞ ሊፈቀድ አይገባውም፡፡ ለህወሓት ወይም ለኢህአዴግ ስልጣን መራዘም ተብሎ፣ ህዝቡ  ጦርነት ውስጥ መግባት የለበትም፡፡ አሁን ህዝቡን በተለያየ አቅጣጫ እያስፈራሩ በስልጣን ለመቆየት ነው፣ ሁሉም ሃይሎች እየተንቀሳቀሱ ያሉት፡፡ ህወሓት በስልጣን ለመቆየት ህዝቡን በዚህ መልኩ እያዘጋጀ ነው፡፡ በሌላ በኩል እነ ብአዴንም በስልጣን ለመቆየት ሲሉ ህዝቡን ባልሆነ መንገድ እየቀሰቀሱት ነው፡፡ ይሄ ሁኔታ በሁሉም ወገኖች መቆም አለበት፡፡ ህዝብ ወደ ጦርነት መገፋት የለበትም፡፡ በመጀመሪያ ይሄ ሁኔታ ነው ተገምግሞ መታየት ያለበት፡፡  
በእርስዎ አመለካከት አሁን ለተነሱት  ችግሮች መፍትሄው ምንድን ነው?
መፍትሔው መደራደር ነው፡፡ ሀገርን በእልህ ለማፍረስ ከመጣደፍ፣ መንግስት በሆደ ሰፊነት መደራደር አለበት፡፡ እንኳን ከሀገር ውስጥ ፓርቲዎች ይቅርና ከሻዕቢያ ጋርም ተደራድሯል፡፡ በእልህና በመገፋፋት ማንም አሸናፊ አይሆንም፡፡ መደራደር ደግሞ የሽንፈት ምልክት አይደለም፡፡ ድርድር ስል ግን የህዝቡን የለውጥ ፍላጐት የሚቀለብስ መሆን የለበትም፡፡ የህዝቡ የለውጥ ፍላጐት በምንም መመዘኛ ለድርድር መቅረብ የለበትም፡፡ ኢህአዴግ እርስ በእርሱ ከሚያደርገው ድርድር በተጨማሪ ከሌሎች ሀገር አቀፍ ፓርቲዎችም ጋር መደራደር አለበት፡፡ የዚህችን ሀገር ችግር ለብቻዬ  እፈታለሁ ቢል የሚሆን አይደለም፡፡
ህወሓት በቀጣዩ ምርጫ ቢሸነፍ ስልጣን ለማስረከብ ዝግጁ ይመስልዎታል?
ይሄ የማይታሰብ ነው፡፡ ህወሓት ከድሮው በባሰ ሁኔታ አፈናውን ቀጥሎበታል፡፡ ከመሃል ሀገር የተፈናቀለ ፓርቲ ነው፡፡ አሁን የቀረችው ትግራይ ብቻ ናት፡፡ እሷን ላለማጣትም ይበልጥ አፋኝ ሆኗል። የተለየ ሃሳብ እንኳ ማዳመጥ የማይፈልግበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ የአምዶም ንግግር በጭብጨባ የተቋረጠው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ በትግራይ ይበልጥ አፈናው ተጠናክሯል፡፡ ሌላ አማራጭ ፓርቲ አያስፈልገንም እያሉ ነው ያሉት፡፡ “አንድ ህዝብ፣ አንድ ልብ፣ አንድ ድርጅት” እያሉ የ19ኛው ክ/ዘመንን ፖለቲካ እያራመዱ ነው የሚገኙት፡፡ ይሄ ደግሞ ይበልጥ አፈናን የሚያስከትል ነው፡፡
ይሄን የፖለቲካ አካሄድ አሳሳቢ የሚያደርገው ደግሞ አንዳንድ የአካባቢው ልሂቃን ጭምር በገንዘብም እየተገዙ ይሁን ግራ እየተጋቡ፣ በጣም አደገኛ የሆነውን ይሄን መፈክር ተቀብለው እያስተጋቡ ስለሆነ፣ እንኳን ለምርጫ የተለየ ሃሳብም ለማቅረብ አስቸጋሪ የሆነበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ በሰብአዊ መብት ጥሰትና በሙስና ወንጀል የሚጠየቁ አካላት በተሰባሰቡበት ሁኔታ፣ ዲሞክራሲና ነፃ ምርጫ የማይታሰብ ነው፡፡

Read 10135 times