Saturday, 12 January 2019 14:36

የምን የምርጫ ጊዜ መራዘም?!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(2 votes)

ዛሬ ሁለት አይነት ኢሕአዴግ አለ፡፡ አንደኛው ኢሕአዴግ ሕወሓትን፣ ኢሕዴንን፣ ደሕዴግን ኦህዴድን በአባልነት የያዘው፣ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያን መንግሥት ሥልጣን ይዞ እየመራ ያለው ኢሕአዴግ ነው፡፡
ይኸኛው ኢሕአዴግ ከስድስት እስከ ስምንት ሚሊዮን የሚደርስ አባል አለው፡፡ አባሉ በአላማም በጥቅም ፍለጋም የተሰባሰበ ነው፡፡ በስሩ የሴትና የወጣቶች ሊግ፣ አደረጃጀት እየተባለ የተሰበሰበም አለው፡፡ ለምሳሌ፡- የአዲስ አበባ እድሮች ምክር ቤት፣ አቶ መለስ ዜናዊ ከመሞታቸው በፊት በዘረጉት አንድ ለአምስት የተጠረነፈ ነው፡፡
ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በፖሊስ ሠራዊትና በደህንነቱ በመከላከያውና በፍትህ አካላቱ ውስጥም በሌላውም የመንግሥት ቢሮዎች ምልምሎቹን አስቀምጦ ሕግን እንደፈለገው ሲጠመዝዝ፣ ሥልጣንን እንዳሻውና እንደፈቀደ ሲጠቀም የቆየ ነው፡፡
ይኸኛው ኢሕአዴግ ከአራት ኪሎ እስከ ተራ የገበሬ መንደር ድረስ የወረደ፣ ከተሞችን እንደ ሸረሪት ድር ተብትቦ የያዘ፣ እያንዳንዱ ዜጋ ለማንጠስ እንኳ ግራና ቀኝ እንዲገላመጥ፣ ሁልጊዜ እንዲሰጋ ያደረገ ነው፡፡ አንድ ታሪክ ለዚህ ማስረጃ ልጥቀስ፡፡ ኢሕአዴግ እንደገባ የመሬት ድልድል አድርጓል፡፡ በደርግ ጊዜ በገበሬ ማህበር አመራር ላይ የነበሩ “ቢሮ ክራት” ተብለው በቂ መሬት እንዲያገኙ ተደርገዋል፡፡
በዚህና በሌሎችም ጉዳዮች ገበሬው ሃሳቡን የገለጠባቸው በርካታ ግጥሞች እንዳሉም ሰምቻለሁ፡፡ ይህን ታውቃለች የተባለች አንድ ሴት እህቴ አገናኘችኝ፡፡ የእሷ ቤት ገበያ ዳር ስለሆነ ከተማው ዳርቻ ከሚገኝ አንድ ሌላ ዘመድ ቤት ተወስደን፣ ድምጽ መቅጃዬን አዘጋጅቼ በይ ንገሪኝ አልኳት፡፡ ለጥቂት ጊዜ ፀጥ ብላ ቆየች፡፡
“አንቱ ጋሼ መንገሩንስ እነግርዎት ነበር፡፡ ነገ የመንግሥት ኮሚቴ፤ በዚህ ሰዓት ምን ትሠሪ ነበር ቢለኝ ምን ብዬ ነው የምመልሰው?” ብላ ጥላኝ ሽው አለች፡፡ ይህ የሆነው በ1989 ጐጃም ደብረኤልያስ ነው፡፡
በዚያን ጊዜ ሕዝቡን እንዲህ እርስ በእርስ እያጠባበቀ፣ አፍኖ መግዛት የጀመረው ኢሕአዴግ አሁን ምን ላይ እንደሚገኝ መገመት አያስቸግርም፡፡ ዛሬም አፋኙ ኢሕአዴግ አለ፡፡ ከእናቱ መቀነት ብር ፈትቶ የሚሰርቅ ጨዋ ሌባ አይደለም፡፡ የእናቱን ብርዋንም መቀነቷንም የሚዘርፈው ጨካኙ ኢሕአዴግ አለ፡፡
በአባይ ግድብ፣ በስኳር ፋብሪካዎች፣ በዩኒቨርሲቲዎች  ግንባታ፣ ከየትናንሹ መ/ቤት ሳይቀር ዘረፋ የፈፀመው ኢሕአዴግ አለ፡፡ በሚሊዮን አይደለም በቢሊዮን የሚቆጠር ብር ይዞ በየቦታው አድፍጦ፣ ለለውጡ ሥጋት ሆኖ የሚገኝ አንዳንድ የኢሕአዴግ አባልም አለ፡፡
በሕግ ከታወቁት ሌላ ሰባት ድብቅ እስር ቤቶች አቋቁሞ፣ ሰዎችን ከእነ ሙሉ አካላቸው ጉድጓድ ከትቶ ሕይወታቸውን የሚያሳጣ፣ አካላቸው ጐድሎ የሚወጡበት ወህኒ ቤት (እሱ ማረሚያ ቤት የሚለውን) ሲያስተዳድር የነበረ፣ በሰው ልጅ ላይ የሚዘገንን ግፍ ሲፈጽም የኖረው፣ ወንዶችንም ሴቶችንም ዘር እንዳይተኩ አድርጐ ያሰቃየው ኢሕአዴግ አለ፡፡ ሕግ ጠፍቶ ዳኛ ጠፍቶ እንጂ ይኸኛው ኢሕአዴግ ሥልጣን አስረክቦ፣ በጠዋት ወደ እስር ቤት መወርወር፣ ለፍርድ መቅረብ የነበረበትና ያለበት ድርጅት ነው፡፡
ሁለተኛው ኢሕአዴግ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው ነው፡፡ በሕዝብ ተከታታይ አመፅና ተቃውሞ ወደ ሥልጣን የመጣ፣ በኢሕአዴግ ውስጥ ያለ አንድ ክንፍ ቢሆንም የሕዝብ እንጂ ሰፊ የድርጅት ድጋፍ አለው የሚባል አይደለም፡፡ እየተከተሉት ያሉትም  የመንግሥት ሥልጣን ከእሱ እጅ ስለአለ እንጂ ይዞት የተነሳውን አላማ ወደውትና ፈቅደውት ነው ለማለትም ያዳግታል፡፡ እንዲያውም ከአራቱ የኢሕአዴግ አባል ድርጅት አንዱ የሆነው ሕወሓት ወደ ተቃውሞ ጐራ ለመንሸራተት ዳርዳር እያለ ይገኛል፡፡ የእሱ ነባር ታጋዮች በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የሚመራውን መንግሥት “በቀለም አበየት የመጣ” አድርገው ሲገልጡት፤ የሕወሓት ዋና ሰው አቶ ስብሐት ነጋ፤ ዶ/ር ዐቢይን ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጐ የመረጠው አሜሪካ ነው ብሎ እስከ መደምደም ደርሰዋል፡፡ እንዲህ በአደባባይ አይውጡ እንጂ ውስጥ ለውስጥ የሚርመሰመሱ ተቃውሞዎች እንዳሉ የሚያስጠረጥሩ ነገሮች አሉ፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሚመራው ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት፣ በአሮጌውና ሊለወጥ ባልታሰበው ወይም ባልተፈለገው የኢሕአዴግ መዋቅር ተተብትቦም ቢሆን፣ የነበረውን አፈና በማስወገድ ዛሬ ሃሳብን በነፃነት መግለፅ ተችሏል፡፡
አሁንም በእስር ላይ ያሉ ብዙ የፖለቲካ እስረኞች ቢኖሩም፣ በጣም ብዙዎችን ፈትቷል፡፡ በውጭ የነበሩ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አገር ቤት እንዲገቡ አድርጓል፡፡  መሣሪያ አንስተው ሲታገሉ የነበሩትም ትጥቃቸውን ፈተው፣ ሰላማዊ የትግል መስመር ውስጥ እየገቡ ናቸው - ከአቶ ዳውድ ኢብሳ ኦነግ በስተቀር፡፡ ሃያ ሰባት አመት ሙሉ በኢትዮጵያ መንግሥት ሥልጣን ላይ የቆየው በአቶ መለስ ዜናዊና አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ይመራ የነበረው ሕወሓት መራሽ የኢሕአዴግ መንግሥት፣ ምን ያህል ግፈኛ፣ ጨካኝና ሞራል የለሽ እንደ ነበር ዶ/ር ዐቢይ የነፃነት በሩን ትንሽ ከፈት አድርገው ለኢትዮጵያ ሕዝብ አሳይተዋል፡፡
ሰው ከነነፍሱ የሚቀበረውን፣ ጥፍር የሚይነቅለውን፣ ፀጉር በእሳት የሚላጨውን፣ ወንዱንም ሴቱንም በሕግ ታራሚ ዘር እንዳይተኩ የሚያደርገውን፣ ከወራሪው ጣሊያን ያላነሰ ግፍ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የፈፀመውን ኢሕአዴግን በደንብ እንድናየው አድርገውናል፡፡ ድሮም የተጠላውን ኢሕአዴግን ይበልጥ እንድንጠላው ሆነናል፡፡
በሀገር ሀብት ተጀምረው የመከኑ ፕሮጀክቶችን ስናስብ፣ ከሀገር የተዘረፈውን በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ስናሰላ፣ “ሞት ለኢሕአዴግ” ብለን መነሳት ያለብን ቢሆንም አልተነሳንም፡፡ በዶ/ር ዐቢይ ጀርባ ላይ ታዝሎ ያለውን የኢሕአዴግ ሬሳ፤ ነፍስ እንዳለው ቆጥረን ከትከሻችን አውርደን ለመጣል የምርጫ ቀን አንድ አመት ከአራት ወር ቀረው እያልን እየቆጠርን ነው፡፡ መች በተገላገልን በምንልበት ወቅት የምርጫው ጊዜ እንዲራዘም የሚፈልጉ ሃይሎች ብቅ ብቅ እያሉ ናቸው፡፡
የምርጫው ጊዜ መራዘም አለበት የሚሉ ወገኖች የሚያነሷቸው ምክንያቶች በሀገሪቱ መረጋጋት አለመኖሩ፣ ተፈናቃይ መብዛቱና፣ ቁጥሩ በትክክል የማይታወቅ ታጣቂ በየክልሉ መኖሩ ነው፡፡
እርግጥ ነው በየቦታው ግጭት አለ፡፡ ሰዎች ይፈናቀላሉ፡፡ በየቦታው የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ዘር እየለዩ ጠብ ያበቅላሉ፡፡ አንዳንድ ቦታም የሰው ሕይወት ይጠፋል፡፡ እነዚህ ደግሞ የዶ/ር ዐቢይን መንግሥት ለመጣል የተነደፉ የትግል ስልቶች ሊሆኑ እንደሚችሉም መጠርጠር ያስፈልጋል፡፡
አሁን ላለው የፀረ ለውጥ እንቅስቃሴ መጠናከር እድል የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ እሳቸው እንደ ልጅ ኢያሱ ከአገር አገር ባይዞሩ ኖሮ፣ ተቀምጠው አልጋውን አደላድለውት ቢሆን ኑሮ፣ ይህ ሁሉ አይሆንም ነበር ባይ ነኝ፡፡ ይህ ማለት ግን የዶ/ር ዐቢይ መንግሥት ጊዜ አምልጦታል ማለት አይደለም፡፡
ዛሬም ከሥር እየቦረቦረው ባለው በአሮጌው የኢሕአዴግ መዋቅር ላይ እጃቸውን ቢያነሱ የሕዝብ ድጋፍ አብሮአቸው እንዳለ ሊያምኑ ይገባል፡፡
ሕዝብና ተቀናቃኝ ኃይሎችም መግፋት ያለባቸው የዶ/ር ዐቢይ መንግሥት ይበልጥ ተጠናክሮ፣ በግድም በውድም ሕግ እንደያስከብር በማስገደዱ ላይ ነው፡፡ የምርጫ ሕጉ በፍጥነት ፀድቆ፣ ድርጅቶች እራሳቸውን ለማስተዋወቅ ያደባባይ ክርክር መጀመር አለበት፡፡ የትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ ለነፃ ምርጫ፣ ለነፃ የፖለቲካ መስመር ክርክር ክፍት እንዲሆን በማድረግ ላይ ማተኮር ያስፈልጋል፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደ ውድድሩ እንደገቡ፣ ያቃታቸው በጊዜ ሜዳውን እንዲለቁ ነው፡፡ በነፃነት ላይ ድርድር የለም፡፡
መቆጠር ያለበት ለኢሕአዴግ እድሜ የሚያራዝም ቀን ሳይሆን እድሜ የሚያሳጥር ቀን ነው፡፡ የምን የምርጫ ጊዜ መራዘም!?

Read 1734 times