Saturday, 12 January 2019 14:38

የለውጥ ጅማሮ በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ

Written by  ወንድወሰን ተሾመ (የማህበራዊ ሳይንስና የስነልቦና ባለሙያ)
Rate this item
(3 votes)

  በአዲሱ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ረቂቅ ህግ 30/70 ወደ 20/80 ተሸጋግሯል

    የዛሬ አራት ወር ገደማ የአንድ አገር በቀል በጎ አድራጎት ድርጅት የቦርድ ሊቀመንበር ለጓደኛው ደውሎለት “ሃሌሉያ ሃሌሉያ---ደስ
ብሎኛል---” አለው፡፡ ይህ ሰው ደስታውንም ሃዘኑንም ከሚያካፍላቸው ጥቂት ሰዎች መካከል ይህ ጓደኛው ይገኝበታል፡፡ እንደዚህ አይነት የደስታ ድምጾቹን ሰምቶ የማያውቀው ጓደኛው፤ “ዛሬ ደግሞ እንዲህ የሚያስፈነድቅ ምን አገኘህ?” ይለዋል ፡፡ የበጎ አድራጎትና ማህበራት ኤጀንሲ(ኤጀንሲው) ህግ ሊቀየር መሆኑን በዜና መስማቱን ይነግረዋል፡፡ ጓደኛው ነገሩ ገባው፡፡ ግን ለምን ይህን ያህል ተደሰተ?---ነገሩን በኋላ
እመለስበታለሁ፡፡
      
   ወላይታ ዞን ኦልቆሴ የምትባል እናት በአንድ ዓለምአቀፍ  በጎ አድራጎት ድርጅት በኩል የድሃ ድሃ ከሚባሉት ሰዎች መካከል ትመረጥና  በእሷ የኢኮኖሚ ደረጃ ካሉ ሌሎች ተረጂዎች ጋር ተደምራ (የሷ ቡድን 20 ሰዎች አሉት)፣ የድርጅቱን እገዛ ማግኘት ጀመረች። ወስዳ የማታውቀውን ስልጠና በመውሰድ፣ የረባ ነገር አምርታበት የማታውቀውን ቦታና በወደቀች ጎጆዋ  ዙሪያ ያሉትን ክፍት ቦታዎች የጓሮ አትክልት ዘር ለመትከል ስራ ጀመረች። ተጠቃሚ እንደትሆን በድርጅቱ፣ በአካባቢው ህብረተሰብና በመንግት የጋራ ተሳትፎ  ከተመረጠች ጀምሮ የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ለተከታታይ ጊዜ በየጊዜው የምታሳየውን የአስተሳስብና የድርጊት ለውጥ ለመከታተል ጎብኝቷታል፡፡ ኦልቆሴን መጀመሪያ ያገኛት ጊዜ  ቃለመጠይቅ ሲያደርግላት፣ ቆዳው ከአጥንቱ ጋር የተጣበቀ የሚመስል ልጇን አቅፋ ስቅስቅ ብላ እያለቀሰች ምላሽ ሰጠችው---የድህነቷ ጥልቀት፣ ብቸኝነቱ፣ ተስፋ መቁረጡ ወዘተ ያስለቅሳታል፡፡ በሁለተኛው ጉብኝቱ  አንድ ክፍል የሆነችው የኦልቆሴ ጎጆ እንደከዚህ በፊቱ ስታፈስ ከርማ ለእሷ፤ ለልጇና የአዕምሮ ህመም ላለበት ባለቤቷ አስቸጋሪ የክረምትጊዜን አሳልፋለች፤ ዝናቡን ለመከላከል ስትልም ጣሪያው ላይ የኮባ ቅጠል ታደርግበት ነበር፡፡ ሆኖም ዘዴው እንደ ሁልጊዜው መፍትሄ አልሆነላትም፡፡ ከድርጅቱ የተቀበለችውን የቀይሥር፣ የካሮት፣ የጥቅል ጎመንና ሌሎች አትክልቶቹን ዘር ባዘጋጀችው ጓሮዋ ውስጥ ብትተክላቸውም ገና ከመሬት ብቅ ብቅ ማለታቸው ነበር፡፡ በምግብ እጥረት ምክንያት የተጎዳውን ልጇን ይዛ፣  ይህንን ሁኔታዋን ለዚህ ፅሑፍ አቅራቢ ስትገልፅለት፤ አሁንም እንደ ቀድሞው እያለቀሰች ነበር፡፡ ለሶስተኛ ጊዜ ሄዶ ሲጎበኛት ቃለመጠይቁን እየሳቀች፣ ፈገግ እያለች መናገር ጀመረች፡፡ ቃለመጠይቁ ተጀምሮ እሰኪጨረስ ድረስ ፈገግታ ከፊቷ አልጠፋም ነበር፡፡ ለምን እንደሆነ ከአንደበቷ ለመስማት ጉጉት ያደረበት ጠያቂ፤ “ላለፉት ሁለት  ተከታታይ ጊዜ መጥቼ ቃለመጠይቅ ሳደርግልሽ ታለቅሺ ነበር፤ ዛሬ ለምን ሳቅሽ፣ ለምን ደስ አለሽ?” ብሎ ጠየቃት፡፡ “ዛሬማ ቡድኔ ባዋጣው እንጨት፣ጉልበትና ገንዘብ ቤቴን አፍርሶ እንደምታየው አዲስ ጎጆ ቤት ሰርቶልኛል፤ የጓሮ አትክልቶቹ ደርሰው ካሮቱን፣ ቀይስሩን፣ ጥቅል ጎመኑን እያማረጥኩ እበላለሁ፤ ከድህነቴ ጥልቀት የተነሳ ከሰው ተገልዬ ነበር የምኖረው፤ አሁን የቡድኔ አባላት እየመጡ ይጠይቁኛል፤ ብዙ ለውጥ እንደማመጣ ተስፋ ማድረግ ጀምሬያለሁ፤ ይህንን የሚረዳኝን ድርጅት እግዚአብሔር ይባርከው፤ ‘ ሃ ድርጂቲአ ጦሳይ አንጆ’ !” አለች-በወላይቲኛ፡፡ ይህ በጎ አድራጎት ድርጅት ምንም መኪና ገብቶበት በማያውቀው መንደሯ ተገኝቶ፣ በሰራው ስራ ህይወቷ በለውጥ ጉዳና ውስጥ ገብቷል፡፡ በመሆኑም የደስታዋ  ምንጭ የህይወት ለውጥ ከመፈጠሩ ጋር የተያያዘ ነበር፡፡
ሰሞኑን የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ ከአገር በቀል ድርጅቶች ጋር ውይይት አድርጎ ነበር፡፡ ከትናንት በስቲያ ሐሙስ ደግሞ ከዓለምአቀፍ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር በካፒታል ሆቴል የሙሉ ቀን የምክክር ወርክሾፕ አካሂዷል፡፡ በዚህ  ወርክሾፕ የኤጀንሲው ሃላፊዎች፤ ከዚህ ቀደም በኤጀንሲውና በበጎ አድራጎት ድርጅቶች መካከል እንደነበረው ሳይሆን አዲሶቹ መሪዎች ከወትሮው በተለየ ድባብ ስብሰባውን መርተውታል፣ ውይይቱን አሳምረውታል፡፡ አንዳንዶች ኤጀንሲው የጠራቸው አልመስል ብሏቸው ውለዋል፡፡ ስብሰባውን የመሩት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ሲሆኑ  ምክትል  ዋና ዳይሬክተር ሆነው የሚሰሩት አቶ ፋሲካው ሞላ በኤጀንሲው የነበሩትን ተግዳሮቶችና ያሉትን ዕድሎች በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ ከጠቅላይ አቃቤ ህግ ቢሮ ዶክተር ጌዲዎን ስብሰባውን በንግግር የከፈቱ ሲሆን ዶክተር ማንደፍሮ እሸቴ የተባሉም ሰው በኤጀንሲው ዙሪያ የታዩትን ክፍተቶች ገለልተኛ በሆነ መልኩ የታዘቡትንና የተረዱትን ለታዳሚዎች አቅርበዋል፡፡
በዚህ ስብሰባ በመድረኩ መሪዎች የቀረቡት እንደተጠበቀ ሆኖ የሚከተሉት ተግዳሮቶችና ክፍተቶች በኤጀንሲው በኩል እንደነበሩ ተሳታፊዎች ዘርዝረዋል፡፡
ኤጀንሲው ለሲቪል ሶሳይቲው ያለው መጥፎ አመለካከትና ሲቪል ሶሳይቲውን በጠላትነት ሲያይ እንደኖረ እንዲሁም የማሸማቀቅ መንፈስ እንደነበረው
ደረጃውን የጠበቀና በወጉ የተሰነደ ገንቢ ግብረመልስ የሌለበት ግንኙነት መሆኑ
የዴስክ ኦፊሰሮቹ (የኤጀንሲው ሰራተኞች) ለተመሳሳይ ጉዳይ የተለያየ ውሳኔ የሚሰጡበት እና ለውሳኔ የሚመች ወጥ አካሄድ እንዳልነበረ
ህጉ ሲቪል ሶሳይቲውን ከማስተዳደር ይልቅ መቆጣጠር ላይ እንደዋለ
ከውጪ በተለየ ክህሎት እና ስራ ተመድበው ወደ አገር የሚመጡ ሰራተኞች የቪዛና የስራ ፈቃድ በጣም ለአጭር ጊዜ መሰጠቱ
ከፍተኛ ቢሮክራሲና ውጣ ውረድ ያለበት አሰራር ነግሶ እንደነበር
ኦፊሰሮች በበጎ አድራጊት ድርጅቶች የውስጥ ጉዳይ እንደሚገቡ፤ አንዳንዴ “ይህንን ዳይሬክተር አንሱ፤ ያኛውን ሹሙ፤ ወዘተ” እስከማለት እንደሚደርሱ
የኤጀንሲው መሪዎች የፖለቲካ ንክኪነት መኖሩ፣
የባንክ ፈራሚዎችን ስም ማስተላለፍ፣ ባንክ አካውንት መክፈትና መዝጋት በኤጀንሲው በኩል  ለባንኮች ደብዳቤ እየተፃፈ በመሆኑና ይህንን ቀላል ነገር ለማድረግ እንኳን ረዥም ጊዜ እንደሚወስድ፤ አንዳንዴም አገሌ ፈራሚ መሆን አይችልም የሚል ውሳኔ እስከመወሰን የሚደርሱበት ሁኔታ መኖሩ
የበጎ አድራጎት ድርጅቶቹ ፋይልና ዶክመንት በእጃቸው እያለ ድርጅቶቹ እንዲያመጡ በተደጋጋሚ መጠየቃቸው
የፋይል አያያዝና የዶክመንቴሽን አሰራራቸው ከዘመኑ እድገት ጋር እንደማይሄድ፤ አንዳንዴም ፋይል ጠፍቷል የሚል መልስ እንደሚሰጡ
ተግባቦቱ (ኮሚኒኬሽኑ) በአንድ አቅጣጫ-ከኤጀንሲው ወደ ሲቪል ሶሳይቱ የሚፈስ መሆኑ እንዲሁም አንዳንድ ኦፊሰሮች ስነምግባር የጎደለው መልስ እንደሚሰጡ፣
ውሳኔ አሰጣጡ ግልፅነት የጎደለውና ደርዝ የሌለው መሆኑ፣
ምዝገባና ሰርቲፊኬት አሰጣጥ ላይ ማን ማንን አግኝቶ አናግሯል እንጂ ተመሳሳይ አካሄድ እንደሚጎድለው
ኦፊሰሮች ሲቪል ሰርቫንት መሆን ሲገባቸው ‘የካድሬ ስራ’ መስራታቸው
የኦፊሰሮች የችሎታ ማነስ ጉዳይ
የንብረት ማስወገድና ድርጅት የመዝጋት ጥያቄዎች ሲነሱ ቀልጣፋ ምላሽ አለመስጠት
ለፕሮጀክቶች ከቀረጥ ነፃ የሚገቡ መኪኖችና ሌሎች ከውጪ የሚገቡ ቁሳቁሶች ከጉምሩክ አሰራር ጋር ተያይዞ የኤጀንሲው ድርጅቶቹን የማገዝ ጉዳይ መጓተት እንዳለበት
የኦፊሰሮች ድርጅቱን ቶሎ ቶሎ መልቀቅ- ይህም ሲቪል ሶሳይቲው ጉዳዩን የጀመረለት ሰው ዳር ሳያደርስለት እንደገና ለአዲስ ሰው የማስረዳትና ራሱን የማስተዋወቅ ነገር ውስጥ እንደሚገባ
የ30/70 የወጪዎች ምደባ ግልፅ አለመሆንና የተለያየ ትርጉም መሰጠት
መመሪያዎች ለግል ትርጉም ክፍተት የነበራቸው መሆናቸውና ሌሎችም ክፍተቶች በተሳታፊዎች ተነስተዋል፡፡
የአገር በቀል በጎ አድራጎት ድርጅት ቦርድ ሊቀመንበሩ፤ “ለምን እንደዛ ተደሰተ?” ብለን ነበር ጥያቄውን ሳንመልስ የተለያየነው፡፡ በወቅቱ ኤጀንሲው በማይረባ ምክንያት የድርጅቱን የባንክ እንቅስቃሴ አግዶበት፣ ለስድስት ወራት ያህል መከራውን ሲበላ ቆይቷል፡፡ ዜናው በተሰማም ጊዜ  ጉዳዩ እልባት አላገኘም ነበር፡፡ እንዲህ ነው ጉዳዩ፡- አንድ ሰው ለኤጀንሲው ስለ ድርጅቱ አሉታዊ ሪፖርት ያደርጋል፡፡ ይህንን ሪፖርት ተከትሎ ኤጀንሲው የድርጅቱን ሃላፊዎች ቢሮው ይጠራና “እንዲህ እና እንደዚያ ትባላላችሁ” ይላል፡፡ የተባለው ነገር ትክክል እንዳይደለና ድርጅቱ በሚታማበት ጉዳይ ሙሉ ህጋዊ ሰነድና አካሄድን ጨምሮ የሚያሳይ ማስረጃ ማምጣት እንደሚችል ገልፆ፣ ኤጀንሲውም ካስፈለገ ጉዳዩን የሚመረምር ቡድን መመደብ እንደሚችልና ድርጅቱ ይህንኑ ለማመቻቸት ዝግጁ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ኤጀንሲው ሰው ልኮ ሳያጣራ አለያም የቀረበለትን ሰነድ ትክክለኛነት ወይም ስህተትነት ሳያጣራ በአንዲት ደብዳቤ የደርጅቱን የባንክ አካውንት በመዝጋት እንቅስቃሴውን አስተጓጓለ፡፡ ድርጅቱ በየወሩ በምግብና በሌሎች ድጋፎች የሚረዳቸው እናቶችና ህፃናት መኖራቸውን ቢያስረዳም የሚሰማው አጣ፡፡ ከስንት ምልልስ በኋላ ወሳኝ ለሆኑ ወጪዎች፣ ጥያቄ ለኤጀንሲው እያቀረቡ እየፀደቀላቸው ደብዳቤ ለባንካቸው እንዲፃፍ መደረግ ጀመረ፡፡
ድርጅቱ ለደሞዝና ወሳኝ ለሆኑ ክፍያዎች ሰነድ እያዘጋጀ፣ ኤጀንሲው ቢሮ ድረስ እየሄደ ከባንክ እንዲፈቀድለት ደጅ ለመጥናት ተገደደ፡፡ እንደ ኦፊሰሩ እይታ አንዳንድ ወጪዎች ላይ “ይህንን አንፈቅድም”ይባልና አስተካክሎ አንዲመለስ ሁሉ ይደረግ ጀመር፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ዳይሬክተሩም ሆነ ሌሎች የድርጅቱ ሃላፊዎች የኤጀንሲውን ኦፊሰሮች “ገፊ ፊት” ማየት ሰልችቷቸዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሲደረግ የጉዳዩ እውነትነት አልተረጋገጠም። ከትንሽ እስከ ትልቅ ወጪዎች የተከናወኑበት ሙሉ ህጋዊ ደረሰኞች፣ አካሄዳቸውን የሚያመለክቱ የሂደት ማረጋገጫዎች በኤጀንሲው ኦፊሰር እጅ ሆኖ ነው፡፡ የአገር በቀል በጎ አድራጎት ድርጅት ቦርድ ሰብሳቢው እንግሊዝ አገር ማስተርሱን ሰርቶ ሲመለስ ነበር “እኔ ያደኩት ሌሎች ሰዎች በስፖንሰርሺፕ ረድተውኝ ነው፤ እኔ አሁን ድሮ ልጅ ሆኜ በነበርኩበት ሁኔታ ያሉትንና በቤተሰብ ችግር ምክንያት መማር የማይችሉትን ልጆች መርዳት አለብኝ፡፡” ብሎ የቅርብ ጓደኞቹን ቢያንስ አንድ ልጅ ትምህርት ቤት እንዲማር ስፖንሰር እንዲያደርጉ በማግባባት ሥራውን የጀመረው፡፡ ይህንን ድርጅት ቀንና ሌሊት ከመደበኛ ሥራው ጋር ደርቦ እየሰራ ለስምንት ዓመታት በነፃ  በዳይሬክተርነት (ምንም ደሞዝ ሳይከፈለው) አገልግሏል፡፡ ድርጅቱ አድጎ ብዙዎችን መጥቀም ቢችልም፣ ኤጀንሲው ባልተጣራ ጉዳይ የቦርድ አመራሩንና አና ሰራተኞቹን ቢሮው ሲያመላልሳቸው ከርሞ፣ ምንም የተጨበጠ ግኝት ሳያገኝ የባንክ አካውንቱን እንደዘጋው፣ ከብዙ ማጉላላት በኋላ እንዲሁ ያለምንም ማብራሪያ እንዲከፈት ደብዳቤ ፅፎላቸዋል፡፡ ለዚህም ነው የበጎ አድራጎት ድርጅቱ አዋጅ ሊቀየር መሆኑን ዜና ሲሰማ “ሃሌሉያ-ሃሌሉያ!” እያለ ለጓደኛው የደወለለት፡፡ እንዲህ አይነት መንገላታት የብዙ ሲቪል ሶሳይቲ አመራሮች እሮሮ ሆኖ ቆይቷል፡፡
የወላይታ ዞን ነዋሪዋ ኦልቆሴ በኤጀንሲው በኩል የሚያጋጥሙትን በርካታ ተግዳሮቶች አልፈው የሚሄዱ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ውጤት ናት፡፡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ፣ ምናልባትም በሚሊዮኖች የሚገመቱ እንደ ኦልቆሴ አይነት ሰዎች በተለያዩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ሥራ በመላው አገሪቱ በሚደረጉ የልማት እንቅስቃሴዎች ህይወታቸው ተቀይሯል፤ በቀን ከሁለት እስከ ሶስት ጊዜ መመገብ ችለዋል፣ ለሰው ልጅ የዕለት ተዕለት ኑሮ ወሳኝ የሆኑትን ተስፋና ለራስ መልካም ግምት/ዋጋ መስጠትን/ አግኝተዋል፣ በራስ መተማመን አዳብረዋል፡፡
ኤጀንሲውና የውጪ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ሐሙስ ዕለት ያደረጉት ውይይት ችግሮችንና ክፍተቶችን ለይቶ ብቻ አላበቃም፡፡ መፍትሄዎችንም አስቀምጧል፡፡
ከተጠቀሱት መፍትሔዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡-
ኤጀንሲው ለሲቪል ሶሳይቲው ያለውን አመለካከት ከጠላትነትና ከጥርጣሬ ወደ መተባበርና ወደ መተማመን መቀየር
ኤጀንሲው የውሳኔ አሰጣጡን ግልፅ ማድረግ
በኤጀንሲው የሚታዩና የማይታዩ ነገሮችን መለየት፡- አስተዳደራዊና ዋና ዋና ውሳኔ የሚጠይቁ ጉዳችን መለየት
መደበኛ የሲቪል ሶሳይቲ ፎረም ማዘጋጀት
ሲቪል ሶሳይቲው ጠንካራ የውስጥ ቁጥጥር መዘርጋት
የኤጀንሲው ሰራተኞች የእውቀትና የክህሎት አቅም እንዲኖራቸው መሥራት
ኤጀንሲው ጥያቄ የሚነሳባቸውን ድርጅቶች በሰለጠነ መልኩና ደረጃውን በጠበቀ አካሄድ መመርመር (አሉባልታ ላይ አለመደገፍ)፡፡
የኤጀንሲውና የሲቪል ሶሳይቲውን ሃላፊነትና ድርሻ በግልጽ ለይቶ ማስቀመጥ
የኤጀንሲውና የሲቪል ሶሳይቲውን ትብብር ማጠናከር
ኤጀንሲውን በበላይነት የሚመራ በእውቀትና በልምድ የዳበረ የቦርድ አባላት መሰየም
የሲቪል ሶሳይቲ ኮድ ኦፍ ኮንዳክት ማዘጋጀት ወይም ማጠናከር
ኤጀንሲውን የሚመሩ አካላት የሙያ ሰዎች እንዲሆኑ ማድረግ
የኤጀንሲው ሰራተኞች ጥሩ የደንበኛ መስተንግዶ ባህሪ እንዲኖራቸው ማሰልጠን
ስብሰባው ማብቂያ ላይ አቶ ጂማ በተሳታፊዎች የተነሱት ጉዳዮች በሙሉ አግባብነት ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው፣ የ30/70 ህግ ወደ 20/80 መሸጋገሩ ሊያስገርማችሁ ቢችልም በአዲሱ ረቂቅ ህግ የ20/80 ትርጉም በግልፅ በመቀመጡ ከበፊቱ የተሻለ ያደርገዋል ብለዋል፡፡  በተጨማሪም በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ በኩል “የሲቪል ሶሳይቲ ተሳትፎ ፖሊሲ” እየተሰራበት እንደሆነ ገልፀው በተለይ የበጎ ፈቃድ ስራዎች በሰፊው እንዲከናወኑ ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡ በመጨረሻም ሁላችንም የተሰባሰበውን የኢትዮጵያን ህዝብ ለማገልገል በመሆኑ በኤጀንሲው በኩል ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮችና ተግዳሮቶች የሚፈቱ ስራዎች እንደሚሰሩ፣ ከበጎ አድራጎት ድርጅቶችም በእውቀትና በክህሎት ዙሪያ የተለየ ልምድ ካላቸው ለኤጀንሲው ማካፈል እንደሚችሉ፤ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችም የለውጡ አካል በመሆን በኤጀንሲው ለሚካሄደው ሪፎርም በሳምንት ወይም በወር  የተወሰነ ሰዓታትን በበጎ ፈቃድ ማገልገል ለሚፈልጉ በራቸው ክፍት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም በአዲሱ ህግ ፈቃድ ማሳደስ የሚባል ነገር አለመኖሩን ጠቁመው፤ በተወካዮች ምክር ቤት እየታየ ያለው አዲሱ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ አዋጅ በፍጥነት ፀድቆ ስራ ላይ እንደሚውል ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል፡፡
ቸር እንሰንብት

Read 7427 times