Saturday, 12 January 2019 14:27

‘ሰባት መቶ’… እንዲህ ቅርብ!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(6 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
በዓሉ እንዴት አለፈ? ስሙኝማ…አንዳንዴ ምንም እንኳን ቃላቱ ‘ገር’ ቢሆኑም ባትጠይቋቸው የምትመርጧቸው ጥያቄዎች ይኖራሉ፡፡ አሀ…የጠያቂውን ስሜት ሊጎዳ ይችላላ! ለምሳሌ የዘንድሮውን ገና፣ “በዓሉ እንዴት አለፈ?” ብሎ መጠየቁ እንደ ወትሮው ዘና ላያደርግ ይችላል፡፡ ዶሮ ሰባት መቶና ሰባት መቶ ሀምሳ ብር በሚጠየቅባት ከተማ እንዴት አድርጎ ዘና ሊያደርግ ይችላል! ምን የተለየ ነገር መጣ! የተለየ ነገር አልመጣማ፡፡ ያው ተርመስመስ ያለ በሚመስል ጊዜ ሁሉ በገንዘብም ሆነ በሌላ ነገር፣ አንዳችን በሌላችን ችግር ከሚገባን በላይ የማትረፍ የግለኝነት ባህሪይ አፍጥጦ ወጣ እንጂ!
የምር ግን ስንት አይነት በጎና ደሳስ የሚሉ ቃላት ከየአቅጣጫው በሚሰሙበት ወቅት፣ “ሁሉም ቢተባበር የት ይደረስ ነበር” በሚባልበት ወቅት ይህን ያህል መተሳሰብ ሲጠፋ…አለ አይደል…እሚረብሻችሁ ነገር አለ፡፡ ዛሬ ነገሩ ሁሉ እንዲህ ከሆነ ነገ ደግሞ ይብስበታል ወደሚል መደምደሚያ ይደረሳል፡፡ ልምዳችን ይህንኑ ነዋ የሚያሳየው! …ዋጋ ሲወጣ እንጂ ሲወርድ ማየት አልለመደብንማ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይሄ በየቦታው በጆንያ እየተሞላ፣ በመኪና እየተጫነ የሚያዘው ረብጣ ብር ለእኛ የተከፋፈለ መሰላቸው እንዴ! የምር እኮ…ተወደደም ተጠላም እንደሚባለው አስተሳሰቦች ምናልባት ወደፊት ቀስ በቀስ የሚለወጡ ካልሆነ በቀር አብዛኞቹ በዓላቶቻችን ከ‘ፉድ እና ድሪንክ’ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ እናማ… “ማን ዶሮ ግዢ አላት፣ ሹሮ በቅቤ ተበልቶ አይከበርም እንዴ!” ማለቱ ለአፍ ቀላል ሊሆን ይችላል፡፡ ታዲያላችሁ… እንደዛ የምንለው ሰዎች ራሳችን ‘የምጽአት ቀን’ የመጣ ይመስል በማለዳ ገበያውን የምናጣብበው እኛው ነን፡፡ እናላችሁ… ዘንድሮ ዶሮና በግ ነጋዴዎቹ ብቻቸውን በአቋራጭ የመካከለኛ ገቢን ጣራ ጥሰው መውጣት የፈለጉ ነው የሚመስለው፡፡ ለዶሮ…ያውም በመደበኛ ዋጋነት… ሰባት መቶና ሰባት መቶ ሀምሳ ብር ሲጠራ ያላስደነገጠ ምን ያስደነግጣል! ለነገሩ ‘ፖዘቲቭ ቲንኪንግ’ በሚሉት አድቪልን በብዙ እጥፍ የሚያስከነዳ ‘ፔይንኪለር’ ስናስበው ትንሽ ማመስገኑ አይከፋም፡፡ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚባለው፣ አንጀታችን ብጥስ ብሎ ዘላለም ‘የጎመን ወዳጆች’ ያደርጉናል…ፈረንጅ ‘ቬጂቴርያን’ እንደሚለው፡፡
በዚህ በኩል ይኸው አሁንም ከምግብ አይነት እጅግ ሁሉን ደራሽ ሊሆን ይገባው ለነበረ ዳቦ እንኳን እየተሰለፍን ነው፡፡ “አንድ እፍኝ ቆሎ ቁርጥም ያደርግና፣ ተመስገን ይለዋል ኑሮ ተባለና…” እንዳልተባለው፣ አሁን ለቆሎ ሁሉ እየተሰለፍን ነው፡፡ (የተገጠመላት እኮ “ቢጠፋ፣ ቢጠፋ ቆሎ አይጠፋም፣” በሚል ነበር!) እናላችሁ…ይሄ ሁሉ ባለበት ምድር ምናምኒዝም፣ ምናምኒዝም የሚሉ ፖለቲከኞች የረሱብን “…ኢዝም” አለ፤‘ችግሪዝም!’ (“…ኢዝም”  የኮፒራይት ጥያቄ ታስነሳ ይሆን እንዴ!)
የምር ግን ይሄ የአንዱን ኪስ አራግፎ የራስን ኪስ ብቻ የመሙላት ነገር አልለቀን ያለ ችግር ነው፡፡ ክፍተት እየፈለጉ…አለ አይደል…“የግዱን ይገዛታል!” አይነት ማርኬቲንግ በቃ የ‘ክፋት ማርኬቲንግ’ በሉት፡፡ (‘የክፋት ማርኬቲንግ’ የሚለው ሀረግ የሆነ ‘ዘ ወርልድ ኢዝ ራውንድ’ ምናምን የሚል መጽሐፍ ውስጥ ይግባልን፡፡)
ስሙኝማ… ከጊዜያት በፊት እኮ ስለ ችግር የሚያወራ ሰው ሲመጣብን እንሸሽ ነበር፡፡ “ደግሞ መጣ!”…ምናምን ብለን ከተመቸ ወደ ማዶ መንገድ መሻገር ነው፡፡ የምር እኮ… መቼም ከችግሮችና ከሰቆቃዎች የተላቀቅንበት ዘመን የለምና፣  አለ አይደል… ደግ ደጉን ማሰቡ ዋጋ አያስከፍልም ብላችሁ ወሬ ስትጀምሩ የድራኩላ ፊልም ጽሁፍ የሚመስል ትረካ ይጀምርላችኋል፡፡
“አጅሬ! ፊትህ እኮ እንዴት እንደሚያበራ ልነግርህ አልችልም፡፡ ቢመችህ ነው የጠፋኸው ማለት ነው፡፡”
“ምን ምቾት አለ! በዚህ ለዲያብሎስ ከእነ ዘጠኝ ቤቱ እንኳን በማይገባ ቦታ ምን ምቾት አለና ነው!” ብሎ ራሱን ችሎ መልስ እንደመስጠት ከዲያብሎስ ጋር ብቻ ሳይሆን ከዘጠኝ ቤቱም ጋር ሊያጋጫችሁ ይሞክራል፡፡ “ኸረ እባክህ ጣልያን ከወጣ መጥረጊያ ያልነካው ይመስል የነበረ ፊትህ፣ ሙቀት ዳር የተቀመጠ ቅቤ መስሏል!” እንዳትሉት፣ቀጥሎ ከማን ጋር እንደሚያጋጫችሁ ስለማታውቁ ትተዉታላችሁ።
“ጤናሽን እንዴት ነሽ?” ትላላችሁ፡፡ ይሄኔ ወይ “ምንም አልል” ካልሆነ ደግሞ “ብዙም አልተሻለኝ» ምናምን ሊባል ይችላል፡፡ ግን ምን ብላ ብትመልስ ጥሩ ነው… “ዘንድሮ ራሱ ሰዉ ሁሉ በሽታ ሆኖ ምን ጤና አለና ነው!” ብላ የሸሻችሁትን ቴረር ወሬ ታራግፍባችኋለች፡፡ ልክ እኮ እያንዳንዱን ሰው እየጠቆመች…“ያቺኛዋ ኩላሊት ኢንፌክሽን ነች፣”  “ያኛው የአንጀት ካንሰር ነው፣” “እዛ ያለው ደግሞ አልዛየመርስ ነው፣” ብላ የምትለይ ነው የሚመስለው፡፡
ለነገሩ ግን፣ እንግዲህ ጨዋታም አይደል…አንዳንዴ “ሰዋችንስ ምን ያድርግ፣ ወዶ አይደለም እኮ!” ትላላችሁ፡፡ የፈለገ ያህል ‘ፖዘቲቭ ቲንኪንግ’ ምናምን ‘ቲንኪንግ’ ቢባል… አለ አይደል…አጅሬ ኑሮ ደግሞ “ሮጠህ የት ልታመልጥ!” በሚል ማጅራታችንን አንቆ ያንጠለጥለናል፡፡  ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ስለ ሰዉ የእለት ተእለት ኑሮ ብዙም ሲወራ አንሰማም። የሁሉም ነገር መሰረት እሱ አይደለም እንዴ!  አንድ ፉርኖና አንድ ብርጭቆ ሻይ የሁሉም ነገር መሰረት አይደለም እንዴ!
ጤና የሁሉም ነገር መሰረት አይደለም እንዴ! የራበው ሰው እኮ፣ ጤናው የጎደለ ሰው እኮ የፈለገ አይነት ቃለ መጠይቅ፣ የፈለገ አይነት “ትናንት ማታ አፋቸውን ሲያሲዛቸው አየህልኝ!” አይነት ነገሮች ሊገቡት አይችልም፡፡ በፊት እኮ… “ስማ  እንትና የሚሉት ሰው ደግ ላያወራ ነው! ቴረር በቴረር ነው እኮ ያደረገኝ!” ብትሉ “አንተስ እንዴት ብለህ ነው ከእሱ ጋር የምታወራው!” ምናምን ይል ነበር፡፡ አሁን ግን “እከሌ ቴረር በቴረር አደረገኝ!” ብትሉ፣ “እና በዚህ ኑሮ ምን እንዲል ትፈልጋለህ!” ይልና የ‘ቴረር’ ደረጃውን ወደ ‘ሬድ’ ያሻግረዋል፡፡
ለምሳሌ በሌሎች ሀገራት ወተት፣ ለህዘቡ ማዳረስ ብቻ ሳይሆን እየተረፈ ይደፋል፡፡ እኛ አገር ወተት መጠጣት ማለት መካከለኛ ደረጃ ገቢ ታልፏል ማለት ነው፡፡ ግን እኮ… አለ አይደል… በከብት ሀብት ብዛቷ የምትነሳ ሀገር ውስጥ ወተት፣ ስጋ ምናምን ቅንጦት መሆን ነበረበት እንዴ!?
ዘንድሮ እኮ ቆሎ እንኳን በሰልፍ ሆኗል፡፡
እናላችሁ… የዘንድሮ በዓል ያሳየን አንድ ነገር ቢኖር፣ ምን ያህል አንዳችን በሌላኛችን ችግር ማትረፍ እንደምንፈልግ ነው፡፡
ስሙኛማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ይሄ ‘የበሉበትን ወጨት የመስበር ነገር አልበዛባችሁም!” የሚያስገርም እኮ ነው! በነገራችን ላይ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ከመደበኛው መስመር ውጪ ስማችሁን በፌቨር ማስነሳት የምትፈልጉ ባለወንበሮችና ባለብሮች ካለፉት ወራት ተማሩማ! ስትወድቁ፣ ወይንም ስትንገዳገዱ በ“ውረድ እንውረድ ተባባሉና…” አይነት ገመድ አቀባይ ነው የሚበዛው…ያውም ከእነኚሁ ሰዎች ሲጠቀም የኖረው፣ አወዳደቁ ላይ ትልቁን ዲጂኖ ይዞ የሚመጣው እሱ ነው፡፡
እናላችሁ… አብሮ ሲያጨበጭ የነበረው ሁሉ “ዓይኔን ግንባር ያርገው!” አይነት ሽምጠጣ እንደልብ ሆኗል፡፡ ምክንያቱም በፊት ከፍ ያለ ቦታ ኖረው የወደቁ፣ ወይም ይወድቃሉ ተብለው ጊዜ የሚጠበቅላቸው ሁሉ ያደረጉት ‘ፌቨር’ ተረስቶ በእነሱ የተጠቀመው ሁሉ ቤተመቅደስ የገባች ምናምን እያደረጋቸው ነው፡፡ “ደጉን ያምጣለት፣ እሱ ባይኖር እኮ አይደለም መኪና ልገዛ አሮጌ ጫማ ፍለጋ ጭድ ተራን ሳስስ እውል ነበር፣” ብሎ ነገር የለም፡፡
“ስማ፣ እሱ ሰውዬ በጣም ነው የረዳህ፣ አይደል!”
“ማን፣ እሱ! መጀመሪያ ይሄን ያህል የት እንቀራረብና ነው! አንዲትም ቀን አግኝቼው አላውቅም፣” እያልን ‘በደህናው ጊዜ’ እኛ ላይ ብር የደፋብንን ሰው፣ በክፉ ጊዜ በተራችን አፈር እንደፋበታለን፡፡
ስሙኝማ… የሰባት መቶ ብር ዶሮ! ሰባት መቶ እንዲህ ቅርብ ትሁን!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 9526 times